"; _gaq.push(['_trackPageview']);(function() { var ga = document.createElement('script'); ga.type = 'text/javascript'; ga.async = true; ga.src = ('https:' == document.location.protocol ? 'https://ssl' : 'http://www') + '.google-analytics.com/ga.js'; var s = document.getElementsByTagName('script')[0]; s.parentNode.insertBefore(ga, s); })();

የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ? (ጥቅምት20 – 26፣ 2004)

ያረጋል አይሸሹም?! ምን አረጉ? ለምን ሸሹ ለምን ተመለሱ? ብዙ ሰው የሚያውቃቸው በቀድሞ ሥልጣናቸው ነው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንት ነበሩ። በቅርቡ ደግሞ የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተደርገው ተሾመው ነበር፤ በዚያ ላይ የተከበረው ፓርላማም አባል ናቸው። ለረጅም ጊዜ በጭምጭምታ ሲወራ የሰነበተው የአቶ ያረጋል በሙስና የመከሰስ ነገር ሰሞኑን እውነት ሆኖ ሰውየው ተከሰዋል። ጭምጭምታው ጎልቶ በነበረበት ወቅት ሰውየው [...]

ያረጋል አይሸሹም?! ምን አረጉ? ለምን ሸሹ ለምን ተመለሱ?

ብዙ ሰው የሚያውቃቸው በቀድሞ ሥልጣናቸው ነው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንት ነበሩ። በቅርቡ ደግሞ የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተደርገው ተሾመው ነበር፤ በዚያ ላይ የተከበረው ፓርላማም አባል ናቸው። ለረጅም ጊዜ በጭምጭምታ ሲወራ የሰነበተው የአቶ ያረጋል በሙስና የመከሰስ ነገር ሰሞኑን እውነት ሆኖ ሰውየው ተከሰዋል። ጭምጭምታው ጎልቶ በነበረበት ወቅት ሰውየው ከኢትዮጵያ ሹልክ ብለው መውጣታቸው ተዘግቦ ሁሉ ነበር፤ በኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችም ታይተው ነበር። አቶ ያረጋል “ሸሹ” የሚለው ወሬ ተጣርቶ ሳያልቅ፣ “ያረጋል አይሸሽም” ብለው ወደ አገር ቤት ተመለሱ፤ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ቆጥረውም ወደቢሯቸው ተመለሱ። አሁን አቶ ያረጋል ምን እንዳደረጉ የማጣራቱ ጉዳይ ለፍርድ ቤት ቀርቧል። አቶ ያረጋል ያደረጉትን “ደረስኩበት” ያለው ከሳቸው አቃቤ ሕግ አበሳቸውን የሚዘከዝኩ 63 ሰነዶችና 9 የሰው ምስክሮች አሉኝ ሲል በፍርድ ቤት ፎክሮባቸዋል። አቶ ያረጋል ምን አረጉ?

አቃቤ ሕግ እንዳለው ሰውየው ብዙ ነገር አድርገዋል። አደራረጋቸውም “መሸሽ ነበረባቸው” የሚያሰኝ ነው። ከኦሮሚያ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት የሙስና ስልት ተገቢ ትምህርት አለመቅሰማቸውንም የሚያሳይ ነው። በሚልዮን ብር የሚቆጠር ፕሮጀክት በቀጥታ እያዘዙ ለአንዱ አማካሪ፣ ለሌላው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ወዘተ ይሰጡና ያሰጡ ነበር ተብሏል። ለምሳሌ ከጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ጋራ በገቡት የቡጨቃ ውል 250 ሺህ ብር እና በየወሩ የ10 ሺህ ብር ክፍያ ሊቀበሉ ተስማምተው ነበር የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። በተመሳሳይ መልክ ከሕግ ውጭ፣ ተገቢው ጨራታ ሳይካሔድ ተሰጡ ለተባሉት የአሶሳ ቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ፣ የጣና በለስ የሴቶች አዳሪ ትምህር ቤት እና የጣና በለስ መምህራን ኮሌጅ ግንባታ በድምሩ ወደ 70 ሚልዮን ብር የሚጠጋ የውል ስምምነት ቢፈረምም ቡጨቃው እንጂ ግንባታው በታቀደለት ጊዜ አልተጠናቀቀም ሲል አቃቤ ሕግ ከሷል።
አቶ ያረጋል ባለፈው ዓመት ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ያስመዘገቡት የግል ሀብትም ሰውየው ምን እንዳደረጉ የሚጠቁም ነው ሲል አቃቤ ሕግ ሊከራከር ሞክሯል። አቶ ያረጋል 340 ሺህ ብር በባንክ፣ 1000 ካሬ ሜትር ቦታ ግልገል በለስ ከተማ፣ 269 ካሬ ሜትር ላይ የተሰራ ቤት በአዲስ አበባ በባለቤታቸው ስም፣ መተከል ውስጥ ለአቅመ አዳም ባልደረሰ ልጃቸው ስም የተመዘገበ 450 ካሬ ሜትር ቦታ፣ በሌላ ልጃቸው ስም ደግሞ 1000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዳለቸው ራሳቸው አስመዝግበዋል።

አዲስ አበቤዎች ስለያረጋል እያወሩ ነው። ይጠይቀሉ፤ እንዲህ እያሉ። “አቶ ያረጋል ከኢትዮጵያ የወጡት እውነት ለመሸሽ አስበው ነበር? ለምን ተመለሱ፤ የሆነ ማዘናጊያ ቃል ተገብቶላቸው፣ “ሌሎቹም ይሰርቃሉ፣ እነሱ ምን ሆኑ” የሚል አቶ መለስን የማመን ቅዠት ውስጥ ገብተው ወይስ የአባታቸው ስም አይሸሽም ስለሆነ? አቶ ያረጋል አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ወንጀል ፈጸሙም አልፈጸሙ ወጥመዱ ውስጥ ወድቀዋል። በፓርቲ ግምገማ አፍ አውጥተው አንዱን ቤቴን ለፓርቲዬ እሰጣለሁ የሚሉ አመራሮች ያሉበት ኢሕአዴግ አቶ ያረጋልን ሊበላቸው የወሰነው ለምን ይሆን? ከሌሎች የበለጠ ስለሰረቁ ይሆን?”

አቶ ያረጋል እና አብረዋቸው የተከሰሱ አንድ የክልሉ የሥራ ሐላፊ እንዲሁም ሌሎች ሦስት የኮንስትራክሽን እና የአማካሪ ድርጅቶች ሐላፊዎች ሕዳር 12 ተመልሰው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግን ማስረጃ ማየት እጀምራለሁ ብሏል። ጥያቄው “ያረጋል አያረግም፤ ይሸሻል አይሸሽም” መሆኑ ቀርቶ “አርጓል አላረገም፤ ሸሽቷል አልሸሸም” ሆኗል። “መሆን አለመሆን” እንዲል ሼክስፒር። ዜናውን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው።
—–

የኢሰመጉ 8 ሚሊዮን ብር እግድ ጸና

ሪፖርተር እንደዘገበው አንጋፋው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራ ኤጀንሲ ስምነት ሚሊዮን ብር ታግዶበታል። ይህ እግድ እንዲነሳለት ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታም ውድቅ ተደርጎበታል። ኢሰመጉ ገንዘቡን ያሰባበሰብኩት ከአገር ውስጥ ነው ቢል፣ ገንዘቡ የተገኘው የአሁኑ ሕግ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በተሰጠው የችሮታ/የዝግጅት ወቅት ነው ቢል የሚሰማው አላገኘም። የኢሰመጉ ዳይሬክተር እንዲያውም ገንዘቡ የተጠራቀመው ባለፉት 18 ዓመታት በተለያየ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። ነገሩን ወደ ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ለሪፖርተር ተናግረዋል። ወጣም ወረደም ግን ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ መደረጉ የሚቀር አይደለም።
የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ በ2001 ሲወጣ፣ አንዱ አላማው በመብት ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የገንዘብ ምንጭ በማድረቅ ማሽመድመድ አለዚያም የኢሕአዴግ ተለጣፊ ማድረግ ነበር። ሕጉ “ልማታዊ” ዓላማውን እያሳካ ነው!
—–

መኢአድ “መሆን አለመሆን”

የኢንጂነር ኀይሉ መኢአድ ከገባበት የውስጣዊ ቀውስ አዙሪት መውጣት አልቻለም። ስለፓርቲው በጋዜጦች የሚነበበው ሁሉ “አገዱ፣ ታገዱ፣ ከሰሱ፣ ሰበሩ፣ ጠሩ፣ አወገዙ…” በሚሉ የቀውስ አመላካች ቃላት ከታጀበ ወራት ተቆጥረዋል። በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባበት ተፈታ ሲባል እየሰፋ፣ ረገበ ሲባል እየከረረ መጥቷል። ከዚህ ቀደም የተወሰኑነትን በማባረር ሌሉቹን ከሥልጣን በማንሣት ችግሩን ለመፍታት የተሞከረ ቢመስልም አሁን በድጋሚ አመራሩ ለሁሉት ተከፍሏል ሲሉ ጋዜጦች እየዘገቡ ነው። “ሰንደቅ” ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ እንዳለው መኢአድ ሰባት ከፍተኛ አመራሮቹን አግዷል። ፓርቲውን ለማዳክም አንጃ ፈጥረዋል በሚል የተባረሩት የፓርቲው የሕግና ሥነ ሥርአት ኮሚቴ ሐላፊ አቶ ጸጋዬ ግዛው፣ የውጭ ግንኙነት ሐላፊው ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፣ የወጣቶች እና የሴቶች ጉዳዮች ተጠሪዎች አቶ አቤል ሙሴ እና ወ/ሮ እጸገነት ይልማ እና የምሥራቅ፣ የምእራብ እና የሰሜን ቀጣና ሐላፊዎች ናቸው።
ነገሩን በአቤቱታ የደረሰው ምርጫ ቦርድ መኢአድ እስከ ሕዳር 30 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ይህን ማሳሳቢያ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል። መኢአድ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው በታህሳስ 2003 ነው ሲሉ ገልጸዋል። ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ማህተም አግተዋል የተባሉ የአዲሱ “አንጃ” አባል ማሕተሙን እንዲመልሱም አዟል።
ሪፖርተር ጋዜጣ ስለመኢአድ ቀውስ ባወጣው ዘገባ ሥራ አስፈጻሚ 10 ለ8 ተከፍሏል ብሏል። አሥሩ ባለፈው ሳምንት የፓርቲውን ዋና ጸሐፊ ማገዳቸውን ሲያስታውቁ፣ ኢንጂነር ኀይሉ የሚገኙበት የስምንቱ ቡድን ሌላውን በአንጃነት በመፈረጅ ከሥራ እንዲታገዱ ወስኗል። በቅርቡ የተካሔደው የፓርቲው የአዲስ አበባ ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫም አመራሮቹን አልተስማሙም።
ፓርቲው በውስጣዊ ውዝግብ በመጠመዱ በአገሪቱ ካሉት 62 ቢሮዎች የሚበዙት መዘጋታቸውን በሁለቱም ጎራ ያሉት አመራሮች ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል። “ፍትሕ” ጋዜጣ በበኩሉ ፓርቲውን ጠቅሶ እንደዘገበው በደቡብ ክልል ጎፋ ልዩ ዞን የሚገኙ አራት ጽ/ቤቶች ሐላፊዎች መታሰራቸውን ዘግቧል።
“መኢአድ ከገባበት ውስጣዊ ቀውስ በጊዜ ካልወጣ ሕልውናው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል” የሚሉ ታዛቢዎችን ማግኘት ለሪፖርተሮቻችን የሚያስቸግር ሥራ አልሆነባቸውም።
—–

ብሔራዊ ባንክ የጥሬ ወርቅ አካፋፋይ ሊሆን ነው

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሽያጭ የሚቀርብ ወርቅ ምንጩ የት እንደሆነ አይታወቅም ይላል የሪፖርተር ዘገባ። ወርቅ ቤቶቹም የወርቁን ምንጭ አያውቁትም። በአዲሱ መመሪያ መሠረት የወርቅና የጌጣጌጥ አምራቾች ወርቅ መግዛት የሚችሉት ከብሔራዊ ባንክ ብቻ ነው።
መመሪያው ከወርቅና ከከመሩ ማእድናት ጋራ የተያያዘ ስራ የሚያከናውኑ ድርጅቶች አዲስ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ይገልጻል። ወርቅ ቤቶቹ አሁን በእጃቸው የሚገኘውን ወርቅ አስመዝግበው የባለቤትነት ማረጋገጫ ማግኘት አለባቸው። የወርቅና የጌጣ ጌጥ ቤቶቹ ከባንኩ የገዙትን ጥሬ ወርቅ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችሉም፤ በሚሠሯቸው ጌጣጌጦችም ላይ የእነርሱ መሆኑን የሚያሳይ የሚታይ ምልክት እንዲያደርጉ ታዘዋል። እስካሁን 130 ድርጅቶችን በዚሁ መመሪያ መሠረት በአዲስ አበባ መመዝገባቸውን የጻፈው ራፖርተር ጋዜጣ በክልል የሚተኙትም በዚሁ መመሪያ እንደሚስተጋገዱ ጠቅሷል።
—–

ጋዜጠኞቹ

ጋዜጠኛ ስለሺ ሐጎስ ሐሙስ ዕለት ብቻውን ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር። ከዚህ ቀደም ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበረው አቃቤ ሕግ አሁንም ተጨማሪ ቀን ጠይቆ እስከ ሕዳር 20 ጊዜ ተሰጥቶታል። “ፍትሕ” ጋዜጣ እንደዘገበው አቃቤ ሕግ ተጨማሪ ቀን የጠየቀው “በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሰነዶችን” ለማቅረብ፣ እና “ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ የተጠርጣሪውን ተባባሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል” ነው። ሌሎች ጋዜጠኞች “እንግሊዝኛ የሚተረጉም ጠፋ ወይስ ገና እንግሊዝኛዎቹ ሰነዶች ራሳቸው ተጽፈው አላለቁም? አቶ መለስ የደነፉበት የመረጃ ክምርስ የት ገባ?” እያሉ ተሳልቀዋል።
ከሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ጋራ የተያዙትና የተከሰሱት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል። ሁለቱ ስዊድናውያን ደግሞ በሁለት ክሶች ተከላከሉ ተብላዋል፤ ሕዳር 26 መከላከያቸውን ይዘው ይቀርባሉ።
—–

የአገር ቤት ምርቃት

“የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ ሦስተኛው አብዮት”
የፍትሕ ጋዜጣ የፊት ገጽ
——
በኢሉባቦር (ኢሉ አባቦራ) ቦንብ ፈንድቶ አራት ሰው ሞተ፤ ስድስት ቆሰሉ።
ቦንቡ የፈነዳው የአካባቢው አስተዳደር ሐላፊዎች በጠሩት ስብሰባ ላይ ነው።

“ፍኖተ ነጻነት” ጋዜጣ
——
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአሜሪካ ሰው አልባ የጦር ጀቶች የመንደርደሪያ ቦታ መስጠቱን አመነ
ሰንደቅ ጋዜጣ
——
ከዜጎቻቸው በማስቀደም ኤርትራውያንን እያስተማሩ ያሉት ምን ቢያስቡ ነው?
ፍትሕ ጋዜጣ
——
ገቢዎች ባለሥልጣን “ልማታዊ የታክስ አስተዳደር ሠራዊት” ሊፈጥር ነው
ሪፖርተር ጋዜጣ
——
በአርባ ምንጭ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ
“ፍኖተ ነጻነት” ጋዜጣ
——
ኢዴፓ ነባር አመራሮቹን በአዲስ እየተካ ነው
ሰንደቅ ጋዜጣ
——
በጦር ሰፈር ልዋጭ ፖለቲካዊ ድጋፍ፤ አዲሱ የአቶ መለስ ሰጥቶ የመቀበል ስትራቴጂ
ፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማርያም፤ አውራምባ ታይምስ
——
የዳውሮ ዞን ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ተነጠቅን አሉ
ፍትሕ ጋዜጣ
——
የሻእቢያ ተላላኪ ኢሕአዴግ ራሱ እንጂ መድረክ አይደለም
ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ፤ የመድረክ መግለጫ
——
የነባር ይዞታዎች የመሬት ስሪት የሚወሰነው ከአራት ዓመታት በኋላ ነው
ሰንደቅ ጋዜጣ
——
ለአማርኛ ፊልም እንግሊዝኛ ርእስ መጠቀም ማኅበረሰቡን መናቅ ነው
ተዋናይ፣ ደራሲና አዘጋጅ ሥዩም ተፈራ፤ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ
—–

የሳምንቱ አባባል

“የአንድ ብሩ ዳቦ እንደ ሰሜን ቀበሮ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው”
አውራምባ ታይምስ፤ ሰሞነኛ አምድ

Comments are closed.

Bad Behavior has blocked 1091 access attempts in the last 7 days.