ይግቡ | ይመዝገቡ
This post is available in: ኸንግሊስህ
28 Dec 2010
አንድ ጥፋተኛ የተባለ ወይም የሆነ ሰው “ይቅርታ” “ጠይቆ” ከእስር ወይም ከሌላ ዓይነት ቅጣት “ነጻ” መደረጉን በራሱ የሚቃወም ሰው ብዙ አይገኝም። ቁም ነገሩ ያለው ይቅር ባዩ “ስለጥፋቱ” ወይም አጠፋ ስለተባለው ነገር የደረሰበት ልባዊ ድምዳሜ፤ ይቅርታውን የሚጠይቅበት ምክንያት እና ፋይዳው ብቻ አይደለም። ይቅርታ ተጠያቂው እና አድራጊውም ወገን ደረሰብኝ ስለሚለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ስለጉዳቱ አድራሽ፣ ይቅርታውን ስለሚሰጥበት የሞራል እና የሕግ መሠረት እንዲሁም ስለይቅርታው ተናጠላዊና ሁለንተናዊ ፋይዳ የሚኖረው እምነትና ግብ የይቅርታውን ምንነት በተጨባጭ ይወስነዋል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሁለቱ መካከል ይቅር አባባዮች አሉ። የእነርሱ ማንነት፣ የሞራል ተቀባይነት፣ በተግባር ለሕሊናዊ ዳኝነት የሚሰጡት ቦታ እና ከእርቁ ውጤት የሚፈልጉት ነገርም እንዲሁ እርቁን እርቅ የሚያደርግ፤ አለዚያም ድራማ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል።
(No Comments)
11 Dec 2010
ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎት ያለው ሰው እንዲያነባቸው የሚመከሩ መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ጊዜ የምንረዳበት መንገድና መጠን ቢለያይ እንኳን ስለ አገራችንም ይሁል ስለሌላ ስለሚጠቅመን ጉዳይ ተቀራራቢ መረጃ (ትርጉም አላልኩም) እንዲኖረን ሊነበቡ ይገባቸዋል የምንላቸው መጻሕፍት (ግምታዊ) ዝርዝር ቢኖረን የሚጠላ አይደለም። “የተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳተ ሕግ ይወልዳሉ” የሚባለው እንዳይደርስብን ፖለቲከኞቻችን ቢያውቁት፣ ቢገነዘቡት የምንላቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲረዱልን ልናግዛቸው ይገባል፤ በአንድ በኩል ፖለቲከኞች የእኛው ስራ ውጤቶች ናቸውና።
ነገሩ ሰፊ ክርክር የማጫር እድል ቢኖረውም አንባብያን የአገራችን ፖለቲከኞች ሊያነቧቸው ይገባል ወይም ቢያነቧቸው ጥሩ ነው የምትሏቸውን መጻሕፍት ዝርዝር እንድታካፍሉኝ ልጋብዝ። በመጨረሻ የመጻሕፍቱን ዝርዝር እዚሁ መልሰን እናትማቸዋለን። መጻሕፍቱ በየትኛውም ቋንቋ የተጻፉ፤ ኢልቦለድም ልቦለድም ሊሆኑ ይችላሉ። ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚ፣ ሕግ ወዘተ እያሉ ማሰቡ ያግዝ ይሆናል። የመጽሐፍ ርእስ ከጠፋ በርእሰ ጉዳይ ለምሳሌም “ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፤ ስለ ሕግ ልእልና ወዘተ ቢያነቡ” ብሎ ሐሳብ መስጠት አይከፋም።
4 Dec 2010
እዚህ ላይ “አማካይ” ርእዮተ ዓለማዊ አማራጫ መቅረብ/መገኘት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገራል። ተገቢም ነው። እኔም ይህን እደግፋለሁ፤ ፖለቲካ በአንድ በኩል ሙከራ ስለሆነም ጭምር። ነገር ግን ሁሉም በአማካይ ፍለጋ ብቻ መጠመድ የለበትም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ወይም የተሻለው አማራጭ አማካዩ ላይሆን ይችላልና። ለዚህም ነው በሌኒናዊ ግራ አመለካከት ታፍኖ የቆየው ፖለቲካ በመሠረቱ የተለየ የሆነውን የቀኝ/ሊበራል አመለካከት ለማስተናገድ ረጅም ጊዜና ትግል ያልጠየቀው። ከትምህርት እና ከከተሜነት መስፋፋት ጋራ የሚወለዱ አዳዲስ ፍላጎቶች ተፈጥረዋል፣ ይፈጠራሉም። ስለዚህም እነርሱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅርጽ እየሰጡ የሚተነትኑ አማራጮች ያስፈልጋሉ።
27 Nov 2010
አንድ የተማረ ሰው ከምንም ተነስቶ ወደ መጨረሻው ደረጃ ለመድረስ የሚያስችለው ውጫዊ ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ይሁንና እጅግ ወሳኙ ግብአት የግለሰቦቹ ውስጣዊና ግላዊ እምነት፣ ፍላጎት እና ግብ ነው። ቀድሞውኑ የምሁራኑ መገለጫ ነባራዊውን/ያለውን እያጸደቁና እያደነደኑ መኖር ሳይሆን ለሰው ልጅ የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ያለውን መለወጥ/መረበሽ ነውና ውጫዊ ሁኔታው ከጅምሩ አጋዣቸው እንዲሆን አይጠበቅም። ይህም ሸክሙን ከውጭ ወደ ውስጥ ይመልሰዋል።
የእኛ የሕዝባዊ ምሁራን እነማን ናቸው? በእኔ ዕድሜ (የላይትማንን ደረጃ ልጠቀምና) ወደ ሦስተኛው ደረጃ መድረስ ችለው የነበሩ የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ብቻ ናቸው። አሁን ደግሞ ጊዜው አጭር ቢሆንም ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው። የፕሮፌሰር መስፍን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ መግባት (በተለይም የቅርብ ጊዜው የውዝግብ ድራማ) የሚያስነሳው ጥያቄ ቢኖርም ሰውየው ከአደባባይ ምሁርነታቸው የወረዱ አይመስለኝም። ምናልባትም አጋጣሚው የአደባባይ ምሁራንን በፓርቲ ፖለቲካ የሚኖራቸውን ተሳትፎ እንድንቃኝ የሚጠይቅ ነው። ነጻነት ባለበት የምእራቡ ዓለም ያሉና የአደባባይ ምሁር (public intellectual) መባል የሚገባቸው ጸሐፊዎች፣ ተናጋሪዎችም አሉ፣ ቁጥራቸው የእድሉን ያህል አይደለም እንጂ።
14 Nov 2010
ጥያቄውን በአቋራጭ ለመመለስ ቀላሉ መፍትሔ “አንድ ብቸኛ የተሐድሶ አነሳሽ ሊኖር አይችልም” ብሎ ውይይቱን በአጭሩ መቅጨት ነው። አለዚያም ፖለቲካችን ዞሮ ዞሮ የአፍሪካ ፖለቲካ ስለሆነ አለዚያም “ያልተጠበቀ ነገር” ወይም “ተአምር” ሊፈጠር እንደሚችል በማመን መልሱን ለጊዜ መተው አማራጭ መልስ ይመስል ይሆናል። ሁለቱም የአጭር መልስ አማራጮች ፖለቲካችን የገባበትን ድቅድቅ ከማሳየታቸውም ባለፈ ቀላል መከራከሪያዎች ተደርገው የሚታዩ አይደሉም። እነዚህን ለጊዜው ትተን ግን አሁን በማኅበረሰባችን ውስጥ ካሉ ኀይሎች/ክፍሎች መካከል ቀጣዩን የፖለቲካ ተሐድሶ በመቀስቀስ የትኛው ምን አይነት አቅም እና ዕድል እንዳለው መገምሙ ጠቃሚ ይሆናል።
1. አገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች? 2. የተማረው ኀይል (ተማሪዎችን ጨምሮ) 3. የተደራጁ አካላት (ሲቪል ማኅበራት፣ የሞያ ማኅበራት ወዘተ)? 4. በሥልጣን ላይ በሚገኘው ቡድን ውስጥ የሚገኙ/የሚፈጠሩ ንዑስ ቡድኖች? 5. የታጠቁ ተቃዋሚ ኀይሎች 6. በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) 7. ክፍለ አህጉራዊ ሁኔታዎች 8. የውጭ ተጽእኖ (በተለይ የምዕራቡ ዓለም እና ቻይና) 9. ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች
(እዚህ ያልተቀሰ ቢኖር እየጨመርን እንደምንቀጥል ታሳቢ በማድረግ) ከእነዚህ መካከል ቀጣዩን የፖለቲካ ተሐድሶ በማስጀመርና በመምራት በተናጠልም ሆነ በጋራ ወሳኝ ድርሻ የሚኖራቸውን ሦስት አካሎች በቅደም ተከተል ምረጡ ብንባል መልሳችን ምን ይሆናል?
Bad Behavior has blocked 1135 access attempts in the last 7 days.
Recent Comments