This post is available in: ኸንግሊስህ
የማኅደረ ጊላይ የለጋነት ዕድሜ እንዲሁ እንደ ዐይን ጥቅሻ እያለፈ ነው። ወደ ኋላ ተመልሶ ሲያስብ ደስ የሚል ነገር ትዝ አይለውም።ሕይወት ልክ ከማለዳ ጣፋጭ እንቅልፍ እንደሚያባንኑት አስፈሪ የልጅነት የተረት ጭራቆች የተሞላች ትመስለዋለች:: ተረት የሚመስሉ ታሪኮችን እየኖረ፣ እየሰማ እና እየታዘበ እዚህ ደርሷል። መባረር፣ ስደት፣ ሞት… እና በትዝታ መዋትት በሕይወቱ ውስጥ እስካሁንም ይገለባበጣሉ።
ሰሞኑን ከናይሮቢ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የካኩማ ስደተኞች ካምፕ ኬኒያ መናገሻ ከተማ ብቅ ብሏል። ለእርሱ ጉዞ አዲስ አይደለም፤ ስንቱን ተጉዟል። ገና የዐሥራዎቹን አጋማሽ በቅጡ ሳይደፍን ከተወለደባት እና አፈር ፈጭቶ ካደገባት አዲስ አበባ እስከ አሥመራ ያለውን የ1176 ኪሎ ሜትር አይረሴ ጉዞ አድርጓል። ጉዞው ግን እንደዚህኛው በፍቃዱ የተደረገ አልነበረም። ያልተጠበቀ እና በስሜት ምስቅልቅል የተሞላ ነበር። ደም አፋሳሹ እና ትርጉም የለሹ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲነሳ ከኢትዮጵያ ተባርሮ አሥመራ ገባ።
“ኤርትራዊ” በመኾናቸው ምክንያት የመባረር ዕጣ እንደገጠማቸው የስሚ ስሚ ቢሰማም ለጋ ዕድሜው ከአባቱ ጋራ የተባረረበትን ምክንያት በቅጡ እንዳይረዳው አድርጎት ነበር። “እኔ በወቅቱ እንኳን በሩቅ የማውቃትን ኤርትራን ቀርቶ ተወልጄ ያደግኩባትን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ምን እንደሚመስል የማሰላስልበት ብስለት ላይ አልደረስኩም። ከትልቁ የዜግነት ጉዳይ ይልቅ የሠፈር ልጅነት ለእኔ ትርጉም ነበረው” ሲል ወደ ኋላ ተመልሶ ያስታውሳል። “‘የጨርቆስ ልጅ’ መባል ያኮራ ነበር” ይላል ማኅደረ የልጅነት ጣፋጭ ጊዜውን ያሳለፈበትን ሰፈር እያሰበ። “የጨርቆስ ልጅነቴን የምገልጸውን ያህል እንኳ ዜግነት የሚባለው ነገር ሳይገባኝ ነው አሻግረው አባ ሻውል የወረወሩኝ።”
ለማኅደረ የአዲስ አበባው ጨርቆስ እና የአሥመራው አባ ሻውል የሚመሳሰሉበት ነገር እንዳላቸው ታይቶታል። ሁለቱ ሰፈሮች ስማቸው ከድህነት ጋራ ተያይዞ ይጠራል። አባ ሻውል በምርጥ ፕላኗ በማትታማው አሥመራ ላይ ያለ ቢኾንም እንደ ጨርቆስ እና መሰል የአዲስ አበባ ሰፈሮች “የድኻ » የሚባል መንደር ነው። ገዛ መንዳ ሐበሻ ከአባ ሻውል ጋራ የሚጠቀስ ሰፈር ነው። የአራት ኪሎን አሮጌ ቄራ፣ የፒያሳን ሠራተኛ ሠፈር ያስታውሳል።
ማኅደረ አባ ሻውልን ለመልመድ አልተቸገረም። ድህነቱም፣ የአራዳ ልጅነቱም ረድቶታል። ግን አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ የአባ ሻውል ልጅ እንዳይኾን ልጓሙን ይይዝበታል። አዲሶቹ ጓደኞቹም እንደ አንዱ የሠፈራቸው ልጅ እንጂ የማንነታቸው አካል አድርገው ለመቁጠር አልፈቀዱም። “ለእነርሱ ኤርትራዊ አይደለሁም፤ ኢትዮጵያዊም አይደለሁም” ይላል። “ለእነርሱ ማኅደረ “አምቼ” ነው። ብዙዎች የሚጠሩትም “አምቼው” እያሉ ነው።
“አምቼ”…? የምን አምቼ?
“ይኼን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት አባ ሻውል ላይ ነው” አለ ማኅደረ “ስለአምቼነቱ” የሰማበትን ቀን እያስታወሰ።“አንዱ ጓደኛዬ በጨዋታ ላይ እንዲህ አለኝ። “ኻብ ሠፈርካ ዕንታይ ከምዝብልካ ትፈልጥ ዶ?” (ምን እንደምታባል ታውቃለህ?) እኔ አዲስ መጤ ምን ሊሉኝ ይችላሉ በሚል ግርምት “አይፈልጥን” ብዬ መለሰኩለት። ያን ጊዜ “አምቼ” መኾኔን ነገረኝ።” የጓደኛውን ገለጻ ተከትሎ ማኅደረ ከሌሎች ኤርትራውያን “የተለየ ዜጋ” መኾኑ ይሰማው ጀመር። ማኅደረ አይወቀው እንጂ “አምቼ” የሚለው ስያሜ እርሱ አዲስ አበባ እያለ አገልግሎት ላይ ውሎ ነበር።
ጁባ የሚኖረው የ40 ዓመቱ ቢኒያም ፍስሐ ከኤርትራውያን ቤተሰቦቹ ጋራ የኖረው አዲስ አባባ 22 ማዞሪያ አካባቢ ነው። ቢኒያም “አምቼ” የሚለውን መጠሪያ በደርግ ጊዜ አዲስ አበባ እያለ መስማቱን ይናገራል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ለተወለደ ኤርትራዊ የተሰጠ መጠሪያ ነበር። ቃሉ የሚገልጸው ኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠሙን ነው” ይላል። መጠሪያው በአንድ ወገን ኤርትራዊ ከኾኑ ወይም ከሁለት ኤርትራውያን ወላጆች ለተወለዱ ዜጎች የሚውል ነው። ስሙ የተወሰደው አዲስ አበባ ከሚገኘው እና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በጣሊያኑ የመኪና አምራች ድርጅት ፊያት መካከል በተደረገው ስምምነት ከተቋቋመው “አምቼ”(AMCE) ኩባንያ ነው። የመኪናው አካላቶች ጣሊያን ተመርተው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገጣጠሙ ሁሉ “አምቼዎች” ኢትዮጵያ ውስጥ “የተገጣጠሙ” የሚል ትርጓሜ ይሰጣል።
አምቼነት ከኤርትራ ጋራ ብቻ አይቆራኝም። ከኢትዮጵያ በተለይም ከአዲስ አበባ ጋራ ባለው ጥልቅ ትሥሥርም ይገለጻል። አሥመራ ላይ “አምቼዎች” በነገረ ሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ። “ብዙ ኤርትራውያን አማርኛ ቋንቋን የሚናገረው አማራ ብቻ ይመስላቸው ነበር። ከ1990 ዓ.ም በኋላ ብዛት ያላቸው አምቼዎች ከኢትዮጵያ ተባርረው አሥመራን አጥለቀለቋት” ይላል ቢኒያም። ከዚያ በኋላ አምቼዎችን አሥመራ ውስጥ ለመለየት ቀላል ነበር። አማርኛ የሚናገሩ፣ በአረማመዳቸው፣ በአለባበሳቸው፣ በአንጻራዊ መልኩ በተላበሱት ግላዊ ነጻነት ይታወቃሉ። የአማርኛ ሙዚቃ በአሥመራ እንግዳ በኾነ መልኩ በስፋት የሚያዳምጡትም አምቼዎች ነበሩ።
“አምቼ” መባል የመገለል ስሜት የሚፈጥርባቸው እንዳሉ ሁሉ ብዙዎች እንደማንነታቸው መገለጫ ይጠቀሙበታል። እንዲያውም የኩራት ምንጭ አርገው የሚወስዱትም አሉ። ኢየሩሳሌም ኀይሌ የከፈተችው “አምቼነቴን እወደዋለሁ” የሚለው አምቼዎች እየተገናኙ የሚጨዋወቱበት የፌስቡክ ገጽ በየቀኑ አባላቱን እያበዛ ነው። በመላው ዓለም የተበተኑ አምቼዎች እየተገናኙ ስለገጠማቸው ነገር ሁሉ የሚወያዩበት ገጽ ነው።
“አምቼ”ዎች በቁጥር ምን ያህል እንደኾኑ የተጨበጠ ወይም በጥናት የተደገፈ ማስረጃ ባይኖርም በስያሜው የሚጠሩ አንዳንዶች ግን “አምቼ”ን እንደ የኤርትራ 10ኛው ብሔር አድርገው ይቆጠሩታል። የ“አምቼ”ዎች ትክክለኛ አኀዝ ባይታወቅም ከጦርነቱ በኋላ ከኢትዮጵያ የተባረሩ ኤርትራውያኖች ቁጥር 70ሺሕ እንደሚደርስ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ማነው የተባረረው?
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ከሆነ በደንበር ጦርነቱ ወቅት ከኾነ አብዛኛዎቹ ረዥሙን የሕይወት ዘመናቸውን በኢትዮጵያ ያሳለፉ ናቸው። በ1990 ዓ.ም ወደ ኤርትራ በመጀመሪያ ዙር በተባረሩ ላይ በተደረገ ሰርቬይ 59 በመቶ የሚኾኑት ከ25 እስከ 60 ዓመት የሚኾነውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ሁሉም በሚባል መልኩ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ሲኾኑ ብዙዎቹም በኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ያልተሳተፉ ነበሩ።
በ1985 ዓ.ም በተደረገው የሕዝበ ውሳኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ እና ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡ 57,710 ትውልደ ኤርትራውያን መካከል 99.5 በመቶ የሚኾኑት ነጻነትን የመረጡ ሲኾን 204 ሰዎች ብቻ ከኢትዮጵያ ጋራ መኖርን መርጠዋል። ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ለ“አገር ደኅንነት ስጋት ናቸው” በሚል ብዛት ያላቸውን ትውልደ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ አስወጥቷል። ብዙዎቹ ትውልደ ኤርትራውያንን ከአገር እንዲወጡ የተደረገው ህግሐኤ (ህግደፍ)ን በገንዘብ በመደገፍ እና ትሥሥር በመፍጠር ተወንጅለው ነበር። በቀጣዩ ዓመት 1991 ዓ.ም በሳምንት ቢያንስ እስከ 1500 ዜጎች ከኢትዮጵያ ሲባረሩ ነበር።
አብዛኛዎቹ ተባራሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው የነበሩ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ልዑክ ቁጥራቸው 250 በሚደርስ የትውልደ ኤርትራውያን ቡድን ላይ ባደረገው ማጣራት መምህራን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች፣ ሜካኒኮች፣ ነጋዴዎች እና የዩኒቨርስቲ መምህራንም ጭምር ከተባራሪዎቹ ውስጥ ተካተው ነበር። ከዚህ ቡድን ውስጥ አንድ የሕክምና ባለሞያ እና ሁለት መነኩሴዎችም ነበሩበት። አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የነበረ ሲኾን ኤርትራን ረግጠው የማያውቁ እና ትግርኛ ቋንቋ የማይናገሩ ነበሩ።
ተባራሪዎቹ ወደ ኤርትራ የሚወሰዱት በአራት የድንበር አቅጣጫዎች ነበር። ብዙዎቹ ወደ አሥመራ የገቡት በኦምሃጀር- ተሠነይ- አሥመራ ሲኾን፣ የተወሰኑ በቀይ መስቀል ተባባሪነት በአሰብ በኩል ወደ ኤርትራ ተሸኝተዋል። ጥቂቶች የጦርነቱ ግንባር በነበረችው ዛላምበሳ እና መረብ ዓዲዃላ በኩል ወደ አሥመራ ተጉዘዋል። ሌሎች ደግሞ ወደ ኤርትራ ሳይኾን ወደ ኢትዮጵያ የጠረፍ ከተሞች ሞያሌ እና ጅቡቲ ተወስደው ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል።
ከካምፓላ 73 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጂንጃ ከተማ የሚኖሩ እና በወቅቱ ወደ ኤርትራ የገቡትን ዜጎች በመቀበል ሂደቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ ውስጥ አዋቂ ተባራሪዎቹ ወደ አሥመራ ሲገቡ የነበረውን ስሜት ለአዲስ ነገር እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፦ “የመጀመሪያውን ዙር ተባራሪዎች ስንቀበል የነበረው ከፍተኛ የቁጭት ስሜት ነበር። በከፍተኛ ስሜትም ነበር። የመጀመሪያዎቹ ተፈናቃዮች አሥመራ ዩኒቨርስቲ እንዲያርፉ ተደረገ፤ ዘመድ ያላቸው በየዘመዶቻቸው እንዲሄዱ ተደረገ። በብዙዎቹ ተባራሪዎች ላይ የላቀ ቁጭት እና ግራ መጋባት ይታይ ነበር።” ይላሉ።
“ሙሉ ቤት እና ሀብት የነበራቸው አባዎራዎች ብርድ ልብስ እና አንሶላ ለመቀበል ሲሰለፉ ለብዙዎቹ አንገት የሚያስደፋ ነበር። እስካሁን ድረስ ያልሻረ ጠባሳ ነው” ሲሉ የተፈጠረውን ችግር ያስረዳሉ። የችግሩ መጠን የተባባሰው ደግሞ የተባራሪዎች ቁጥር በየቀኑ እየናረ ሲመጣ እና የአሥመራ አቅም ከሚችለው በላይ ሲኾን ነበር። ያውም ብዙዎች ከመላው የቤተሰባቸው አባላት ጋራ የመምጣት ዕድል ባለገኙበት ኹኔታ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በሁለት የተባራሪዎች መቀበያ ጣቢያ ባደረገው ሰርቬይ በሰኔ 1990 ወደ ኤርትራ ከተባረሩት ውስጥ 63 በመቶ የሚኾኑት አዋቂ መላሾች ከልጆቻቸው ተለያይተው እንደመጡ ተናግረዋል። ብዙዎቹም ሀብት እና ንብረታቸውን በወጉ ለማደራጀት እንኳ ዕድል አልነበራቸውም። ይህን መሰሉ ትውልደ ኤርትራውያንን ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ ከኢትዮጵያ የማስወጣቱ ሂደት በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ነቀፋ ያሰነዘረ ነበር። ነቀፋው እና ትችቱ በወቅቱ በነበረው ኹኔታ ላይ ብቻ የተወሰነ እና ተባራሪዎች ከዓመታት በኋላ ሊገጥማቸው የሚችለውን የማኅበራዊ ኑሮ ቀውስ ከግምት ውስጥ የከተተ አልነበረም።
ይህ ሁሉ ታሪክ ከተፈጸመ ከዐሥር ዓመት በኋላ ያለው የተባራሪዎች በተለይም የ“አምቼ”ዎች ሕይወት በምስቅልቅል ኹኔታዎች፣ በማንነት ቀውስ እና በግራ መጋባት የተሞላ ነው። ለአዲስ ነገር ታሪካቸውን ያጋሩ “አምቼ”ዎችም ይህንኑ እውነታ ይቀበሉታል። ለደኅንነት በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ኹኔታውን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ የጂንጃው ውስጥ አዋቂም ወደ ኤርትራ የገቡት አምቼዎች የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቡናዊ ችግሮችን መጋፈጣቸውን ይመሰክራሉ።
የአምቼነት ዕዳ
እንደ ማኅደረ ያሉ ብዛት ያላቸው የትውልደ ኤርትራውያን ልጆች እና ወጣቶች አሥመራን ካጥለቀለቁ በኋላ ያጋጠማቸው ያልጠበቁት እና ካደጉበት በብዙ የሚራራቅ ነበር። ብዙዎቹ አሥመራን እና ነዋሪዎቿን ሲያስተውሉ እጅግ ወግ አጥባቂ እና የውጭ ሰው እና አስተሳሰብ በቀላሉ የማያስገባ ዝግ መኾናቸው ተረዱ። እነርሱ ካላቸው አንጻራዊ የኾነ “ተራማጅ” ማኅበራዊ መስተጋብር አንጻር ከአሥመራ ነባር ነዋሪዎች ጋራ መዋሃድ እጅግ ፈታኝ ነበር። የሚናገሩት ቋንቋ አማርኛ በመኾኑ አምቼዎች ሙሉ በሙሉ ከአሥመራ ነዋሪዎች ጋራ እንዳይዋሃዱ አርጓቸዋል።
“በአረማመድ ሳይቀር ማን አምቼ እንደኾነ ትለያለህ” ይላል ቢኒያም። “አምቼ”ዎች በሚሰሙት ሙዚቃም ተነጠለው ይታወቃሉ። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጫፍ በደረሰበት ሰሞን እንኳን በአሥመራ እንዲሁም ከረንን በመሰሉ አነስተኛ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ትናንሽ የመዝናኛ ቤቶች ውስጥ ሳይቀር የአማርኛ ሙዚቃ እንደልብ ማጫወታቸው በጤና አልታየም። ይህንን ተከትሎም የአማርኛ ሙዚቃዎችን በየምሽት ክበቦች ማጫወት እንዲቀር ታግዷል።
“ከመባረሩ ሂደት ጋራ በተያያዘ ብዙዎቹ የሥነ ልቡና ተጽዕኖ ውስጥ ነበሩ።” ይላል ቢኒያም። ማንነታቸው ሁለት ቦታ የተሰፋ ነው። አዲስ አበባ እና አሥመራ። ማኅደረም ከዚህ አልወጣም። ከአደገበት ቀዬ ተነቅሎ ያለ ውዴታ እና ፈቃዱ፤ በሚያዋርድ እና የሰውነት ክብርን በሚነካ መልኩ ወደ ኤርትራ መላኩን ያብሰለስለዋል። ዛሬ ልቡ ለኤርትራዊነት ያጋድላል። ግን ኤርትራዊ በመባልም ምሉዕነት አይሰማውም። “የጓደኞቼ ፍቅር እና ወዳጅነታቸው ለአፍታ ባይጓደልብኝም ስያሜዋ አንዳች ክፍተት በልቤ ውስጥ ፈጠረች። ኤርትራንም እንደ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያዬ እንጂ ቋሚ አገሬ ለማለት የማልደፍራት እንደኾነች ገባኝ። ኢትዮጵያዊ ነኝ እንዳልል መባረሬ መልሱን ሰጥቶኛል” ሲል የተፈጠረበትን ግራ መጋባት ያስረዳል። “የማልክደው ነገር ከኢትዮጵያ በመባረሬ ለኤርትራ ያለኝን ፍቅር መጨመሩ ነው።”
ማኅደረ ያንን ጊዜ የሕይወቱ “አስጨናቂ” እና “አስቸጋሪ” ወቅት አድርጎ ይቆጥረዋል። ከሁሉ ፈተና የኾነበት ገቢ ማግኘት አለመቻሉ ነበር። የአባቱ ዘመዶች የመረዳዳት ጠንካራ ባህል ታክሎበት እንኳ ኑሮን መግፋት እንደ አለት ጠጥሮበት ነበር፡፡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራትም የሚያስችል ምንም ዐይነት ቀዳዳ አልነበረም።
ለአብዛኛዎቹ “አምቼ”ዎችም ሕይወት እንዲያ ነበረች። ከብሔራዊ አገልግሎት ከተረፉ አሥመራ ውስጥ አለ የተባለውን ማንኛውንም ሥራ በመሥራት ይታወቃሉ። በብዙ የአሥመራ ነዋሪዎች የማይደፈሩ እንደማስተናገድ ያሉ ሥራዎችን ሳይቀር ይሠራሉ። አንዳንድ እንስቶችም ተገደው ወደ ሴተኛ አዳሪነት ገብተዋል። አንዳንዶችም በአሥመራ ባልተለመደ ኹኔታ ለአደገው ዝርፊያ ተጠያቂ የተደረጉት እነርሱው ናቸው። “ሌብነት፣ ማታለል እና በቡድን መደባደብ ከአምቼዎች ጋራ ብቻ እየተያያዘ የሚነሳ ነገር ኾኖ ነበር” ይላል መኖሪያውን ናይሮቢ ያደረገው በፀጋ ሳህለ። ይህ ተደራራቢ ከመጥፎ ነገሮች ጋራ የመዛመድ ችግር የገጠማቸው አምቼዎች የመገለል እና የራሳቸውን ክበብ በመሥራት መራቅን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል።
የኤርትራ መንግሥት የሚከተለው ዜጎችን በወታደራዊ አመለካከት የመቅረጽ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ለአምቼዎች የሚመች አልኾነም። የኤርትራ መንግሥት መሪዎች አክራሪ የኤርትራዊ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ናቸው። ይህ የአምቼ ማንነት ከተገነባበት መሠረት ጋራ የሚፋለስ ነው። የአምቼዎች ብሔራዊ ማንነት በኢትዮጵያም በኤርትራም ፖለቲከኞች እና ልሂቃን ዘንድ እውቅናም ገና አልተሰጠውም።
አምቼዎች ማንነታቸው የተገነባው በሁለት ጠንካራ ብሔርተኛነትን በሚያቀነቅኑ (ኢትዮጵያ እና ኤርትራ) ወገኖች መካከል ነው። ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትም ኾነ የኤርትራ ብሔርተኝነት አንዱ ለአንዱ እውቅና የሚሰጡ አይደሉም። ተፎካካሪ ናቸው። የሁለቱም ብሔርተኝነት አቀንቀኞች “ቀናተኞች” ናቸው። አንደኛው ሌላውን አይቀበልም። አሥመራ የሚናኘው የብሔረተኝነት አመለካከት “ለ30 ዓመት ከኢትዮጵያ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በተደረገውን ጦርነት እና ድል “ ውስጥ የበቀለ እና ያደገ ነው። የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትም ለኤርትራ ብሔርተኝነት እውቅና የሚሰጥ ሳይኾን እንደ ስኅትተ እና ክህደት ይቆጥረዋል። የአምቼዎች ማንነት የተገነባው ደግሞ የአንዱን የብሔርተኝንት እንቅስቃሴ በመናድ እና የሌላኛውን በመደገፍ ሳይኾን በሁለቱ የብሔርተኝነት አጽናፎች መካከል ያለውን መካከለኛ ቦታ ይመርጣል። አምቼዎች ማንነታቸውን የሚገልጹት በሁለቱ ብሔራዊ “ቤቶቻቸው” ነው። ሁለቱንም እንደቤታቸው ያያሉ። ነገር ግን ከሌላኛዋ “ቤታቸው” ኢትዮጵያ በግድ የተነቀሉ ናቸው። አምቼዎች በትዝታ እና በቁጭት ወደ አዲስ አበባ በሐሳብ መመለሳቸው አልቀረም። ላደጉባት አዲስ አበባ ልዩ ፍቅር እና ግምት አላቸው። ከአዲስ አበባ የተነጠሉበት መንገድ ደግሞ አዲስ አበባን በበጎ ብቻ እንዳያስታውሷት አርጓቸዋል።
አምቼዎች ኑሮ በአሥመራ እጅግ ፈታኝ ኾኖባቸዋል። ኢኮኖሚው እና ማኅበራዊው ችግርም ቶሎ ሊቀረፍ ያልቻለ ነበር። ብዙዎቹ ከድንበር ጦርነቱ በኋላም አሁንም ብሔራዊ አገልግሎት ከመስጠት አልወጡም። መቼ እንደሚወጡም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና እግዜር ብቻ የሚያውቁ ይመስላል። አሥመራ ላይ ያለው የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር በየጊዜው ፍፁም አምባገነንነቱን እያጠናከረ መሄዱ የአምቼዎችን ሕይወት መፈናፈኛ እንዳይኖረው አድርጎታል። እንደ ማኅደረ ያሉት ግን ተሳክቶላቸው አገራቸውን ጥለው ዳግም ስደት ገብተዋል።
ዳግም ስደት……ዘጸአት ለአምቼ
አሥመራም ያልደላቻቸው ብዙ “አምቼዎች” ኤርትራን ለመልቀቅ ድንበር ማቋረጥ ጀመሩ። ወደ የመን፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን። ለደላሎች ብዙ መክፈል ግድ ይላል። ገንዘብ ያላቸው ብቻ ለቀናት የእግር ጉዞ በማድረግ ከኤርትራ ደንበር ጠባቂዎች ተደብቀው ወደ ከሰላ (ሱዳን) በሕገ-ወጥ መንገድ ለመውጣት ይሞክራሉ። የተሠነይ-ከሰላ መንገዱ አንዱ ሲኾን ከኤርትራ ለመውጣት እስከ 4ሺሕ ዶላር የሚቀበሉት አስተላላፊዎች ሌሎችም በሮች አሏቸው። የቻሉ ይወጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ ተይዘው ይታሠራሉ ወይም ይገደላሉ።
በዚህ መልክ ኤርትራን ለቀው ከተሰደዱት መካከል አንዱ ቢኒያም ነበር። እርሱ እንደ አብዛኛዎቹ አምቼዎች በድንበር ግጭት በተነሳው ጦርነት ምክንያት ራሱን አሥመራ ላይ አላገኘውም። በ1983 ዓ.ም ደርግ ሲወድቅ ወደ ኤርትራ ሄደ። ከአዲስ አበባ አስመራ በአውቶብስ እየተመላለሰ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን፣ ሲጋራ እና ማስቲካ ይነግድ የነበረው ቢኒያም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲነሳ አሥመራ ላይ ነበር፤ ድንበርም ተዘጋ። ብዙዎችም ተባረሩ። ያኔ አሥመራ ላይ መቅረት ግድ ኾነ።
ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የነበረው ቢኒያም ንግዱን ቢቀጥልም ከእንድ አስቸጋሪ ነገር ጋር ተፋጠጠ። እንደ ደንቡ የብሔራዊ አገልግሎት ግዴታውን መወጣት ነበረበት። በኤርትራ መንግሥት ሕግ መሠረት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 40 ዓመት የኾናቸው ዜጎች የብሔራዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ሦስተኛ ልጁን እርጉዝ የነበረችውን ባለቤቱን ጥሎ ላለመሄድ ያልፈለገው ቢኒያም ከባለሥልጣናቱ ጋራ ድብብቆሽ ጀመረ። ቁጥጥሩ ጥብቅ እየኾነ ሲመጣ የቀረው ሁለት አማራጭ ነበር። ወደ ብሔራዊ አገልግሎት መሄድ ወይም ከሀገር መውጣት።
አገር ጥሎ መውጣት ግን ቀላል አልነበረም። በየቦታው ያሉትን ኬላዎች ማለፍ፣ በአልሞ ተኳሽ ወታደሮች የሚጠበቅ ድንበርን ማለፍ ይጠይቅ ራሱን የቻለ ፈተና ነበር። ከአሥመራ ተሰነይ በአውቶብስ የተጓዘው ቢኒያም ድንበር አቋርጦ ከሰላ ለመግባት የ17 ሰዓት የእግር ጉዞ መሄድ ግድ ኾኖበታል። “እኛ የወጣንበት መንገድ አሪፍ ነበር” ይላል ቢኒያም። የወታደሮች አፈሙዝ የሌለበት፤ ይህን መንገድ የሚያውቁ ሰዎች ግን በወቅቱ “ጫን ያለ” ክፍያ ነበር የሚጠይቁት።
የተጠየቀውን 1500 ዶላር ከፍሎ የሱዳን የድንበር ከተማ የኾነችው ከሰላ የደረሰው ቢኒያም በድንበር ጠባቂ ፖሊሶች እጅ ላይ ይወድቃል። “ከሰላ ስገባ ጀለቢያ አድርጌ ነበር። ጸጉረ ልውጥ ስለኾንኹ በፖሊሶች ተያዝኩ። በኪሴ 3000 ዩሮ እና 200 ዶላር ነበረ። ፖሊሶቹ ራቁቴን አድርገው ፈተሹኝ” ይላል። የኮሎኔል ማዕረግ ካለው ፖሊስ ፊትም እንዲቀርብ ተደረገ። “የሚያውቁት ገንዘብ ዶላር ስለነበር የያዝኩትን 200 ዶላር ሰጠኋቸው። ዩሮውን ስላላወቁት ለቀቁኝ” ሲል እንዴት ለመቋቋሚያ ብሎ የያዘው ገንዘብ እንደተረፈለት ይናገራል። ዛሬ ራሱን ጁባ ከማግኘቱ በፊት ከአገር አገር ዞሯል። ካርቱም- አዲስ አበባ- ናይሮቢ-ሉዋንዳ -ካምፓላ።
አሁን ኬንያ የሚገኘው ማኅደረ ድንበር ከመሻገሩ በፊት ኤርትራውያንን እና አምቼዎችን ማስኮብለል ሥራው ነበር። ከባድ የኾነበትን የአሥመራ ኑሮውን ትንሽ መልክ ያስያዘው ይኼው ሥራው ነበር። ወደዚህ ሥራው ደግሞ ያመጣው የ“ኮምቢሽታቶው ጮሌ” ሚካኤል ነበር። ሚካኤል የአባ ሻወል ሠፈር ልጅ ነው። ነገር ግን ውሎው እና ተግባሩ ኮምቢሽታቶ በመኾኑ ነበር የ“ኮምቢሽታቶው ጮሌ” የሚል ስያሜውን ያገኘው። በጣም ተግባቢ ነው።
ሚካኤል እና ማኅደረ የተግባቡት የ“ኮምቢሽታቶው ጮሌ” ማኅደረ ዘወትር ከማይጠፋባት “በረኸት ሻይ ቤት” በትዝታ ሲናውዝ ያገኘው ቀን ነበር። “አንቺ አምቼ አሁንም ሠፈር አልለመድሽም ?” አለው ማኅደረን! በቀላሉ ተግባቡ። ወዳጅነታቸው ጠነከረ። ሳምንቱን ሙሉ አይነጣጠሉም። ውሏቸው “ካምቦሎ”፣ “ትራቮሎ”፣ “ፊያት”፣ “ሳንፍራቼስኮ”፣ “አክሪያ” እና ሌሎች ሠፈሮች ኾነ። ማኅደረ አዲስ አባባ እያለ ወደ ሲኒማ ኢትዮጵያም ኾነ ሲኒማ አምባሳደር ብቅ የማለት ልምድ አልነበረውም። በአሥመራ ግን ደንበኛ ኾነ። በ“ሲኒማ አዝመሪኖ” እና በ“ሲኒማ ካፒታል” በየቀኑ ይታደማል። ሚካኤል ይከፍላል፤ ማኅደረ ይዝናናል።
አንድ ቀን የአሥመራ መለያ የኾነው ካቴድራል ወደ ሚገኝበት ኮምቢሽታቶ ተያይዘው ነጎዱ። አምባሳደር ሆቴል እዚሁ አቅራቢያ ይገኛል። በአቅራቢያው ወደሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ወዳለው ቤት ተያይዘው ሄዱ። “ፈጠን ብለህ ግባ” አለው ሚካኤል ኋላ እና ፊቱን እየተገላመጠ። “የሕንጻውን ዋና በር እንዳለፍኩ ግድግዳ ተደገፌ ጠበቅኹት። ‘ተከተለኝ’ የሚል ትዕዛዝ ብቻ ሰጥቶኝ ነጠር ነጠር እያለ ከፊት ለፊቴ ይመራኝ ጀመር” ይላል ማኅደረ ።
የገቡት ከሕንጻው ጀርባ ካለች አነስተኛ ክፍል ነበር። ሦስት ወጣቶች አትነጋገሩ የተባሉ ይመስል በፀጥታ ተቀምጠዋል። ሚካኤል ንግግር አላበዛም። “በማለዳ ተነስታችሁ እዚሁ እንገናኛለን፤ ቻው” የሚል ቃል እንደተናገረ አንደኛው ወጣት ለሚካኤል በእጁ አንድ ነገር አስጨበጠው። “ተረጋግታችሁ ውጡ” የሚል ትዕዛዝ ብቻ ሰጥቶ በጥንቃቄ ሕንጻውን ለቀቀው ወጡ። የኮምቢሽታቶውን ጮሌ ዋነኛ የገቢ ምንጩ በድብቅ ከኤርትራ የሚወጡ ዜጎች “መርዳት” መኾኑን ማኅደረ ያወቀው በዚያ አጋጣሚ ነበር።
የኮምቢሽታቶው ጮሌ ዋና ሥራ ተጓዦቹ ከአሥመራ እንዲወጡ መርዳት ነው፤ ከዚያ በሻገር ስላለው ደግሞ ሌሎች ባልደረቦቹ ይጨነቁበታል። ከተሳካ እስከ ኢትዮጵያ ወይም ሱዳን ድንበር ያደርሳሉ። ከዚያ በኋላ ያለው ጣጣ የስደተኛው ይኾናል። በወቅቱ በርካቶች በውትድርናው ሥራ የመረራቸው፣ ሳዋን የሚሸሹ እና የተሻለ ኑሮ የሚፈልጉ ወጣቶች ነበሩ። ውቧ ግን ሕይወት አልባዋ አሥመራም ሰልችታቸው ነበር። ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለብዙ አምቼዎች። የመንግሥት ቁጥጥር ከፍተኛ በመኾኑ ዜጎችን ማስኮብለል ቀላል ሥራ አልነበረም። እጅግ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። ከሞት ጋራ አንገት ለአንገት ተናንቆ የሚሠራ ነው።
ከቀናት ምክክር እና ልምምድ በኋላ ማኅደረ የሚካኤል ረዳት ኾነ። የተሰጠው ሚና ደግሞ ከኢትዮጵያ የተባረሩ እና መመለስን የሚሹ አምቼዎችን ማገናኘት ነበር። ሥራው መልካም ነበር፤ ገቢ አለው። ነገር ግን ሕይወት ከወዲህ ወዲያ የሚያላጋቸውን ለጋ ወጣቶች አደጋ ባለው ጉዞ ለማሾለክ ለህሊናው ፈታኝ ኾኖበታል። ግን ሕይወት ሌላ የተሻለ ምርጫ አልሰጠችውም። “አስገራሚው ነገር በየቀኑ ከሁለት ያለነሰ ሰው ለመኮብለል እንደሚፈልግ ማወቄ ነበር። አገር የሚሰደድ ነው የሚመስለው። እንደዚህ ጥብቅ የመንግሥት ቁጥጥርም እያለ የሚኮበልል ሰው ማግኘት ሳይኾን እንዴት ለማስኮብለል እንደሚቻል ነው የሚቸግረው” ይላል።
ማኅደረ በመጨረሻ ራሱን ለዳግም ስደት አጨው። አሥመራ ቢቆይ ከአባ ሻውል እስከ ኮምቢሽታቶ…እንደ ልብ ወዲህ ወዲያ ሲል እንደማይኖር ያውቀዋል። ሳዋ አፉን ከፍቶ ይጠብቀዋል። “በአዝመሪኖ ያለው ቆይታዬም በሳዋ ግዞት መጠናቀቁ ስለማየቀር ከወዲሁ ልኮብልል ስል ራሴን መከርኩት” ይላል ውሳኔ ላይ ስለደረሰበት ወቅት እና ኹኔታ ሲያብራራ። ለስደት የመረጠው መንገድ ግን ሌላ ፈተና ይዞ መጣ። ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይነት ቢወስዳትም የኤርትራን ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የማንነት ጥያቄው አፍጥጦ መጣበት “እኔ የማን ነኝ?” የሚል።
“አሥመራን እስከምለቅ በስጋት ውስጥ ጥያቄውን አዳፈኜው የነበረ ቢኾንም አክሱም ከተማ ስደርስ ዐይኑን አፍጥጦ መጣብኝ” ይላል። ከማኅደረ ጋራ አብረው የኮበለሉት ወደ ሽመልባ መጠለያ ካምፕ ሲገቡ እርሱ ግን ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ። አዲስ አበባ ጥቂት ከሰነበተ በኋላ ወደ ኬኒያ አቀና። ብዛት ያላቸው አምቼዎችም የማኅደረን መንገድ ተከትለዋል።
ሥርጭት በምሥራቅ አፍሪካ
አምቼዎች ከአዲስ አበባ እና አሥመራ ውጭ በመላው የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች ተበትነዋል። በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች ካርቱም፣ ጁባ፣ ካምፓላ፣ ናይሮቢ፣ ሞምባሳ፣….እና በመላው ዓለም ይገኛሉ። ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ደግሞ በብዛት ይገኛሉ። በተለይ ጁባ እና ናይሮቢ።
ከሞይ ጎዳና ዳር ቆሞ ለሚመለከት ናይሮቢ በግልጽ በሚታይ ኹኔታ በሁለት የተከፈለች ከተማ ነች። ዌስትላንድ (Westland) እና ኢስትላንድ (Eastland) በሚል። ምዕራቡ የከተማዋ ክፍል በአረንጓዴ የተሸፈነ፣ አልፎ አልፎም ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ያሉበት፣ በብዛት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የኬንያ ዜጎች፣ ሕንዶች እና የሌሎች አገራት ዜጎች የመኖሪያ ሥፍራ እና መዝናኛዎች የበዙበት ነው። ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ከሚኖሩባቸው የኬኒያ መንደሮች መካከል አንዱ የኾነው “ሐርሊንግሃም” በዚሁ ምዕራባዊ የናይሮቢ ክፍል (ዌስትላንድ) ይገኛል።
ወደ “ያያ የንግድ ማዕከል” የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ለሚጓዝ ሁሉ ከዳገቱ ላይ ኾኖ “ሐርሊንግሃም” የሚባለው አካባቢ ይቀበለዋል። የአካባቢው ሰላማዊ መኾን እና ማራኪነት አቅሙ ያላቸውን ሐበሾች የሚስበውን ያህል፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ በጋራ ለመኖር ለቆረጡ የሐበሻ ስደተኞችም መሰባሰቢያ ስፍራ ነው። ሐርሊንግሃም ለመድኀኒዓለም ቤተክርስቲያን ቅርብ ኾኖ መገኘቱም የበለጠ ተመራጭ አድርጎታል። ዐይንዎን በአካባቢው በማይጠፉት ሐበሾች ላይ ያሳርፉ። ምን አልባት ለናይሮቢ አዲስ ከኾኑ ኤርትራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ከሚለው መለያ በተጨማሪም “አምቼዎችንም” እዚህ ያገኟቸዋል። አብዛኞቹ አምቼዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል የመዋለል ስሜት ይሰማቸው እንጂ ወደ ኤርትራዊነት ማጋደላቸው አልቀረም፡፡ በተለይም ግማሽ ኤርትራውያኑ በቂ የሚሉትን ምክንያት ያሰቀምጣሉ፡፡ ለአብዛኞቹ ከኢትዮጰያ ወገን ካሉ ዘመዶቻቸው ይልቅ ከኤርትራ በኩል የሚዛመዱ የመረዳዳት ባህላቸው ጠንካራ መኾን ለዝንባሌያቸው ምክንያት ነው፡፡ በፀጋም ይሄን ሃሳብ ያጠናክራል፡፡ “በስመ ኤርትራዊ እርዳታ ብትጠይቀ የሚነፍግህ የለም፡፡ አገር ቤት ብትሄድ ደግሞ ሰርጉም ሃዘኑም ለብቻህ ስለማትወጣው መደጋገፉ የጠነከረ ነው”
በናይሮቢ ያለው የስደተኞች የአኗኗር ዘይቤም ይሄን የሚያሳይ ነው፡፡ ኤርትራውያኑ (አምቼዎቹን ጨምሮ) በአንድ ስፍራ አጀብ ብለው መኖርን ይመርጣሉ፡፡ ለአንዱ በተላከው የድጎማ ገንዘብ የተቸገረ ወገናቸውን ጭምር ይረዱበታል፡፡ መጠለያ የሌላቸውን በዙር በየቤታቸው ከማስጠለል አንስቶ ወርሃዊ የቤት ኪራይ በመክፈል ጭምር አለኝታነታቸውን ያሳያሉ፡፡
የሐርሊንግሃም ጉዳያችንን ከጨረስን “አምቼዎች” በስፋት ወደሚኖሩበት ወደ ምሥራቃዊው ናይሮቢ እናዝግም፤ ከአምቼው ማኅደረ ጊላይ ጋራ። የናይሮቢ ምሥራቁ ክፍል ከምዕራቡ በተቃራኒው ብዙ ለምለም ነገር የማይታይበት፣ ድህነት የደቆሳቸው መንደሮች በብዛት የሚገኙበት እንዲሁም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባቸውን ሥፍራዎች አካቶ የያዘ ነው። ከ“ኢስሊ” ሌላ “ቻይሮድ” ወደ ሚባለው ሰፈር ቢያቀኑ ብዛት ያለቸውን ሐበሾች ችምችም ባለው መንደር መካከል ያገኟቸዋል። በዚህ ሥፍራ ዳር እና ዳር በአማርኛ የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ይመለከታሉ።
ከ“ካተሪና ሎጅ” ፊት ለፊት “አሥመራ ሆቴል” ጎላ ብሎ ይታያል። ኢትዮጵያውንም በብዛት ቢገኙም የኤርትራውያኑን ያህል አይኾኑም። ብዙኀኑ በምግብ ሥራ፣ በችርቻሮ እና በመጠጥ ንግድ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። አካባቢው ከኪስዋሂሊ እና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ይልቅ ትግርኛ እና አማርኛ ጎልተው የሚነገሩበት ነው።
ካሪያኮር እና ፓንጋኒ የሚሉት አካባቢዎች በሐበሻ የሚዘወተሩ ቢኾንም የኤስሊን ያህል ግን ሐበሻን አያስተናግዱም። ኤስሊ የሶማልያውያን የበላይነት እየነገሠ የመጣበት ትልቁ የንግድ ሥፍራ ነው። በብዙ መልኩ ከአዲስ አበባው መርካቶ ጋራ ይቀራረባል። ይኹንና ኤስሊ የሚንቀሳቀሰውን የዶላር መጠን መርካቶ በዓመት ለማንቀሳቀስ አቅም ያለው አይመስልም። በዚህ ወከባ እና ግርግር በበዛበት ሥፍራ ሐበሾችም የራሳቸው ድርሻ አቸው። ሁለተኛ፣ ዘጠነኛ፣ ዐሥረኛ እና ዐሥራ አንደኛ የሚባሉት መንገዶች በብዛት ሐበሾችን የያዙ ክፍሎች ናቸው። ሚሚ ሱቅ፣ ቴዲ ሙዚቃ ቤት፣ የባህል መደብር . . የመሳሰሉት የአማርኛ ማስታወቂያዎች ጎልተው የሚታዩት ግን በተለይ በዘጠነኛ እና በዐሥረኛ መንገዶች ነው።
በናይሮቢ ጉራንጉሮች ውስጥ የእሱን መሰል ታሪክ ያላቸው አሚቼዎች ጉዞ ገታ ያድርጉ እና ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ይጓዙ። ከናይል ወንዝ አቅራቢያ ከተሠራው እና የጁባ ዐይን ከኾነው “ብሪጅ” ሆቴል ተነስተው ጉዞዎን ቢያደርጉ እዚህም እዚያም ሐበሾችን ይመለከታሉ። “ኮኞ ኮኞ”፣ “ገበል ኩጁ”፣ “ኒው እና ኦልድ ከስተመስ”..እንዲሁም በመላዋ ጁባ ቢዘዋወሩ እንደልብ የሚያገኙት እነርሱኑ ነው። ጁባ ሮድ በሚገኘው “ኩሽ ሆቴል” ገብተው ዐይንዎን ጣል ቢያደርጉ እዚህም እዚያም አበሾች ክብ ሠርተው ሲያወጉ ስልክ ሲደውሉ፣ ጥሪ ሲቀበሉ ያያሉ።
ጁባ የደቡብ ሱዳን ልብ የኾነች የንግድ ከተማ ነች። ወደ ምግብ ቤቶች ጎራ ሲሉ የሚያስተናግዱዎትም አዲስ አባባ የሚያውቋቸው ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ሊኾኑ ይችላሉ። ጁባ ነፍስ የምትዘራው በኤርትራውያን እና በኢትዮጵያውያን ነው። ከከፍተኛ የመንግሥት አማካሪዎች እስከ ሾፌር፣ ነጋዴ፣ አስተናጋጅ፣ ወያልነት….ድረስ ጁባ ትዘወራለች። አምቼዎች ከኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መሳ ለመሳ ኾነው ሕይወታቸውን ይገፋሉ። ቢኒያም እዚህ ይኖራል። ማኅደረ ደግሞ ኬንያ። ብዙዎች “አምቼዎች” እንደ ቢኒያም አሊያም እንደ ማኅደረ ዕድለኞች አልነበሩም። ዛሬ በሕይወት ተርፈው ታሪካቸውን ለማውራት ዕድሉን አላገኙም።
አሳዛኙ ዕጣ
አንዳንዶቹ እጅግ ዘግናኝ በሚባለው የባድመ ጦርነት ከለብ ለብ ሥልጠና በኋላ እንዲሳተፉ ተደርገዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ያባረራቸው ብዛት ያላቸው አምቼዎች አሥመራ በገቡ በስድስት ወር ጊዜ ወስጥ ወደ ሳዋ ወታደራዊ ማሠልጠኛ እንዲሄዱ ይደረጉ ነበር። የሳዋ ስምንተኛ እና ዘጠነኛ ዙር ሠልጣኞች ብዙዎቹ አምቼዎች ናቸው። ሥልጠናውን እንደጨረሱ እጅግ ዘግናኝ እና ለሰው ሕይወት ደንታ ባልነበረው የባደመ ጦርነት ተማገዱ። ብዙዎቹም ሕይወታቸውን እና አካላቸውን አጥተዋል። አሳዛኙ ዕውነታ ደግሞ “አምቼ”ዎች በጦርነቱ ወቅት በሁለቱም ወገኖች የማይታመኑ መኾናቸው ሕይወታቸውን የበለጠ ያከፋው እንደነበር አዲስ ነገር ዩጋንዳ -ጂንጃ ውስጥ ያነጋገራቸው ለጉዳዩን ቅርበት የነበራቸው ግለሰብ ያስረዳሉ።
“ጦርነቱ ላይ ስለ ተሳተፉት ወጣት ትውልደ ኤርትራዊ ዜጎችን (አምቼዎችን) አስብ። በተለይ አንዳንዶቹ ወጣቶቹ ኢትዮጵያዊ ነን ብለው የሚያስቡ፤ ከአዲስ አባባ ውጭ ሌላ ከተማ ዐይተው የማያውቁ ነበሩ” ይላሉ ውስጥ አዋቂው። “በሕይወትህ አስበህ እና ገምተህ በማታውቀው መልኩ ለማታውቀው አገር ወታደር ኾነህ ራስህን ብታገኘው ምን ይሰማኻል? ከእኛ ወዲያ የአበደ አለ?” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ኹኔታ በጥያቄ መልክ ያስቀምጡታል።
ማኅደረ ይህን መሰል ታሪኮችን ኖሯቸዋል። ተረት የሚመስሉት እውነተኛ የትራጄዲ ታሪኮች ቁጥር ስፍር የላቸውም። “ከአዲስ አባባ ወጥቶ የማያውቅ የ18 ዓመት ልጅ ከአባቱ ጋራ ወደ ኤርትራ ተባረረ፤ ለምን እንደተባረረም በቅጡ ያልተረዳ ወጣት። አሥመራ በገባ በስድስት ወሩ ሳዋ ገባ፤ ባድመ ላይ ሞተ። ለምን ሞተ?…” ማኅደረ ይጠይቃል። አባቱ የልጃቸውን ሞት ከሦስት ዓመት በኋላ ሰሙ። ባዶ ሕይወት። የማኅደረ- አምቼ ትዝታዎች፤ በናይሮቢ።
ከ10ኛ ብሔረሰብ ወደ አምቼዎች ዓለም
“አምቼ”ዎችን አንዳንዶች “ግራ የተጋቡ” ሲሉ ይገልጿቸዋል። የአዲስ ነገር ዘጋቢዎች ይህን ዘገባ ለማጠናቀር በተንቀሳቀሱባቸው የምሥራቅ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች ናይሮቢ፤ ካምፓላ፣ ጁባ፤ ካርቱም፣..እና ሌሎች ትንንሽ ከተሞች ግን “አምቼ”ዎች ያላቸው ማኅበራዊ ፋይዳ አይተዋል። አምቼዎች “ድልድዮች”፣ “ሰላም አስከባሪዎች” የሚሉ ስያሜዎች ያገኙትም በማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ባላቸው አበርክቶት ነው።
“አምቼ”ዎች የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ሕዝቦች የሚያገናኙ፤ በሁለቱም ውስጥ የሚገኘውን ደካማ እና ጠንካራ ጎን የሚረዱ ናቸው። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል አንዱ ለአንዱ ያለውን አሉታዊ ግምት ለመፋቅ በአንድ ተመሳሳይ ወቅት ለኤርትራም፤ ለኢትዮጵያም ወግነው የሚከራከሩ ናቸው።
በጁባ፣ ናይሮቢ፣ ካምፓላ፣ በመሳሰሉ የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች በምድር ወገብ ፀሐይዋ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ሐበሾች ወደ ከፈቷቸው ቡና ቤቶች እና ባሮች ጎራ በሉ። የአብርሃም አፈወርቂን ሙዚቃ እንደሰማችሁ የቴዎድሮስ ካሳሁንን “ኻብ ዳህላክን” ወዲያው ልታደምጡ ትችላላችኹ። ሌላም ዘፈን …፤ “አዲስ አበባ ቤቴ” የሚለውን ዘፈን ጭምር ሁሉ። እነዚህን ዘፈኖች ሲሰሙ ያስከፈቱትን የላጋር ቢራ ቶሎ ቶሎ የሚጎነጩ …ሲጋራቸውንም በላይ በላዩ የሚያጨሱ ወጣቶች ልትታዘቡ ትችላላችሁ። በሙዚቃው ውስጥ ሕይወታቸውን እያነበቡ ትላንትን፣ ዛሬን እና ነገን እያሰቡ እንደሚኾን አትጠራጠሩ።
ብዙዎች “አምቼ”ዎች እንዲህ ዐይነት ሙዚቃ ሲያደምጡ በትዝታ እና በቁጭት ወደ አዲስ አበባ በሐሳብ መመለሳቸው አይቀርም። በአንዳንዶች ሕሊና ከዐሥር ዓመት በፊት ያዩዋትን አዲስ አበባ በዐይነ ሕሊናቸው ድቅን ትላለች። “አምቼ”ዎች ላደጉባት አዲስ አበባ ልዩ ፍቅር እና ግምት አላቸው። ከአዲስ አበባ የተነጠሉበት መንገድ ደግሞ አዲስ አበባን በበጎ ብቻ እንዳያስታውሷት አድርጓቸዋል። ታዲያ በሐሳብ መናወዛቸውን የሚያናጠብ ጸብ ብዙ ጊዜ አይጠፋም።
ጁባም ኾነ ናይሮቢ፣ ካምፓላም ኾነ ካርቱም ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን አብረው የሚታደሙባቸው የምሽት ክበቦች አንዳንድ ጊዜ ጸብ አያጣቸውም። በአንድ ዜማ አብረው ሲደንሱ የነበሩት እና ራሳቸውን “ሀበሻ “ እያሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሊጣሉ ይችላሉ። “በሀበሾቹ” መካከል ፀብ ከተነሳ “ሰላም አስከባሪዎች” በገላጋይነት ከተፍ ይላሉ። “ጁባ ላይ አምቼዎች ‘ሰላም አስከባሪዎች’ ተብለው ይታወቃሉ” ይላል ቢኒያም።
በመላው የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች ተበትነው የሚገኙት ከኢትዮጵያውያን እና ከኤርትራውያን ስደተኞች ወገኖቻቸው መሳ ለመሳ የስደት ኑሮቸውን እየገፉ የሚገኙ “አምቼ”ዎች ልክ በመላው ዓለም እንደተበተኑ የስያሜ ተጋሪዎቻቸው ሁሉ እርስ በእርስ ባላቸው ትሥሥር ይታወቃሉ። “I Love being Amiche” በተሰኘው የአምቼዎች ፌስ ቡክ ገጽ ላይ አስተያየቱን የሰጠ አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ምኞቱን አስቀመጠ። “አምቼዎች አንድ ላይ የምንኖርበት ዓለም ቢኖረን እንዴት ደስ ባለኝ።”
“አምቼ”ዎች ሕልማቸው በእነርሱ ምኞት ብቻ እንደማይሳካ ያውቁታል። ሥልጣን ላይ ያሉት የፖለቲካ ቡድኖች ለጥያቄዎቻቸው የሚኾን መልስ ይዘዋል። ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ፍፁም ፈቃደኝነት ባይታይባቸውም። ማኅደረ ግን ለማንነት ጥያቄው መፍትሄ ያለው ይመስላል። “ከኢትዮጵያዊነት እና ኤርትራዊነት በላይ የጨርቆስ እና የአባ ሻወል ልጅ መባል ይበልጥብኛል” ይላል። ብዙ አምቼዎች በሚገናኙበት የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ሰለሞን ዘርዐይ የሚባል አባል ይህችን ግጥም አሰፈረ።
ብለነው ብለነው ካልኾነ ነገሩ
አምቼና ዶላር የትም ነው አገሩ።
ዘገባ- ሱቢ ዓለሙ፣ ማስረሻ ማሞ
…
ማጣቀሻ ጽሑፎች
1, ERITREA & ETHIOPIA: LARGE-SCALE EXPULSIONS OF POPULATION GROUPS AND OTHER HUMAN RIGHTS VIOLATIONS IN CONNECTION WITH THE ETHIOPIAN-ERITREAN CONFLICT, 1998-2000)
2,Case Material on Ethnic Eritrean Deportees from Ethiopia Concerning Human Rights Violations : The Uprooted
Case Material on Ethnic Eritrean Deportees from Ethiopia Concerning Human Rights Violations
by Prof. Asmarom Legesse
3, Jennifer Riggan, Ph.D. In Between Nations: EthiopianBorn Eritreans, Conflict and Nationalism Paper presented at the International Studies Association Annual Meeting New York City, February 1518, 2009
4,
WEHA BEWKTUT EMOCHEEEE…..
This news is intended to give the impression to the readers that the rhetoric of economic development is ridiculous.
Just out of curiosity, has anyone ever seen any positive news about Ethiopia on ANO?
man neber kahun behuala etiban yemibal neger anteyikim yalew_….tiyake milikit ….