This post is available in: ኸንግሊስህ
(መሐመድ ሰልማን-ከመርካቶ )
ይቺ አገር ፈሪሃ -እግዚአብሔር (በዐረብኛ/ተቅዋ) ያለ ልክ የሰፈነባት የምድራችን ክፍል ናት፡፡ ሕዝቦቿም ለፈጣሪ ተንበርካኪ እና ጨዋዎች ናቸው፡፡ ይህን መግቢያዬን የሚጠራጠር ሰው ካለ በፒያሳ ወይም በመርካቶ እንደ ገብስ ተሰጥቶ እና ተዘርግቶ የሚቸረቸረውን የወርቅ ብዛት ጎራ ብሎ ይመልከት፡፡ በአንድ ወቅት ዛሬ በሕይወት በሌለችው “አዲስ ነገር ጋዜጣ” ላይ (ነፍሷን ይማር) “ኢትዮጵያዊ ድኻ ለምን አይሰርቅም” የሚል ውብ መጣጥፍ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ጽሑፉ ለመንደርደርያነት ያነሳኹትን ሐሳብ እንደ አንድ ምክንያት የሚቀበለው ይመስለኛል፤ ይቀበለዋልም፡፡
ንቅሳት እንኳ የመስረቅ አቅም አላቸው የሚባሉት የመርካቶ ሌቦች “ኪስ ሲያወልቁ” ያገኙትን መታወቅያ እና ጠቃሚ ሰነድ ለባለቤቱ የመመለስ ጥሩ ባህል አላቸው፤ ምንም ቢሰርቁ ሰው እስከመግደል ድረስ የሚጨክን አንጀት የላቸውም። እንዲያው ሳስበው የእንጀራ ጉዳይ ኾኖባቸው እንጂ ባይሰርቁ ደስ የሚላቸው ይመስለኛል፡፡ የአገሬ ሌቦች ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያደረባቸው ለመኾናቸው “ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ” የለኝም የምለውም ለዚሁ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱም ታላላቅ ሃይማኖቶች ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጠቅሳለች፤ ለያውም በተደጋጋሚ፡፡ አሜሪካም ኾነች እንግሊዝ ይህን የመጠቀስ ዕድል አላገኙትም፡፡ አሜሪካ ለከፋቸው ስደተኞች መጠለያ መኾን የጀመረችው ገና በቅርቡ ነው፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ግን ገና ያኔ ጥንት በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የነቢዩ መሐመድን ደቀ መዛሙርት (ሰሀባዎች) ‹‹ግሪን ካርድ›› ሰጥታለች፡፡ ለነገሩ ከአሜሪካ ጋራ ምን አፎካከረን?!ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ ተጠቀሰች ስንል መርካቶንም እንደሚያጠቃልል ልብ ማለት ያሻል፡፡ ምክንያቱም መርካቶ የምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ኢትዮጵያም መርካቶ ውስጥ አለች።
በልጅነቴ ከሌባ ጋራ የተዋወቅኩት በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ ነው፡፡ የመርካቶው ታላቁ አንዋር መስጊድ በታላላቅ ሌቦች በተደጋጋሚ ይደፈራል፡፡ ለሶላት ጫማቸውን ያወለቁ ምዕመናን ፊታቸውን ወደ ፈጣሪ መልሰው ጎንበስ ቀና ሲሉ የጫማ ሌቦች ምድራዊ ተግባራቸውን ያከናውናሉ። በዚህ ኹኔታ ቢያንስ በቀን አንድ ሌባ መስጊድ ውስጥ ይያዛል፡፡ በዚህን ጊዜ ሌባው ከመቅደስ ወደ መስጊዱ ግቢ ይወሰድ እና “የዱላ እንካ ቅመሱን” እስኪጠግብ ይሰጠዋል። ሁሉም ሰው ጡቻ፣ ጥፊ፣ ቡጢ፣ ጫማ-ጥፊ፣ ቃሪያ ጥፊ፣ የፊት ጠረባ/የኋላ ጠረባ ወዘተ ያቀምሰዋል፡፡ ጀለቢያ ያጠለቁ ትልልቅ እና ወፋፍራም እንዲሁም ቦርጫም ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ቀሚሳቸውን ሽቅብ እየሰበሰቡ እግራቸውን ሌባው ላይ ለማሳረፍ ይሞክራሉ፡፡ ያ ሁሉ ምዕመን አንድ ሌባ ሲደበድብ የሚፈጠረው ትዕይንት ትንግርት የሚሉት ዐይነት ነው። እኔም የድርሻዬን በነጻነት የመሰንዝር አጋጣሚው ስለሚፈጠርልኝ መስጊድ ውስጥ ሌባ በተገኘ ቁጥር ውስጥ ውስጡን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በልጅነት ለወላጆቻቸው ሳይናገሩ መስጊድ አብረውኝ ይመጡ የነበሩ ክርስቲያን ጓደኞቼም በዚሁ ሌባን ተጋግዞ በመደቆሱ ተግባር ይዝናኑበት ነበር፡፡
እኔ ባደኩባት መርካቶ ጥቂት ክርስቲያን ጎረቤቶች ነበሩን፡፡ ‹‹ራጉዔል አይደል ወይ የአንዋር ጎረቤቱ›› እንዲል ቴዲ አፍሮ፡፡ እንደ ዛሬ ረመዳን ሲመጣ አብሮነታችን ይደረጃል፡፡ አብረን ‹‹እናፈጥራለን››፣ ፀሐይ እስክትጠልቅ ጠብቀን ተምር እና ሳምቡሳ አንዳንዴም ሾርባ እንጋራለን፡፡ አንዳንዴ በረመዳን ወቅት ቁርሳቸውን እስከተሲያት ባለመብላት ጭምር በፆም ያግዙኝ ደግሞም ይተባበሩኝ ነበር፡፡ በርግጥ ደህና ቁርስ ሳያገኙ ቀርተውም ሊኾን ይችላል፡፡ በልጅነታችን ከእነዚሁ ጓዶቼ ጋራ በፆም ጉዳይ ላይ መበሻሸቃችን የተለመደ ነበር፡፡ እነርሱ ”ማታ ማታ እየበሉ ቀን ቀን መፆም ምኑ ያስደንቃል?” እያሉ ይሞግቱኛል፡፡ እኔም የተራበችዋን ትንሽ ሆዴን እያሻሸሁ “ሽሮ እና ምስር ግጥም አርጎ እየበሉ ፆምኩኝ እንዴት ይባላል?” ስል የመልስ ምት እሰጣለሁ፡፡ በብሽሽቁ የማሸነፍ ዕድል የነበረኝ እኔ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም ጓደኞቼ ስጋ እና የስጋ ወጤቶችን የሚያገኙት አልፎ አልፎ በበዐላት ሰሞን ብቻ ነበር፡፡ ይህ ኹኔታም ”እናንተኮ ዓመቱን ሙሉ ሁዳዴ ላይ ናችሁ” እያልኩ እንድዘባበትባቸው አግዞኛል፡፡ያም ኾኖ በረመዳን “ከሲኒማ ራስ” ቴምር እየገዛን እንዝናናለን፣ ቴምር መግዣ ሳንቲም ካጣንም ጥቂት ቴምር እና ጥቂት ሳምቡሳ ከቤት እየደበቅኩ ይዤላቸው እሄድ ነበር፡፡ ክርስቲያን የሰፈር ጓደኞቼ ረመዳን ሲመጣ የሚከፋቸው ዘወትር እሁድ ጠዋት አስፋልት ላይ በምናደርገው የእግር ኳስ ጫወታ ደከም ስለምልባቸው ብቻ ነበር፡፡
እነርሱም ቢኾን ውለታ ለመመለስ ለጥምቀት ጃንሜዳ ይዘውኝ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ ለዚያውም አርሞኒካ አስታጥቀው፡፡ “ሆያ-ሆዬ” ጭፈራ ከልጆች ገቢ ማስገኛነቱ ባሻገር ራሱን የቻለ ሃይማኖታዊ ትርጉም እና ሥርዐት ያለው መኾኑን ያወቅኹት ከጎረመስኹ በኋላ ነው፡፡ በልጅነታችን የሃይማኖት ሥርዐቶችን እንፈጽም የነበረው እንደ ባህል እንጂ ከጽድቅ ቆጥረነው አልነበረም።
ማን እንደጀመረው ባይታወቅም በአገሬ ሙስሊም እና ክርስቲያን ተቻችለው ሳይኾን ተዋደው ኖረዋል፡፡ (ተቻችለው የሚለው ቃል ምንኛ ይጎረብጣል!) የእኔ የልጅነት ትውስታ በራሱ በምስክርነት መቅረብ የሚችል ነው፡፡ ከእኒያ የልጅነት ወዳጆቼ መሀል አሁን ብዙዎቻችን ከሃይማኖት መንሸራተት ጀምረናል፡፡ አንዳንዶቻችን በተቃራኒው አምርረናል፡፡ አንዳንዴ “ሆያ-ሆዬ” ክርስቲያናዊ ተግባር እንደኾነ ሲሰበክ እሰማለኹ፡፡ ከሃይማኖቴ ውጭ ሌላ ወዳጅ እንዳላፈራ እጎተጎታለኹ፡፡ በየአጋጣሚው የማነባቸው አዳዲስ መንፈሳዊ መጻሕፍትም ስለ ፍቅር የሚሰብኩበት ቃላት ጎድለውባቸዋል፡፡ ይልቁንም መጪው ዘመን በሃይማኖቴ ላይ አደጋ የሚያንዣብብበት እንደሚኾን የሚተነብዩ እና ነቅቼ እንድጠብቅም የሚያስጠነቅቁ ናቸው፡፡
በተቃራኒው ጎራ የሚጻፉ መጻሕፍትም በተመሳሳይ መልኩ ተናዳፊ ናቸው፡፡ ሃይማኖትን የሚያክል የማይጨበጥ ነገር ቤተ-ሙከራ አስገብተን መረመርነው፣ ዘረዘርነው የሚሉ ቀሳውስት ውዝግብ የሚያስነሱ ነጥቦችን እያነሱ ይሰብካሉ፡፡ ከቤተ-ሙከራው ሲወጡም አማኙን የሚያስቀይም ውጤት ይዘው ይንጎራደዳሉ፡፡ ያንኑ በመጽሐፍ ፣ በሲዲ፣ በቲ-ሸርት ካልታተመልን ይላሉ፡፡የኔዋ የአሁኗ መርካቶ በዚህ ሁሉ ተቃርኖ የተሞላች ናት፡፡ ከሰሞኑ በጋራ የተጀመሩት የፍልሰታ እና የረመዳን ፆሞች ደግሞ ተቃርኖውን አጉልተው እያሳዩኝ ነው፡፡ በተለይም በመርካቶው ሼ- መንደፈር፡፡
ረመዳን እና ፍልሰታ- የሁለት ሳንቲም አንድ ገፅታ
እንዲህ ምዕመናን ልብ በሚገዙበት የፆም ወቅት ግርግር ትንፋሽ ባሳጣት መርካቶ በተሽከርካሪዎች ላይ ተንቀሳቃሽ ቤተ-ክርስቲያኖችን እና መስጊዶችን ታሰማራለች፡፡ በድምፅ ማጉያ ስብከቶች አቅሏን ትስታለች፡፡ መንዙማ እና መዝሙር፣ ዳእዋ እና ስብከት ልክ ባጣ ላንቃ የ“ካሴት ግዙን ትድናላችሁ” ተማጽኖ ያቀርባሉ፡፡ ገነት እና ጀነት የሚገባውን ምዕመን ቁጥር ለማሳደግ የሞንታርቦ ድምፅ ይጨምራሉ፡፡ በድምፅ ጉልበት መንግስተ-ሠማያት ይወረስ ይመስል።
የ16 ቀናት ዕድሜ ያለው የፍልሰታ ፆም ከሁዳዴ ቀጥሎ ምዕመናኑን ወደ ቤተክርስቲያን ደጃፎች የሚጠራ ነው፡፡ ነጠላ ያጣፉ ሴት ምዕመንት በአያሌው ወደ ደብረ ኀይል ቅዱሰ ራጉዔል ቤተክርስቲያን ይጎርፋሉ፡፡ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ሙስሊም ምዕመናንም ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ ያለ ልክ ይተማሉ፡፡ 15ኛ ቀኑን ያስቆጠረው የረመዳን ፆም ለዚህ ምክንያት ትመት ነው፡፡ የቀሳውስቱ ቆብ እና የሙስሊም ኮፍያ፣ የምዕመኑ ነጠላ እና የሙስሊም ጀለቢያ ተጣምረው ወደ ጎረቤታሞቹ አንዋር እና ራጉዔል ይገባሉ። ትዕይንቱ በተለይም ዘወትር አርብ የተለየ ግርምትን ይፈጥራል፡፡
በአንዋር መስጊድ እና በቅዱስ ራጉዔል ቤተክርስቲያን አጥሮች መካከል ያለው ርቀት አንድ መኪናን ብቻ ማሳለፍ የሚያስችል ነው። በእነዚህ የአምልኮ ስፍራዎች የሚገኘው ሕዝብ ደግሞ አጥሮቹን አልፎ የሚፈስ ነው። በመኾኑም ምዕመናኑ በዐቢይ የጸሎት ወቅቶች በዙርያቸው የሚገኙትን የተሽከርካሪ ጎዳናዎችን ለመጠቀም ይገደዳሉ፡፡
በተለይም አንዋር መስጊድ በረመዳን የጁምዐ ስግደት የምዕመናኑ ቁ|ጥር በአራት እና አምስት እጥፍ ስለሚጨምር የመርካቶን ሲሶ በጸሎት ስፍራነት ለመጠቀም ይገደዳል፡፡ በደቡብ በኩል እስከ “ሲኒማ ራስ”፣ በምዕራብ እስከ “ጣና ገበያ” አንዳንዴም እስከ “ምዕራብ ሆቴል”፣ በሰሜን እስከ “ጎጃም በረንዳ” እንዲሁም በምሥራቅ እስከ አሜሪካን ግቢ ድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህ ኹኔታ ከሚፈጥራቸው አስገራሚ ትዕይንቶች አንዱ ሰጋጆቹ የራጉዔልን ዙርያ አጥር ለመጠቀም መገደዳቸው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ነጠላ እና አባያ፣ ጥምጣም እና ጀለቢያ ባይፈቅዱትም ትከሻ ለትከሻ፣ መሳ ለመሳ ለመቆም ይገደዳሉ፡፡
ዘወትር ምሽት በረመዳን ወር የሚሰገደው የ‹‹ተራዊህ›› ስግደት ዘለግ ያለ ሰዓትን ይወስዳል፡፡ አማኞች መኪናዎቻቸውን በሁለቱም የእምነት ስፍራዎች ዙርያ እየኮለኮሉ ያቆሟቸዋል፡፡ ሶላት ሲሰግዱም የራጉዔልን አጥር ተደግፈው ጭምር ነው፡፡ መስገጃዎቻቸው የራጉዔልን ሕንፃ በረንዳዎች ጭምር አካሎ ይይዛል፡፡ ዘወትር ምሽት ይህንን አስገራሚ ክስተት ባስተዋልኹ ቁጥር በካሜራ ቀርጾ ለማስቀረት ይዳዳኛል፤ ተሳክቶልኝ ባያውቅም።
የጁምዐ ስግደት ላይ ሃይማኖታዊ ዲስኩር (ኹጥባ) በአሰጋጁ (ኢማሙ) አማካኝነት ይቀርባል። አንዳንድ ጊዜ በተመሳሳይ ከራጉዔል የቅዳሴ ዜማ ይለቀቃል፡፡ ከሁለቱም ጎረቤት የእምነት ስፍራዎች በድምፅ ማጉያ የሚስተጋቡት ድምፆች እርስ በርስ ስለሚራበሹ ምእመናኑ ሁለቱንም ከማዳመጥ ውጭ ምርጫ ያጣሉ። ከሁለቱም ጎራ ያሉ አማኞች ይህ ኹኔታ የሚፈጥርባቸውን እውነተኛ ስሜት ባላውቅም ለእኔ ግን ትርጉሙ የትየለሌ ይኾንብኛል፡፡ በዐረብኛ እና በግዕዝ ወደ አምላክ የሚተላለፉ ተማጽኖዎች፡፡
የቅዱስ ራጉዔል ቤተክርስቲያን እንደ ብዙዎቹ አቻዎቹ አጥሩን አስታኮ ያስገነባው ግዙፍ ሕንፃ ፎቁ ለደብረ ኀይል ቅዱሰ ራጉዔል ትምህርት ቤትነት ሲያገለግል ምድሩ ላይ ያሉት ቤቶች ደግሞ የንግድ ቤት ኾነው ያገለግላሉ። በእነዚህ ሱቆች በአመዛኙ የሞባይል መለዋወጫዎች፣ በስተ ምዕራብ ባሉት ሱቆች ሻንጣ እና ብርድ ልብስ፣ ኦርቶዶክስ ዘ-ተዋህዶ መዝሙር ቤቶች እና በስተ ምሥራቅ ባሉት ሱቆቹ ደግሞ ኢስላማዊ ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ናቸው፡፡ በዚሁ ሕንፃ ላይ የሚገኘው ዘመናዊው “ሄኒ-ፔኒ ካፌ” ለረመዳን ኢስላማዊ ምግብ እና መጠጦችን ያቀርባል፡፡ ይህ የቅዱስ ራጉዔል ሕንፃ የአርክቴክት ዲዛይኑ የመስቀል ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራ ነው። ኾኖም በሥሩ ከሚገኙት ሱቆች ውስጥ አባያ ( ሙስሊም ሴቶች የሚለብሱት ቀሚስ)፣ ኒቃብ (ፊትን በከፊል የሚሸፍን)፣ ሂጃብ (ጸጉርን የሚሸፍን)፣ ቡርቃ (ከዐይን በስተቀር መላ ሰውነትን የሚሸፍን) እንዲሁም ጀለቢያ እና መስገጃዎች ይሸጡበታል፡፡ ይህ ኹነት ለአንዳንዶች ከቢዝነስ ፍልስፍና ከፍ ያላለ ትርጉም ሊኾን ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ከዚያም የላቀ ትርጉም አለው።
ድህነታችን እና ባህላችን ተጋግዘው የፈጠሩት ጥብቅ ጉርብትና ማኅበራዊ ሕይወታችንን ይጫኑታል፡፡ ይህ ኹኔታ በሃይማኖት መሥመሮችም የሚገለጥበት ጊዜ አለ። እናቴ እነ መምሬ ቤት ጠበል ቅመሱ ሲባል ከመሄድ አትቦዝንም። ከክርስቲያን አብሮ አደጎቼ ጋራ የነበረን ወዳጅነት አንድ ጊዜም ቢኾን በሃይማኖት ስሜት የተቀኘበት ወቅት ትዝ አይለኝም። አንዳንድ ጓደኞቼ አሁንም ድረስ የኢስላም አቡጊዳ የኾኑትን የዐረብኛ ፊደላትን እና ጥቂት የቁርዐን አንቀጾችን በቃላቸው ማነብነብ እንደሚችሉ አስተውያለኹ፤ እንደ እኔ ከሙስሊም ቤተሰብ ለወጡ ብዙ ዜጎች ቄስ ትምህርት ቤት ሙዋዕለ-ሕፃናት እንጂ የክርስትያን ተቋም ኾኖ ተሰምቶን አያውቅም፡፡
ይህ ስሜት በአዲሱ ትውልድ እየተሸረሸረ ይመስለኛል። የአሁን ሙስሊም ወዳጆች አገራዊ ከኾኑ ጉዳዮች አልፈው ለኢራቅ ሕዝቦች አለኝታነት ይሰማቸዋል። ይህን እንደ ስኅተት ባላየውም ከስሜታቸው ጀርባ ያለው ምስል ግን ያስፈራኛል። ቤታቸው ውስጥ አሁን አሁን የማያቸው መጻሕፍትም ኾኑ ሲዲዎች የጽዮናዊት እሥራዔልን ሤራ እንዴት መበጣጠስ እንደሚቻል የሚያትቱ፤ አልያም ደግሞ ሌሎች ሃይማኖቶች እንዴት ኢስላምን ለማጥፋት ቀን ተሌት እየሠሩ እንደኾኑ ለማሳመን የሚጥሩ ናቸው። በየሳምንቱ አርብ የሚወጡ መንፈሳዊ ጋዜጦችም ቢንላደን በኔቶ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥፋት አጋነው የሚዘግቡ ናቸው፡፡
አንዋር መስጊድን እና ራጉዔል ቤተ-ክርስቲያንን በሚለዩት አጥሮች መሀል ባለው ጎዳና እነዚህ አስፈሪ ጭብጥ ያላቸው የኅትመት ውጤቶች እንደ ቆሎ ይቸረቸራ፤ ከሁለቱም ጎራ። ይህንን ጽሑፍ ለማሰናዳት በስፍራው ባንዣበብኩባቸው ቅጽበቶች ብቻ ያየኋቸውን የኅትመት ውጤቶች ብቻ ብዘረዝር ፍርኀቴ ይበልጥ ግልጽ የሚኾን ይመስለኛል።
“የኢየሱስ ማንነት ተደረሰበት…
“ሚዛኑ ቢጠፋ ወርቁ ጠፋ፣ ሴቶችን የበደለ ክርስቲያን ወይስ ኢስላም”
“ኢየሱስ ነቢይ ወይስ ፈጣሪ”
“ቁርዐንን ማን ደረሰው”
“የኢየሱስ ማንነት ለእስላሞች መልስ”
የመርካቶ የአንዋር መስጊድ እና የደብረ ኀይል ቅዱሰ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን ፍጥጫ፣ ፍቅር እና ተቃርኖ የመላ አገሪቱን ስሜት አይወክልም ለማለት ያዳግታል፡፡ እየቀጨጨ ያለ አብሮነት፣ እየጎመራ የሚመስል የሌላውን የማንኳሰስ አባዜ፣ የእኔን ብቻ ስሙኝ የሚለው ውትወታ፣ ጠበብ ያለ ሃይማኖታዊ አቋም ወዘተ …፡፡
በቅርቡ የ“ሚሊቴሪ ተራ” ነጋዴዎች አክሲዮን ማኅበር አባላቱን በራጉዔል ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ስብሰባ ይጠራቸዋል፡፡ በሚያስገነቡት ሕንፃ ጉዳይ ላይ እንዲመክሩ፡፡ አንዳንድ የማኅበሩ አባላት ታድያ ሙስሊሞች በመኾናቸው የሙስሊም ቆባቸውን አድርገው ወደ ስብሰባው ይገባሉ። ሰብሳቢዎቹም ያሉት ቤተ ክርስቲያን ቅጽር በመኾኑ ቆባቸውን እንዲያወልቁ ይጠይቃሉ። ሙስሊም አባላትም “ይህን ካወቃችኹ ለምን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰበሰባችሁን?” በሚል ስብሰባውን ረግጠው ይወጣሉ። አንዳንዶችም ለፀብ ይጋበዛሉ። እንዴት መታገስ ተሳናቸው?
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሃይማኖታዊ ፉክክሩ እና ትንኮሳው የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ጭምር የጠየቀ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ አቶ አባይ ፀሐዬ ትኩሳቶችን ለማርገብ ላይ ታች ባዝነዋል። የሁለቱም እምነት ተከታዮች በሃይማኖታዊ ክብረ-በዐሎቻቸው ላይ ተከታዮቻቸውን ሆ- ብለው አደባባይ እንዲወጡ በማባበል እግረ መንገዳቸውን ጡንቻቸውን ለማሳየት ተጠቅመውበታል። አንዳንዴ ከሃይማኖታቸው መሠረታዊ አስተምህሮዎች ጭምር በሚጣረስ መልኩ አስጸያፊ ቃላት ጨዋ በሚመስል መንገድ ተለዋውጠዋል፡፡ የክሩሴድ ጦርነት ክተት የታወጀ እስኪመስል ዛቻን ያዘሉ ጽሑፎችን በአልባሳት እያተሙ ለአደባባይ አብቅተዋል። ይህች ደሴት እኔ ከምከተለው ሃይማኖት ሌላ ለማስተናገድ ቦታ የላትም ሲሉም ያወጁ ነበሩ። ይህን መሰሉን ነገር ስመለከት አብሮነታችን በቋፍ ያለ መስሎ ይሰማኛ፤ እንዲህም አስባለኹ፡፡ ብዙ የተባለለት የ‹‹ሼ-መንደፈር›› ታሪካችን ታሪክ ብቻ ሊኾን ይችላል። አላህ እና እግዚአብሔር ካልታደጉት በቀር።
the link for Dereje Haile’s news is mistakenly connected to Googlenewspaper. Please, fix it. Otherwise, it is a superb online media!
Keep it up!
-