መድረክ ወደግንባርነት ተሸጋገረ
መድረክ ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ ግንባር ዴሞክራሲና ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰራ፣ መገንጠልን እንደማይደግፍ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርአት እንዲሰፍን ሕገ መንግሥቱ በሕዝብ ውሳኔ እንዲሻሻል እንደሚሠራ፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት እንደሚተጋ ገልጿል።
የመድረክ ወደ ግንባርነት መሸጋገር በምርጫ ቦርድ መጽደቅ እንደሚኖርበት አንድ የሕግ ባለሞያ ለአዲስ ነገር ዘጋቢ ገልጸዋል።
ኢሕአዴግ አዲሱን የተቃቃሚዎች ትብብር ለመበታተን የሚያደርገውን ጥረት በአዲስ መልክ መጀመሩ እንደማይቀር በስፋት እየተነገረ ነው።
(ሙሉ ገ.)
ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም፡- የኢህአዴግ ግንባር ላለፉት 20 ዓመታት ሥልጣኑን ለብቻው ተቆጣጥሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሰቆቃ ለመቋቋም “ግንባርን በግንባር ነውና መግጠም የሚቻለው መድረክም ሲያካሂደው የሰነበተውን ውይይት በስኬት አጠናቆ ወደ ግንባርነት ለመሸጋገር መወሰኑን የመድረኩ የአመራር አባል ዶ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ፡፡
ለዚህ የግንባር ምስረታ ውሳኔ በመድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በሙሉ አንድ ፓርቲ አንድ ድምጽ በሚል መርህ ነው ከስምምነት ላይ ደርሰው ወደግንባር የመጣነው በማለት ያብራሩት ዶ/ር መረራ “ቀደም ሲል የነበሩ ውህደቶችና ግንባሮች የፈረሱበትን ምክንያቶች በሙሉ ተምረንበታል” ብለዋል፡፡
“በግንባሩ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በሙሉ በራሳቸው ነጻና የመወሰን ብቃት ያላቸው ነገር ግን በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው የሚሰሩ ናቸው፣ ሁሉንም ልዩነቶቻችንን አስወግደን ቢሆን አንድ ፓርቲ እንሆን ነበር” ብለዋል፡፡
“ኢህአዴግ ላለፉት 20 ዓመታት ወደ ሰሜን ሲሄድ ህዝቡን አማራና ኦሮሞ ሊያጠፋህ ነው፣ ወደ አማራ ክልል ሲሄድ ደግሞ ኦሮሞው አገሩን ሁሉ ሊወስድብህ ነው፣ እንደገና ወደ ኦሮሞ ክልል ሲያመራ ደግሞ እነመረራ እንደገና ነፍጠኛውን ተሸክመውብህ መጡ እያለ በከፋፍለህ ግዛው ስትራቴጂው ነው ሁሉን እየገዛ ያለው፣ ይህን ለመከላከል በአንድነት ግንባር ሆነን መንቀሳቀስ ግድ ይለናል፤ ሕዝቡም ከ10 ዓመት በፊት ይህን ተረድቶ ነው ‘ተባበሩ አሊያም ተሰባበሩ’ ያለው ብለዋል፡፡”
ኢህአዴግ ራሱ የአንድ ፓርቲ የበላይነት እያንጸባረቀ አይጠቀምበትም እንጂ የአራት ድርጅቶች ግንባር ነበር ያሉት የመድረክ የአመራር አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “ነገር ግን ሦስቱ ፓርቲዎች የይስሙላ ናቸው፤ እኛ ግን ስድስቱም ፓርቲዎች የራሳቸው ህልውና ኖሯቸው አንዱ አንዱን ሳይጫን በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ የሚሰራበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በማበልጸግ የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነትን እያጠፋን በሀገር ጉዳይ ላይ አንድነትን እንገነባለን” ብለዋል፡፡
በመድረክ ግንባር ሥር ከሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥ “አንድነትን እንጂ መገንጠልን የሚደግፍ ፓርቲ የለም፣ ሁላችንም በጋራ በፍትሕና በዴሞክራሲ የምንኖርባትን ኢትዮጵያ መመስረት እንፈልጋለን” ብለዋል- ዶ/ር ነጋሶ፡፡
መድረክ ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ ግንባር ዴሞክራሲና ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰራ፣ መገንጠልን እንደማይደግፍ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርአት እንዲሰፍን ሕገ መንግሥቱ በሕዝብ ውሳኔ እንዲሻሻል እንደሚሠራ፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት እንደሚተጋ ገልጿል።
የመድረክ ወደ ግንባርነት መሸጋገር በምርጫ ቦርድ መጽደቅ እንደሚኖርበት አንድ የሕግ ባለሞያ ለአዲስ ነገር ዘጋቢ ገልጸዋል።
ኢሕአዴግ አዲሱን የተቃቃሚዎች ትብብር ለመበታተን የሚያደርገውን ጥረት በአዲስ መልክ መጀመሩ እንደማይቀር በስፋት እየተነገረ ነው።
No comments yet... Be the first to leave a reply!