የማይዋጠው “ቦጅ ቦጅ”
(አበበች በላቸው) መቸም “ቦጅ በጅን” የማያውቅ ተጋዳይ አለ ማለት ያስቸግራል። ቦጅ ቦጅ የእንግሊዝኛው (HOTCH POTCH) በአርሶ አደር አማርኛ ሲነገር ነው። ቦጅ ቦጅ ለአንድ ምግብ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን በትግሉ ጊዜ ተጋዳይ ያገኘውን ሁሉ ሰብስቦ እንጀራውንም፣ ድርቆሹንም፣ ወጥ የነካካውንም አንድ ላይ አድርጎ የሞቀ ውሃ/የተፈላ ውሃ ተቸልሶበት ፍርፍር አይሉት ፍትፍት ብቻ ያን ተተራምሶ የተሠራውን ምግብ ነበር ቦጅ ቦጅ [...]
(አበበች በላቸው)
መቸም “ቦጅ በጅን” የማያውቅ ተጋዳይ አለ ማለት ያስቸግራል። ቦጅ ቦጅ የእንግሊዝኛው (HOTCH POTCH) በአርሶ አደር አማርኛ ሲነገር ነው። ቦጅ ቦጅ ለአንድ ምግብ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን በትግሉ ጊዜ ተጋዳይ ያገኘውን ሁሉ ሰብስቦ እንጀራውንም፣ ድርቆሹንም፣ ወጥ የነካካውንም አንድ ላይ አድርጎ የሞቀ ውሃ/የተፈላ ውሃ ተቸልሶበት ፍርፍር አይሉት ፍትፍት ብቻ ያን ተተራምሶ የተሠራውን ምግብ ነበር ቦጅ ቦጅ ይል የነበረው። የበረከትን መጽሐፍ እንዳነበብኩ ትዝ ያለኝ አንዳንዴ አልዋጥ የሚለኝን ቦጅ ቦጅ ነው።
ከሁሉ አስቀድሞ የበረከት ቦጅ ቦጅ የአንድ ሰው ሐሳብ ብቻ እንዳልኾነ መረዳት ይገባል። በረከት እንደሚለው ረቂቁን የኢሕአዴግ ቱባ ቱባ መሪዎች (መለስንም ጨምሮ) አንብበውታል፤ ሐሳብም ሰጥተውበታል። በዚህ ረገድ ቦጅ ቦጁ የእርሱ ሥራ ብቻ ሳይኾን የኢሕአዴግ መሪዎችም እንደኾነ መረዳት ተገቢ ነው። በረከት የቸከቸከው ውሸት እና በሐሳብ ደረጃም እጅግ ዝቅተኛ የኾነው ይኸው ሥራ በጋራ የተሠራ ለመኾኑ እና ይህም የኢሕአዴግን መሪዎች ችሎታ ዝቅተኛነት ብቻ ሳይኾን እንዲህ ያለ ውሸት በመጽሐፍ ደረጃ ለማውጣት ያላቸውንም የመዋሸት ድፍረት ጭምር የሚያሳይ ነው።
በረከት ቦጅ ቦጁን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ብሎ ይሰይመው እንጂ ጠቅላላው የጽሑፉ ይዘት ግን ከወያኔ እና ሻዕቢያ ጦርነት ጀምሮ ኢሕአዴግ ያለፈበትን ሂደት የሚዘበዝብ ነው። መቼም ይኼን ዝባዝንኬ እንኳ ነጥብ በነጥብ፣ አርእስት በአርእስት እንኩዋን አስተያየት ይሰጥበት ቢባል መጽሐፍ ይወጣዋል። ግን ደግሞ ለምኑ ነው መልስ ወይም አስተያየት የሚሰጠው? ያልሰማነውን እና የማናውቀውን የኢሕአዴግ ውሸት አልጻፈልንም። አዲስ ነገር ቢኖር በየጊዜው በኢሕአዴግ በተለይም በመለስ ዜናዊ የተነገሩትን ቅጥፈቶች አንድ ላይ ሰብስቦ፣ ቀምሮ እና ደምሮ ማቅረቡ ነው። ደግሞ የሚገርመው የማያውቃቸውን እና ያላነበባቸውን መጻሕፍት እና ደራስያን ተራ በኾነ ጥራዝ ነጠቅነት መጠቃቀሱ ነው። በዚህም “እውቀቱን” ሊያሳን ሞክሯል። ነገር ግን ያ “እውቀት” መለስ ካሠመረለት ገደብ ያለፈ አልኾነም። በዚህም አዋቂነቱን ሳይኾን የባለጌ ሊቅነቱን አስመስክሯል።
ይኹን እንጂ እነዚህ የእውቀት ደረጃቸው ዝቅተኝነተ በየገዜው እየወረደ ያሉ የኢሕአዴግ መሪዎች አንድ የሚያወቁት እና የተካኑበት ነገር ቢኖር ተንኮል ነው። ሕዝቡ እነርሱ የሚሉትን ሁሉ እንደሚጠላ ስለሚያውቁ፣ በአንድ የአስተሳሰብ ጎዳና እንዲሄድላቸው ከፈለጉ የዚያን ነገር ተቃርኖ ይሠራሉ። በዚህም ሕዝቡን (ምሁሩንም ጭምር) አሳስተውታል። እኔም በዚሁ ጉዳይ ላይ ብቻ በማተኮር አስተያየቴን እሰጣለሁ። ከነዚህም ማሳሳቻዎች አንዱ የድሮውን የተማሪ እንቅስቃሴ (ከዚያም ተራማጁን) የሚመለከት ነው።
ኢሕአዴግ/ወያኔ ከተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደተፈጠረ አርጎ ራሱን ሲክብ ቆይቶአል። ገና አዲስ አበባን ሳይዙ አንዳንድ ኦፕሬሽናቸውን ሳይቀር “ኦፐሬሽን ዋለልኝ” እያሉ በመሰየም በማያቋርጥ ዘዴ ኢሕአዴግ እና ወያኔ የተማሪው እንቅስቃሴ ቅጥያዎች እንደኾኑ አድርገው ያቀርባሉ። ይህን የሰማ እና ታሪካቸውን በውሉ ያላጤነው ሁሉ እውነት እየመሰለው “እነዚህን አውሬዎች የፈጠረብን” በመሰለ የተማሪውን እንቅስቃሴ በአሉታዊ መንገድ የሚያይ አልጠፋም። ይህ ከባድ ስህተት ነው። በፀረ-ወያኔ ትግሉ ላይም አንድምታ ሊኖረው ይችላል። እስቲ ይህን ጉዳይ በመጠኑ ዘርዘር አድርገን እንየው።
ከራሳቸው ከሰዎቹ ብንነሳ፤ ከመሀላቸው ማናቸው ናቸው በተማሪዎች እንቅስቀሴ የተካፈሉ ብለን ብንጠይቅ አንድም ሰው አናገኝም፤ በርግጥ ከመሀላቸው ሁለቱ (አረጋዊ በርሄ እና መለስ) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማሕበር ኮንግሬስ አባል ነበሩ፤ ለዚያውም ወደ መጨረሻ ገደማ (እነ ዋለልኝ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በሁዋላ) እንደኾነ እናውቃለን። ለሎቹ ግን የተማሪው እንቅስቃሴ በዞረበት አልዞሩም ነበር። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከኢሕአዴግ መሪዎች መሀል አንዳቸውም በተማሪ እንቅስቃሴ ታጋይነት እንዳልነበሩበት ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ ይፈልጋል። ስለዚህም የተማሪው እንቅስቃሴ ባነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምንም ተካፋይነት ስላልነበራቸው በጥያቄዎቹ ላይ የነበራቸው እውቀት የስሚ ስሚ እንጂ ቀጥተኛነት የለውም።
ሁለተኛ በአመለካከት ደረጃም ቢኾን የተማሪው እንቅስቃሴ ወደ ግራ ወያኔ/ኢሕአዴግ ደግሞ ወደ ቀኝ ናቸው። ሌላ ሌላውን ትተን የርዕዮተ ዓለማቸው ደም ሥር በኾነው በብሔር ጥያቄ እንኳ በስሙ ሊነግዱበት የሚሞክሩት ዋለልኝ የሄደው ባንድ መንገድ፤ እነርሱ ደግሞ በተቃራኒው መንገድ እንደሚሄዱ መታወቅ አለበት። ብዙ ሰው የዋለልኝን ጽሑፍ አንብቦ ስለማያውቅ እነርሱ ዋለልኝ ያለውን ሥራ ላይ እንደሚያውሉ አድርጎ ይረዳዋል። በመሠረቱ የሚያደርጉት ግን ዋለልኝ ካለው የተገለቢጦሹን ነው። እንዴት?
ቦጅ ቦጅ በረከት እንዲህ ይለናል፤ “አባል የኾንኩበት የታጋይ ትውልድ ከስድሳዎቹ አጋማሽ እስካሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተዋናይ ነው። የመጀመርያዎቹ እና ከተማሪው ንቅናቄ ፈልቀው የትግሉን ፈለግ ያስተማሩን መሪዎቻችን በብዙ መልካም አቋሞቻቸው መሞገስ ያለባቸውን ያህል፣ በልምድ እና በአተያይ እጥረት ትግሉን ወደፊት ማራመድ ሲያቅታቸው በእኛ ትውልድ መተካታቸው አይቀሬ ኾነ (ገጽ 8)። ይህን የጭቃ ምርግ እንተርበው ብንል ርቃኑን ለቆመው በረከት ሌላ ርቃን እንዳለው መፈለግ ስለሚኾን እንተወዋለን። ዋናው ጉዳይ ግን የዚህ ቅጽ ሐሳብ እኛ ኢሕአዴጎች የእነ ዋለልኝ ተከታዮች፣ ትምህርታቸውንም በሥራ ለመተርጎም የቆምን ነን የሚል ነው። ከዚሁ “ትምህርት” (የገባቸው ይመስል!) አንዱ የብሔር ጥያቄ ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ዋናው ከተማሪው እንቅስቃሴ “የወረሱት” የብሔር ጥያቄን ነው ይሉናል። ለዚህም የፈረደበት ዋለልኝ ይማልበታል። ለመኾኑ ዋለልኝ ያለው ለእነዚህ ጉዶች ገብቷቸዋል? ዋለልኝ ምንድን ነው ያለው? ባጭሩ፦
_ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ አገር እንደኾነች፣ እነዚህም ብሔረሰቦች በእኩልነት መኖር እንደሚገባቸው፣ በእኩልነት ለመኖር የብሔር ጭቆና በተለይም የአማራው (አንዳንዴም የትግራይ) የበላይነት ማክተም እንዳለበት፣ ለዚህም ሁሉን የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሶሻሊስት ሪፖብሊክ እንደሚያስፈልግ፣ እስከዚያ ድረስ ግን ጭቆናን ተቃውመው የተነሱት ሁሉ መደገፍ እንዳለባቸው፣ እንቅስቃሴዎቹ ግን እኛ የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊ ሶሻሊስት ሪፖብሊክ ሊያመጡልን አይችሉም፤ መሪዎቻቸው (የኤርትራው ኢ.ኤል.ኤፍ -ያኔ ሻዕቢያ አልነበረም- የባሌው እንቅስቃሴ) አድሃሪዎች በመኾናቸው . . .
የዋለልኝ ጽሑፍ መሠረታዊ ሐሳብ ይኸው ነው። በዚህ ጽሑፍ “የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ መወሰን”፣ “ተገንጥሎ ሌላ መንግሥት እስከማቋቋም ድረስ መብት አላቸው” የሚለው የወያኔ/ኢሕአዴግ ወንጌል በዋለልኝ ጽሑፍ ውስጥ አንድም ቦታ አይገኝም። (አንባብያን ከዚህ ጽሑፍ ጋራ የተያያዘውን የዋለልኝ ጽሑፍ ይመልከቱ)። የእነ መለስ ወንጌል የተገኘው ከዋለልኝ ሳይኾን የአገር ቤቱ የተማሪ እንቅስቃሴ በኀይለ ሥላሴ ፖሊስ ተጨፍልቆ በነበረበት ወቅት በውጭ አገር ከወጣው ከብርሃነመስቀል ረዳ ጽሑፍ ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ሰዎች ግን የኢሕአፓን ሰው እንደ መምህር/ተምሳሌት ከሚወስዱ ቢሞቱ ስለሚሻላቸው ስለ ብርሃነ መስቀል አያነሱም። በረከት እና አለቃው መለስ ቋቅ ይበላቸው እንጂ ታሪኩ እንዲህ ነበር። ስለዚህ በብሄር ጥያቄም ኾነ በሌላው ዋለልኝ ወዲህ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወዲያ የምንለውም ለዚህ ነው።
ሦስተኛው ጉዳይ የብርሃነ መስቀል ጽሑፍ ለምን ዓላማ እንደተጻፈ በፍጹም ሊገባቸው አልቻለም። እነርሱ ያቺ “ተገንጥሎ ነጻ መንግሥት እስከማቋቋም ድረስ” የምትለዋን መዝሙር ብቻ የሙጥኝ ብለው እዚያው ላይ ስለቆረቡ እንጂ ጉዳዩ እንዲህ ነው። በ1963 ዓ.ም ላይ ውጭ አገር ባለው የተማሪ እንቅስቃሴ በብሔር ጥያቄ ላይ ልዩነት ይነሳል። በሰሜን አሜሪካ ያለው በእነ እንድርያስ እሸቴ የሚመራው ማኅበር (ኤዙና) በብሔር ጥያቄ ላይ ከዋለልኝ በተጻራሪ የኾነ ውሳኔ ያሳልፋል። ያኔ አልጀርያ የነበረው ቡድን በጉዳዩ ተነጋግሮበት ዋናው ጉዳይ በጊዜው በአንድ በኩል በተማሪው መሀል ሰፍኖ የነበረውን ማን አህሎኝነት ለማዳከም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ለመጀመር አመቺው ቦታ ኤርትራን መገልበጫ ማድረግ ስለነበር በብሔር ጥያቄ ላይ “የብሔሮች መብት ተገንጥሎ ነጻ መንግሥት እስከማቋቋም ድረስ ይሄዳል” የሚለውን ሐሳብ ማስፋፋት አስፈላጊ ነበር። ለብርሃነ መስቀል ጽሑፍ መነሻ የኾነው ይህ ነበር። ብርሃነ ይህ መብት ይህን ይመስላል ከማለት አልፎ የኤርትራን መገንጠል አልደገፈም። እንግዲህ “እስከመገንጠል ድረስ” የሚለውን መፈክር ያስያዛቸው ብርሃነ መስቀል እንኳ የኤርትራን መገንጠል አልደገፈም። መለስና ኢህአዴግ የብርሃነ መስቀል ሃሳብም አልገባቸውም። “እስከ መገንጠል” የምትለዋ ሀረግም ብትሆን በፖሊሲ ደረጃ እንዴት እንደምትታይ አልገባቸውም። ብርሃነ መስቀል ግን በደምብ ያብራራዋል። ለዚህ ነው አንዳንዴ እነዚሀ ሰዎቸ ምኑን ነው ያነበቡት የሚያሰኘው።
የወያኔ/ኢሕአዴግ ሰዎች የብሔር ጥያቄን እንዴት ያዩታል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በእነርሱ አስተሳሰብ አንደኛ ፖለቲካ ሲባል፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሲባል የሚጀምረው በብሔር ጥያቄ ነው። ስለዚህም ዲሞክራሲ እና መንግሥት የሚተረጎመውም ከዚሁ ከብሔር ጥያቄ አንጻር ነው። የፖለቲካ ፈጣሪ የብሔር ጥያቄ ስለኾነ ሁሉም ሰው የሚለካው “እስከ መገንጠል ድረስ” የሚለውን በመደገፍ እና ባለ መደገፍ ላይ እየተመዘነ ነው። በአገዛዝ ደረጃም ወያኔ/ ኢሕአዴግ የአማራን የበላይነት በትግሬ የበላይነት ተክቶታል። ከሁሉም በላይ አስከፊ የኾነ የዘር መከፋፈል በመፍጠር ሰዉ ሁሉ በየብሔረሰቡ እና ጎጡ እንዲወሸቅ አድርገውታል። በዚህ አስከፊ አገዛዛቸውም የትግራይ ሕዝብ እንዲጠላ እስከማድረግም እየተጓዙ ነው።
እስኪ እንዲያው ላንዳፍታ ወደ 60ዎቹ መለስ ብለን እነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ እና ማርታ የተሰውለት ሥርዐት የዚህ ዐይነቱ ነበርን ብለን እናሰላስል?
የበረከት ቦጅ ቦጅ ገና ከመጀመርያው በዚህ መሠረታዊ ውሸት ይጀምራል። ከዚያ በሁዋላ ያለውንማ ምን ማንሳት ያስፈልጋል?
Comments are closed.