መሀመድ ሰልማን
ደብረብርሃን፣ ባኬሎ፣ ጣርማ በር፣ መዘዞ፣ ማዞርያ፣ ጓሳ፣ መሀል ሜዳ፡፡ እነዚህ ወዳልተዘመረለት የጓሳ ምድር የሚያደርሱ የኢትዮጵያ ትንንሽ ከተሞች ናቸው፡፡ አዲስ አበባን መነሻ ካደረግን 260 ኪሎ ሜትር መራቅ ይኖርብናል፡፡ ይህ ድንቅ ስፍራ እንደ አክሱም ሽቅብ የተቀሰረ ሀውልት የለውም፤ እንደ ላሊበላ በፍልፍል ድንጋይ አልታነፀም፤ እንደ ኤርታሌ የሚንተከተክ ላቫ አልፈጠረበትም፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ የተዘረጋ የፕላቶ ሸንተረር ነው፡፡ ግን ልብን ወከክ የሚያደርግ፣ ቢያዩት ቢያዩት የማይጠገብ እንዲሁም የማያልቅ፣ እንዲሁም የማይደክም ግን ደግሞ ሩቅና ሰ…ፊ!

ፈጣሪ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ሲባል መጀመርያ የተዘረጋው የተራራ ሰንሰለት ይህ ስፍራ መሆን አለበት አልኩ፤ለራሴ፡፡
ተፈጥሮን አይቶ ዝም ማለት እንጂ በንግግር አልያም በጽሑፍ ለመተንተን መሞከር ከንቱ ነው፡፡ የሕንጻን ውበት ስንት ጡብ እንደፈጀ፣ ስንት ማገር እንዳቆመ፣ ስንት ብር እንደተከሰከሰበት፣ እየተነተኑ ማዳነቅ ብዙ ጥረት አይጠይቅም፡፡ እንደ ጓሳ ያለ ዝም፣ ዥው ያለ ተፈጥሮን ግን ምን ብለው ይገልጹታል?
የአቶ መለስ እርጥብነት
የጓሳ ጎረቤት ከተማ “መሀል ሜዳ” ትባላለች፡፡ መብራት፣ ውሀ፣ ሆስፒታልና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን እንደአቅሚቲ ያሟላች የገጠር ከተማ ነች፡፡ ያሳለፍነው ምርጫ ከመካሄዱ ወራት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ተገኝተው ከጎበኟቸው ትንንሽ የሰሜን ሸዋ ከተሞች አንዷ ይቺው “መሀል ሜዳ” ነበረች፡፡
“ምንድነው የሚቸግራችሁ?” እያሉ አቶ መለስ ከገበሬዎች ጋር በአግዳሚ ወንበር ቁጭ ብለው መከሩ አሉ፡፡ የሰሜን ሸዋ ሕዝብ አንድ የአገር መሪ በዚህን ያህል ቅርበት ሲያናግረው የመጀመርያው በመሆኑ ጉድ አለ፡፡ መብራት ሃያ አራት ሰዓት እንዲሆን፣ ቴሌቪዥን እንዲዳረስ፣ መንገድ እንዲወጣ ወዘተ እያለ “አሉብኝ” የሚላቸውን አንገብጋቢ ችግሮች ለእርሳቸው በፊት ለፊት ተናገረ፡፡ እርሳቸውም አንዳች ሳያስቀሩ በቢክ እስክሪብቷቸው በመጻፍ ማስታወሻ ያዙ፡፡ ይህ የሆነው ታድያ በወርሃ ሚያዝያ ነበር፡፡
ይህንን ሁኔታ በወቅቱ በቅርበት የተከታተለው በኀይሉ ደምሰው የሚባል ልጅ-እግር ገበሬ ታድያ ስለእርሳቸው ታላቅነት ሲናገር ቃላት ያጥረዋል፡፡ “እርሳቸው እርጥብ መሪ ናቸው፤ ሚያዝያ እዚህ እንደመጡ ጀምሮ ዝናብ በዝናብ ሆነናል፡፡ ይኸው የእርሳቸው እርጥብነት በዓመት ሁለት ጊዜ እንድናመርት አስችሎናል፡፡ መብራቱንም ቃል በገቡት መሰረት 24 ሰዓት አደረጉልን፡፡ የተባረኩ መሪ ናቸው፡፡ ለምርጫ ግልብጥ ብለን ነው የመረጥናቸው” ሲል አድናቆቱን ገለጸልኝ፡፡ “የጃንሆይና የጃማይካ ታሪክ ጓሳ ላይ ተደገመ?” አልኩኝ በሆዴ፡፡
አቶ መለስ “መሀል ሜዳ” የመጡ ጊዜ ታድያ ሰውየው ያረፉበት ስፍራ “ሕይወት ሆቴል” በሚባል አነስተኛ የገጠር መዝናኛ መሆኑ ተነግሮኝ ይህንኑ ለማረጋገጥ ሄድኩኝ፡፡ ሆቴሏ በከተማዋ መሀል ትገኛለች፡፡ ሙሉ በሙሉ የጭቃ ቤት ስትሆን ጥግ ጥጉን የተሰሩ ወደ ጎን ያዘመሙ መኝታ ክፍሎችና አንድ ምግብ ቤት በውስጧ ይዛለች፡፡ የሆቴሉ እመቤት የሀበሻ ቀሚስ አድርገው፣ ግዙፍ መነፅራቸውን ደቅነው ለምሳ ቤታቸው የተገኘውን ሰው ለማብላት ተፍ ተፍ ሲሉ አገኘኋቸው፡፡
ስለ አቶ መለስ ሳነሳባቸው ከመቅፅበት ትኩረታቸውን ወደ እኔ አዞሩት፡፡ “እውን አቶ መለስ በዚህች ቤት አድረዋል?” ስል ጠየቅኳቸው፡፡ “ማደርስ አላደሩም..” አሉና ወይዘሮዋ ጫወታ ጀመሩ፡፡ “እርሳቸው እዚህ አላደሩም፡፡ ግን ምሳ ያዘጋጀሁላቸው እኔ ነኝ፡፡ እዚህ አንተው የተቀመጥክባት ቦታ ላይ እኔ ያዘጋጀሁላቸውን የፆም ብፌ ነው የበሉት፡፡ እጄ ጣፍጧቸው ነው የበሉልኝ፡፡”
“ስንት ብር አስከፈሏቸው?” ስል ጠየቅኳቸው፡፡ አማተቡ፡፡ “እርሳቸውን አላስከፍልም፤ ለምን ብዬ፡፡ ብሩን የከፈሉኝ የወረዳው አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡”
“መለስን ታድያ ምንም አላሉትም?”
“በልቶ ሲጨርስ አድናቂዎ ነኝ፡፡ (መለስን አንተም አንቱም እያሉ ነው የሚጠሩት) ይኸው የቁልፍ መያዣዬም አንተው ነህ ብዬ…(ንግግራቸውን አቋርጠው ወደ ሂሳብ መቀበያው በመሄድ መሳብያው ላይ ተሰክቶ የነበረውን ቁልፍ ይዘው መጡ) ይህችን የሱ ምስል ያለባትን ቁልፍ አሳየሁት፡፡ ሳቀና ፈረመልኝ፡፡ ፈጣሪ ይጠብቅህ ብዬ መርቄ ሸኘሁት፡፡”
በአካባቢው ካገኘኃቸው ገበሬዎች ውስጥ በአመዛኙ በአቶ መለስ ጉብኝት ከደስታቸው ያልተላቀቁ ነበሩ፡፡ የተወሰኑት ግን አንድ ቁጭት አለባቸው፡፡ “ጓሳን ቢጎበኝልን እንዴት ሸጋ ነበር” ይላሉ፡፡ ጓሳ መከበሪያቸው ናት፡፡ ጓሳ የክብር ማሳቸው ናት፡፡ ይህችን ድንቅ ስፍራ ታድያ እኚህ “እርጥብ መሪ” አላዩላቸውም፡፡ ይህ ልክ እንደ ጓሳ ሳር ዘወትር ይቆጠቁጣቸዋል፡፡፡
የጓሳ ማኅበረሰብ
በብዙኀን መገናኛ ብዙ የተዘመረለት የአውራምባ ማኅበረሰብ ነው፡፡ የጓሳ ማኅበረሰብ ግን ብዙ ያልተዘመረለት ራሱ የቀመረው ድንቅ ባህል እንዳለው ተረድቻለሁ፡፡በተለይ የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ፡፡
በጓሳ ሰንሰለታማ ተራሮች የሚገኘውን ማንኛውምንም የተፈጥሮ ሀብት የነካ ጉድ ፈላበት፡፡ የጓሳ መንዞች በዚህ ቀልድ አያውቁም፡፡ “እረገነ !›› ብለው ይዝታሉ፡፡ ይህ የመጨረሻ ቁጣቸውን የሚገልጹበት ቃል ነው፡፡ የሚገርመው የአካባቢው ነዋሪዎቸ እንደ “አጣዬ” ካሉ ዝቅተኛ ቦታዎች ከብት ገዝተው በጓሳ ሲያልፉ እንኳ የበጎችን አፍ በቆዳ ሸብበው ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፤ ምንም አይነት ጉዳት በአካባቢው እጽዋቶች እንዳያደርሱ፡፡
መንዞች ድሮም በቃላቸው ያደሩ፣ ከዛቱ የማይመለሱ፣ በበቀል የሚንተገተጉ ህዝቦች ናቸው ይባላል፡፡ የልጆቻቸው ስሞችም ይህንን ለማመልከት የተቀመሩ ይመስላሉ፡፡ ደምሰው፣ ዳምጠው፣ በኀይሉ፣ እርገጤ፣ ደምመላሽ የሚሉት ስሞች እጅግ የሚዘወተሩ ናቸው፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር በኢኮ ቱሪዝም ልማት ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች እንደሚሉት ህዝቡ በተለይ በጓሳ ተራሮች ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ነካህበት ማለት በአይኑ መጣህበት እንደማለት ነው፡፡

መንግሥታት ተቀያይረዋል፡፡ የጓሳ ማኅበረሰብ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ያለው አቋም ግን አልተቀየረም፡፡ ጥናቶች እንደሚያስረዱት የጓሳ-መንዝ ሕዝብ ለተፈጥሮ ጥበቃ ማድረግ የጀመረው አሁን ሳይሆን ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ዙርያ ተጠቃሽ የሆኑ ጥናቶች የጓሳን ማኅበረሰብ ከሰሀራ በታች ካሉ ለተፈጥሮ ጥበቃ ንቃት ካላቸው ማህበረሰቦች ቀደምቱ ሲሉ ይጠቅሱታል፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱን ያለማንም እገዛ የሚጠብቅበት የራሱ የሆነ ስርዓት አለው፡፡ ይህም የ”ቀሮ ስርዓት” ይባላል፡፡ በ”ቀሮ ስርዓት” መሰረት ማንኛውም በጓሳ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ከሦስት እስከ አምስት ተከታታይ ዓመታት ተጠብቆ ይቆያል፡፡ ይህ ጥበቃ የጓሳ ሳርን የሚያካትት ሆኖ ማንኛውንም ግጦሽ ወይም አጨዳ በዓመት ከጥቅምትና ህዳር ወር ውጭ ማካሄድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
አጥባቂ የኦርቶዶክስ አማኝ የሆነው የጓሳ ማኅበረሰብ በተለምዶ በየዓመቱ ከሐምሌ 12 ጀምሮ የሐዋርያት ፆም ሲፈታ ጓሳ ለጥበቃ ዝግ መሆኑን ያውጃል፡፡ ከዚህ ቀን በኃላ ማህበረሰቡ በመረጣቸው ሚሊሻዎች አካባቢው ይጠበቃል፡፡ ማንኛውንም በጓሳ ተራሮች ውስጥ የሚገኝን ተፈጥሮን መነካካት ፍፁም ክልክል ሆኖ ይቆያል፡፡
በነገራችሁ ላይ ጓሳ የሳር ስም ነው፡፡ በመንዝና አካባቢው ይህ የሳር አይነት ከእያንዳንዱ ነዋሪ ጋር ጥልቅ ቁርኝት አለው፡፡ በተለምዶ ከሚታወቀው የሳር አይነት ዘለግ ያለና ከርደድ ያለ ሆኖ ለልዩ ልዩ ተግባራት የሚውል የሳር አይነት ነው፤ ጓሳ፡፡ ማኅበረሰቡ ይህንን ሳር ለግጦሽ፣ ለሳር ክዳን ቤት መስሪያ፣ ለጭቃ ግድግዳ መስሪያ፣ ለአለንጋና ገመድ መስሪያ፣ ለማገዶና ምግብ ማብሰያ፣ለኮፍያ፣ ጊሳ ለሚባል የዝናብ ልብስ ፣ ሙሬ ለሚባል የቤት መጥረጊያ መስሪያ ይጠቀሙበታል፡፡ ሕዝቡ ዝተትና በርኖስን ከበግ እየሸለተ የመስራት ልምድም አለው፡፡
በጓሳ ምድር “የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ” የሚለው ግጥም እምብዛም ትርጉም የለውም፡፡ አደይ አበባ በጓሳ እንደ አረም ዝም ብሎ መቼም የሚበቅል ነው፡፡ በተራ የግጦሽ መሬት እጅግ የሚያማምሩ በተለያዩ ቀለማት ያጌጡ የአበባ ዝርያዎች ወፍ ዘራሽ ሆነው ይበቅላሉ፡፡ ከአበቦቹ መሀል ደግሞ ጅብብራ የተሰኘው ዘምባባ መሰል ተክል ግትር ብሎ በየተወሰነ ርቀት ይታያል፡፡
የጓሳ አውቶብሶች
ይህ ማኅበረሰብ ችግር ሲገጥመው ይሰበሰባል፡፡ “እስቲ መላ ምቱ” ለማለት፡፡ ከደብረብርሃን እስከ ሞላሌ ትራንስፖርት ቢኖርም ሕዝቡ ከሞላሌ እስከ መሀል ሜዳ በሰው ጉልበትና በጋማ ከብት እቃ ማጋዝ ሰለቸው፡፡ “መላ በሉ” ተባለ፡፡ የማኅበረሰቡ ሽማግሌዎች መላ ዘየዱ፡፡ እያንዳንዱ የጓሳ አባል አንድ በግ አዋጣ ተባለ፡፡ አንድ እንደጓሳ ሳር የጠነከረ “ኤንትሬ” የጭነት መኪና ተገዛ፡፡ በጎች ተደማምረው “ኤንትሬ” ሆኑ፡፡ አካባቢው የሚታወቅበትን ዝተትና ቂቤን እንደልቡ ማጓጓዝ ቻለ፡፡ ወደ አጎራባች አገሮች፡፡ በኤንትሬው፡፡
ደግሞ በሌላ ጊዜ ወደ አካባቢው የሚመጡ አውቶብሶች ሲሻቸው ዋጋ እየጨመሩ፣ ሲላቸው አንሄድም እያሉ ተሳፋሪውን አንገላቱት፡፡ የጓሳ ሕዝብ ተቀየመ፡፡ “መላ ምታ” ተባለ፡፡ እንደተለመደው በግ አዋጣ ተባለ፡፡ በጎች ተደምረው “ካቻማሊ” ሆኑ፡፡ አራት ምን የመሳሰሉ ፈጣን ካቻማሊዎች ተገዙ፡፡ አሁን ታድያ የጓሳ መንዝ ሕዝብ ያለው እየከፈለ የሌለው እየተመዘገበ በካቻማሊው ሽር ይላል፡፡ የአካባቢው ሰዎች ተመኩ፤ በጓሳ አውቶብሶች፡፡ በማኅበረሰባቸው፡፡
የጓሳ ብርቅዬዎች
111 የወፍ ዝርያዎች በጓሳ ይገኛሉ፡፡ አልተሳሳትኩም፤ አንድ መቶ አስራ አንድ። በጠቅላላው በኢትዮጵያ ከሚገኙት 861 የወፍ ዝርያዎች ታድያ 12 ከመቶ የሚሆኑት መገኛቸው ጓሳ-መንዝ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ብርቅዬ አእዋፋት ውስጥ 45 በመቶ ያህሉ የሚገኙት ጓሳ ነው፡፡ በቁጥር 14 የሚሆኑ በአገራችን ብቻ የሚገኙ ወፎች መኖርያቸው ጓሳ ነው፡፡ በተለይም አንኮበር ዘረበል ወፍ (Ankober Serin Serinus) እና ደረተ ነጠብጣብ ኩሊሊት (Spot breasted Plover) የተባሉት በምድራችን ላይ በመጥፋት አደጋ ላይ ናቸው ከሚባሉት ውስጥ የሚመደቡት አእዋፋት መገኛቸው ጓሳ ብቻ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ከሰሜናዊ ዋልታና ከአፍሪካ በአየር ንብረትና በወቅቶች መፈራረቅ የሚሰደዱ 38 የሚሆኑ አእዋፋት መናኸሪያ ናት፤ ጓሳ፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ብቻ መገኛውን ያደረገው ጭላዳ ዝንጀሮ (gelada baboon) ከሰሜን ተራራዎች ቀጥሎ ሌላ መገኛው በጓሳ-መንዝ ነው፡፡ ቁጥሩ ከ 500 እስከ 1400 ይደርሳል የሚሉ ጥናቶች አሉ፡፡ በጓሳ የሚገኙት የጭላዳ ዝንጀሮዎች “ባለደም ልብ (bleeding hearts)” የሚባሉት መሆናቸው በጎብኚዎች ተመራጭና ብርቅዬ ያደርጋቸዋል፡፡ ደረታቸው ላይ ባለው የልብ ቅርጽ ያለው ቀይ ቆዳ የተነሳ “ባለደም/የሚደማ ልብ” የሚለው ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
የጭላዳ ዝንጀሮዎቸ አኗኗር በራሱ መሳጭ ገፅታ አለው፡፡ እስከ አራት የሚጠጉ ወንዶችና እስከ አስር የሚጠጉ ሴቶች እንዲሁም በእነርሱ ስር ያሉ ጥገኛ የቤተሰቡ አባላት በአንድ ላይ የመኖር ልምድ አላቸው፡፡ የቡድኑ ታላላቅ አባላት የቤተሰቡን አባላት ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የጓሳ ሳርን እንደ ሰው እጭድ እያደረጉ ሲቅሙት በቅርብ ማየት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡
የጓሳ ብርድና የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ
የጓሳ ብርድ አይጣል ነው፡፡ በተለይ የሌሊቱን የጓሳ ቅዝቃዜ የሰሀራ በረሃ አይመልሰውም፡፡ በየዓመቱ መስከረም፣ ጥቅምትና ህዳር ጓሳ ከፍተኛ ብርዳማ ሌሊቶችን ታስተናግዳለች፡፡ ከዜሮ በታች እስከ 10 ዲግሪ ሴንትገሬድ ቅዝቃዜ ከሚመዘገብባቸው የኢትዮጵያ ጥቂት ከተሞች አንዱ ጓሳ-መንዝ ነው፡፡ የጓሳ ተራሮች ቀን ቀን በውብ ጥጥ መሰል ጭጋግ ይጋረዳሉ፡፡ ይሄኔ እጅግ አስገራሚ ዉበት ይፈጠራል፡፡ ምሽት ግን ፈረንጅን ምንጃርኛ የሚያስደንስ ብርድ ይነግሳል፡፡
የመንዝ ነዋሪዎች ይህንን የማይታመን ቅዝቃዜ ለመከላከል በሹራብ ላይ ጃኬት፣በጃኬት ላይ ኮት፣ በኮት ላይ ዝተት፣ በዝተት ላይ ካፖርት፣ በካፖርት ላይ ደብረብርሃን ብርድልብስን ደርበው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በአካበቢው ባለ ትምህርት ቤት መምህራኑም ተማሪዎቹም በብርድልብስ ተጀቡነው ነው የሚማማሩት፡፡ አንድ መንግስታዊ ቢሮ ቢገቡ ስራ አስኪያጁ በተሸከርካሪ ወንበር ውስጥ በብርድልብስ ራሱን ቀብሮ ያገኙታል፡፡ ለሰርግ ተጠርተው ቢሄዱ እድምተኞቹ በሚያማምሩ ባለቀለም የደብረ ብርሃን ብርድልብስ ተሸሞንሙነው ያገኟቸዋል፡፡
ጓሳ፡ የቀይ ቀበሮዎቹ ምቾት
ጓሳ ከባህር ጠለል በላይ ከ3200-3700 ከፍታ ላይ የረጋ ስፍራ ነው፡፡ ብርቅዬዎቹ ቀይ ቀበሮዎች ታድያ እንደጓሳ የሚመቻቸው ማረፍያ የላቸውም፡፡ ከዘመድ ወዳጅ ሊጠያየቁ በየምሽቱና ንጋት ላይ ከ4 እስከ 9 ቀበሮዎች ሆነው በቡድን ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሚያጠቃ ጦር ከመጣ በሚል ነው ሁልጊዜ በቡድን የሚንቀሳቀሱት፡፡
ጓሳ ግን ቤታቸው ናት፡፡ ቀይ ቀበሮዎች በጓሳ ብዙም ስጋት አይገባቸውም፡፡ማኅበረሰቡ እንደሚጠብቃቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ይመስላሉ፡፡ ለዚህም ነው መሸት ባለ ቁጥር በቀላሉ ቀይ ቀበሮን ማየት የሚቻለው፡፡
የአርሲ ከፍተኛ ተራራማ ቦታዎች፣ የሰሜን ተራራዎቸ፣ የባሌ ተራሮችና የጓሳ ፕላቶዎች ቀይ ቀበሮዎቻችን የሚገኙባቸው የአለማችን ብቸኛ ቦታዎች ናቸው፡፡ በነዚህ ስፍራዎች በጠቅላላው 500 የሚሆኑ ቀይ ቀበሮዎቸ ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከ250 በላይ የሚገኙት በባሌ ተራሮች ነው፡፡ በጓሳ የሚገኙት የቀይ ቀበሮዎች ብዛት ግን 42-47 ቢሆን ነው፡፡
የሚገርመው ግን አንድ ቱሪስት ቀይ ቀበሮን የማየት ሰፊ እድል ያለው ከየትኛውም ቦታ ይልቅ በጓሳ-መንዝ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ጓሳ ከየትኛውም የቱሪስት መዳረሻ በላይ ብርቅዬ አእዋፋትና እንሰሳትን ከሚያደናግጡ ነገሮች የተጠበቀች ናት፡፡ ማኅበረሰቡ ለዚህ ዋንኛው ተመስጋኝ ነው፡፡ በሸገር በየደቂቃው የሚደመጠው “ቅድሚያ ለእግረኛ” የሚለው አዋጅ ጓሳ ሲደርሱ እንዲህ ተቀይሮ ይገኛል፡፡ ቅድሚያ ለብርቅዬ እንሰሳት!
ቱሪስትና ጓሳ
ጓሳ-መንዝ 111 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ስፋት አለው፡፡ ከመዲናችን ከግማሽ ቀን ባነሰ ይደረሳል፡፡ ለዚህ ድንቅ ስፍራ ብዙ የሚሉት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ከየዓለማቱ የሚመጡ ጥቂት የብዝሀ-ሕይወት ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ አካባቢው ብዙ የተሰራበት አይደለም፡፡ በቱሪዝም አስጎብኚነት የሚሰሩ ባለሙያዎች ግን የባሌ ተራሮችንና የሰሜን ተራሮችን መተካት የሚችል ብቸኛው ስፍራ ጓሳ ነው ሲሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ እኔ ይህንን ቦታ ለመጎብኘት በሄድኩባቸው ቀናት የቢቢሲ የዶክመንተሪ ቡድን በአካባቢው ለ15 ቀናት ቆይታ አድርጎ ዘጋቢ ፊልም በመስራት ላይ እንደነበረ ተመልክቻለሁ፡፡
የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ቦታውን በበቂ ሁኔታ ካስተዋወቁት ለኢትዮጵያ አዲስ ላሊበላ እንደማግኘት ነው ይላሉ ቦታው ላይ ቅድመ-ጥናት ለማድረግ የተገኙ የአንድ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት፡፡ በተለይ ይህ አካባቢ ለቱሪስቶች ራስ ምታት ከሆኑት ተመጽዋች ሕጻናትን የመሳሰሉ ትእይንቶች የሌሉበት በመሆኑ፣ ከዋና ከተማ በቅርብ ርቀት መገኘቱና ማህበረሰብን መሰረት ባደረገ “ኢኮ-ቱሪዝም” ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የባሌና የሰሜን ተራሮችን የቱሪስት ፍሰት የሚጋራ ስፍራ እንደሚሆን ግምታቸውን ረገጥ አድርገው ይናገራሉ፡፡ እስከ አሁንም የዘገየው ስላልተዘመረለት ብቻ ነው፡፡
በጓሳ ህልም የሚመስሉ የጎጆ ቤት ስብስቦችን ማየት ይቻላል፡፡ ወንድ ልጅ ጎጆ ሲወጣ በዚያው ግቢ ውስጥ ሌላ ጎጆ ይሠራል፡፡ የቤተሰቡ አባል ጎጆ በወጣ ቁጥር የቤቱ አጥር እየተለጠጠ ይሄዳል፡፡ ሕዝቡ የተሻለ መኖሪያ አያስፈልገውም ባይባልም ጎጆዎቹ በራሳቸው የቱሪስት መስህብ የመሆን አቅም አላቸው፡፡ የቤቶቹን አሰራሮች ተከትሎ ተመሳሳይ የቱሪስት ማረፍያ ሎጆችን መገንባት ከጓሳ ሕዝብ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ለያውም በግ ሳይዋጣ፡፡
በጣም የሚያሳዝን እና የሚገርም ነገር ነው! ሌላ ምንም ማለት አይቻልም::
እርግጠኛ ነኝ አቶ ነጋሶ የተሻለ ነገ ይመጣላቸዋል:: መለስ ስልጣን ሲለቅቅ (ሲለቅቁ)ፕሮፌሰር ፧ የተባበሩት መንግስታት አማካሪ ምናምን ምናምን ይሆናል አይደለ ተረቱ :)
i’m really disappointed withdr.negasos monthly penstion money.the leading party tplf andhis cadres(kangaro make with him ridiculous game).how ot could be tha one who lead ethiopian for 5years on presdent..they decide 1197.60 it is less than 50€ very embarrassing judgement….those who make this!!!
may god keep ethiopian for those tyrant administration