"; _gaq.push(['_trackPageview']);(function() { var ga = document.createElement('script'); ga.type = 'text/javascript'; ga.async = true; ga.src = ('https:' == document.location.protocol ? 'https://ssl' : 'http://www') + '.google-analytics.com/ga.js'; var s = document.getElementsByTagName('script')[0]; s.parentNode.insertBefore(ga, s); })();

ይቅር ባይ፣ ይቅር ተባይ፣ ይቅር አባባይ አሉ? ይቅርታና እርቅስ?

አንድ ጥፋተኛ የተባለ ወይም የሆነ ሰው “ይቅርታ” “ጠይቆ” ከእስር ወይም ከሌላ ዓይነት ቅጣት “ነጻ” መደረጉን በራሱ የሚቃወም ሰው ብዙ አይገኝም። ቁም ነገሩ ያለው ይቅር ባዩ “ስለጥፋቱ” ወይም አጠፋ ስለተባለው ነገር የደረሰበት ልባዊ ድምዳሜ፤ ይቅርታውን የሚጠይቅበት ምክንያት እና ፋይዳው ብቻ አይደለም። ይቅርታ ተጠያቂው እና አድራጊውም ወገን ደረሰብኝ ስለሚለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ስለጉዳቱ አድራሽ፣ ይቅርታውን ስለሚሰጥበት የሞራል እና የሕግ መሠረት እንዲሁም ስለይቅርታው ተናጠላዊና ሁለንተናዊ ፋይዳ የሚኖረው እምነትና ግብ የይቅርታውን ምንነት በተጨባጭ ይወስነዋል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሁለቱ መካከል ይቅር አባባዮች አሉ። የእነርሱ ማንነት፣ የሞራል ተቀባይነት፣ በተግባር ለሕሊናዊ ዳኝነት የሚሰጡት ቦታ እና ከእርቁ ውጤት የሚፈልጉት ነገርም እንዲሁ እርቁን እርቅ የሚያደርግ፤ አለዚያም ድራማ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል።

This post is available in: ኸንግሊስህ

የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በይቅርታ ከእስር ሊፈቱ ነው ሲባል ዓመታት ተቆጥረዋል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር የአራት ሃይማኖቶች መሪዎች ለዚሁ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን መግለጻቸውና ተስፋ መስጠታቸው ብቻ ነው። የይቅርታው ወሬ በስፋት መነገር እንደጀመረ ከየአቅጣጫው የሚሰማው አስተያየት ግን ሌሎችንም ተመሳሳይ አጋጣሚዎችን የሚያስታውስ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት አቶ ስየ አብርሃ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና ሌሎቹም “ይቅርታ ካልጠየቁን” የሚለው ጥያቄ በተቃዋሚው ጎራ የፖለቲካው ማጠንጠኛ እስኪመስል አሰልችቶን እንደነበር አይዘነጋም። ብዙዎቹ ይቅርታ መጠየቁን የፈለጉት ለፖለቲካዊ ዓለማ፣ የአሸናፊነት ጥማታቸውን ለመወጣት፣ “አሳየናቸው” ብሎ ለመመጻደቅ እንጂ ስለ እርቅ ወይም እርሱ ስለሚያስከትለው ውጤት የምር አስበውበት አይደለም። በሌላ በኩል አቶ መለስና ደቀ መዝሙሮቻቸው “ይቅርታ የሚባል ነገር የለም” እያሉ ሲፎክሩ ከርመው “ድንገት” ከ“ይቅር ባዮች” ብጽእና ለመሰቀል ሲሞክሩ ታዝበናል።

በተመሳሳይ አጋጣሚዎች የሚፈጸሙት ድርጊቶች እና የሚሰሙት አስተያየቶች እንደማኅበረሰብ ይቅርታን አሸናፊነትን የማሳያ ተራ መሳሪያ አድርጎ ከመመልከት አለመላቀቃችንን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ኢሕአዴግ ባለፉት አምስት ዓመታት “ይቅርታ እና እርቅ” የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ገና ቤተ መንግሥቱ አካባቢ ዝር አለማለታቸውን በተግባር አሳይቶናል። በቅርቡ ብርቱካን የተፈታችበት ሁኔታ በፖለቲካ መዋቅራችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡም ውስጥ ጥልቅ የአስተሳሰብ ችግር እንዳለ ያለተጨማሪ ማስረጃ የሚያረጋግጥ ነው። ከመንግሥት ውጭ ያለው አካልም የዚሁ በሽታ ተጠቂ ነው።

አንድ ጥፋተኛ የተባለ ወይም የሆነ ሰው “ይቅርታ” “ጠይቆ” ከእስር ወይም ከሌላ ዓይነት ቅጣት “ነጻ” መደረጉን በራሱ የሚቃወም ሰው ብዙ አይገኝም። ቁም ነገሩ ያለው ይቅር ባዩ “ስለጥፋቱ” ወይም አጠፋ ስለተባለው ነገር የደረሰበት ልባዊ ድምዳሜ፤ ይቅርታውን የሚጠይቅበት ምክንያት እና ፋይዳው ብቻ አይደለም። ይቅርታ ተጠያቂው እና አድራጊውም ወገን ደረሰብኝ ስለሚለው ጉዳት ብቻ ሳይሆን ስለጉዳቱ አድራሽ፣ ይቅርታውን ስለሚሰጥበት የሞራል እና የሕግ መሠረት እንዲሁም ስለይቅርታው ተናጠላዊና ሁለንተናዊ ፋይዳ የሚኖረው እምነትና ግብ የይቅርታውን ምንነት በተጨባጭ ይወስነዋል። ብዙውን ጊዜ ደግሞ በሁለቱ መካከል ይቅር አባባዮች አሉ። የእነርሱ ማንነት፣ የሞራል ተቀባይነት፣ በተግባር ለሕሊናዊ ዳኝነት የሚሰጡት ቦታ እና ከእርቁ ውጤት የሚፈልጉት ነገርም እንዲሁ እርቁን እርቅ የሚያደርግ፤ አለዚያም ድራማ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል።

አንድ ነጥብ በድጋሚ ላስረግጥ፤ እነዚህ በሦስቱም ወገኖች ዘንድ ሊፈተኑ የሚገባቸው ነገሮች ተሟሉም አልተሟሉም እንዲሁ “በሰብአዊነት” ብቻ የታሰረ “ከተጸጸተና ይቅርታ ከጠየቀ” መፈታቱን መደገፍ ከእርቅና ከይቅርታ ጥልቅ ሞራላዊና ስነልቦናዊ ትርጉምና ውጤት ጋራ ተፈጥሯዊ ግንኙነት ላይኖረው ይችላል። እንዲህ ሲሆን ይቅርታ ጠያቂውም፣ ሰጪውም ሆነ አሸማጋዩ ወገን (አንዱ ወይም ሁሉም) ድራማ እየሠሩ እንኳን ቢሆን እነርሱ ብዙዎቻችን በተግባር የማናውቀውንና የማናደርገውን የይቅርታ መንፈስ ተጋሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። እርቁም ቁስልን የሚያጠግ “መድኀኒት” ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው እርቅ ጀግንነት ነው የሚባለው፤ ሕሊናና ልብ በአንድነት ቆርጠው ካልገቡበት የማይደረስበት ልእልና ስለሆነ። ማራኪ ምርኮኛውን በነጻ ሊለቀው ይችላል፤ ይህ ማለት ግን በመካከላቸው እርቅ ወርዷል ማለት አይደለም። ምርኮኛ “ይቅርታ ጠይቅ” ተብሎ ይቅርታ ቢጠይቅ፣ ማራኪው “ይቅር አልኩ፤ ታረቅኩ” ብሎ ሊናገር ይችላልን? ውለታና እርቅ ለየቅል ናቸው።

ቀደም ሲል በገለጽኩት የሰብአዊነት መሠረት የደርግ ባለሥልጣናት እንዲፈቱ የሚፈልጉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ተቃራኒውን ድምጽ ከሚያሰሙት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጡ እገምታለሁ። እኔም መፈታታቸውን የምደግፈው ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ይቅር ተባዮቹ (ይቅርታ ጠያቂዎቹ)፣ ይቅር ባዮቹ እና አባባዮቹ በተመሳሳይ የመንፈስ ደረጃ ያሉ አልመሰለኝም፤ የይቅርታና የይፈቱ ወሬውም ከሰብአዊ አዘኔታ ባሻገር የይቅርታውን መሠረቶች እና ፋይዳዎች ገና አንስቶ አልጨረሰም። በዚህ ዙሪያ ሊነሱ ከሚችሉት ጥያቄዎች ጥቂቱን አንስቼ የራሴን አስተያየት ላክል።

  1. አራቱ/አምስቱ ወገኖች (ይቅርታ ጠያቂዎቹ፤ ይቅርታ ሰጪዎቹ- ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ይቅር አባባዮቹ) በተቀራራቢ የግንዛቤ፣ የሞራል ልእልና እና ቁርጠኝነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
  2. አምስቱ ወገኖች ይቅርታውን ከሚፈልጉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መካከል መሠረታዊ የሚሏቸውን ይጋሯቸዋል?
  3. ይቅርታው በውጤቱ እነዚህን ወገኖች የሚያስተሳስር ፋይዳ አለውን?

በግሌ ይቅርታ ጠያቂዎቹ ከሌሎቹ ወገኖች በተሻለ በዘመናቸው ስለሆነው ነገር በእርጋታ ለማሰብ የሚያስችል አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው ይሰማኛል። የእስር ቅጣቱ ካስከተለባቸው ጉዳት በላይም ያለፈውን በመገምገም እና አሁን ያለፉበትን በማሰላሰል የሚገጥማቸው ስነልቦናዊ ጉዞ የበለጠ ይፈትናቸዋል። ስለእያንዳንዱ ሰው በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም (ባይገባም) ብዙዎቹ ከልባቸው ሊጸጸቱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም ይቅርታውን የሚጠይቁት ከእስር ለመፈታት ብቻ እንደማይሆን እገምታለሁ። ይህም ለይቅርታ እና ለእርቅ በተሻለ ደረጃ የተገቡ ያደርጋቸዋል የሚል ተስፋ አለኝ።

ከብዙ ይቅርታ ጋራ ሌሎቹ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ለይቅርታ ውል ወደሚያበቃ የመንፈስ እርጋታና ልእልና የደረሱ አይመስለኝም፤ ይህ አስተያየት ግን “የኢትዮጵያ ሕዝብ”ን አይመለከትም። ይቅርታው ይወርድበታል እስከሚባልበት ጊዜ ባለው ጊዜ እዚያ ይደርሳሉ ካልተባለ በቀር ከሌሎቹ ወገኖች (ተበዳዮችና ቤተሰቦቻቸው፣ መንግሥት እና አሸማጋዮቹ/ይቅር አባባዮቹ) የሚበዙት ስለእርቁ የሚገባውን መንፈሳዊ ዝግጅት ስለማድረጋቸው እጠራጠራለሁ።

ከተበዳዮችና ከቤተሰቦቻቸው ወገን በብዛት የሚሰማው ድምጽ ቁጣና ቂም ጨርሶ ያልለቀቀው ነው፤ “ይቅር ብንልም አንረሳላችሁም” የሚል ቅድመ ሁኔታ መሰል ማሳሰቢያ የሚቀመጥለት ነው (ይረሳ ወይም ሊረሳ ይችላል ያለ ወገን ያለ ይመስላል)። በሌላ በኩል ደግሞ “የሃይማኖት መሪዎቹ እንዴት እኛን በግል መጥተው አላናገሩንም” የሚሉ “የክብራችን ተነካ” ቅሬታዎች በሚዲያ ይቀርባሉ። አልፈውም “ባለሥልጣናቱ ላደረሱት ጭፍጨፋ ተገቢው የቅጣት ውሳኔ ስለተላለፈባቸው ይህንን ውሳኔ ለማስቀልበስ መሯሯጥ አያስፍልግም ሲሉም ይከራከራሉ።” ይህን መሰል አቤቱታዎች ጥያቄውን የአገርና የሕዝብ ከመሆን ፈጽሞ ነጥለው የጥቂቶች ያደርገዋል። እነዚህ ድምጾች ምን ያህሉን ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚወክሉ በእርግጠኝነት መናገር አይቻል ይሆናል፤ መገመት ግን ይቻላል። እነዚህ ሰዎች “ለእርቅ የበቁ እና የተገቡ ናቸው” ለማለት አልችልም፤ እውነተኛ ይቅርታ ለመስጠትም እንደዚያው። እርግጥ በተቃራኒው ለይቅርታ የበቁና የተገቡ እንደሚኖሩ ተስፋዬ ነው። ይህን አስተያየት ስሰጥ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” የሚል “የአያገባህም፤ አይገባህም” አስተያየት ሊሰጥ እንደሚችል እገምታለሁ። በግልም ይሁን በቤተሰብ በደርግ ስለደረሰብን በደል እንደ አዲስ ለመናገር ጊዜው ስላልመሰለኝ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ለመስጠትም ተጎጂነት የግድ ሊሆን ስለማይገባው ከዝርዝሩ መቆጠብን መርጫለሁ።

መንግሥትን በተመለከተ ብዙ ማለት የሚገባ አይደለም። በቃልም በድርጊትም መንግሥታችን ስለ ይቅርታ ያለውን እምነትና ግንዛቤ አይተናል።

ቀሪው አካል የይቅርታ አዋላጆቹ ናቸው፤ የሃይማኖት መሪዎቹ። በቅድሚያ ምንም ቢሆን ይህንንም መሞከራቸውን አልነቅፍም፤ እንዲሳካላቸው እመኛለሁ። ከዚያ ውጭ ግን እነርሱም ቢሆኑ ያለባቸው ሸክም ከባድ ነው። የይቅርታና የእርቅ ምክንያት ለመሆን እውነተኛና ፈታሒ መሆን ያስፈልጋል፤ ይህ ቢያስቸግር እንኳን ተደርጎ መቆጠርን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ በተግባር እንጂ ልብስ በማሳመርና መጽሐፍ በመጥቀስ የሚገኝ ጸጋ አይደለም። ከዚህ አንጻር ቤተ ሃይማኖቶቹም ሆኑ መሪዎቻቸው ስለፍትሕ በእውነትና ያለአድልዎ ሲናገሩ ተሰምተው አያውቁም፤ በአገሩ የሌሉ እስኪመስል ድረስ የንጹሐን መከራና ሞት በተመለከተ “እንጸልይ” የማለት ፍቅርና ሐላፊነት እንደሚሰማቸው አሳይተውን አያውቁም። ተባባሪ መሆኑም በቀረላቸው በጸደቁ ነበር። ስለዚህ ከመንፈስና ከሞራል ልእልና አኳያ ካያነው፣ በእኛ በተራዎቹ ዜጎች ዐይን እነርሱም ይቅርታና እርቅን ለማዋለድ ገና የበቁ ሆነው አይታዩም። እንደዚህም ሆኖ ግን ይህ ሙከራቸው በራሱ ወደምንናፍቀው ደረጃ የሚሸጋገሩበት አጋጣሚ እንዲሆንላቸው በመመኘት “ይቅናችሁ” እንላቸዋለን።

ይቅርታው ለምን ተፈለገ?

የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታውን የጠየቁት ከእስር ለመፈታት ብቻ ከሆነ ከአካላዊ እስር እንጂ ከመንፈስ እስራት አይፈቱም። የእኛን አገር አላቅም እንጂ በሌሎች ቦታዎች ይቅርታ የሚሰጡም ሆነ የሚቀበሉ ሰዎች ስነልቦናዊ እገዛ/ምክር የሚያገኙበት እድል ይሰጣቸዋል። በዚህ በኩል የተደረገ ነገር ስለመኖሩ አልሰማሁም፤ ነገር ግን ቢኖር ለሁለቱም ወገን ጠቃሚ ነው። መንግሥትም ቢሆን ይህን መሰል እርምጃዎች ፖለቲካዊ ጥቅም እንዳላቸው ሳይዘነጋ (ፖለቲካዊ ጥቅም ማግኘቱ ነውር የለውም) ከዚያም ሰፋ አድርጎ ቢመለከት አገራዊ ጥቅም እንደሚኖረው አያጠራጥርም። ይህ እውነታ ለአሁኑ መንግሥት ይሠራል ወይ ብሎ መጠየቅ ሌላ ጉዳይ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ታሳሪዎቹ ሊፈቱ የሚችሉበት የሕግ ሥርዓት በራሱ ሊታይ የሚገባው ቁም ነገር ነው። የሕግ ባለሞያዎቻችን አንዱ በአመክሮ ሊፈቱ ይችላሉ ይላል፤ ሌላው ደሞ በእነርሱ ክስ ጥፋጠኛ የተባለ ይቅርታም አመክሮም የለውም ይላል። ከሕጉና ከፍልስፍናው በተጨማሪ በግለሰብም ይሁን በማኅበረሰብ ደረጃ ስለ ወንጀልና ወንጀለኞች ያለን አመለካከት፣ ስለ ይቅርታ በተግባር ያለን እምነት ሁሉ “የይቅርታ” ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የውይይቱ አካል የሚሆኑ ናቸው።

የቀድሞዎቹ ባለሥልጣናት ይቅርታ መደረጉ የሚኖረውን ፋይዳ ለመመዘን የሚያስቸግር መስሎ ይታያል። በግሌ አጋጣሚው ስለ ታሪኩ እንድንነጋገር ከማድረግ አልፎ፤ በቀጥታ ከተጎጂዎችና በበዳዮች መካከል ያለውን ግንኙነት (ቢያንስ በመንፈስ) ከማከሙ በቀር የተለየ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ይህ ድርጊት ከተፈጸመ 30 ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። አዲሱ ትውልድ ከዝና በቀር የሆነውን አያውቀውም። ይቅርታው ዛሬ ባለው የአገሩቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የሚያስከትለው ተጨባጭ ውጤት አይኖርም።

በአሁኑ ሁኔታ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ መፍጠር ይችል የነበረው የቅንጅት አመራሮች በድጋሚም ብርቱካን የተፈቱበት “የይቅርታ” እና “የእርቅ” ሁኔታ እውነተኛ ቢሆን ነበር። ከዚያም በፊት በነበሩት አጋጣሚዎች በ1980ዎቹ የፖለቲካ ቀውስ የተፈጠሩትን “ቁስሎች” እና መሰሎቻቸውን ማከም በተገባ ነበር። አሁንም መተማመንን ለማምጣት እና መጥፎ ስሜቶችን ሊያስቀር የሚችል አገራዊ እርቅ ያስፈልጋል፤ አልረፈደም። ይህ ማለት ይቅርታ ጠያቂያና ተቀባይ በስም ተለይተው፣ በአድራሻ ተጠርተው የሚጠያየቁበት ግለሰባዊ መልክ ያለው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በእርቅና በፍቅር መንፈስ ሊታከሙ የሚገባቸው ስሜቶች አሉ። የቤት ሥራው የሁሉም ወገን ነው፤ የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ። በተረፈ አሁን ባለንበት ሁኔታ የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ በቀጥታ በግለሰቦች፣ ግፋ ቢል ደግሞ “ከታሪክ ጋራ” የሚደረግ እርቅና ትምህርታዊ ትውስታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ካለው ለመረዳት ዝግጁ ነኝ።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

[አንድ ለቅዳሜ] ስለ ፖለቲከኞቻችን ምን ይነበባል? እነርሱስ ምን ያነባሉ?

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎት ያለው ሰው እንዲያነባቸው የሚመከሩ መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ጊዜ የምንረዳበት መንገድና መጠን ቢለያይ እንኳን ስለ አገራችንም ይሁል ስለሌላ ስለሚጠቅመን ጉዳይ ተቀራራቢ መረጃ (ትርጉም አላልኩም) እንዲኖረን ሊነበቡ ይገባቸዋል የምንላቸው መጻሕፍት (ግምታዊ) ዝርዝር ቢኖረን የሚጠላ አይደለም። “የተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳተ ሕግ ይወልዳሉ” የሚባለው እንዳይደርስብን ፖለቲከኞቻችን ቢያውቁት፣ ቢገነዘቡት የምንላቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲረዱልን ልናግዛቸው ይገባል፤ በአንድ በኩል ፖለቲከኞች የእኛው ስራ ውጤቶች ናቸውና።

ነገሩ ሰፊ ክርክር የማጫር እድል ቢኖረውም አንባብያን የአገራችን ፖለቲከኞች ሊያነቧቸው ይገባል ወይም ቢያነቧቸው ጥሩ ነው የምትሏቸውን መጻሕፍት ዝርዝር እንድታካፍሉኝ ልጋብዝ። በመጨረሻ የመጻሕፍቱን ዝርዝር እዚሁ መልሰን እናትማቸዋለን። መጻሕፍቱ በየትኛውም ቋንቋ የተጻፉ፤ ኢልቦለድም ልቦለድም ሊሆኑ ይችላሉ። ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚ፣ ሕግ ወዘተ እያሉ ማሰቡ ያግዝ ይሆናል። የመጽሐፍ ርእስ ከጠፋ በርእሰ ጉዳይ ለምሳሌም “ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፤ ስለ ሕግ ልእልና ወዘተ ቢያነቡ” ብሎ ሐሳብ መስጠት አይከፋም።

This post is available in: ኸንግሊስህ

ባለፈው ሳምንት የአገራችንን ፖለቲካ ለመረዳትም ይሁን ወደ ፊት ለማራመድ ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ አዲስ የርእዮተ ዓለም ትንተና መሆኑን ጠቆም አድርጌ ነበር። ይህ የመረዳት ፍለጋ ብዙ ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አድርጎኛል። የዛሬው ትኩረቴ በፖለቲከኞቻች በኩል ፖለቲካችንን መረዳት ነው፤ ፖለቲከኞቻችንን መተቸት ብቻ ሳይሆን መረዳት እና መርዳትም እንደሚያስፈልግ ከማመን ጋራ።

በጥያቄዎች ልጀምር። እኛ ስለፖለቲከኞቻችን ምን የምናነበው ነገር አለ? ስለ ፖለቲከኞቻችን ምን ተጽፏል፤ ምንስ እየተጻፈ ነው? ፖለቲከኞቻችንስ ምን ያነባሉ።

ስለ እነርሱ ምን ይነበባል?

የአንድን ማኅበረሰብ ፖለቲካ ለመረዳት የዋና ዋና ተዋናዮቹን ግለሰባዊ ሕይወት ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው። እኛ በዚህ በኩል የታደልን አይደለንም። እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ፖለቲከኞቻችን የሕይወት ታሪክ የተጻፉ ሁነኛ መጻሕፍት በጣም ጥቂት ናቸው። አሉ ከሚባሉት መካከል ባለታሪኩ ከሞተ በኋላ የተጻፉት ይበዛሉ፤ አለዚያም እርሱ በሕይወት እያለ ተክለ ስብእናውን ለመገንባት የተጻፉ “መወድሶች” ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ አይጠቅሙም ማለቴ አይደለም፤ መሪዎቹ በሕይወት እያሉ ለእነርሱው የፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተጻፉት እንደሚበዙበት ግን አያጠራጥርም።

ካነበብኳቸው መካከል አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሳተሙት የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ታሪክ በጥልቀቱና በስፋቱ በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፤ ፋይዳው ታሪካዊነት ቢጫነውም። ተቺዎች ጸሐፊው ለንጉሠ ነገሥቱ መጠነኛ ድጋፍ አድርገዋል ቢሉም የመጽሐፉን ደረጃ የሚያወርደው ሆኖ አላገኘሁትም። የልጅ ኢያሱ፣ የአጼ ምኒልክ፣ የአጼ ዮሐንስ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ታሪኮች አሉ። ሌሎችም እንዲሁ ይኖሩ ይሆናል። እነዚህኞቹ ግን በምርምር ጥልቀታቸው የአምባሳደር ዘውዴን ያህል ሊጠቀሱ የሚችሉ ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደለሁም።

ገነት አየለ ከኮሎኔል (ፕሬዚደንት) መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በዋናነት ይዞ የወጣው ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም። ነገር ግን በማንኛውም መለኪያ እንደ ጥናት/ምርምር ሥራ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል አይደለም። ስለ መንግሥቱ ለሚሠሩ ቀጣይ ሥራዎች በጥሩ ግብአትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ መረጃዎችን ግን አካቷል፤ ጥሩ ጅምርም ነው፤ ብቸኛ ሙከራም ነው። በቅርብ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕይወት ታሪክ የታተሙትን ሁለት መጻሕፍት ስላላነበብኳቸው አስተያየት ከመስጠት ልቆጠብ፤ ስለመጻሕፍቱ የሰማሁት ቢኖርም።

ስለ ፖለቲከኞቻችን ተጻፉ የምንላቸው መጻሕፍት ጥቂት እና ባለሞያ “ገለልተኛ” ጸሐፊ የሚያጥራቸው ብቻ አይደሉም። ሁሉም ስለ አገር መሪዎች ብቻ መጻፋቸውም ግለሰቦቹ በፖለቲካችን ውስጥ ያለቸውን ቦታ የሚጠቁም ጭምር ነው። ሰዎቹ በሕይወት እያሉ የእነርሱን ሕይወት የሚተች መጽሐፍ ማሳተም እንደማይቻልም ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ ውጭ ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢኖሩ በንጉሡ ዘመን ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ሰዎች የጻፏቸውና ገና አሁን በመታተም ላይ የሚገኙ ግለ ታሪኮች ናቸው። ፋይዳቸው ከሞላ ጎደል ታሪካዊ ነው። ስለ አገር መሪዎች መጻፉ ባልከፋ ነበር፤ እርሱም ግን በጣም ጥቂት እና ጥልቀት የሚጎድለው ነው።

ስለ አገር መሪዎቹ ግለሰባዊ ማንነት የሚያወሱት መጻሕፍት ትንሽ ናቸው። ከእነርሱ ውጭ በዙሪያቸው፣ በስራቸው ስላሉት አማካሪዎችና ሹመኞች፤ እንዲያም ሲል እነርሱን በመቃወም በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች/ፓርቲዎች ውስጥ ስላሉ ቁልፍ ሰዎች ጭራሹን ደፍረን የምናቀርበው የተጠናቀረ መረጃ የለንም። ቴክኖሎጂ እጅጉን በሚያግዝበት በዚህ ወቅት በመጽሐፍ ደረጃ እንኳን ባይሆን በአጫጭር ጽሑፎች መልክ በርካታ የተጣሩ እና ደርዝ የያዙ መረጃዎችን ማግኘት በቀለለ ነበር። በአገራችን የህትመትም ይሁን የኢንተርኔት ሚዲያ በአመዛኙ ስለፖለቲከኞቻችን የሚነበበው መረጃ በድጋፍና በተቃውሞ ማጽደቂያነት ነው፤  በጠንካራ የጋዜጠኛ ሞያዊ ምርመራ ላይ የተመሠረተ አይደለም። የጽሑፎቹ ጭብጥም ስለግለሰቦቹን መረጃ ከመስጠት በበለጠ አቋማቸውን ከመደገፍ/ከመቃወም አንጻር የሚተረክ ነው። ራሳቸው ግለሰቦቹ የሚሉትን እንዳለ በማተም፤ ተቃዋሚዎቻቸው አለዚያም ደጋፊዎቻቸው የሚተርኩትን ብቻ በማቅረብ ላይ መንጠልጠል ያጠቃዋል።

አለመታደል ሆኖ ፖለቲከኞቻች ደግሞ እንኳን ስለ ግለሰባዊ ታሪካቸውና አቋሞቻቸው ቀርቶ ስለፖለቲካዊ አመለካከታቸው፣ ስለ ፓርቲያቸውም ጭምር መጻፍ የሚቀናቸው አይደሉም። እርግጥ ብዙዎቹ እንጻፍስ ቢሉ መጻፍ የሚችሉ ናቸው ወይ ብሎ ነገር የሚፈልግ አንባቢ አይጠፋ ይሆናል። እንዴትም በተጻፈና በተተቸ ምንኛ መታደል ነበር።

የፖለቲካ መሪዎችን በተመለከተ እንኳን ለሕዝብና ለተመራማሪዎች ቀርቶ ለራሳቸው ፓርቲ አባላትና ረዳቶች የሚሆን በቂ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ታዲያ ፖለቲከኞቻችንን እንዴት እንወቃቸው? እንዴትስ እንረዳቸው? ግለሰቦቹ የሚመሯቸው ፓርቲዎች ስለ አመራሮቻቸው ታሪክ በይፋ የሚነግሩን ነገር በጣም ውስን ነው። የፖለቲከኞችን ሕይወት እንደሚስጥር መያዝ የፖለቲካችን አንድ ባህል ነው። ይህ በአንድ በኩል የዋናው ባህላችን ቅጥያ ተደርጎ ይታይ ይሆናል። ይህ ባህል ጠቃሚ ነው አይደለም ወደሚለው ክርክር አሁን መግባት አያስፈልገንም። ነገር ግን ባህሉ ፓለቲከኞቻችንን ከግለሰባዊ ማንነታቸው አንጻር እንዳናውቃቸው አድርጎናል።

“ስለ ፖለቲካኞቻችን ምን ይነበባል?” ቢሉ “በአብዛኛው ሐሜት” ብሎ መመለስ ስሕተት አይሆንም።

ምን ያነባሉ?

ስለ ፖለቲከኞቻችን ማንነትና ሕይወት በቂ መረጃ አለማግኘታችን አንዱ ችግር ነው። ከዚሁ ከንባብ ጋራ በተያያዘ ግን “ፖለቲከኞቻችንስ ምን ያነባሉ? ምን አንብበዋል?” ብሎ መጠየቅ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም። “ሰዎቹ የሚያነቡት መጽሐፍ ቀጥተኛ ውጤት ናቸው ወይም ይሆናሉ” ብሎ መደምደም አይቻልም። ፖለቲከኞች እንደ ማንኛውም ሰው የሚያነቧቸው መጻሕፍት ተጽእኖ ያደርጉባቸዋል፣ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ። ከዚያም አልፎ የመጽሐፍ ምርጫቸው ስለ ሰዎቹ የሚነግረን ነገር ይኖር ይሆናል።

የንባቡን ነገር በሌላ አንጻር እንመልከተው። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎት ያለው ሰው እንዲያነባቸው የሚመከሩ መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ  ጊዜ የምንረዳበት መንገድና መጠን ቢለያይ እንኳን ስለ አገራችንም ይሁል ስለሌላ ስለሚጠቅመን ጉዳይ ተቀራራቢ መረጃ (ትርጉም አላልኩም) እንዲኖረን ሊነበቡ ይገባቸዋል የምንላቸው መጻሕፍት (ግምታዊ) ዝርዝር ቢኖረን የሚጠላ አይደለም። “የተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳተ ሕግ ይወልዳሉ” የሚባለው እንዳይደርስብን ፖለቲከኞቻችን ቢያውቁት፣ ቢገነዘቡት የምንላቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲረዱልን ልናግዛቸው ይገባል፤ በአንድ በኩል ፖለቲከኞች የእኛው ስራ ውጤቶች ናቸውና።

ነገሩ ሰፊ ክርክር የማጫር እድል ቢኖረውም አንባብያን የአገራችን ፖለቲከኞች ሊያነቧቸው ይገባል ወይም ቢያነቧቸው ጥሩ ነው የምትሏቸውን መጻሕፍት ዝርዝር እንድታካፍሉኝ ልጋብዝ። በመጨረሻ የመጻሕፍቱን ዝርዝር እዚሁ መልሰን እናትማቸዋለን። መጻሕፍቱ በየትኛውም ቋንቋ የተጻፉ፤ ኢልቦለድም ልቦለድም ሊሆኑ ይችላሉ። ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚ፣ ሕግ ወዘተ እያሉ ማሰቡ ያግዝ ይሆናል። የመጽሐፍ ርእስ ከጠፋ በርእሰ ጉዳይ ለምሳሌም “ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፤ ስለ ሕግ ልእልና ወዘተ ቢያነቡ” ብሎ ሐሳብ መስጠት አይከፋም።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል አራት፤የመጨረሻ]

ፒያሳ እንዲህ ያወጋሁህን ያህል ብቻ አይደለችም። ምኑን ነካሁትና?! ፒያሳ በሕይወት የተሞላች ብትሆንም ብዙ ሲባልላት ባለመስማትህ ግነ ተገርመህ ይሆናል። አትገረም። “ለእነ እንትና ተዘፍኖ ለፒያሳ ሳይዘፈን ይቅር?” ብለህም ይሆናል። አትቆጭ። ምክንያቱ ወዲህ ነው፤ ፒያሳን ለመግለጽ ቋንቋም ወኔ ይጎለዋል። ቋንቋን ራሱን በፒያሳ ሕይወት ተመስጦ ልታገኘው ትችላለህ። ፒያሳን ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ ፒያሳን መኖር የበለጠ ሐሴት ይሰጣል፤ የስጋም የነፍስም። ይሄው ስንት ዓመታችን ፒያሳን ስንኖራት።

የፒያሳ ልጆች ፒያሳን አብረሃቸው እንድትኖር ጋብዘውሃል። ወደ ግብዣው ስትሄድ ግን እስካሁን የሰጠሁህን ምክር በልብህ ያዝ፤ አለበለዚያ የእንትን (የፈለከውን ሰፈርና ከተማ ስም እዚህ ጋ ማስገባት ትችላለህ) ልጅ ነው ብለው ይጥሉሃል። ፒያሳ፤ ማሃሙድ ጋ እንገናኝ!

This post is available in: ኸንግሊስህ

መሐመድ ሰልማን

ፒያሳ ቅልብጭ ያለች ናት፤ እንደዚህ ጽሑፍ የተንዛዛች እንዳትመስልህ፡፡ “ችቦ አይሞላም” የተዘፈነለት የሴት ወገብ አይተህ  ወይንም ነክተህ ወይም ደግሞ አቅፈህ ታውቃለህ? እንደዚያ ማለት ናት ፒያሳ፡፡ ትርፍ ነገር አታይባትም፡፡

የፒያሳ ልጅም ቀልጠፍ ያለ ነው፡፡ አይዝረከረክም፡፡ እንደ ሱሉልታ ልጅ በኮት ላይ ሹራብ አይደርብም፡፡ የዶሮ ማነቅያ ለማኞች እንኳ ሳንቲም ከሰጠኻቸው አይቀበሉህም፤ ወይም ደግሞ አንድ ብር አድርገው ይመልሱልኸል፡፡ ሳንቲም ኮተት ነው፡፡ ፒያሳ አካባቢን የሚያዘወትሩ የታክሲ ወያሎችን አስተውለህ ከሆነ ሳንቲም አይሰጡኹም፡፡ እያጭበረበሩህ እንዳይመስልህ፤ ላንተው ኪስ አዝነው ነው፡፡

ለምን እንደኾነ አላውቅም ሌሎች የአዲሳባ ሰፈሮች እንዲሁ አንዳች ነገር እንደጎደላቸው ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ መርካቶን ውሰድ፤ አፍና አፍንጫው አይታወቅም፡፡ ኮልፌን ውሰድ- ሆድና ጀርባው አይታወቅም፤ ቦሌን ውሰድ-ሴቱና ወንዱ አይታወቅም፤ አራት ኪሎን ውሰድ-ምሁሩና መሀይሙ አይታወቅም፤ ሳሪስን ውሰድ ጫቱና ጫኙ አይለይም፤ ጨርቆስን ውሰድ – በርና መስኮቱ አይለይም፡፡ ፒያሳ ሂድ- ‹‹አሟልቶ አይሰጥ ፈጣሪ›› የሚለውን አገርኛ ቢሂል ከማስታወሻ ደብተርህ ትሰርዛለህ፡፡

ይህንን ጽሑፍ የምጽፍልህ አራዳ ላይ ሆኜ ቁልቁል ‹‹ማህሙድ ሙዚቃ ቤት››ን እያየሁ፣ የፒያሳ ወይዛዝርት ሽው እልም እያሉብኝ፣ ያዘዝኩት ማክያቶ እየቀዘቀዘብኝ-እያስሞቅኩኝ፣ ብእሬ ቆንጆ ገላን ባየ ቁጥር እየከዳኝ እንደሆነ ልትገነዘብ ይገባል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ላይ አንዳንድ የቃላትና የሰዋሰው ግድፈት ቢያጋጥምህ ‹‹ቆንጆ ልጅ በ‹‹ማሃሙድ ጋ››አልፋ ነው›› እያልክ እለፈኝ፡፡

ይህ የፒያሳ ወግ እንደረዘመብህ ይሰማኛል፡፡ በነገርህ ላይ ሰፈሮች ለረዘመ ነገር ምላሻቸው ምን እንደሚመስል ታውቃለህ? መርካቶ ወሬ ካረዘምክ ዋጋ ይጨምሩብኻል፤ ቦሌ ወሬ ሲረዝም ራሳቸውን ያማቸዋል፤ ቦሌ መድኀኔዓለም ያጥወለውላቸዋል፤ ጨርቆስ ወሬ ካረዘምክ ‹‹49 ቁጥር ባስ ታመልጥኸለች›› ይሉኻል፤ የአብነት ልጆች ወሬ ካረዘምክባቸው በሹል ድንጋይ መሀል አናትህን ይፈነክቱኸል፤ የፒያሳ ልጆች ወሬ ስታረዝምባቸው ተጨማሪ ኬክ ያዛሉ፡፡ እጅግ ተናደውብኻል ማለት ነው፡፡

ተጨማሪ ኬክ ከማዘዝህ በፊት ይህንን ጫወታዬን እቋጫለሁ፡፡

የፒያሳ ቤርጎች

መቼ ለታ ማሃሙድ ጋ የመቀጣጠር ጥቅሞቹን ዘርዝሬልህ ሳበቃ፣ የፒያሳን ካፌዎችና ቆንጆ ተስተናጋጆቻቸውን በሚገባ ካስኮመኮምኩህ በኋላ ዶሮ ማነቂያ አስገብቼህ፣ በአላሙዲ አጥር አሻግሬህ፣ ዛሬ ቦታው የኮልኮሌዎች መዋያ እንደሆነ አርድቼህ፣ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ አስመሽቼህ ነበር ጫወታዬን የገታሁት፡፡ አስታወስክ?

ዛሬ ትንሽ ጋደም ብለን እናውጋ፤ በፒያሳ ቤርጎዎች፡፡ ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን ቤርጎ (በዘመናዊው አጠራር ሆቴል) ያበረከተችው ፒያሳ ናት፡፡ ጣይቱ ሆቴል፡፡ ይህን በልቦናህ ይዘህ ወደ ዝቅተኛ ማደርያዎች ስታማትር ሰራተኛ ሰፈርን ታገኛለህ፡፡

በፒያሳ ማደርያ በሁለት ይከፈላል፡፡ በኮንቦርሳቶና በግድግዳ፡፡ ለምሳሌ በዶሮ ማነቅያና በሰራተኛ ሰፈር ያሉ ማደርያዎች ዋጋቸው ከሀያ እስከ 40 ብር ሲሆን ከቀጣዩ ጎረቤትህ የሚለይህ ግን ኮምቦልሳቶ የሚባል ቀላል “ቴክኖሎጂ” ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ከጎንህ ያለውን የቤርጎ ተከራይ ገመናዎችና በእንቅልፍ ልቡ የሚጫወታቸውን ቀላል የትንፋሽ መሳርያዎች ለመስማት ትገደዳለህ፡፡ ጫን ያለው የሚያንኮራፋ ቤርጎ ተከራይ ሲመጣ ደግሞ የምትሰማው ሙዚቃ ወደ ጃዝ ከፍ ይላል፡፡ ከሁሉም የከፋው ግን ጎረቤትህ ሴት ይዞ የገባ ከሆነ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የሚሰማህ ሙዚቃ የጣልያን ኦፔራ በኦርኬስትራ ታጅቦ ሊሆን ይችላል፡፡

ሠራተኛ ሰፈር በቤርጎ ብቻ ሳይሆን በሕጻናትና ወጣቶችም እየተጥለቀለቀ ነው፡፡ በሰፈሩ ያለውን የሕጻናት ብዛት ስታይ የዚህ ሰፈር አባቶች እና እናቶች ማታ ማታ ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሠሩ ይገባኻል፡፡ የትኛው ልጅ የየትኛው ቤት አባል እንደሆነ የሚለየው በሚያሰማው የአለቃቀስ አይነት ነው እየተባለ ይቀለዳል፡፡ የሠራተኛ ሰፈር አባወራዎችና እማወራዎች እነዚህን ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሕጻናት ለማሳደግ ታድያ ለፒያሳ የውድቅት ሰለባዎች አልጋ ያከራያሉ፡፡ ችግሩ አልጋ ተከራይ ሲጠፋ በዚያው በሚከራይ አልጋ ላይ ሌላ ልጅ ሠርተው ያድራሉ፡፡ ሠራተኛ ሰፈር!!!

ፒያሳ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቱሪስቶች አልጋዎችን ታከራያለች፡፡ ‹‹እቴጌ ጣይቱ››እና ባለቤታቸው ከዓመታት በፊት ያባረሯቸው ፈረንጆች የ‹‹እቴጌ ጣይቱ››ን ረከስ ያለ አልጋ ፍለጋ ዳግም ፒያሳን አጥለቅልቀዋታል፡፡ ፒያሳ ጥልያን በጣልያን ሆናለች፡፡ በፒያሳ ከምትገምተው በላይ ፀጉረ ልውጥ በዝቷል፡፡ ለፒያሳ ጩሉሌዎችም አዲስ የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ጣይቱ ማዶ ያሉ ሰፈሮች በሙሉ ወደ ኢንተርኔት ካፌ የተለወጡት ወደው አይምሰልህ፡፡ ፈረንጅ በዝቶ ነው፡፡ ከሰሞኑ አንድ አባት አርበኛ በዚያ ጋር አልፈው ምን አሉ መሰለህ፡፡ ‹‹ጥልያንን አባረነው አልነበረም እንዴ?!››

‹‹ዉጥማ ሆቴል››፣ ‹‹ባሮ መኝታ››፣ ‹‹አንኮበር እንግዳ ማረፍያ›› ሁሉም ከጣይቱ ጀርባ የሚገኙ ፈረንጅ ተኮር መኝታ ቤቶች ናቸው፡፡ አንተም እገባለሁ ካልክ ቆዳህን ማድማት አይጠበቅብህም፡፡ ኪስህን እንጂ፡፡

የፒያሳ ጣእም

ፒያሳን በካፌዎቿ እንጂ በምግብ ቤቶቿ የሚያውቃት ሕዝብ እምብዛም ነው፡፡ ይህ ግን ድንቁርና ድህነት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፒያሳ ችግር አይደለም፡፡ እመነኝ፡፡ በከተማችን ትልቁ፣ ዝነኛውና ውዱና ተወዳጁ ምግብ ቤት የሚገኘው በፒያሳ እንደሆነ የፒያሳ ልጆችም አንዳንዴ ይዘነጉታል፡፡ የከተማችን ዲፕሎማቶች፣ ባለ ሀብቶች፣ ባለሟሎች ዘናጭ ምግብ መብላት ሲሹ የት የሚሄዱ ይመስልኻል፡፡ ቦሌ እንዳትለኝና እንዳልስቅ፡፡ ፒያሳ ነው የሚመጡት፡፡ ካስቴሌ፡፡

ካስቴሌን ጥቂት ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ምግብ ቤቱ በተፈጥሮው ድምፁን አጥፍቶ ነው የሚሰራው፡፡ ስታየው ምግብ ቤትም አይመስል፡፡ ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት በስተቀኝ አምስት እርምጃ አይርቅም፡፡

ካስቴሌ እንደማንኛውም ምግብ ቤት መስሎህ ዘለህ ዘው እንዳትል፡፡ ለነገሩ ዘበኛው ወዝህን አይቶም ቢሆን ይከተልኻል፡፡ የዚህ ቤት ዘበኞች ‹‹ሽሮ-በል››ና ‹‹ስጋ-በል›› ዜጎችን በፍጥነት እንዲለዩ ተደርገው የተገሩ ናቸው፡፡

እዚህ ቤት መብላት ካማረህ ብዙውን ጊዜ አስቀድመህ በስልክ ቦታ አሲዘህ ነው መሄድ ያለብህ፡፡ ደግሞ ተኳኩለህ፣ ዘንጠህ ብትሄድ ይመከራል፡፡ አልያ እጅህን ልጥታጠብ ስትነሳ ተስተናጋጆች አስተናጋጅ መስለሃቸው ‹‹ሄሌ !ማነህ! እዚህ ጋ እስኪ የዳቦ ክሬም ጨምር›› ይሉኸል፡፡ በዚህን ጊዜ ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ ደርሶብህ በልቼ እወፍራለሁ ያልከው ሰውዬ ከስተህ ትመለሳለህ፡፡

ዘወትር ምሳ ሰዓት ላይ ‹‹ቪ ኤይት››፣‹‹ፌራሪ››፣‹‹ሀመር››፣‹‹ኤስካሌድ››፣‹‹ኤክስ ፋይቭ››፣ ‹‹ሬንጅሮቨር››፣ ‹‹ኢንፊኒቲ›› የመሳሰሉ የሚሊዮን ብር መኪናዎች በካስቴሌ ምግብ ቤት በር ላይ እንደቀልድ ተሰድረው ታያለህ፡፡ ጠርጣሪ ከሆንክ ደግሞ ትጠረጥራለህ፡፡ አንዳች ባለጸጋ የፒያሳን ምድር ረግጧል ስትል፡፡ አልተሳሳትክም፡፡ በካስቴሌ መናኛ ሰው አይገባም፣አይበላም፡፡ ደጅ የቆሙ መኪናዎችን ግን እንዲጠብቅ ሊፈቀድለት ይችላል፡፡ ከዚህ ቤት በር መኪና ጠብቀህ የሚሰጥህ ‹‹ቲፕ›› ዶሮ ማነቅያ ውስጥ ምን የመሰለ ቅቅል ታዝበታለህ፡፡

የምትወዳት ፍቅረኛ ካለችህ ግን ምን ታደርግ መሰለህ፤ ከየትም እንዴትም ብለህ ብር አጠራቅም፡፡ ፒያሳ ማህሙድ ጋ ቅጠራት፡፡ ፒያሳ ካስቴሌ ምሳ ጋብዛት፡፡ ምን አለ በለኝ ትጋባላችሁ፡፡

የፒያሳ ቡቲኮች

የሆነ ሰፈር ልብስ ልትገዛ ገብተህ ይሆናል፡፡ ሻጩ እንዲህ ይልኸል፡፡ ‹‹አባዬ፤ ይሄን ጃኬት ፒያሳ 800 መቶ ብር ይሉኻል፡፡ እኛ ላንተ ብለን ነው…ባገር ዋጋ ልበሰው…ትከሻ አለህ፤ ሄዶብኻል! (አንተ የትከሻህን ገለባነት ስለምታውቀው ሳቅህ ይመጣል) አታውልቀው ያምርብኻል!  እኔ ለናቴ ልጅ አልሸጠው…!!! ምትገዛበትን ንገረኝና እንስማማ…››

ፒያሳ ዋጋ ይቆለላል፡፡ ሌላ ቦታ 300 ብር የምትገዛውን ልብስ ፒያሳ እጥፉን ትጠይቅኻለች፡፡ ለውድ አፈሯ ግብር መሆኑ ነው፡፡ ምናለ ብትከፍል?! “ከፒያሳ ነው የገዛሁት” ስትላት ሴት ጓደኛህ ትመካብኻለች፡፡ እመነኝ፡፡ ከዚያ በኋላ “መች ነው የምንጋባው?” ትልህ ይሆናል፡፡ ልብስ ጫማ ከገዛህ ከፒያሳ ግዛ፡፡ ዝናህ ለጉረቤት ይተርፋል፡፡ የጨርቆስ ልጅ ከሆንክ ደግሞ ዝናህ በሰፈሩ ይናኛል፤ ኪሎ ስጋ የገዛህ ይመስል፡፡

ሲኒማ  ላ ፒያሳ

ስማኝማ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማ የት እንደተጀመረ ታውቃለህ? ፒያሳ ነው፡፡ ካላመንክ ሂድ ቴዎድሮስ አደባባይ፡፡ ‹‹ሰቫስቶፖል›› አፍንጫውን ወደቀሰረበት አቅጣጫ ተመልከት፡፡ ሰይጣን ቤትን ወይም ሸይጣን ቤትን ታገኛለህ፡፡ ካላመንከኝ የታሪክ መጸሕፍትን ፈትሽ፡፡ እኔ የነገርኩህን ይደግሙልኻል፡፡ በዚህ ቦታ ‹‹ዋልታ›› ረዥም ፎቅ ሊሰራበት ነው፡፡  ፎቅ ሳይቆምበት ቶሎ እየው፡፡ ታድያ ስትገባ አማትበህ፣ አልያም ‹‹ቢስሚላህ፣አኡዙ ቢላህ›› ብለህ ግባ፡፡ ሰይጣን ቤት መሆኑን አትርሳ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ሲኒማ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከ 85 በመቶ በላይ የሚገኙት በፒያሳ እንደሆነ ማን በነገረህ፡፡ ፒያሳ የኢትዮጵያ ሆሊውድ ልትላት ትችላለህ፡፡‹‹ሰይጣን ቤት››፣‹‹ሲኒማ ኢትየጵያ››፣ ‹‹ማዘጋጃ ቤት››፣ ‹‹አገር ፍቅር››፣‹‹ሲኒማ አምፒር››፣ ‹‹እስክስታው ቤት››፣ እንዲሁም አገር በቀል የዶሮ ማነቅያ ቪዲዮ ቤቶች ወዘተ ሁሉም ፒያሳ ነው ቤታቸው፡፡

ድሮ ‹‹ሲኒማ ኢትዮጵያ›› አልሳም ያለችህን ፍቅረኛ ወስደህ በፊልም አሳበህ የከንፈር ዳር ድንበሯን የምትጋፋበት ቤት ነበር፡፡ ሆኖም እጣህ ሆኖ ሴት ጓደኛህን ይዘህ የገባህ እለት የህንድ ፊልም ከከፈቱብህ አለቀልህ፡፡ ጓደኛህ ከህንዶቹ እያየች አልሳም ትልኸለች፡፡ ለማፏጨትም ለመሳምም ያልተመቸ ሲኒማ ምኑን ሲኒማ ነው?!

እኔም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይኸው ‹‹ሲኒማ ኢትዮጵያ›› የምሄደው ከደጁ የሚሸጡትን የእንግሊዝኛ መጽሔቶች ለመግዛት ብቻ ሆነ፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?

የባቅላባ ፍቅር

ፒያሳን የምወድበት ሌላው ምክንያት ባቅላባን ስላስተዋወቀችኝ ነው፡፡(አንዳንዶች ‹‹ቫቅላባ›› ነው የሚባለው ይላሉ፡፡ እኛ ምናገባን፣ ባቅላባውን እንጂ ሆሄያቱን አንበላቸው፡፡)

ትዝታ ገብረትንሳኤ ወመኮንን ባር፡፡

“መኮንን ባር” የፒያሳ አድባር ነው፡፡ ይህ ቤት የማን ነው? የሕዝብ ይመስለኛል፡፡ ባለቤቱን አይቼው አላውቅም፡፡ ደግሞ ባለቤት ያለውም አይመስለኝም፡፡ እንዴት በእኔ እድሜ እንኳ አይታደስም? እነዚያ በሕጻናት መዋያ ትምህርት ቤቶች ያሉትን ወንበሮች የሚመስሉ ትንንሽ ቡናማ መቀመጫዎች፣ ባቅላባ ከሚያካክሉ ትንንሽ ጠረጴዛዎች ጋር አሁንም አሉ፡፡ እንደነበሩት፡፡ ወደፊትም የሚኖሩ ይመስለኛል፤ ከማይደበዝዘው ግርማ ሞገሳቸው ጋር፡፡

አንጀቴን የሚበሉ አስተናጋጆች ያሉበት ቤት ነው፤ መኮንን ባር፡፡ ከቤቱ ጋር ያረጁ፣ ያጎነበሱ ውድ አስተናጋጆች፡፡ ቲፕ ባልተለመደበት ዘመን ሥራ ጀምረው እንጂ እስከዛሬ እነርሱም ባለ ባር በሆኑ ነበር እላለሁ፤ በሆዴ፡፡ ለማንኛውም ለረዥም ዓመት ስላስተናገዳችሁኝ እጅ እነሳለሁ፡፡ ከልቤ፡፡

ባቅላባ ቤት የወንበርን ጥቅም ያወቅኩበት ቤት ነው፡፡ ወንበር ከያዝክ የሚታዘዝህ ይመጣል፡፡ ውሀ ይቀርብልኻል፤ ባቅላባህ ይመጣልኻል፤ ስትጨርስ ጠረጴዛህ ይጸዳልኻል፡፡ ወንበር ከሌለህ ግን ሄደህ፣ ተሰልፈህ፣ ከፍለህ፣ ባቅላባ ለመውሰድ ሌላ ሰልፍ ይዘህ፣ ሹካና ማንኪያ ለማግኘት ደግሞ ሌላ ሰልፍ ይዘህ፣ ውሃ ለማምጣት ደግሞ ሌላ ሰልፍ ጠብቀህ፣ ሰርተህ ትበላለህ፡፡ ወንበር ጥሩ ነው፡፡ ግን ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ መልቀቅም ይገባል፡፡ አገኘኹ ብለህ 20 ዓመት በባቅላባ ወንበር ላይ መወዘፍ የለብህም፡፡ ይህች ዓረፍተ ነገር ፖለቲካ መሰለችብኝ ልበል? ግን ንጹሕ ነገረ ባቅላባ ናት።

ባቅላባ ዛሬም አለ፡፡ እስከ ስምንተኛው ሺህ ይኖራል፡፡ ዋጋው ስምንት ብር ደርሷል፡፡ ሰልፉም እንደዚያው፡፡ ሌላ ትውልድ በተራው እየበላው ነው፡፡ በእነዚያው አስተናጋጆች፡፡

ዳላስ ሙዚቃ ቤት

ፍቅረኛህን ‹‹ማሃሙድ ጋር ጠብቂኝ›› ስትላት ተሳስታ ተሻግራ ከጠበቀችህ እድለኛ ናት፡፡ ካንተ በላይ የሚያስደስቷትን ሙዚቃዎች እየሰማች ነው ማለት ነው፡፡ ከዳላስ ሙዚቃ ቤት፡፡ ይህ ቤት የየመን ዝርያ ባላቸው ሐበሾች የተያዘ ነው፡፡ ከፒያሳ ፍቅር እንዲይዝህ ከሚያስችሉ አዚሞች አንዱ ነው፤ ዳላስ፡፡

እጅግ የቆዩ የሚጣፍጡ ሙዚቃዎችን ዛሬም ድረስ ያስኮመኩማል፡፡ ከዚህ ቤት የሚደመጡ ሙዚቃዎች ዘፋኞቹ በህይወት የሌሉ ወይም ደግሞ ዘፋኞቹ ራሳቸው የረሷቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ኦልዲስ-በት- ጉዲስ››፡፡

አንድ አንባቢዬ ዳላስን እንዴት ገለጸው መሰለህ፤ ‹‹The soundtrack of Piassa››፡፡

ዘላለማዊ የሆኑ ዘመን የማይሽራቸው የሱዳንና የአገረሰብ ሙዚቃዎች በዚህ ቤት ይዘወተራሉ፡፡ በቲቪ የምታውቀው ጀማሪ ዘፋኝ እዚህ ዳላስ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ሲያንዣብብ ካየኸው አንድ ነገር ጠርጥር፡፡ ሊከትፍ ወይ ሊመነትፍ ነው፡፡

የፒያሳ ጭንቅላት

የፒያሳ ሆድ ካስቴሌ ነው። የፒያሳ ሀብት ወርቅ ቤቶቿ ናቸው፡፡ የፒያሳ ጆሮ ዳላስ ነው፤ የፒያሳ አይን ሲኒማ አምፒር ነው፤ የፒያሳ መልክ ውብ ሴቶቿ ናቸው፡፡ የፒያሳ ራስ ቅል ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ የፒያሳ ጭንቅላት ማን ነው?

ወዳጄ ኾይ! በፒያሳ ውብ ጫማና ልብስ ብትሽቀረቀር፣ ካስቴሌ ሄደህ ከርስህን ብትሞላ፣ አምፒር ሴት ሸጉጠህ ኋላ ወንበር ላይ ብትወሸቅ፣ ፒሳ ኮርነር ብትነጠፍ፣ በባቅላባ ጣእም እጅህን ብትቆረጥም፣ በኤንሪኮ ኬክ ብትንሳፈፍ፣ ማህሙድ ጋ ልጅቱን ጥበቃ በጭንቅላትህ ብትተከል፣ በዳላስ ሙዚቃ ብትመሰጥ፣ በሰንሻይን ሻምፓኝ ብትራጭ፣ የዶሮ ማነቂያን ቁርጥ ብትዘነጥል፣ ጭንቅላት ባዶ ከሆነ ምን ዋጋ አለው?

ጭንቅላትም ልክ እንደሆድህ ምግብ እንደሚፈልግ ታውቃለህ። ለዚህ ፒያሳ ብሪትሽ ካውንስል አለልህ፤ ነበረልህ፡፡ ዛሬ ስልጣን መሰይጠን ነው ብለው በስደት ሆነው አገርህን በእውቀት ከሚያሾሯት ኢትዮጵያውያን የሚበዙት ጭንቅላታቸውን የት የኮተኮቱት ይመስልኻል? በብሪትሽ ካውንስል ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ብሪትሽ ካውንስል ደግሞ የፒያሳ የእውቀት አድባር ነው፡፡ የዚህን ቤት ውለታ የምታውቀው እውቀት ጠገብ ከሆኑ ሰዎች ጋር በፒያሳ ካፌዎች በአንዱ ቁጭ ብለህ የማውጋት እድል ከገጠመህ ነው፡፡ ብሪትሽ ካውንስል ዓለምን አሳይቷቸዋል፡፡ ጭንቅላታቸውን ትራንስፎርም አድርጎላቸዋል፡፡ የጭንቅላታቸው ትራንስፎርመር እንዳይቃጠል ረድቷቸዋል፡፡ ገና ድሮ፤ የትራንስፎርሜሽንና የምናምን እቅድ ሳይጠነሰስ፡፡ ጠንሳሾቹም ሳይጠነሰሱ፤ ሳይጠነስሱም፡፡

በዚህ ቤት ኢትዮጵያውያን በሼክስፒርኛ ተቀኝተዋል፣ በፕላቶኛ ተፈላስፈዋል፣በመጻሕፍት ባህር ተንቦራጭቀዋል፡፡ በየምእራብ አገራቱ ፈረንጅ ያቃተውን ሳይንስ የሚፈትሉት እኒህ ጥቂት ኢትጵያውያን የብሪትሽ ካውንስል ቡቃያዎች ናቸው፤ የብሪትሽ ካውንስል ውለታም አለባቸው፡፡ አፋቸው በእንግሊዝ አፍ ለማሰልጠን መሄጃ ያጡ ብቅ የሚሉት እዚህ ነበር፤ ለልጆቻቸው መጻሕፍት የሚዋሱ ወላጆችን ማየት ብርቅ በነበረበት ዘመን በብሪቲሽ ካውንስል በሽ ነበሩልህ። ለማትሪክ ዘመቻ የሚዘጋጁ ጮሌዎችም ለንባብ ሲንጋጉ ታያቸው ነበር።

ምን ዋጋ አለው ታድያ፡፡ ይህ የፒያሳ ጭንቅላት ዛሬ ራስ ቅሉ ብቻ ነው ያለው፡፡ በውስጡም ጸረ ሰላም እና ጸረ ልማት የሆኑ እርኩሳን የኤንጂኦ መናፍስትን እያስጮኹ የሚያስወጡ የባህል መድኀኒት አዋቂዎች ተቀምጠውበታል፡፡ ብሪትሽ ካውንስል፣ ነፍስ ይማር!

ማሰርያ አንቀጽ

ፒያሳ እንዲህ ያወጋሁህን ያህል ብቻ አይደለችም። ምኑን ነካሁትና?! ፒያሳ በሕይወት የተሞላች ብትሆንም ብዙ ሲባልላት ባለመስማትህ ግነ ተገርመህ ይሆናል። አትገረም።  “ለእነ እንትና ተዘፍኖ ለፒያሳ ሳይዘፈን ይቅር?” ብለህም ይሆናል። አትቆጭ። ምክንያቱ ወዲህ ነው፤ ፒያሳን ለመግለጽ ቋንቋም ወኔ ይጎለዋል። ቋንቋን ራሱን በፒያሳ ሕይወት ተመስጦ ልታገኘው ትችላለህ። ፒያሳን ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ ፒያሳን መኖር የበለጠ ሐሴት ይሰጣል፤ የስጋም የነፍስም። ይሄው ስንት ዓመታችን ፒያሳን ስንኖራት።

የፒያሳ ልጆች ፒያሳን አብረሃቸው እንድትኖር ጋብዘውሃል። ወደ ግብዣው ስትሄድ ግን እስካሁን የሰጠሁህን ምክር በልብህ ያዝ፤ አለበለዚያ የእንትን (የፈለከውን ሰፈርና ከተማ ስም እዚህ ጋ ማስገባት ትችላለህ) ልጅ ነው ብለው ይጥሉሃል። ፒያሳ፤ ማሃሙድ ጋ እንገናኝ!

2 Responses to “ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል አራት፤የመጨረሻ]”

  1. Lovely!
    Gebrielin ye Arada lij neh!!!

  2. A very nice writing. Big thanks for the author.

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ከሙስና ጋር በተያያዘ አንዳንድ የኦሮሚያ ሐላፊዎች ከስልጣን ተነሱ፤ ለእስር የተዳረጉ ይገኙበታል

This post is available in: ኸንግሊስህበፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሰበታ- ሀዋስ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ እና በዓለም ገና ከተማ የሚገኙ የአምስት ቀበሌ ሊቀመንበሮች ከመሬት ሽያጭ ሙስና ጋር በተያያዘ  ህዳር 22 ቀን 2003 ዓ.ም ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የሰበታ ከተማ የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡ የዜና ምንጮቻችን ለሪፖርተራችን እንደገለጹት ሰሞኑን የሰበታ ከንቲባ [...]

This post is available in: ኸንግሊስህ

በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሰበታ- ሀዋስ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ እና በዓለም ገና ከተማ የሚገኙ የአምስት ቀበሌ ሊቀመንበሮች ከመሬት ሽያጭ ሙስና ጋር በተያያዘ  ህዳር 22 ቀን 2003 ዓ.ም ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የሰበታ ከተማ የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡

የዜና ምንጮቻችን ለሪፖርተራችን እንደገለጹት ሰሞኑን የሰበታ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ሀሰኖን ጨምሮ በዓለም ገና እና በወለቴ ከተሞች ያሉ የቀበሌ ሊቀመንበሮች በሙሉ ከአዲስ አበባ በመጡ የደህንነት ሠራተኞችና ከኦሮሚያ ጽ/ቤት በመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በተገኙበት የተገመገሙ ሲሆን የኦሮሚያ ጽ/ቤት ሁሉንም ጥፋተኛ በማለት ከኃላፊነት አንስቷል፡፡

በዚህም የሰበታ ከተማ ከንቲባ በነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ ምትክ ከኢሉባቡር ዞን ኦህዴድን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ዓለሙ ጫንያለው ሲሾሙ፣ በየቀበሌዎቹ የነበሩት ሊቀመንበሮች ሁሉ ከኃላፊነት ተነስተው ምክትሎቻቸው እና ሌሎች የአስተዳደር አባላት ኃላፊነት እንዲረከቡ ተደርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመሬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከሦስት ሣምንት በፊት በድንገት በደህንነት ሠራተኞችና በሲቭል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስራ አምስት በላይ የሰበታ፣ ዓለም ገና እና ወለቴ አካባቢዎች የአስተዳደር ሠራተኞችና መሃንዲሶች ከነበሩበት የዱከም ጊዜያዊ ማረሚያ ቤት  ትላንት ወደ ቃሎቲ ማረሚያ ቤት መዘዋወራቸውንና በጸረ ሙስና ኮሚሽን ክስ እንደተመሠረተባቸው የዜና ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

ከአስተዳደር ሠራተኞቹ ጋር በከፍተኛ ሙስና ክስ የተመሰረተባቸው መሐንዲሶች ወ/ሪት ሚሚ ሀ/ጊዮርጊስ፣ አቶ ታምራት ቅቢ፣ አቶ ታሪኩ ተፈራ፣ አቶ ፈለቀ፣ ወ/ሪት መሠረት፣ አቶ አብደላ እና ሌሎች የመሬት ደላሎች እንደሚገኙበት ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

[አንድ ለቅዳሜ] የአዲስ ርእዮተ ዓለማዊ ትንተና ጅማሮ

እዚህ ላይ “አማካይ” ርእዮተ ዓለማዊ አማራጫ መቅረብ/መገኘት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገራል። ተገቢም ነው። እኔም ይህን እደግፋለሁ፤ ፖለቲካ በአንድ በኩል ሙከራ ስለሆነም ጭምር። ነገር ግን ሁሉም በአማካይ ፍለጋ ብቻ መጠመድ የለበትም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ወይም የተሻለው አማራጭ አማካዩ ላይሆን ይችላልና። ለዚህም ነው በሌኒናዊ ግራ አመለካከት ታፍኖ የቆየው ፖለቲካ በመሠረቱ የተለየ የሆነውን የቀኝ/ሊበራል አመለካከት ለማስተናገድ ረጅም ጊዜና ትግል ያልጠየቀው። ከትምህርት እና ከከተሜነት መስፋፋት ጋራ የሚወለዱ አዳዲስ ፍላጎቶች ተፈጥረዋል፣ ይፈጠራሉም። ስለዚህም እነርሱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅርጽ እየሰጡ የሚተነትኑ አማራጮች ያስፈልጋሉ።

This post is available in: ኸንግሊስህ

(ይህ ጽሑፍ ደረሰ ጌታቸው ካስነበበን መጣጥፍ ጋራ ተያይዞ ሊነበብ የሚችል ነው። ሐሳቡ ቀደም ሲልም ሲብላላ የነበረ ቢሆንም የደረሰ ጽሑፍ አንዳች ነገር እንድል አነሳስቶኛል። እንደ ወጉ ቢሆን እኔም በእንግሊዝኛ መጻፍ ነበረብኝ፤ ሆኖም ቢያንስ “አንድ ለቅዳሜ” በአማርኛ ብቻ እንድትጻፍ የተሠራውን ስርአት ማክበር አለብኝ። ባይሆን አስፈላጊ ከሆነ ወደ እንግሊዝኛ እመልሰዋለሁ።)

የማንኛውንም ማኅበረሰብ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በተለያየ መንገድ መከፋፍል እና ማጥናት ይቻላል። ከማኅበረሰቡ ክፍሎች ማንነት በመነሣት፣ አለዚያም ጎልተው ከሚንጸባረቁት ርእዮተ ዓለማዊ ልዩነቶች አንጻር ነገሩን መመልከት ይቻላል። እንደ አጥኚው ፍላጎት የሚለዋወጡ ሌሎችም ብዙ መንገዶች ይኖራሉ። በርእዮተ ዓለማዊ ልዩነት መነሻነት የሚደረገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንተና ላለፉት 40 ዓመታት የራሱን ኡደት ማድረጉ አልቀረም። ሆኖም አከፋፈሉ ማኅበረሰቡ የተቀየረውን ያህል መሻሻል አላሳየም። ምናልባት ለዚህ ችግር ቀዳሚውን ሐላፊነት መውሰድ ያለባቸው የሶሲዎሎጂ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ናቸው።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የርእዮተ ዓለም ትንተና በግርድፉ ብንቃኝ ዓለምን በበዝባዥና ተበዝባዥ መደብ ለሁለት በመክፈል ለመረዳት የሚሞክረው አመለካከት ፍጹማዊ የበላይነት ይዞ እንደቆየ እንረዳለን። በመካከል በግራ ዘመሞቹ ፓርቲዎች መካከል የነበረው ልዩነት ርእዮተ ዓለማዊ ይዘት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ቢያሳይም በመሠረቱ ግን ተመሳሳይ ነበር። ለዚህም ነው ዋናው ልዩነታቸው የትንተና ሳይሆን የስልት ሆኖ የቆየው። ኢሕአፓ፣ ሜኤሶን፣ ኦነግ፣ ህወሓት፣ ህግሓኤ/ሻእቢያ ዝርዝሩ ረጅም ነው።

አነሳሳቸው ላይ ተመሳሳይ ይመስሉ የነበሩት እነዚህ ቡድኖች በሒደት በአንዳንድ ጉዳዮች መሠረታዊ ልዮነቶችን ማሳየት ጀምረዋል። ኦነግን እና ህወሓትን የመሳሰሉት ቡድኖች በሒደት የመደብ ትንተናን ወደ ጎን እየገፉ የብሔር ትነተናን የርእዮተ ዓለማቸው ማዕከል አድርገው መንቀሳቀስ ቀጠሉ። ስለዚህም ኢትዮጵያን በብሔሮች ግንኙነት እንጂ በኢኮኖሚና በታሪክ መስተጋብር ማንበብ ሙሉ በሙሉ አቆሙ። የትነተናቸው የመጨረሻ ማብቂያም የኢትዮጵያ ችግር “የቅኝ ግዛት ጥያቄ” ከዚያ መለስ ካለ ደግሞ “የብሔረሰቦች እስር ቤት”ን የማፍረስና “እስረኞቹን” ነጻ የማውጣት ሆነ። እነዚህን ቡድኖች “የግራ ጽንፈኞች” የሚሏቸው ሰዎች አሉ። በአጭሩ ሌኒንን እና ስታሊንን ሊያስንቁ የተነሱ የግራ ግራ ሰልፈኞች ነበሩ። (በነገራችን ላይ ዝነኛዋ የዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ ሐሳቧ የእርሱ [ብቻ?] እንዳልነበረች፤ ነገር ግን የዋለልኝ ብሔረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ጀርባ – አማራ የባላባት ልጅ- ጽሑፉን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ እንዳስመረጠው የሚናገሩ አሉ። የጉዳዩን የሰላ ገጽታ የሚያሳይ ታሪክ ነው።)

በተቃራኒውም የነበሩት ደግሞ በአብዛኛው የግራ ጋራ ሰልፈኞቹን ጥያቄ (የብሔር-ቅኝ ግዛት ትንተና) ከመሠረቱ በመቃወም ማንኛውም ጥያቄ በኢትዮጵያ አንድነት ማእቀፍ ውስጥ የሚፈታ መሆኑን አስረግጠው ተነሱ። ጥያቄውንም በአመዛኙ በወትሮው የማርክሲስት ትንተና ብቻ ማስተናገድን መረጡ፤ በዝባዣ-ተበዝባዥ፣ ፊውዳል-ጭሰኛ…። በአመዣኙ ኢህአፓን የመሳሰሉትን ቡድኖች እዚህ መመደብ ይቻል ይሆናል። ለዝርዝሩ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በሒደቱ የተንጸባረቁትን ልዩነቶች በስፋት እንደሚነግሩን ተስፋ አደርጋለሁ።

የዘመነ ደርግ የፖለቲካ ትንተና በአመዛኙ በዚሁ ይዘት ዘልቋል። በሒደቱ ግን አዳዳሲ እይታ ያላቸው ቡድኖች መምጣታቸው አልቀረም። ይህ ጎልቶ የታየው ደግሞ ከደርግ ውድቀት በኋል ነው። የኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል “የኢትዮጵያን አንድነት” ሲያቀነቅን የቆየው ቡድን (ከዚያ በፊት የነበሩት የአገሪቱ መሪዎች ሁሉ ማለት ይቻላል) የቆመበትን እና የሠራውን ሁሉ በማፈራረስ ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ዙሪያ መለስ የቀደመውን ርእዮተ ዓለም መሠረቶች የማፍረስ ፕሮጀክት ውስጥ ኦነግ እና ህግሓኤ (ከህውሓት ጋራ የጀመሩት የጫጉላ ሽርሽር በመሸዋወዳ እስኪጠናቀቅ ድረስ) “በየሰፈራቸው” ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ አንድነትና በብሔር ትንተና ጉዳይ ከሕወሓት/ኦነግ/ህግሓኤ ጎራ በተቃራኒ የቆሙትን ብድኖች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻል ይመስለኛል። አንደኛውና ጎልቶ የወጣው ከሞላ ጎደል የብሔር ጥያቄን ከመሰረቱ በትነተና መሣሪያነት የማይቀበልና ቀሪው ችግርም መተንተን ያለበት በኢትዮጵያ አንድነት ማእቀፍ ውስጥ ብቻ መሆኑን የሚያምን ነው። በሂደት ድምጹ መሰማት የጀመረውና የሁለቱንም ጎራዎች ቀልብ መሳብ የቻለው አመለካከት ደግሞ በሁለቱ አማካይ መስመር ላይ ለመራመድ የሚሞክር ነው፤ የብሔር ትንተናን በተወሰነ መልኩ ይቀበላል፣ “ልዩነቱ መፈታት ያለበት ግን በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ ነው” ይላል። ብዙ ጊዜ ከዚህ አመለካከት ጋራ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እየተደባለቀ የሚቀርበው ሌላው እይታ “ከሊበራሊዚም” የግለሰብ ትንተና የሚነሳ ነው። በከረረ ትርጉም ካየነው የግለሰብ ነጻነት ትንተና ለብሔር ትንተና መሠረታዊ መነሻዎች ቀጥተኛ እውቅና አይሰጥም። በምርጫ 97 እንደታየውም እነህወሓት “የግለሰብንም የብድንም መብት እናስከብራለን” የሚል አዲስ ትንተና እንዲያቀርቡ የገፋፋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ “ለየትኛው ቅድሚያ ትሰጣላችሁ?” የሚለው ጥያቄ ለሁለቱም ጎራዎች ፈታኝ ነው። ከጥቂት ፖለቲከኞች በቀር ብዙዎቹ ይህን ጥያቄ በቀጥታ አይመልሱትም፤ እርግጥ በቀጥታ መመለስ አይኖርባቸውም ይሆናል።

በመሠረቱ፣ ደረሰም በጽሑፉ እንደጠቆመው፣ እነህወሓት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ መንግሥት (ስቴት) የቆመበትን ርእዮተ ዓለማዊ መሠረት ከስሩ ለመናድ ሲነሱ በምን እንደሚተኩት አላሰቡበትም፤ መተካት እንዳለባቸውም አያምኑም ነበር። ይህ በቸር አገላለጽ ትእቢትና አለማወቅ ከመባል የዘለለ ስም ሊሰጠው የሚችል አልነበረም። አገርን ለማፍረስ አገር የቆመበትን “ትንተና” (ትምህርተ ጥቅሱ ትንተናው አፈታሪክም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ለማስታወስ ነው) ሊቀናቀን የሚችል “ትንተና” መፍጠርን ይጠይቃል። ግራ ሰልፈኞቹ ይህን አልሞከሩም አልልም። አገሪቱ ካለፈችበትና ከደረሰችበት፣ ከውስጣዊና ውጫዊ እውነታዎች አንጻር ግን “ትንተናውን” ማሻሻል እንጂ ከስሩ መናድ እንደማይቻል ወይም እንደማያስፈልግ ባለፉት 20 ዓመታት በተግባር አይተናል።

የለውጡ መጠን የሚያነጋግረን ቢሆንም  በሁለቱም ጎራዎች ርእዮተ ዓለማዊ ለውጥ መደረጉ ግልጽ ይመስለኛል። እርግጥ ለውጡ በእርግጥ ርእዮተ ዓለማዊ ነው ወይስ የስልት ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው። ለዚህ ጥያቄ ለጊዜው መልስ የለኝም።

እውነቱን ለመናገር በድኅረ አብዮት ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነጻነታቸው ተገድቦ የነበሩ ዜጎች መኖራቸው ባይካድም ሃይማኖትን የርእዮተ ዓለሙ መሠረት አድርጎ የሰበከ ፓርቲ መኖሩን እጠራጠራለሁ። በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መሠረት ባይኖራቸውም ሃይማኖትን የብሔር ትንተናው ማብላያ (ማባባሻ) አድርገው በመጠቀምም የግራ ግራዎቹ የሚደርስባቸው ያለ አይመስለኝም፤ ዛሬም ድረስ። በአጠቃላይ ግን የሃይማኖት ቀጥተኛ ተጽእኖ እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት በፖለቲካችን ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወቱ ሙሉ በሙሉ ቀርቷል ማለት አይደለም። (በሌላ ጽሑፍ እንመለስበት ይሆናል።)

ብዙውን ጊዜ ስለርእዮተ ዓለም ልዩነት ሲነሳ ለውይይት የሚቀርበው የብሔር ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እና የመሬት ባለቤትነት ጉዳዮች ናቸው። እርግጥ ሁለቱም የአንድን አገር መሠረታዊ ህልውና የሚወስኑ እንደመሆናቸው በቀዳሚነት መነሳታቸው ስህተት አይደለም። ምናልባትም ገና እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ገና በሚያቀራርብ መልኩ ስላልመለስን በዚሁ ተጠምደን መቆየታችን የማይቀር ነው። ይህ ግን ፖለቲከኞች ሌሎችንም የሕይወት ገጽታዎችና አማራጮች የሚተነትኑበት የተሟላ ርእዮተ ዓለማዊ መነጽር አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም። ስንት ፓርቲዎች ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፣ ስለ ግለሰባዊ ነጻነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት፣ ስለ ሕግ፣ ትምህርት ወዘተ በደፈናው ከሚነገር መፈክር መሰል “ትንተና” ባለፈ ጠለቅ ያለ ግንዛቤና ርእዮተ ዓለማዊ ትንተና እንዳላቸው አላውቅም። በጋዜጠኝነት ያነጋገርኳቸው ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ግን ገና ብዙ የሚቀራቸው መሆናቸውን መደበቅ አልችልም። “አይዞን ይሻሻላል!” ብለን እንለፈው።

አዲሱ ትንተና የታለ?

የድኅረ አብዮት ኢትዮጵያ ትውልድ አባላት እና የድኅረ ደርግ ፖለቲካ ተዋናዮች አዲሱ ሁኔታ፣ አዲስ ወይም የተሻሻሉ ርእዮተ ዓለማዊ ትንተናዎችን እንደሚሻ የዘነጉት ይመስላል። በአንድ በኩል አንድም ርእዮተ ዓለማዊ ታማኝነት የሌላቸው የፖለቲካ ደላሎች ፓርቲ እያቋቋሙ አደባባይ ሲቆሙ ማየት ስለፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን ስለማኅበረሰባችንም ብዙ ነገር ይናገራል። በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካን የምር ይዘው ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ሰዎች አዲሱን እውነት በብቃት የሚተነትን እና አዲሱን ትውልድ የሚያሳምን ርእዮተ ዓለማዊ ምልከታ ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት አናሳ ነው። ምሁራኑ ገና ርእሰ ጉዳዩ ሊጠና እንደሚገባውም ያስታወሱ አይመስልም፤ አለዚያም ጥናቶቻቸውን አላደረሱን ይሆናል።

በእኔ እምነት የብሔር ጥያቄ በፖለቲካው መድረክ አንኳር ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ይቆያል። ሆኖም ጥያቄው በ1960ዎቹ በተነሳበት ስሜት እና ግብ በአሁኑ ሁኔታ ትርጉሙን ያጣ አሮጌ ንትርክ ነው። ጥያቄው አግባብ ሆኖ ለውይይት የሚጋብዘውና መሠረቱ ሊሰፋ የሚችለው የኢትዮጵያ አንድነት ተቃራኒ ተደርጎ ካልቀረበ ብቻ ነው። በተቃራኒውም እውነታው ተመሳሳይ ነው። ይህ የርእዮተ ዓለምም የስልትም ለውጥን ይጠይቃል። በዚህ በኩል ኢሕአዴግም ሆኑ ሌሎቹ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች የርእዮተ ዓለም ሽግሽግ ማድረጋቸው በግልጽ የሚታይ ነው። ሽግሽጉ ከልብ ይሁን ካንጀት ለመፈተን የሚያስችል የውይይት መድረክ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ተገቢ ሽግሽግ ነው።

የዚያኑ ያህልም የብሔር ጥያቄ መኖሩን ከጅምሩ የማይቀበል ያለውን ያህል ጥያቄው መኖሩን ነገር ግን ከኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ሊፈታ እንደሚቸል የሚያምን አለ። ከዚህ በተለየ ግን የቀደመውን የመደብ ክርክር በመተው፤ በምትኩ የሊበራሊዝምን የግለሰብ ነጻነት ፍልስፍና በመተርጎም የብሔር ጥያቄን የማይቀበለው አመለካከት የበለጠ ጠንካራ ሆኖ የመውጣት አቅም ሊያገኝ ይችላል። ወቅቱ የብሔር ጥያቄ አመለካከት የፖለቲካ ስልጣን የያዘበት በመሆኑ ካልሆነ ይህ አመለካከት ዋናው ተፎካካሪ መሆኑ የማይቀር ነው። በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ ነጠላ የሊበራሊዝም ፍልስፍና ዘለላዎች ቀስ በቀስ የአገሪቱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅኝት ተቀላቅለዋል፤ ከጊዜው አኳያም በተለይ በከተሞች ለመታወቅ ችሏል። ይህም የኢኮኖሚ አማራጩንም በስፋት ለውጦታል። ኢሕአዴግ እና በአጠቃላይም የግራ ግራው ሁሉንም “በደርግነት” ቢፈርጅም ዋናው ርእዮተ ዓለማዊ ተግዳሮት እየመጣበት የሚገኘው ከሊበራሊዝም ነው (ሁሉንም በደፈናው ኒዎሌበራል እያለ የሚጠራውን የምርጫ ማጭበርበሪያ ትተነው መሆኑ ነው፤ ውሸት ስለሆነ።)

እዚህ ላይ “አማካይ” ርእዮተ ዓለማዊ አማራጫ መቅረብ/መገኘት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገራል። ተገቢም ነው። እኔም ይህን እደግፋለሁ፤ ፖለቲካ በአንድ በኩል ሙከራ ስለሆነም ጭምር። ነገር ግን ሁሉም በአማካይ ፍለጋ ብቻ መጠመድ የለበትም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ወይም የተሻለው አማራጭ አማካዩ ላይሆን ይችላልና። ለዚህም ነው በሌኒናዊ ግራ አመለካከት ታፍኖ የቆየው ፖለቲካ በመሠረቱ የተለየ የሆነውን የቀኝ/ሊበራል አመለካከት ለማስተናገድ ረጅም ጊዜና ትግል ያልጠየቀው። ከትምህርት እና ከከተሜነት መስፋፋት ጋራ የሚወለዱ አዳዲስ ፍላጎቶች ተፈጥረዋል፣ ይፈጠራሉም። ስለዚህም እነርሱን ርእዮተ ዓለማዊ ቅርጽ እየሰጡ የሚተነትኑ አማራጮች ያስፈልጋሉ።

በመጨረሻ አንድ ሌላ ጥያቄ ላንሳ። ለመሆኑ “ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከርእዮተ ዓለም በላይ የህልውና ጥያቄ አለባት” ለሚሉት ሰዎች ምን ምላሽ አለ? ለካስ ይህም ራሱ ርእዮተ ዓለማዊ አቋምን ታሳቢ ያደረገ ክርክር ነው!

[በነገራችን ላይ]

ሰሞኑን ባለሥልጣናት ንብረታቸውን ማስመዝገብ መጀመራቸው ተዘግቧል። ለሌሎቹም አርአያ መሆን የሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ንብረታቸውን አስመዝግበው ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል መባሉ ተሰምቷል። እሰየው የሚያሰኝ ዜና ነው። ብዙዎች ግን ጓጉተዋል። የአቶ መለስ ንብረት ዝርዝር ምን ይሆን? መቼም የባንክ ደብተር አይኖራቸው። በስማቸው የተመዘገበ ንብረት ይኖራቸው ይሆን? ከየት አምጥተው! ሀብታቸው መጻሕፍት ብቻ ናቸው። ምስኪን። “ሲጋራ እንኳን የምትገዛለት እኮ ሚስቱ ናት” አለኝ አንድ የእርሳቸው ብጤ ምስኪን።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ነርሶችን የምትገፋም “የምትሸጥም” አገር

የሥራ አጥ ቁጥሩ ምጣኔ በዓመት በ20 በመቶ እየተመነደገ ኢሕአዴግ የጉልበት ሠራተኞችን ጭምር ከውጭ ለማስመጣት ያቅዳል፤ ከመቶ ዓመታት በፊት የተዘረጋ የባቡር መሥመር ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ያለ አሳቢ እና ያለ አስተዋይ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንኳ ሳይጠገን ተዘግቶ፤ በድንገት ከ6000 ኪሎ ሜትር በላይ የሚኾን የባቡር መሥመር ለመዘርጋት አምስት ዓመት ብቻ በቂ ነው የሚል ሐሳብ ይደመጣል። በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት መካከል እናደርሳታለን የሚለው የኢሕአዴግ ዲስኩር ተነግሮ ሳያበቃ በሸቀጦች የዋጋ ውድነት እና በፖለቲካዊ ነጻነት ዕጦት ኑሮውን መቋቋም የከበደውን ማኅበረሰብ ለልማቱ መዋጮ ማድረግ አለብህ በሚል ስብከት ሊያጠምቁት ካድሬዎች ቁጭ ብድግ ይላሉ። ኢሕአዴግ እያለፈባቸው ያሉት ተቃርኖዎች ብዙ ናቸው።

This post is available in: ኸንግሊስህ

ነፍሰ ጡር በቃሬዛ ተሸክሞ አዋላጅ ፍለጋ ብዙ ማይል ማቋረጥ እና መንከራተት ዛሬም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያልተነካ እና ያልተቀረፈ ችግር ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በሰፊው እያሰማራሁ ነው የሚለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገና ያልደረሰባቸው እና መፍትሄ ያላገኘላቸው የኤችአይቪ እና የወባ በሽተኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ባለፉት ዓመታት ከድርቅ ጋራ በተያያዘ ለረኀብ ከተጋለጡት 13 ሚልዮን በላይ ዜጎች ውስጥ ለችጋር በሽታ የተጋለጡትንም መንግሥት የቁጥር መከራከርያ የመጫወቻ ካርድ አድርጓቸው ነበር። ከጤና ጋራ በተያያዘ በየጊዜው ለሚታየው ችግር አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫ በቂ የኾነ የጤና ባለሞያ በየክልሉ እና በየገጠር ወረዳዎች እንዲዳረስ ማድረግ ነው። ሰሞኑን የተሰማው ዜና ግን “ሳይተርፋት ታበድር ሳትቀበል ሞተች” የሚባለውን ተረት እውነት የሚያደርግ ይመስላል፤ መንግሥት ነርሶችን እያሠለጠነ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ ላይ ሊሰማራ ነው።

ይህን መረጃ የወጣው በዚህ ሳምንቱ የሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ ዕትም ላይ ነው።  አስገራሚው ዜና የኢሕአዴግን የፖሊሲ አቅጣጫ ውድቀት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። እንደ ጋዜጣው ዘገባ መንግሥት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ነርሶች ለውጭ ገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጭ የማድረግ ዕቅድ አለው። በመጀመርያው ዙርም 200 ያህል ነርሶችን ለይቶ ለመላክ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጽፏል። ይህ ዐይነቱ ዕቅድ እንደ አገር ሲታይ መጥፎ ተብሎ የሚታሰብ ወይም በራሱ ሐሳቡ ችግር ያለበት አይደለም። ነገር ግን ችግር ኾኖ የሚወጣው ኢኮኖሚያዊም ኾነ ማኅበራዊ ትርፍ ለማምጣት የሚያስችል ደረጃ ላይ የሌለውን የኢትዮጵያን የሕክምና ዘርፍ ለትርፍ ማጨቱ እውነት ሲኾን ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕክምና የጥራት ደረጃ አጠያያቂ ኹኔታ ውስጥ ባለበት እና በቂ የኾኑ የሕክምና ባለሞያዎችን በአግባቡ ማሰማራት ካልተቻለባት አገር ነርሶችን አሠልጥኖ መላክ የአመራር ችግር መኖሩን ማሳያ ነው።

ለዚህ ወለፈን አንዱ ማሳያ በሕዳር ወር ይፋ የተደረገው የወርልድ ባንክ መረጃ ነው። “Migration and Remittances Factbook 2011” በሚል ርዕስ ሥር የተቀመጠው መረጃ እንዲህ ይነበባል፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሠለጠኑት 26.4 በመቶ የሚኾኑት እና በዚያው በኢትዮጵያ ውስጥ ከተወለዱት 29.7 በመቶ የሚኾኑት ዶክተሮች በስደት ላይ የሚገኙ ሲኾን  እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ለሌሎች አገራት የሚገብሩ ናቸው። እነዚህን ዶክተሮች ጨምሮ በነርሲንግ የሠለጠኑ ባለሞያዎች ለስደት የተዳረጉት በአነስተኛ ክፍያ፤ በሞያዊ ነጻነት ዕጦት እና በአስተዳደራዊ ብልሹ አሠራር ምክንያት ነው። በየጊዜው ለሚጨምረው የጤና ባለሞያዎች ፍልሰት ይህ ችግር ያለው አሉታዊ አስተዋጽዖ እንደ ቀላል የሚወሰድ አይደለም። አኀዙንም እያሻቀበው ነው።

የብሉይዎቹም (Classical) ኾኑ ወቅታዊ የኾኑት የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች የዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዐትን በተመለከተ የሚያስማማ ኀልዮት አላቸው። አንድ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሸቀጥ አቅራቢው አገር ካለው አንጻራዊ አብላጫ ታይቶ የሚመዘን ነው፡፡ የሸቀጡ በአገር ውስጥ ተትረፍርፎ መገኘት፣ ከሌሎች አጋራት ጋራ ሲነጻጸር አነስተኛ የኾነ የምርት ወጪ ማስከተል መቻሉ፣ በሌሎች የአገር ውስጥ ሀብቶች የሚተካ መኾኑ እና ሸቀጡን በመላክ የሚገኘው ጠቀሜታ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ኪሳራዎችን ለመሸፈን የሚያስችል መኾኑ ግምት ውስጥ የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው፡፡

ከእነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ኢትዮጵያ ስትፈተሽ ነርስ “ለመሸጥ” የሚያስችል የተግባርም ኾነ የኀልዮት ብቃቱ የላትም፡፡ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው የ2010 ዓ.ም መረጃ ኢትዮጵያ ያሏት የጤና ባለሞያዎች ቁጥር አገሪቷ ካለባት ከፍተኛ የጤና ችግር ጋራ ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዶክተር ለ20 ሺሕ ሰዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ግዴታው ሲኾን ለ10 ሺሕ ዜጎች እንዲሁ በተመሳሳይ ሁለት ነርሶች ብቻ ናቸው የተዘጋጁት፡፡ አንድ የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያ 10 ሺሕ ዜጎችን እንዲያገለግል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም በጤና ባለሞያዎች እና በማኅበረሰቡ ያለውን የአገልግሎት ጥመርታ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ሳይቀር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል።

ዛሬ የዓለም አቀፍ ሽያጭ ጉዳይ የተነሳባቸው የነርሶችም ስደት ቁጥር ከሌሎች አገራት ጋራ ሲነጻጸር ከፍተኛውን ምጣኔ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሠለጠኑት ነርሶች መካከል 16.8 በመቶ የሚኾኑት በስደት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ያፈጠጠው እና ያገጠጠው እውነታ ይህ ኾኖ ሳለ አገሪቷ በባለሞያዎች በቁጥርም በጥራትም ራሷን ሳትችል የባለሞያ ሽያጭ ውስጥ እንድትገባ መታሰቡ መንግሥት አሁንም በጥናት ላይ የተመሠረተ እና ዘላቂ የኾነ መፍትሄ ማምጣት በሚችል ዕቅድ ላይ ከመመሥረት ይልቅ ከ“ድንገቴ” ዕቅድ ምትኀት ሊወጣ አለመቻሉን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይኹንና ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ኾኖ የሚቀጥል ከኾነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክትባት የሚሰጥም ባለሞያ ማግኘት ሕልም ይኾናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና ችገር ለመፍታት እና የጤና ባለሞያዎችን ፍልሰት ለመቀነስ ፖሊሲ መቅረጽ  ያስፈልጋል የሚል ተማጽኖ ሲቀርብ ነበር። ችግሩን ለመቅረፍ ከቀረበው የፖሊሲ አማራጭ ይልቅ መንግሥት ነርሶችን በመላክ የንግዱ አንደኛው ተዋናይ በመኾን ከሐሳቡ በተቃራኒ ቆሟል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖሊሲዎች እና የአሠራር የእርስ በርስ መጣረስ እየበዛ ነው፡፡ ስለ “አምስት ዓመት የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” መስበክ የጀመረው ኢሕአዴግ አገሪቷን ጥበብ ከተሞላበት እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ካገናዘበ መፍትሄ እና ዕቅድ ይልቅ በተዐምራት ወደፊት ሊያሠግራት እንደሚችል የሚያሳየው በተቃርኖዎች ውስጥ ኾኖ ነው፡፡

የሥራ አጥ ቁጥሩ ምጣኔ በዓመት በ20 በመቶ እየተመነደገ ኢሕአዴግ የጉልበት ሠራተኞችን ጭምር ከውጭ ለማስመጣት ያቅዳል፤ ከመቶ ዓመታት በፊት የተዘረጋ የባቡር መሥመር ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ያለ አሳቢ እና ያለ አስተዋይ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንኳ ሳይጠገን ተዘግቶ፤ በድንገት ከ6000 ኪሎ ሜትር በላይ የሚኾን የባቡር መሥመር ለመዘርጋት አምስት ዓመት ብቻ በቂ ነው የሚል ሐሳብ ይደመጣል። በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት መካከል እናደርሳታለን የሚለው የኢሕአዴግ ዲስኩር ተነግሮ ሳያበቃ በሸቀጦች የዋጋ ውድነት እና በፖለቲካዊ ነጻነት ዕጦት ኑሮውን መቋቋም የከበደውን ማኅበረሰብ ለልማቱ መዋጮ ማድረግ አለብህ በሚል ስብከት ሊያጠምቁት ካድሬዎች ቁጭ ብድግ ይላሉ። ኢሕአዴግ እያለፈባቸው ያሉት ተቃርኖዎች ብዙ ናቸው።

በዚህ ወቅት የጤና ባለሞያዎቹ የጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆል እና ከሕዝቡ ቁጥር ሥግረት ጋራ አለመመጣጠን ትልቁ መነጋገርያ በኾነበት ወቅት የሕክምና ባለሞያዎች ሽያጭ ወደ አደባባይ ብቅ ማለቱ ችግሩን ለማቀጣጠል ተጨማሪ ግብዐት ይኾናል፡፡ መንግሥት የጤና ባለሞያዎችን ቁጥር በማብዛት የማኅበረሰቡን ጤና መጠበቅን ዋነኛ ግብ ማድረግ ሲገባው በተቃራኒው እየተጓዘ መኾኑ ብዙዎችን ማስገረሙ አልቀረም፡፡

መንግሥት መድረክ ላይ እንደሚናገረው የባለሞያዎችን ሽያጭ (በቀጣይም የማኅበረሰብ ሳይንስ ተማሪዎችን ለመላክ ዕቅድ እንዳለው ሪፖርተር ጠቅሷል)  አንዱ የውጪ ምንዛሬ ማስገኛ መንገድ ሊያደርገው ይመስላል፡፡ በርግጥ አገሪቷ ውስጥ የመሥራትም ኾነ በሰላም የመኖርን ነጻነት ተነፍገው በስደት የሚገኙ ዜጎች ለአገሪቱ የሚያስገኙት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የሚካድ አይደለም፡፡ በየጊዜው የሚወድቅ የሚነሳውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት በመደጎም አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ከ40 ሚልዮን ዶላር አልፎ የማያውቀው በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚገኘው ገንዘብ በአሁኑ ወቅት 3.5 ቢልዮን ዶላር ደርሷል፡፡

ይህ ገንዘብ ለአጭር ጊዜ ችገሮች ማስተንፈሻ መጥቀሙ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ለሚስተዋለው የሠለጠነ ባለሞያ እጥረት እንዲሁም ይኼን ተከትሎ በረዥም ጊዜ ውስጥ ለሚከሰተው የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉስቁልና እና ምስቅልቅል ማካካሻ ሊኾን ግን አይችልም፡፡ የዛሬ የባለሞያዎች ዕጦት ነገ በምንም መልኩ ሊመለስ ወደማይችል ችግር መንዳቱ ግልጽ ነው፡፡ እስከዚያው ግን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕሙማንን ለመስዋዕትነት አቅርቦ “ነርስ የመሸጥ ንግድ” ላይ ሊሰማራ ያሰበ መንግሥት አፍርተናል።

One Response to “ነርሶችን የምትገፋም “የምትሸጥም” አገር”

  1. Lovely!
    Gebrielin ye Arada lij neh!!!

  2. A very nice writing. Big thanks for the author.

Leave a Reply

You must be to post a comment.

Bad Behavior has blocked 572 access attempts in the last 7 days.