የትናንቱ የፍርድ ቤት ድራማ በተደናገጡና በተምታቱ ምስክሮች ለቅሶ ተገባደደ፤ ዛሬ ይቀጥላል
“ዘመኑ እና ዐቃቤ ሕጎች፤ እግዚአብሔር ያያል” እስክንድር ነጋ
የመጨረሻው ምስክር ዛሬ ይሰማል፤ ደበበ እሸቱ ይሆን?
(ሙሉ ገ./ አዲስነገርኦንላይን)
ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ፡- የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት ወንጀል በከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ላይ በኢቲቪ አኬልዳማ ዶኩመንተሪ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችን በዋና ምስክርነት አቀረበ፡፡ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ አርቲስት ደበበ እሸቱ 29ነኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የትናንትናውን የችሎት ውሎ የተከታተሉት ሪፖርተሮቻችን እና የተከሳሽ ቤተሰቦች ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው አቀናብረነዋል።
(ሙሉ ገ./ አዲስነገርኦንላይን)
ማክሰኞ ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ፡- የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት ወንጀል በከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ላይ በኢቲቪ አኬልዳማ ዶኩመንተሪ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችን በዋና ምስክርነት አቀረበ፡፡ ብዙዎቹ መስካሪዎች በጭንቀትና በመርበትበት ሲናገሩ፣ አንዳንዶቹም ሲያለቅሱ ነበር። ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ አርቲስት ደበበ እሸቱ 29ነኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የትናንትናውን የችሎት ውሎ የተከታተሉት ሪፖርተሮቻችን እና የተከሳሽ ቤተሰቦች ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው አቀናብረነዋል።
የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና በክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ላይ መስክረው ሲወጡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ዘመኑ እግዚአብሔር አለ፤ ያያል!” በማለት ሲናገር አቶ ዘመኑ ዓይኑን በእጆቹ ሸፍኖ እያለቀሰ በመውጣት ወደ ፖሊስ ሚኒባስ ገብቷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ 28ተኛ ምስክር ተደርገው የቀረቡት አቶ አበበ ታፈሰ በችሎት ፊት አልቅሰው ዳኞች አረጋግተዋቸዋል፤ የአንድነት ፓርቲ አባል አሳምነው ብርሃኑ በአንዷለም አራጌ እና በናትናኤል መኮንን ላይ በጭንቀት ተውጦ እንዲመሰክር ተደርጓል፡፡
በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ትላንት ለሙሉ ቀን ዐቃቤ ሕግ በወንጀሉ ቀጥተኛ የተሳትፎና እውቀት አላቸው የተባሉት ዋና ዋና ምስክሮች ሲደመጡ 22ተኛ ምስክር ተደርገው የተቆጠሩት አቶ ሰብስቤ ማርዮ በኤርሞን አካዳሚ ኮሌጅ የጥበቃ ሥራ ይሰሩ እንደነበርና በኋላም በእድገት በትምህር ቤቱ ውስጥ ፎቶ ኮፒ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል። በ2003 ዓ.ም ታህሳስ ወይም ጥር ወር ናትናኤል የመሥሪያ ቤታችን ላይብራሪያን ሆኖ ስለሚሰራ ወደ እኔ መጣና ከአንድ ደስታ ወረቀት በላይ ኮፒ የሚያደርገው ነገር እንዳለውና እንድተባበረው ጠየቀኝ፣ ይህ ብዙ ነው ወረቀት ፈርሜ ስለማወጣ ይከብደኛል ስለው በበነጋታው በቦርሳው አንድ ሙሉ ደስታ ወረቀት አመጣና እኔ እየፈራሁ ከድርጅቱ ሥራ ጎን ለጎን አብረን ኮፒ አደረግን፤ ወረቀቱ በአራት የተከፈለ ሲሆን የነጻነት ለውጥ ጥሪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ ፖሊስ፣ መከላከያ ይላል፣ በሌላ በኩል ማሳሰቢያ ለጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ይልና የሕዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ የሕዝብ ነውጥ ይመጣል ይላል፣ በወቅቱ እኔ ሥፈራ ናትናኤል ችግር የለም ብሎ ምሳ ጋብዞኝ ሃምሳ ብር አስጨበጠኝ ብለዋል፡፡
23ተኛ ምስክር አቶ ታምራት ሻማ ቤተ እሥራኤላዊ መሆናቸውን ገልጸው ለዐቃቤ ሕግ መሪ ጥያቄ የመጣሁት በአቶ ምትኩ ዳምጤ፣ በአቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፣ እና በአቶ ፋሲል የኔአለም ላይ ለመመሥከር ነው ያሉ ሲሆን አቶ ምትኩ ሃምሌ 2003 ዓ.ም የግንቦት 7 አባል እንደሆነ ነግሮን እኛንም አባል እንድንሆን አማከረን፤ አቶ ፋሲል የተባለ የኢሳት ጋዜጠኛ እና የግንቦት 7 አመራር እንደሆነ ነገረን፡፡ የተለያየ የአመጽ ጥሪ እንድናስተላልፍ አቶ ምትኩ እኔን፣ ተስፋሁንን እና ደረጄን መለመለን፡፡ ሐምሌ ላይ ከአቶ ፋሲል ጋር ግንኙነት ስለነበረን በጀት መደበልን፡፡ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ኮምፒውተር፣ ቤት ለመከራየት ፕሮፖዛል ላክንለት፣ ቤት በ3 ሺህ ብር ኪራይና ለእኛም በወር አምስት ሺህ ብር እንዲከፍለን ወደ 30 ምናምን ሺህ እልክላችኋለው አለው፡፡ መስከረም ወር ላይ አቶ ታምራት የተስፋሁንን ስልክ ለፋሲል ሰጥቶት ደወለለትና አበበ ቀስቶ ደውሎ እንደሚያገኘውና የአመጽ ጥሪ ባለ 15 ነጥቦች ወረቀት ታዘጋጃላችሁ አለው፡፡ ከዚያም አበበ ደውሎለት ኮልፌ እፎይታ አካባቢ ተገናኝተው 2 ሺህ የአመጽ ወረቀት ሰጠውና የእነርሱ ቤት እሩቅ ስለነበር እኔ ቤት አሳደርኩት፡፡ በበነጋታው ወረቀቶቹን ከመገናኛ እስከ ኮተቤ እንድንበትን ተወስኖ በተዘጋጀንበት ጊዜ በፖሊስ ተያዝን ብሎ መስክሯል፡፡
24ተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር አቶ ተስፋሁን አናጋው ኃይሌ ለዐቃቤ ሕግ መሪ ጥያቄ የመጣሁት በአቶ ምትኩ ዳምጤ፣ በአቶ አንዷለም አራጌ፣ በአቶ ናትናኤል መኮንን፣ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እና በፋሲል የኔአለም ላይ ምሥክርነት ልሰጥ ነው ያለ ሲሆን በ2003 ዓ.ም ጥቅምት ወር የሰሜን አፍሪካ ብጥብጥ የተቀሰቀሰበት ነበር፤ምትኩ ጓደኛዬ ነው ወንድሜ ማለት ነው ደውሎ ቤቱ ጠራኝና ኢሳት ቲቪ ከፍቶ አሳየኝ፣ በወቅቱ ፕሮግራሙን የሚመራው ፋሲል ነበር- ልክ እንደ ግብጽ ብጥብጥ ለመፍጠር፡፡ ይህን ፕሮግራም አይቼ ሲመሽ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ እያለ አቶ ምትኩ ስልክህ ሂሳብ አለው አለኝና አሜሪካን አገር ለሚገኘው ፋሲል የኔአለም ምልክት አደረገለት እና በእኔ ስልክ ደወለለት፡፡ ፕሮግራሙ ጥሩ ነው በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያም ውስጥ ብጥብጥ ሊቀሰቀስ ይችላል ካለው በኋላ ከእኔ ጋር አስተዋወቀው፡፡ ከዚያ በኋላ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ይደውልልኝ ነበር፡፡ በስኳር፣ ዘይት መወደድ መረጃ እየሰጡት እያጋነነ ያቀርብ ነበር፡፡ የካቲት 21 ቀን 2003 ዓ.ም መገናኛ ቤተ እስራኤል አካባቢ ሰልፍ ለመውጣት ጠይቀን ተከልክለን ተመለስን፤ ምትኩ ይህን መረጃ ሰጥቷቸው አንድ ሰው በፖሊስ ተገደለ ሲሉ በኢሳት አጋነው አቅርበውታል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ምስክሩ ብዙ ነገሮችን እንደ ሌሎቹ ምሥክሮች ቀደም ሲል ከተናገሩት የሳቱ ሲሆን በዐቃቤ- ሕግ ድጋሚ መሪ ጥያቄዎች ደግሞ የሚከተሉትን ተናግሯል፡፡በኢትዮጵያ የአመጽ ጥሪ ለማድረግ እኔ፣ ታምራት፣ ደረጄ ተመልምለን ቤት ተከራየን፣ ለፋሲል በስልክ እኔ የአንድነት ፓርቲ አባል መሆኔን ስገልጽለት ማንን – ማንን ታውቃለህ አለኝ፤ ከፍተኛ አመራሮችን ስነግረው አንዷለምን እንደሚያውቀው እና ናትናኤልን ግን እንደማያውቀው ገልጾልኝ እነርሱን እንዳገኝ አዘዘኝ፡፡ ከዚያም በሐምሌ ወር አንድ ቀን አንድነት ቢሮ ሄጄ አንዷለምን አገኘሁት፡፡ አንዷለም ናትናኤልን ጠራውና አንድነት ውስጥ የተቋቋመ ቡድን አለ ከዚያ ውስጥ አንተም አንዱ ነህ አለኝ (በዚህ ጊዜ አንዷለም በኀዘን ይስቅ ነበር)፡፡
ከዚያም ወረቀት ጽፈን ለማሰራጨት ነበር የተዘጋጀነው፤ መስከረም 2004 ዓ.ም ፋሲል ደውሎ መኢዴፓ እና ኢአዴድ የተባሉ ሁለት ፓርቲዎች ሰልፍ ስለጠሩ አግዟቸው አለንና አበበ ቀስቶ ይደውልልሃል አግኘው አለኝ። ኮልፌ አጠና ተራ ፎቶ ኮፒ ቤት ሄጄ ለ2 ሺህ ኮፒ ሊደረግ 2 መቶ ሲቀረው ደረስኩ፡፡ ከዚያም መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ.ም አቶ ምተኩ ላምበረት፣ ጉርድ ሾላ እና ሲኤም ሲ እንድንበትን ገልፆልን መስከረም 12 ቀን በፖሊስ ተያዝን፡፡ ወረቀቱ የተቃውሞ ጥሪ ነው የሚለው፣ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ፣ የታክሲ አመጽ፣ ካለ በኋላ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የተቋቋመ ቡድን አለ ያለኝ ፋሲል የኔአለም ሲሆን ለዚህ ተግባር ከ5 መቶ ሺህ ብር እስከ 6 መቶ ሺህ ብር ተመድቧል አንዷለም አራጌ ይመራዋል ብሎኛል፤ አንድነት ፓርቲ ለአንዷለምና ለናትናኤል ሕጋዊ ከለላ እንዲሆናቸው ነው፣ 2003 ዓ.ም ገና ሲቃረብ ፋሲል በግሌ መቶ ዶላር ልኮልኝ ተጠቅሜበታለሁ ብሏል፡፡
ምሥክሩ ከተከላካይ ጠበቆች በቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄ አቶ አንዷለምና አቶ ናትናኤልን አንድነት ፓርቲ የትኛው ቢሮ አገኟቸው ሲባሉ ማስታወስ ባለመቻላቸው ፕ/ር መሳይ በስካይፒ ህዝባዊ ንግግር አድርገው ሲጨርሱ ውጪ ነው ያገኘኋቸው አሉ፤ የተከላካይ ጠበቃ የሕጋዊው የአንድነት ፓርቲ አባል ነዎት ሲሏቸው አዎን ያሉ ሲሆን በፓርላማ አሸባሪ ድርጅትየተባለው የግንቦት 7 ፓርቲ አባል ነዎት ሲሉት አይ አይደለሁም በግሌ ነው በማለታቸው ጠበቃው ስለዚህ በእርስዎ አማካኝነት አንድነትና ግንቦት 7 የተገናኙበት መሰላል የለም ማለት ነው ሲሉት እኔ እንጃ ያለ ሲሆን እሺ ሊበተን የነበረውስ ወረቀት የግንቦት 7 ነው ወይ ተብሎ ሲጠየቅ እኔ አላውቅም በማለት መልሷል፡፡
25ተኛ ምሥክር የመኢዴፓ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ጎፎሌ፣ በክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፣ በፋሲል የኔአለም እና በእስክንድር ነጋ ላይ ለመመስከር መምጣታቸውን ገልጸዋል። በምስክርነታቸውም ከአበበ ቀስቶ ጋር ከ1997 ዓ.ም በፊት ጀምሮ በፓርቲ ሥራ እንደሚተዋወቁ እና አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ከምርጫ 2002 ዓ.ም በኋላ ወደ ኡጋንዳ በመሰደዳቸው እርሳቸው የፓርቲው ዋና ጸሐፊ መሆናቸውን ገልጸው በዚህ የተነሳ ከአበበ ቀስቶ ጋር ከምርጫ 2002 ዓ.ም በኋላ አንዳንድ የፖለቲካ ሥራዎችን አብረን እንሰራ ነበር፤ ከአቶ እስክንድርና ከአቶ ፋሲል ጋር ያስተዋወቀኝ አበበ ቀስቶ ነው፤ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት በተዘጋጀንበት ወቅት አቶ ፋሲል በስልክ ያበረታታኝ ነበር ብለዋል፡፡
ከእስክንድር ጋር ለሁለት ቀን ብቻ ነው የተገናኘሁት፣ እርሱም ጳጉሜ 2 ቀን 2003 ዓ.ም ሲሆን ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል ተገናኝተን እርሱ ታዋቂ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ስለሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ነበር የተነጋገርነውና ምክሩን የጠየቅነው፡፡ በወቅቱ እስክንድር የቱን ፓርቲ እንደጠራን፣ የቱን ፓርቲ እንዳልጠራን አያውቅም ነበር፡፡ ከዚያም መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም ከአበበ ቀስቶ ጋር ሆነን እስክንድርን አገኘነው፡፡ ከዚያም እስክንድር ሕዝባዊና ሠላማዊ አመጽ ለማድረግ የምግብ ማቆም አድማ፣ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ሐሳብ ሰጠኝ፡፡ እኛ ሰልፉን ልንጠራ ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ፈቃድ የጠየቅነው ሁለት ፓርቲዎች ብቻ ነን፡፡ እስክንድር ግን ሁሉንም ፓርቲዎች እንድናሳተፍ ጠይቆን ነበር፡፡
ሰልፉን ለማካሄድ የገንዘብ ችግር ካለ ከየትኛውም የውጭ ኀይል ምንም አይነት ድጋፍና ትብብር አትጠይቁ ያለን ሲሆን አንተ ጋር ሃያ ሺህ ብር፣ እኔ ጋር ሃያ ሺህ ብር ሌላው ጋር ሃያ ሺህ ብር አድርገን እናካሂደዋለን ብሎኝ ነበር ብሎ መስክሯል፡፡
ፋሲል የኔአለም በአበበ ቀስቶ አማካኘነት ለሁለት ቀን በስልክ አግኝቶኝ ወደ ፊት የተጠናከረ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉና ከአበበ ቀስቶ ጋር እንደሚገናኙ አውቅ ነበር፡፡ አቶ አበበ ቀስቶ በ2004 ዓ.ም ለሚካሄደው ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ፋሲል በፋይናንስ እንደሚረዳው ይነግረኝ ነበር፡፡ ከዚያ 2 ቀን ሌላ እስክንድርን አግኝቼው አላውቅም፡፡ ፋሲል ግን ለአበበ ቀስቶ ለትራንስፖርት ብሎ አንድ ሺህ ሁለት መቶ (1200 ) ብር እንደላከለትና ልናደርግ የነበረው ሰልፍ ሁለት ቀን ሲቀረው ደግሞ ስምንት ሺህ አምስት መቶ (8500) ብር ላከልኝ ብሎ ለፓርቲያችን የሁለት ወር የቢሮ ኪራይ ከፍሎልናል፤ ሰሜን ሆቴል ፕረስ ኮንፈረንስ ስናካሂድም ስድስት መቶ አሥራ አምስት (615) ብር ከፍሎልናል፤ ለሕዝብ ልንበትነው የነበረው ወረቀት በኑሮ ውድነት፣ በመሬት ሊዝ አዋጅ፣ በግብር፣ በተባረሩት የቴሌ ሰራተኞች ጉዳይ የሚያተኩር እኔ 7 ነጥቦችን ጽፌ የነበረ ሲሆን በኋላ አበበ ቀስቶ 15 ነጥቦች አድርሶ አርቅቆት አምጥቶት ነበር ብሎ መስክሯል፡፡
በአቃቤ ሕግ ድጋሚ ጥያቄ፣ አቶ ዘመኑ እስክንድር ፣ ፋሲል እና አበበ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ጓደኞች መሆናቸውን ተናግሮ የፓርቲያችንን ጠቅላላ ጉባዔ ስናደርግ የአውሮፓ ተወካይ ስላልነበር በዚህ ጉዳይ ላይ እና በጋዜጣ አስተያየት በሰጠሁበት ሃሳብ ላይ ከፋሲል ጋር ተነጋግረን ነበር፤ እኛ በምናደርገው እንቅስቃሴ ፋሲል በገንዘብ እንደሚደግፈን አበበ ነግሮኝ ነበር ብሏል፡፡
አቶ እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛና ተንታኝ መሆኑን አውቃለሁ፣ በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ምክር እንዲሰጠን አቶ አበበ ነው ያገናኘን፡፡በዚህ ሰልፍ ላይ ሕዝብ ወጥቶ አልገባም ካለ ኃላፊነቱን የሚወስደው መንግሥት ነው፤ ይህን የነገረኝ አበበ ነው እንጂ ከእስክንድር ጋር አላወራንም ብሎ መስክሯል፡፡ እስክንድር ወደ ፊት የሲቪክ ማህበራትን አስተባብሮ ታላቅ ሠላማዊ ሰልፍ የመውጣት እቅድ እንዳለው ነግሮን ነበር ብሏል፡፡
አቶ ዘመኑ ሞላ ምስክርነቱን ጨርሶ ፍርድ ቤቱ ለተከላካይ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ሲፈቅድ እስክንድር ብድግ ብሎ ቆመና ክቡር ፍርድ ቤት ምስክሩን እኔ ራሴ መስቀለኛ ጥያቄ እንድጠይቀው ይፈቀድልኝ ሲል ጠየቀ፤ ዳኞቹም ልትጎዳ ስለምትችል መጀመሪያ ከጠበቆችህ ጋር ተመካከርና በእነርሱ በኩል ብትናገር ይሻልሃል አሉት፡፡ እስክንድር እኔ እውነቱ ወጥቶ ብጎዳም ልጎዳ! እውነቱ ይውጣ እኔ ምንም ሚስጥር የለኝም አለ፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን ምናልባት እኛ ስንጠይቀው ያልነገረን በአእምሮው የሚጉላላ ነገር ካለ ቢናገር መልካም ነው በማለታቸው እስክንድር እኔ እውነቱ ይውጣና የሚያስቀጣኝም ከሆነ ልቀጣ፣ የሚጎዳኝም ከሆነ ልጎ ዳ አለ፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄህን አሳጥረህ በመስቀለኛ ጥያቄ ደንብ በተነሳ ጉዳይ ላይ ብቻ ጠይቅ አሉት፡፡
“አቶ ዘመኑ ውይይታችን በምን ተጀመረ? ሰላማዊ ሰልፍ ይቅር፣ አያዋጣም አልነበር ያልኳችሁ?” “አዎን” በማለት አቶ ዘመኑ መለሱ፣ “አዎን ሰላማዊ ሰልፉ ሊቀለበስና አላስፈላጊ ነገር ሊፈጠር ይችላል ብለኸናል፣ ነገር ግን እኛ ለከንቲባው ጽ/ቤት ደብዳቤ ስላስገባን የአንተን ሃሳብ አልተቀበልንም በሰላማዊ ሰልፉ እንቀጥላለን አልንህ፡፡”
“እኔ ጋር ስለፋሲል አንስተን አውርተናል?” በማለት እስክንድር ላቀረበው ጥያቄ “አይ አላነሳንም” በሚል አቶ ዘመኑ መለሱ፤ “በሁለተኛው ቀን የገንዘብ ጉዳይ ሲነሳስ” አለ እስክንድር፣ “ከውጪ ከየትም የገንዘብ ድጋፍ አትቀበሉ፤ ሃያ ሃያ ሺህ ብር እኛው እናዋጣ ነበር ያልከን” በማለት ዘመኑ መለሰ፡፡ “እኔ በመርህ ደረጃ ከሃያ ሺብር በላይ ለማይጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከማንም ጋር አትነካኩ፤ ሀገር ውስጥ ያለ እንቅስቃሴ የሀገር ቤት ነው አልኳችሁ እንጂ እንዴት ብዬ ነው ‘ይቅር አያዋጣም’ ላልኩትና ለማልደግፈው ሰልፍ ሃያ ሺህ ብር አዋጣለሁ ብዬ ቃል የምገባው?” ብሎ አቶ ዘመኑን ጠየቀው፤ በመጨረሻም “ስንለያይ ከኔ የምትጠብቁት ሃያ ሺህ ብር ነበር?” በማለት ጠየቀው። አቶ ዘመኑም “አዎን፣ ከአንተ የምንጠብቀው ሃያ ሺህ ብር አልነበረም” አለ፡፡ “እናንተ ሰላማዊ አመጽ ብላችሁ የምትጠሩትን እኔ ተቀብየዋለው?” በማለት እስክንድር ሲጠይቅ አቶ ዘመኑ “አይ እኛ ነን ሰላማዊ አመጽ የምንለው አንተ ግን ሠላማዊ ሰልፍ ነበር የምትለው” በማለት መልሷል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በድጋሚ ጥየቃ አቶ ዘመኑን እያስጨነቀ የጠየቃቸው ሲሆን ገንዘብ ከውጭ እንዳትጠይቁ ብሎናል ብለዋል ለምንድን ነው በሚል ላነሳው ጥያቄ አቶ ዘመኑ እስክንድር ጋዜጠኛ ነው ወደ ፊት የሲቪክ ማህበራትን በማስተባበር ለሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፍ እኔ ሃያ ሺህ ብር እሰጣለሁ ብለዋል በማለት ቃሉን አጥፎ መሰከረ፡፡በዚህ ጊዜ እስክንድርነና ጠበቃው ተነሱና እስክንድር እኔ እንዴት ለማልደግፈውና ይቁም ላልኩት ሰላማዊ ሰልፍ ሃያ ሺህ ብር አዋጣለሁ ብሎ ሲጠይቀው አቶ ዘመኑ አላልክም በማለት እንደገና ቃሉን ወደ ቀድሞው ነጥብ መለሰ፡፡
ከዚያም ዐቃቤ ሕግ ለአቶ ዘመኑ በመርህ ደረጃ በሚል ነበር የምትነጋገሩት በሚል ላቀረበው ጥያቄ አቶ ዘመኑ ብሩን ካጣችሁ እኔ እሰጣችኋለሁ ብሎ እንዳለን ነው እኔ የተረጎምኩት በማለት መልስ ሰጥቶ አቶ ዘመኑ ጨርሰሃል ተብሎ ሲወጣ እስክንድር ተነስቶ እጁን ወደ ላይ እያሳየ “ዘመኑ እግዚአብሔር አለ፤ ያያል፤ ዘመኑ እግዚአብሔር አለ ያያል! እናንተም ዐቃቤ ሕጎች እግዚአብሔር ያያል” በማለት ሲናገር አቶ ዘመኑ አይኑን በእጁ ይዞ እያለቀሰ በፖሊስ ታጅቦ ወጥቷል፡፡ በዚሁም የጠዋቱ ችሎት ለከሰሃት ተቀጥሮ ተበተነ፡፡ የአዳራሹ ሰው በተለይ ሴቶች ያለቅሱ ነበር፡፡
ከሰአት በኋላ የዋለው ሦስተኛ ወንጀል ችሎት
26ተኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው የአንድነት ፓርቲ አባል አቶ አሳምነው ብርሃኑ ከሀገር ውጪ ባሉ የግንቦት 7 አመራር መስፍን አማን እና ውቤ፣ በሀገር ውስጥ ደግሞ በአቶ አንዷለም አራጌ እና በናትናኤል መኮንን ላይ ሊመሰክር መምጣቱን ገልጿል። ከመስፍን አማን ጋር ቀደም ሲል በ1997 እንደሚተዋወቁና በፌስ ቡክ ተጻጽፎ መገናኘቱንና ስለሀገር ውስጥ ሁኔታ፣ ፖለቲካ ግለጽልኝ ብሎ እንደጠየቀውና እርሱም ይህን ለማድረግ ገንዘብ ጠይቆት የፉት ቦል ክለብ የሚል በሽፋን እቡዕ እንቅስቃሴ መስርተው የአባል መሙያ ፎርም በኢሜል ተልኮለት ሰዎችን በመመልመል ለግንቦት 7 አባል እንደሚያደርጉ ገልጾ፣ ናትናኤል የቦሌና የጨርቆስ ክፍለ ከተማ ሲመለምል እርሱ ደግሞ የሌሎችን መልምሎ እንደላከለትና በኋላ መልስም ገንዘብም እንዳላከለት ተናግሯል፡፡
የካቲት መጨረሻ 2003 ዓ.ም ከአንዷለም ጋር በሰሜን አፍሪካ ብጥብጥ ጉዳይ እንደተወያዩና እዚህ ሀገር ይሄን የሚፈጥረው ፓርቲ ነው ግለሰብ በሚል መነጋገራቸውን፤ አንዷለም “ተደራጁ፣ አደራጁ” እንዳላቸውና ከናትናኤል ጋር እንዲገናኙ እንዳደረጋቸው፤ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ፣ ለወጣቶች ጥሪ” የሚል ወረቀት እንዲበትኑ መታዘዙን እንደሚያውቅ፤ ወረቀቱን ፒያሳ ተቀብሏቸው በአቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ የካ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መበተኑን፣ ከዚያም በፖሊስ ተይዞ መታሰሩን ገልጾ አሁን ተጣርቶ ተለቅቄያለሁ በማለት በመሳቀቅ ሲናገር ተደምጧል፡፡
የተከላካይ ጠበቆች ባነሱበት መስቀለኛ ጥያቄዎች የተምታታው አቶ አሳምነው አንድ ጊዜ የግንቦት 7 አባል ነበርኩ፣ በሌላ ጥያቄ ደግሞ የግንቦት 7 አባል አልነበርኩም በማለት መልሷል፤ አቶ ናትናኤል ምስክሩን ለመጠየቅ ሲነሳ ፍርድ ቤቱ “ወይ ጠበቃህ ይጠይቅ አሊያም ጠበቃህን ትተህ አንተ ጠይቅ” በማለት ጥያቄ እንዳያነሳ ከልክሎታል። ፍርድ ቤቱ “በጠዋቱ ችሎት አቶ እስክንድር እጃቸውን እያወዛወዙ የተናገሩት በምስክሮች እና በፍርድ ቤቱ ላይ ጫና አሳርፏል ስለዚህ ይህ ችሎት ግልጽ ነው የችሎት ሕግ አክብሩ” ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የዐቃቤ ሕግ 27ተኛ ምስክር አቶ ሳምሶን ሌላይ ገ/ማርያም ሰሜን ጎንደር መተማ ቲንግና ሬስቶራንት የራሰቸው መሆኑን ገልጸው አቶ ዮሐንስ ተረፈ (አቶ ጳውሎስ) እና አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ (አቶ ግርማ) በስልክ ከጎንደርና ከኡጋንዳ እንደሚደውሉለትና ሰዎችን ወደ አውሮጳና አሜሪካ ለመላክ ወደ ሱዳን እንዲያሻግርላቸው እንደሚጠይቁት እና እንደተባበራቸው፣ አቶ ዘለሌ አቶ ግርማ በሚል ስም በሱዳን ስልክ እንደሚደውልልት፣ ወደ አውሮፓ ይሄዳሉ የተባሉት ሰዎች ወደ ኤርትራ ሄደው በሽብርተኝነት እንደሚሰለጥኑና ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱና የተወሰኑት ተቸግረናል ብለው ደውለው እውነቱን እንደነገሩት መስክሯል፡፡
የዐቃቤ ሕግ 28ተኛ ምስክር አቶ አበበ ታፈሰ እድሜ 40 የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ነዋሪ መሆናቸውንና የላዳ ታክሲ ሾፌር መሆናቸውን፣ በአቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ፣ በዮሐንስ ተረፈ እና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ሊመሰክሩ መምጣታቸውን ገልጸው አንድ ቀን 2003 ዓ.ም አቶ ዘለሌ ደውሎላቸው ግንቦት 7 ፓርቲ ውስጥ መግባት ትፈልጋለህ ወይ ብለው ጠይቀዋቸው ፈቃደኛ መሆናቸውን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሁለት ሰው ለትምህርት አውሮፓ የሚሄድና ሁለት ሰው ደግሞ ለወታደርነት እንዲመለምሉ ተጠይቀው ለወታደርነት ሰው እንዳላገኙና ለአውሮፓ ጉዞው ግን እርሳቸውንና አንድ ሌላ ሰው መልምለው በተሰጣቸው ፍላሽ ዲስክ አማካኝነት የግንቦት 7 ፓርቲን መመሪያ እንዳነበቡና የጉዞ ካርታ ተመልክተው ከመለመሉት አንድ ሰው ጋር በጎንደር መተማ አድርገው ወደ ሱዳን ከዚያም ኤርትራ እንደወሰዷቸውና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አቀባበል እንዳደረጉላቸው፣ ከኤርትራዊው ኮሎኔል ፍጹም ጋር የኮምፒውተር፣ የሽጉጥ፣ የቦምብ እና የፈንጂ ስልጠና መውሰዳቸውን የእርሳቸው ፍላጎት ግን ወደ አውሮፓ መውጣት እንደ ነበር እየተጨናነቁ እያላባቸውና ለደቂቃዎች ዝም በማለት እያለቀሱ መስክረዋል፡፡ (ፍርድ ቤቱ “አይዞዎት፣ ይረጋጉ” እያላቸው)
28ተኛው ምስክር ከተከላካይ ጠበቆች በቀረበባቸው መስቀለኛ ጥያቄ ምንም የኮምፒውተር እውቀት እንደሌላቸውና ተጠቅመው እንደማያውቁ፣ ቤታቸውም ኮምፒውተርም እንደሌላቸው ተናግረው ነገር ግን በአንድ ቀን ከሰው ኮምፒውተር ተውሼ ሚስጥር ስለሆነ ማንም በሌለበት ከፍቼ የግንቦት 7 መመሪያና የጉዞ ካርታውን ተመለከትኩ ብለው ምስክርነት የሰጡ ቢሆንም ኮምፒውትር ያዋሳቸውን ሰው ስም እና ስለሁኔታው ማስረዳት ሳይችሉ ቀርተው በቃ አንድ ሰው ዝም ብሎ አዋሰኝ በማለት አልቅሰዋል፡፡
ሌሎች ምስክሮች 7 ሆነን ነው ከጎንደር መተማ ሱዳን የገባነው ቢሉም እርሳቸው ሁለት ብቻ ነን 7 መሆናችንን ያወኩት ኤርትራ ነው ብለው መስክረው ስቅስቅ ብለው አልቅሰዋል፡፡
የዐቃቤ ሕግ 29ኛ ምስክር አቶ መኳንንት ጸጋዬ ሰሜን ወሎ የጤና ባለሙያ መሆናቸውን ገልጸው በሻምበል የሸዋስ ይሁንአለም እና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ መስክረው ለዛሬ ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም የመጨረሻው የዐቃቤ ሕግ 29ኛ ምስክር (ደበበ እሸቱ ነው የሚል መረጃ አለ) ሊደመጥ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ማምሻውን ችሎቱ ተበትኗል።
No comments yet... Be the first to leave a reply!