የአገር ቤት ጋዜጠኞች ምን ጻፉ ( ከጥቅምት 27 እስከ ሕዳር 2/2004 ዓ.ም)
ማስፈራራትን እንደ ማበረታታት አድረገው በፍርኀት የተለወሰ ምክር የሚያቀርቡላችሁን አትስሙዋችው ተመስገን፤ የፍትሁ ተመስገን፤ ሲጽፍ ብዕሩ የማያወላዳው ተመስገን፤ ምሬቱን መደበቅ የማይችለው ተመስገን፤ በዚህ ሳምንት “አንድ በሉ” በሚለው ዐምዱ ሥር ማስፈራራትን እንደ ማበረታታት አድረገው በፍርኀት የተለወሰ ምክር የሚያቀርቡላችሁን አትስሙዋችው፤ ከእነርሱም ራቁ፤ እነርሱን በመስማት የሚመጣ አንዳች ለውጥ የለም የሚል መልእክት ያለው አንድ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ተመስገን መሮታል፡፡ ከባልደረቦቹ [...]
ማስፈራራትን እንደ ማበረታታት አድረገው በፍርኀት የተለወሰ ምክር የሚያቀርቡላችሁን አትስሙዋችው
ተመስገን፤ የፍትሁ ተመስገን፤ ሲጽፍ ብዕሩ የማያወላዳው ተመስገን፤ ምሬቱን መደበቅ የማይችለው ተመስገን፤ በዚህ ሳምንት “አንድ በሉ” በሚለው ዐምዱ ሥር ማስፈራራትን እንደ ማበረታታት አድረገው በፍርኀት የተለወሰ ምክር የሚያቀርቡላችሁን አትስሙዋችው፤ ከእነርሱም ራቁ፤ እነርሱን በመስማት የሚመጣ አንዳች ለውጥ የለም የሚል መልእክት ያለው አንድ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ተመስገን መሮታል፡፡ ከባልደረቦቹ መታሰር በኋላ የጋዜጠኝነትም ኾነ የፖለቲከኛነት አሊያም የነጻነት ናፋቂነት ዕጣ ፈንታ በጥቂቶች እጅ (በተለይ በአቶ መለስ ዜናዊ መዳፍ ውስጥ) መውደቁ አሳስቦታል፡፡ ያሳስበው እንጂ በፍጹም ተስፋ መቁረጥ አይታበትም፡፡ ያለ መስዋዕትነት የሚፈልጉት ነጻነትም ሆነ ድል በቀላሉ መገኘት እንደማይችል እየጻፈ ነው፡፡
ብዙዎች የለውጥን ናፍቆት ሲያልሙ እና አስተያየታቸውን በአደባባይ ሲያሰሙ አንድ መካሪ ይመጣባቸዋል፡፡ “ተው አርፈህ ተቀመጥ!!”፣ “ሌላው ኢትዮጵያዊ አንተ ሞተህለት እንዲያልፍለት እንጂ አብሮህ አይሞትም!!”፣ የሚሉ፡፡ እነዚህ ዐይነቶቹ መካሪዎች የማስፈራርያ እና የማደንዘዣ ምክሮችን እየመከሩ ለውጥ ናፋቂነትን እና አምጪነትን እየገደሉት ነው ይላል ተመስገን፡፡ የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት “አዲስ ራዕይ” በታህሳስ 2003 ዕትሙ ላይ አሁን ላሉት ተቃዋሚዎች ሥልጣን የማስረከብ ፍላጎት እንደሌለው ማተቱን ይገልጽ እና በቀጥታ በቅርቡ ልጆቻቸውን ወደ ቻይና ስለላኩት የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጉዳይ ያወሳል፡፡
ተመስገን እነዚህ ሰዎች አሁን ላሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥልጣን ማስተላለፍ እና የማስረከብ ፍላጎት ከሌላቸው ያሰቡት አንድ ነገር ሊኖር ይችላል ሲል ይተነብያል፤ ልጆቻቸው በራሳቸው ላይ ተቃዋሚ መስለው እንዲመጡ ትምህርት እና ሥልጠና ሰጥቶ ቀጣዩም ዘመን ከእጃቸው ሥር እንዳይወጣ ማድረግ፡፡ “ብልህ አይደሉም ብለህ ማማትህን ፈጽመህ ተው፤ መታገልህን አታቁም፣ መብትህን መጠየቅህንም አትተው፤ ነገር ግን ‘ተው ይቅርብህ’ እና አገር ለቀህ ውጣ ለሚሉህ መካሪዎች በቅርቡ የወጣውን የሙባረክን ፊልም ፈልግና ጋብዛቸው፡፡ የፈርኦንን አገር ላለፉት 30 ዓመታት በፈርኦናዊ አካሄድ ሲቀጠቅጥ የነበረው ሙባረክ የተቃውሞ ድምፅ ሲነሳበት መጀመርያ የሌባ ጣቱን ቀስሮ ያለው “ላ ላ ላ ላ . . ሥልጣኔን አልለቅም ነበር” . . . .በኋላ ግን ተቃውሞው እያያለ ሲመጣ እና ሰዉ ሁሉ ወደ ነጻነት አደባባይ (ታህሪር ስኩሬር) ሲጎርፍ ሙባረክን ጠርጎ ከማስወጣት የታደገው አንዳች አልነበረም፤ ይቅርብህ ብለው ለሚነገሩህ እና ፈርተው ለሚያስፈራሩህ ይሄኑ አስረዳቸው” እያለ ቀጥላል፡፡
እናም ይላል በመጨረሻ ተመስገን “እናም ‘ኮሽ’ ባለ ቁጠር የሚደናበሩ ዘመድ አዝማዶችህን ምክር እየሰማ “ከአገር በላይ ሕይወት አለ የሚለውን” ፍልስፍና እርሳው፡፡ ከአገር በላይ ያለው ወይ ሰማይ ወይ የሰው አገር ነውና፤ የሰው አገር ደግሞ ዜግነትም ሰጠህ ጥገኝነት ያው የሰው ነው፡፡ የአንተ እና የእኔ ክብርም ኾነ ኩራት በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው መሰል ብዙዎች
“አጥንቴም ይከስከስ
ደሜም ይፍሰስላት . . .” እያሉ መስዋዕት ኾነው ያለፉት፡፡
እኔ ብሔርተኛ ስለኾንኩ ባንዲራውን ረግጬ እንደማላልፍ ያውቃሉ
መኢአድ መተራመሱ አልቆመም። መተራመስ ከጀመረም ዓመት ግድም ሊኾነው ነው። ጉዳዩ የሥልጣን ጥም ይመስላል። አንዱ ከአንዱ ጋራ በቀጥታ ምረጡኝ ከማለት ይልቅ በውስጣቸው እርስ በርስ በመፈራራት ራሳቸውን ዕጩ አድርገው ከማቅረብ ይልቅ በምርጫው ወቅት ሁለቱም ወገኖች ፊታቸውን አዙረው ወደ ኢንጂነሩ ሄዱ፤ ባንዲራ አንጥፈው ለመኗቸው፤ እርሳቸው ደግሞ ብሔርተኛ ስለኾንኹ ያንን ማለፍ አልቻልኩም ሲሉ ይህንኑ ጉዳይ ለሪፖርተር ጋዜጠኛ ሃይሌ ሙሉ ተረኩለት።
እንዲህ ነበር ያሉት ኢንጂነር ሃይሉ “ . . . . .አንድ ሰው ዕድሜው ከ70 በላይ ካለፈ በፖለቲካ ፓርቲው ውስጥ መቀጠል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ትግሉ እንደዚህ ሀይ ሀይ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በየቦታው ሂዶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እኔ በሽተኛ ነኝ አልችልም ብዬ ተናገርኩ፡፡ ግን የሚሰማኝ አልነበረም፡፡ ከዚያ በድንገት ይመጡና ሰንደቅ ዓላማ አንጥፈው እያለቀሱ መለመን ጀመሩ፡፡ ያኔ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ እኔ ብሔርተኛ ነኝ እውነቱን ለመናገር ያን ሰንደቅ ዓላማ በምንም ዓይነት ረግጬ እንደማልወጣ ያውቃሉ፡፡ ሊሆን አይችልም ስላቸው ነገሩ እስኪስተካከል ቀጥልልን ስላሉን ባልፈልግም በፕሬዝዳንትነቴ ቀጠልኩ፡፡ ፕሬዝዳንት ኾኜ ከተመረጥኩ በኋላ ለጠቅላላ ጉባዔው ብዙ ጊዜ ተቀዳሚ ምክትል እከሌ ዋና ጸሐፊ እከሌ ብዬ አቀረብኩ፡፡ በዕለቱ በተካሄደው ጉባዔ ከሥራ አስፈጻሚዎች መካከል የማይሠራ ሰው ካለ የማባረር ሥልጣን እንዲኖረኝ ጠቅላለ ጉባዔው ፈቅዶልኛል፡፡ ያን ጊዜ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጌ የመረጥኩት አቶ ያዕቆብ ልኬን ነበር፡፡ የእርሱ ተቃዋሚዎች የነበሩት በምርጫዬ ተናደዱ፡፡ ከዚያ በፊት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበረው ዕድሉን ሰጥቼው አልሠራም፡፡ ስለዚህ ይህ ሰውዬ ቢሠራ ይሻላል ብዬ እርሱን አቅርቤ ተመረጠ፡፡ ልክ ምርጫው ተመርጦ ሥራ ሊጀምር ሲል የታዲዮስ ወገን የነበሩት ቤቱን ዘግተው አትግቡ አሉን፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የመጀመሪያው ብጥብጥ የተከሰተው፡፡
ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው?
ዓለማየሁ ገላጋይ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ለፍትህ ጋዜጣ በተጋባዥ ጸሐፊነት አንድ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ “ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው” በሚል፡፡ የዓለማየሁ ጽሑፍ የሚያጠነጥነው በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከክብራቸው የተዋረዱ እና የእንስሳትን ያህል እንኳ ክብር የማይሰጣቸው ናቸው በሚለው ላይ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት በተለያዩ አገራት በዜጎቹ ላይ ለሚደረጉ ሕገወጥ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ሰብአዊ መብት መገፈፎች እና አሰቃቂ የሆኑ የአካል ጉዳት አደጋዎች ሲደርሱባቸው አፉን ዘግቶ በመቀመጡ ነው፡፡
ዓለማየሁ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳው በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ወጥቶ የነበረው የአስመሮም ኀይለ ሥላሴ ጉዳይ እና ያገኘው ምላሽ ነበር፡፡ መንግሥት የዜጋውን ሕይወት እንዲታደግ ጥሪ ቀርቦለት ከቀሩት 10 ቀናት ውስጥ 8ንቱን ምንም ዐይነት ምላሽ ሳይሰጥ ተኝቶበት ነበር፡፡ ግን በመጨረሻ ቴዲ አፍሮ የግለሰቡን ሕይወት ከሞት አትርፋል፡፡ ይህ እንግዲህ ለዜጎቹ ጥበቃ እና ከለላለ የሚያደርግ መንግሥት ሲጠፋ ግለሰቦች ገነው የሚወጡበት ትዕይንት ከመሆን አልፎ “የኢትዮጵያዊ ዋጋ ስንት ነው?” የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ ሊያስነሳ የሚችል መኾኑንም በጹሑፉ አብራርቷል፡፡
የዓለማየሁ ጸሑፍ ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት እንደኾነ ይነገረን የሚል ለዘብተኛ ጽሑፍ ይመስላል፡፡ በአገሩ ውስጥ ያለውን ዜጋውን ሰብአዊ መብት ያለ ርህራሄ እየረገጠ ላለ “መንግሥት” ይኼ ምኑ ነው እና በዚህ ሰዓት ይነሳል ሊያስብል ይችላል፡፡ ምጸቱ ግን አስመሮም የተወለደው ትግራይ፣ ኑሮውን ማሻሻል ያቀተው በትግራይ፣ ለስደት የተዳረገው ከትግራይ ሲኾን የአድኑኝ ጥሪውን የላከውም ከትግራይ ለተነሳው የሕወሓት ቡድን ገዢ ነበር፤ ምን ዋጋ አለው ትግራይም ተወለደ፣ በኢትዮጵያዊነትም ተጠራ ከሥልጣን ጋራ ቀጥተኛ ተያያዥነት እስከሌለው ድረስ ማን ለአስመሮም ግድ አለው? ቴዲ አፍሮ ግን በሕወሃት ሰዎች ቢታሰርም ኢትዮጵያዊ አደጋ ላይ (ያውም የሞት አፋፍ ላይ) መሆኑን እየሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ስላልሆነለት አስፈታው፡፡ እውነት ግን ዓለማየሁ የጠየቀው ጥያቄ አገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያለውን ኢትዮጵያዊ ጨምሮ ዋጋው ስንት ነው? ክብሩስ አለወይ? ክብሩን እና ዋጋው ሲነጠቅስ የት ነበር? ጥያቄው እጅግ የዘገየ ቢመስልም ወቅታዊ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ትንንሾቹን ዓሶች ወደ ወህኒ እያወረዳቸው ነው፤ አንዳዶቹን ደግሞ በገንዘብ እየቀጣ ነው
2004 ከመጥባቱ በፊት ያረጋል አይሸሹም ሊታሰሩ እንደታሰበ ጉምጉምታ ነበር። እውነት ኾነ፤ ወህኒ ወረዱ። የሠሩት የሙስና ወንጀል ሳይኾን ከመስመራቸው ወጥተው ፖለቲካዊ አስፈጻሚነታቸውን በአግባቡ ስላልተወጡ ነው ይህ የኾነው የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ኢሕአዴግ እና አቶ መለስ በየጊዜው እና የፖለቲካ ውጥረት በበዛባቸው ጊዜያት ሁሉ የሕግ የበላይነት አለ ብለው ለመፎገር የሚጠቀሙባቸው የጦስ ዶሮዎች አሏቸው። የዚህ ዓመቱ መባቻ የጦስ ዶሮ አቶ ያረጋል አይሸሹም ነበሩ። አልሸሽም ቢሉም አልቀረላቸውም።
ሪፖርተር እንደዘገበው በዚህ ሳምንት ደግሞ መሬት ሲቸበችቡ የነበሩ 22 የሚኾኑ የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ወደ ወህኒ ተግዘዋል። የሰበታ ከተማ ከንቲባ እና የሱሉልታ እንዲሁም የመናገሻ ከንቲባ ይገኙበታል። በሱሉልታ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በማሕበር ተደራጅተው መሬት በመውሰድ የቤት ዕጦትን ለማቃለል የሚፈልጉ ሰዎች የክልሉ ባለሥልጣናት የሙስና ሰለባ መኾን ከጀመሩ ሰንብተዋል። ዓመታትም ተቆጥረዋል። አባዱላ ገመዳ የክልሉ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት በቀጥታ እርሳቸው ዘንድ የተዘረጋ እና እርሳቸውንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የመሬት ሽያጭ እንደነበር ይነገራል። አሁን እርሳቸው የተዋካዮች ምክር ቤት ውስጥ የይስሙላውን ወንበር ይዘዋል፤ ተጎልተዋል። ሰንሰለቱ ግን እየተበጣጠሰ ጉቦ አቀባዮቻቸው ነበሩ የሚባሉት ወደ ወህኒ እየተጓዙ ነው።
እንደ ሪፖርተር ዘገባ በኦሮሚያ ሦስት ከተሞች ላይ መሬት የሸጡ 22 ሐላፊዎች ከስድስት ወራት እስከ 16 ዓመታት በሚደርስ እና በገንዘብ ተቀጥተዋል። ለክስ የቀረቡት 47 ሰዎች ናቸው። ነገር ግን የተከሳሾቹ ቁጥር ከዚያም እንደሚልቅ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጃ ታደሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
ብርሃኔ ንጉሴ የፌስ ቡክ አብዮትን እና ወጣቱን አጣጣለ
ብርሃኔ ንጉሴ በፋና ኤፍ ኤም ላይ “ኢትዮፒካ ሊንክ” የሚባል ፕሮግራም አዘጋጅ ነው። ብርሃኔ የፕሮግራሙን ስም ለምን የእንግሊዝኛ ስያሜ እንደሰጠው ግልጽ አይደለም። ብርሃኔ እልል ያለ የመንግሥት ደጋፊ ነው። የቅርብ ሰዎቹ ለሕወሓት እና ለባለሥልጣናቱ ከማሸርገድ ባለፈ አንገቱን ሊሰጥላቸው ምንም አይቃጣውም ይሉታል። የአቶ መለስን የልደት በዐል በፕሮግራሙ ላይ ከማክበር ጀምሮ ታዋቂ ባለ ሥልጣናትን በድንገት እየደወሉ “ውስጥ አዋቂ” በሚባል ሥራ የአጎብዳጅነት ሥራ ይሠራሉ ሲሉ የሚያሙዋቸውም ቀላል አይደሉም። ብርሃኔ በግልጽ የኢሕአዴግ ደጋፊ መኾኑን ይናገራል።
አሁን ሰሞኑን፤ እጅግ በጣም በቅርቡ የሕወሓት እውቅ ታጋይ ነው እየተባለ የሚነገርለት ሙሴ ላይ የተመረኮዘ ፊልም ሠርቷል። ኢትዮ ቻናል ደግሞ የማይሞግት ቃለ መጠይቅ አድርጎለታል። ብርሃኔ ንጉሤ የዐረቡን ዓለም የናጠውን የሶሻል ኔትወርክ አብዮት ከሕወሓቶቹ ጋራ አነጻጽሮ አጣጣለው። የተጠየቀው ጥያቄ ዋና ገጸ ባሕርይ አድርገህ ስለወሰድከው ሙሴ ንገረን ተብሎ ነው። እርሱ ግን እንዲህ አለ . . . . .
“በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለም ደረጃ ለሠላም፣ ለነጻነት እና ለዲሞክራሲ የሚደረጉት ትግሎች የተጋጋሉበት ወቅት ነበር። የዓለም ተማሪዎች እነ ቼጉቬራ፣ ማኦ፣ ሆቺሚኒ በየአገራቸው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በየአገራቸው ለማድረግ ጥረት ያደርጉ ነበር። ስለዚህ በእኛም አገር በወቅቱ የነበረውን ፊውዳላዊ ሥርዐት ለመገርሰስ እና የዲሞክራሲ ሥርዐት ለማስፈን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እኩልነትን ለማረጋገጥ ትግሎች ይደረጉ ነበር።
እነ ዋለልኝ ጥላሁን፣ ማርታ በወቅቱ የነበረውን የአማራ ገዢ መደብ በመቃወም የሁሉም ሕዝቦች እኩልነት፣ ነጻነት፣ መብት መረጋገጥ አለበት ሲሉ ትግል ያደርጉ ነበር። ምክንያቱም በዚያ ጊዜ የነበረው ወጣት እንዳሁኑ ወጣት በፌስ ቡክ፣ በሂፕ ሆፕ፣ በአይቲ በሆሊውድ ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ ሳይኾን ዓለማቀፋዊው የቼጉቬራ የነጻነት ትግል ተጽዕኖ ውስጥ ስለነበር ለሕዝብ የመታገል ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ያገኘው ድርጅት ውስጥ ገብቶ መታገል ይፈልጋል። ስለዚህ ሙሴም ከፍተኛ የትግል ስሜት ስላደረበት አሥመራ ተወልዶ ስላደገ ከሚማርበት የሕንጻ ኮሌጅ ለቆ ሻዕቢያን ተቀላቀለ። ይኹንና ሙሴ አሁን ባለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊ በመኾኑ፤ ማለትም በእናቱም በአባቱም የትግራይ ተወላጅ ነበር። እዚያ ኾኖ እንዴት ለአገሩ መታገል እንዳለበት ያስብ ነበር። ከዚያ ደርግ መጣ እና የተማሪዎችን ትግል በሙሉ አዳፈነው። ስምንት የሚኾኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስዩም፣ ዐባይ ጸሐዬ የመሳሰሉት የትጥቅ ትግል ለማድረግ ወደ ትግራይ ይሄዳሉ። የተወሰኑት ግን ሻዕቢያ ልምድ ስላለው ዕገዛ ለማግኘት ወደ ኤርትራ ይሄዳሉ።”
ለብርሃኔ ንጉሤ ትክክለኛው የመታገያ መንገድ የያኔው የእነ ሙሴ አካሄድ ብቻ ነው። ዛሬ ዓለም ብዙ ስልቶች እንዳሉት ማየት አልፈለገም። በሰሜን አፍሪካ ብቻ ሦስት አምባገነኖች በፌስ ቡክ አብዮት ተጠርገው ከጫዎታ ውጭ ኾነዋል። ዛሬ ልደታቸውን በሬዲዮ ፕሮግራም የሚያከብርላቸው እና ስማቸውን ጠርቶ የማይጠግበው አቶ መለስ እርሱኑ ስለሚፈሩ ከውጭ ያሉ ድረ ገጾችን እንደሚያፍኑ ረስቶታል። የአማራውን ገዢ መደብ ለመታገል የአማራው ብሔር ተወላጆች ሲወጡ በአደባባይ ድንጋይ ይዘው የወጡ ሕጻናትን የገደለውን የህውሓት ገዢ ለመቃወም ምነው አንድ እንኳ የሚጠቀስ የትግራይ ኤሊት ጠፋ የሚለውን ጥያቄ እንሚያስከትል ያሰበ አይመስልም። ስለዚህ የዚህ ዘመን ወጣት ለብርሃኔ ወጣት አይደለም። ምክንያቱም ልክ እርሱ እንደሚለው የሆሊውድ ሰለባ ነው። እርሱ ደግሞ ሆሊውድ ደርሶ መጥቷል። ወጣቱን የበለጠ ሰለባ ለማድረግ ይኾን?
የአገር ቤት ምርቃት
- “መታሰር … እእእ … ለመታሰር አልፈልግም። በደርግ ጊዜ ወደሰባት ዓመታት ስለታሰርኩኝ፣ እስር ምን እንደሆነ ስለማውቅ እስር መፍራት አለብኝ። ፍርሃቴ ግን ገደብ አለው። ለምሳሌ በዚህ ፍርሃት ህሊናዬ አድርግ የሚለኝን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ ለመታገል የሚያደርገውን ጥረት በፍርሃት ምክንያት አላቆምም ግን እስራትን አትፈራም ወይ? ብትለኝ እስራትን እፈራለሁ። እስራትንም በደንብ አውቀዋለሁ።”
ዶክተር መረራ ጉዲና ከአውራምባ ታይምስ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ መታሰርን ይፈራሉ ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ
“ውብሸትን የማውቀው በስም ነው፤ ስሙን የነገረኝ ፖሊስ ነው”
ዐቃቤ ሕግ ሰሞኑን ለፍርድ ቤት ምስክር ብሎ ያቀረበው ምስክር
“ኢሕአዴግ ጌታ ነው”
የሽሙጥ ዐምድ ጸሐፊው አቤ ቶኪቻው ከአገር ከመውጣቱ በፊት በፍትህ ላይ ላይ ለጻፈው ጽሑፍ ለሁለተኛ ጊዜ የተጠቀመበት ርእስ።
“በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ 24 የሽብር ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ”
ሪፖርተር
- “ኢዴፓ አዲሱ የሊዝ አዋጅ የዜጎችን ሀብት የማፍራት መብት ይጻረራል አለ- አዋጁ እንዲለወጥ ጠይቋል”
አዲስ አድማስ
የሳምንቱ ድንቅ አባባል
- “ ‘ኮሽ’ ባለ ቁጠር የሚደናበሩ ዘመድ አዝማዶችህን ምክር እየሰማ “ከአገር በላይ ሕይወት አለ የሚለውን” ፍልስፍና እርሳው፡፡ ከአገር በላይ ያለው ወይ ሰማይ ወይ የሰው አገር ነውና፤ የሰው አገር ደግሞ ዜግነትም ሰጠህ ጥገኝነት ያው የሰው ነው፡፡ የአንተ እና የእኔ ክብርም ኾነ ኩራት በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ነው፡፡”
ተመስገን ደሳለኝ የፍትህ ዋና አዘጋጅ እና ዐምደኛ


Comments are closed.