የሙስሊሞች ተቃውሞ አገራ አቀፍ እየሆነ ነው፤ ኢሕአዴግ ሙስሊም አባላቱን “ለምክክር” ለነገ ቅዳሜ ጠርቷል
(ሩቂያ ሰ./ አዲስ ነገር ኦንላይን)
* በአዲስ አበባ በተከሰተ ግጭት ሰዎች ተጎድተዋል
* “[መጅሊሶች] ራሳችሁንም መንግሥትንም ከዚህ አጣብቂኝ አውጡ” የመንግሥት ተወካይ
በአዲስ አበባ የአሊያ ትምህርት ቤት እና መስጂድ የተጀመረው የሙስልሞች የአደባባይ ተቃውሞ ስምንተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረበት በዚህ ሳምንት አገር አቀፍ መልክ እየያዘ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ ነገር ያደረሱዋቸው መረጃዎች ጠቆሙ። ሰሞኑን ከተለያዩ ክልሎች የተሰበሰበውን 300 ሺህ ፊርማ ጨምሮ በድምሩ ከ500 ሺህ በላይ የአቤቱታና የተቃውሞ ፊርማ ተሰብስቦ በሕዝብ ለተመረጠው ኮሚቴ መድረሱ ተዘግቧል። ሁኔታው እጅግ እያሳሰበው የመጣው መንግሥት የተወካዮቹን ቁጥርና አይነት በመጨመር ነገሩን ለማብረድ እየሞከረ ነው።
(ሩቂያ ሰ./ አዲስ ነገር ኦንላይን)
በአዲስ አበባ የአሊያ ትምህርት ቤት እና መስጂድ የተጀመረው የሙስልሞች የአደባባይ ተቃውሞ ስምንተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረበት በዚህ ሳምንት አገር አቀፍ መልክ እየያዘ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ ነገር ያደረሱዋቸው መረጃዎች ጠቆሙ። ሰሞኑን ከተለያዩ ክልሎች የተሰበሰበውን 300 ሺህ ፊርማ ጨምሮ በድምሩ ከ500 ሺህ በላይ የአቤቱታና የተቃውሞ ፊርማ ተሰብስቦ በሕዝብ ለተመረጠው ኮሚቴ መድረሱ ተዘግቧል። ሁኔታው እጅግ እያሳሰበው የመጣው መንግሥት የተወካዮቹን ቁጥርና አይነት በመጨመር ነገሩን ለማብረድ እየሞከረ ነው።
የአዲስ አበባ ዘጋቢዎቻችን በዛሬው ዕለት ለስምንተኛ ሳምንት በአወሊያ መስጂድ በቀጠለው የዓርብ ስግድት ተቃውሞ በመቶ ሺህ ሊገመቱ የሚችሉ ምእመናን መገኘታቸውን ተመልክተዋል። በዛሬው ዕለት በሕዝብ የተመረጠው (17 አባላት ያሉት) ጊዜያዊ ኮሚቴ የካቲት 5 ቀን ከመንግሥት ጋራ ስላደረገው ውይይት ባቀረበው ሪፖርት መንግሥት እስከ የካቲት 26 ቀን ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ቃል መግባቱን ገልጿል። ኮሚቴው “እስከ የካቲት 26 መልስ ካልሰጠን፣ መልስ አንሰጥም ማለት ነው። ሁላችሁንም የሚያስደስት መልስ እንሰጣለን፣ ነገር ግን ታገሱ” የሚል ማስተማማኛ ከመንግሥት እንደተሰጠው ሪፖርቱን በጉጉት ሲጠብቅ ለነበረው ሕዝብ አስታውቋል። እስከዚያው ድረስም ጊዜያዊ ኮሚቴው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔድ ኢማሞች፣ ሙስሊም ባለሃብቶች እና ምሁራን የሚገኙበት የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ማቀዱን ገልጿል። ኮሚቴው “በአዲስ አበባ ምእመናን የተመረጠ ነው” ከሚል መነሻ የአዲስ አበባውን መጅሊስ እንዲረከብ የቀረበው ሐሳብ በኮሚቴው በራሱ ውድቅ ተደርጓል። የኮሚቴው አባላት በንባብ ባቀረቡት ሪፖርት “ዛሬም ሆነ ወደፊት በየትኛውም የመጅሊስ መዋቅር ውስጥ አንሠራም። ለምርጫም አንቀርብም” በማለት ችግሩን የመፍታት እንጂ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት እንደሌላቸው በይፋ አስታውቀዋል። ይህም ለሕዝብ ያላቸውን ታማኝነት የሚያረጋግጥ ተደርጎ ተወስዶላቸዋል።
ከጊዜያዊ ኮሚቴው ጋራ የተገናኘው የመንግሥት ተወካዮች ቡድን በተመሳሳይ ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) አመራሮችም ጋራ መወያየቱ ታውቋል። በዚህ ውይይትም ከደኅንነት ሹማምነት መካከል አንዱ ናቸው የተባሉት (አለቃ) ጸጋይ ለመጅሊሱ አመራሮች ጠበቅ ያለ መሳሰቢያ መናገራቸውን የቅርብ ምንጮች ተናግረዋል። “ራሳችሁንም መንግሥትንም ከዚህ አጣብቂኝ አውጡ። አለበለዚያ ቀዩን ካርድ ለእናንተ ማውጣታችን አይቀርም።” በሌላ በኩል እየቆየ ነገሩ ያሳሰበው የሚመስለው ኢሕአዴግ በየደረጃው የሚገኙ ሙስሊም አባላቱን “በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር” በሚል ለነገ ቅዳሜ ስብሰባ መጥራቱን የተለያዩ የአዲስ ነገር ምንጮች ገልጸዋል።
ይኸው ከዓርቡ ሳምነታዊ ስግደት ጋራ ተያይዞ በመገለጥ ላይ ያለው በመጅሊሱ ላይ ያነጣጠረ ተቃውሞ ወደሌሎች ከተሞችም መዛመቱ እየተነገረ ነው። ከዚሁም ጋራ ተያይዞ ዛሬ ዓርብ የታተመው “ሠለፊያ” ጋዜጣ እንደዘገበው ከአፋር፣ ጅማ፣ ገለምሶ፣ አሰላ፣ ወልቂጤ፣ ትግራይ፣ ከኩፍቱ፣ አላማጣ እና ምዕራብ ወለጋ ዞን የተሰበሰበ ከ300 ሺህ የሚበልጥ የሕዝብ አቤቱታ ፊርማ በሕዝብ ለተመረጠው ጊዜያዊ ኮሚቴ ቀርቧል። ይሁንና ይህንን የአቤቱታ ፊርማ ለማሰባሰብ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች የታሰሩባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውም ተዘግቧል። በዚህም በወልቂጤ 15፣ በምዕራብ ወለጋ 5፣ በትግራይ 18 ሰዎች መታሰራቸው ተነግሯል። በአዲስ አበባም በንፋስ ስልክ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ከአራት ያላነሱ ሰዎች መታሰራቸውን ምንጮች ለአዲስ ነገር ገልጸዋል።
በመጅሊሱ ላይ የሚደረገው ተቃውሞና ግፊት ቀጥሎ የአፋር ኡለማዎች ከዚህ በኋላ ለፌዴራሉ መጅሊስ እውቅና እንደማይሰጡ በመግለጽ ለመጅሊሱ ለራሱ እና ለመንግሥት በደብዳቤ ገልጸዋል። በሶማሌ ክልልም የአሕበሽን ስልጠና ተካፍለው የተመለሱና የመጅሊሱ የሥራ ሐላፊዎች ሳይታሰሩ እንዳልቀረ ተሰምቷል፤ ሆኖም የአዲስ ነገር ዘጋቢዎች ጉዳዩን ለማረጋገጥ አልቻልንም።
በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንም በየአገሩ በሚገኙ ኮሚኒቲዎቻቸው በኩል ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፤ ለጊዜያዊ ከሚቴው ያላቸውን ድጋፍ፣ ለመጅሊሱ ያላቸውን ተቃውሞ የሚገልጹ ደብዳቤዎችን በላካቸው ታውቋል። ጊዜያዊ ኮሚቴው በሪፖርቱ እንዳለው የትግራይ ሙስሊሞች ኮሚዩኒቲ በካናዳ፣ የአፋር ኮሚዩኒቲ በካናዳ፣ የኦሮሞ ሙስሊሞች ኮሚዩኒቲ በካናዳና በዳላስ፣ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኔትወርክ በአውሮፓ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ኮሚዩኒቲ በካናዳ ከእነዚሁ ውስጥ የሚተቀሱ ናቸው። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል የተባለው የሙስሊም ዳያስፖራ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር በቅርቡ አዲስ አበባ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ተቃውሞ የበረታበት መጅሊስ የካቲት 3 እና 4 ቀን በአዲስ አበባ መስጂዶች ስብሰባ ቢጠራም ብዙ እንዳልጠገኘለት የአዲስ ነገር ምንጮች ገልጸዋል። በአንዳንዶቹ መስጅዶችም ስብሰባዎች በጠብና በሁከት ተጠናቀዋል። በሰለሃዲን መስጂድ በተቀሰቀሰ ጠብ ከመጅሊሱ ተወክለው የተላኩት ሰዎች አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸውና ከመካከላቸውን የተፈነከቱ እንደነበሩ እማኞች ገልጸዋል። መጅሊሱ የሾማቸው የመስጂዱ ኢማም በጠቡ መካከል እጃቸው ሳይሰበር እንዳልቀረ ተሰምቷል። ትናንት ሐሙስ የበኒን መስጂድ ምክትል ኢማም መጅሊሱን በመደገፍ መናገራቸው ያስነሳው ረብሻም የፖሊስን ጣልቃ መግባት የጋበዘ ነበር። ሰውየው እንዲህ አሉ፣ “መጅሊስን መቃወም ሐራም ነው።” እንደተሰማው ኢማሙ ከመስጂዱ የወጡት በፖሊስ ታጅበው ነው።
በተቃውሞና በግፊት ከየአቅጣጫው የተወጠረ የሚመስለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) አመራር ከአጣብቂኙ በአሸናፊነት ለመውጣት ጥረት ማድረጉ እንዳልቀረ ለማወቅ ተችሏል። ታዛቢዎች የመጅሊሱ የመጫወቻ ካርዶች እንዳለቁ ያምናሉ። የመጨረሻው ካርድ በአቶ መለስ እጅ የሚገኘው ካርድ ነው። መጅሊሱ በፖለቲካው መስክ ተቃዋሚዎቹን “በአክራሪነት” እና “በሽብርተኝነት” በመፈረጅ የመንግሥትን ድጋፍ የማግኘት ስትራቴጂው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መሥራቱ ቢታወቅም ገንፍሎ የወጣውን የበርካታ ሙስሊሞች ተቃውሞ ሊገታ የሚችል አልሆነም። መንግሥትም የሕዝብን ጥያቄ “የአክራሪ እና የሽብርተኛ” እያለ መጠርጠሩን ሙሉ በሙሉ ባይተውም መጅሊሱን እንደቀድሞው በደፈናው ከመደገፍ ስትራቴጂው በማፈግፈግ ላይ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ። በብዙ መልኩ መንግሥትም ቢሆን ብዙ ካርዶች በእጁ የሉም።
በቅርቡ “በኢትዮጵያ ውስጥ የአልቃኢዳ መረብ ተጋለጠ” በሚል የተሰራጨውን ወሬ እንደታሰበው የብዙ ሙስሊሞችን ትኩረት የሚስብ እንዳልሆነ አንድ አስተያየት ሰጪ ለአዲስ ነገር ተናግረዋል። “አሁን ለሌላ አጀንዳ ጊዜ የለንም፤ በመጅሊሱ ላይ ባነጣጠረው ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃውሞዋችን ውጤት እስክናገኝ አንቀጥላለን” ብለዋል እኚሁ ማንነታቸውን መግለጥ ያልፈለጉ ግለሰብ። ብዙ ታዛቢዎች መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዳደረገው የለውጥ ጠያቂዎችን ፍላጎት በማኮላሸት፣ ታማኞቹ ባሉበት እንዲቀጥሉ ያደረገበትን ስትራቴጂ በመጅሊሱ ላይ መድገም መቻሉን ይጠራጠራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ይህኛው የሙስሊሞች የለውጥ ጥያቄ ይፋ የወጣ የሕዝብ ድጋፍ ስላለው በቀላሉ ለማዳፈን የማይቀል መሆኑ ነው። በተጨማሪም መንግሥት ከዚህ ቀደም በ1987 በአንዋር መስጊድ የተከሰተው አይነት ግጭት በሙስሊሞች መካከል እንዲነሳ ፈጽሞ እንደማይፈልግ ብዙዎች ይገምታሉ። “መንግሥት ከአንዋር መስጊዱ ጥፋት ትምህርት ወስዷል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ምእመን ይናገራሉ። ቀዩ ካርድ የሚገኘው በሕዝበ ሙስሊሙ እና በመንግሥት እጅ ነው። መንግሥት ቀዩን ካርድ ለመጅሊሱ ቀድሞ ካልሰጠ ካርዱ በእርሱ ላይ እንደማይመዘዝ ማስተማመኛ ያለው አይመስልም። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ቀጣዮቹን ዓርቦች የሚጠብቁት ለፈጣሪያቸው የተለመደውን ምስጋጋና ልመናቸውን ለማቅረብ ብቻ አይደለም። ቀዩ ካርድ።፤
No comments yet... Be the first to leave a reply!