የመድረክ አመራሮች እና የመንግሥት ጋዜጠኞች ተወዛገቡ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር ሲል በትናትናው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመራሮቹ ከመንግሥትና ከህወሓት የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ጋራ ተወዛገቡ።
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተሳተፉ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ ድርጅት፣ እና ባለቤትነታቸው የህወሃት የሆኑት የራዲዮ ፋና እና የዋልታ ጋዜጠኞች “በጥያቄና መልስ ላይ የመጣንበትን ተቋም መመልከቱን ትታችሁ ለጥያቄያችን ብቻ መልስ ብትሰጡን፤ እኛ ጋዜጠኞች ነን” ሲሉ ለመድረክ አመራሮች አቤቱታ አከል ተቃውሞ አስምተዋል።
(ሙሉ ገ./ አዲስነገር ኦንላይን)
ዓርብ ጥር 18 ቀን 2004 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር ሲል በትናትናው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመራሮቹ ከመንግሥትና ከህወሓት የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ጋራ ተወዛገቡ።
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተሳተፉ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ ድርጅት፣ እና ባለቤትነታቸው የህወሃት የሆኑት የራዲዮ ፋና እና የዋልታ ጋዜጠኞች “በጥያቄና መልስ ላይ የመጣንበትን ተቋም መመልከቱን ትታችሁ ለጥያቄያችን ብቻ መልስ ብትሰጡን፤ እኛ ጋዜጠኞች ነን” ሲሉ ለመድረክ አመራሮች አቤቱታ አከል ተቃውሞ አስምተዋል።
የመድረክ የአመራር አባላት ዶ/ር መረራ ጉዲና “እናንተ የመንግሥት ጋዜጠኞች እኮ እንደ ካድሬ አስተኳሽ ሆናችሁ፤ የኢህአዴግን ጥያቄዎች መጠየቃችሁን አቁማችሁ የጋዜጠኝነት ሙያ ሥነ ምግባር እና ብቃት የሚጠይቀውን ሕዝባዊ ጥያቄ በንጽህና እንድትጠይቁ በሕዝብ ገንዘብ የቀጠራችሁ የኢህአዴግ መንግሥት ቢፈቅድላችሁ እኛም ራሳችንን ለመከላከል ወደዚህ ዓይነት ግንኙነት ባልገባን፤ ለኛም እዝኑልን” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበርና የመድረክ የአመራር አባል ዶ/ር መረራ በበኩላቸው “እውነት ለመናገር የእናንተ ሥራ የጋዜጠኝነት ሳይሆን ለኢህአዴግ ግብዓት የሚሆነውን መርጣችሁ የተልዕኮ ሥራ ነው የምትሠሩት፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አዲስ ዘመን ጋዜጣ የእኛን ሙሉ መግለጫ በትክክል ለሕዝብ አታቀርቡም፡፡ በአድሏዊነት ትቆራርጡታላችሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምንናገረውን ሳይሆን እጃችን ሲወራጭ እያሳያችሁ ሌላ ታወራላችሁ፡፡” በማለት ወቅሰዋል።
“አብዛኛው ኢህአዴግ በሚሰራው እንደ አኪልዳማ አይነት ፕሮፓጋንዳዎች እናንተ ዜና ለመስራት በሚል መጥታችሁ የቀረጻችሁትንና በአድሏዊነት ያበጃጃችሁትን ድምጽና ምስል አቅርቦ ነው ስማችንን የሚያጠፋው፣ ክስ የሚመሰርትብን፡፡ እናንተ አድነት ቢሮ መጥታችሁ ያነሳችሁትን ድምጽና ምስል አስረክባችሁ አይደል መንግስት ለተንኮል ስም ለማጥፋት እየተጠቀመበት የሚገኘው?” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ “የፕሬስ ነጻነትን ባንደግፍና ዴሞክራሲያዊ ባንሆን ኖሮ እናንተ የምትሰሩትን ሥራ በማየት ብቻ ሁለተኛ በቢሯችን እንዳትገኙ ማድረግ እንችል ነበር፣ ነገር ግን ለምን እንደምትጠቀሙበት እያወቅን እንኳ ለታሪክ ይቅረብ በሚል ነው እንጂ እዚህ እንድትገቡ አያስፈልግም ነበር” በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡
የሁኔታውን መካረር ያስተዋሉት የመድረክ ሊቀመንበር ዶ/ር ሞርጋ ፉሪሳ “ዛሬ ለጋዜጣዊ መግለጫ በአጀንዳ የጠራናችሁ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር ስንል በመሬት ዓዋጁ ላይ በማተኮር ነው፤ እናንተ ግን ሆን ብላችሁ የኢህአዴግን የተንኮል አጀንዳ ይዛችሁ ሰሞኑን በአፋር የተካሄደውን እገታ ታወግዛላችሁ አታወግዙም፣ ሕገመንግስቱን ትለውጣላችሁ አትለውጡም የምትሉትን አቁማችሁ በተያዘው አጀንዳ ላይ ብቻ እንደ ጋዜጠኛ ጥያቄ ካላችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይቅርታ አድርጉልን” በሚል ተናግረዋል።
የአረና ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበርና የመድረክ የአመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት “በአፋር ውስጥ ስለሞቱ ሰዎች ያነሳችሁትን ጥያቄ እዚህ ላይ እኔ የሚያስገርመኝ ኢሕአዴግ ፈረንጅ ሲሞት ነው የሚጮኸው እንጂ ዜጋ ሲሞት አይጮህም፡፡ ሁለት ጊዜ አፋር ላይ ፈረንጆች ሲሞቱ አዋጅ ታውጇል፡፡ አካኪ ዘራፍም ብሏል፡፡ ግን እስቲ ሰሜን ትግራይና ሰሜን አፋር ሂዱና በየቀኑ የሚፈጸመውን ነገር ለማወቅ ሞክሩ፤ የመንግሥትም ነጻ ጋዜጠኞችም፡፡ ባለፈው ጊዜ አንድ ዓመት ሆኖታል፣ ከሽራሮ ወደ ባድመ የምትሄደው አቡቶቡስ በፈንጅ ተመታ ወደ 30 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ስለዚህ አልተነገረም በአዲስ ዘመንም፣ በቴሌቭዥንም አልሰማሁም፣ በማንም አልሰማሁም፡፡ በየቀኑ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በዛላንበሳ፣ በፆረና አካባቢ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ እንዲያውም ከሦስት ቀን በፊት በአዲነብር አካባቢ፣ በሽሬ አካባቢ 40 ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ይሄ አልተነገረም አልሰማንም፣ ፈረንጅ ቢሆን ግን፣ አንድ ፈረንጅ ቢታፈን ግን ወሬውን በአንድ ጊዜ እንሰማ ነበር፡፡ እነርሱ ድምጽ አላቸው ኀይል አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጋ ግን በመንግሥት ዓይን በጣም ደካማ ምንም የማይታሰብ፣ ቢሞትም ቢቸገርም ቢደኸይም ንብረቱ መሬቱ ቢወሰድም ምንም ሊያመጣ አይችልም የተባለ ነው፡፡ይሄ መታወቅ ያለበት ይመስለኛለኛል” ብለዋል፡፡
ስለዚህ ጉዳይም ስለዘላቂ መፍትሄው ከ10 ዓመት በፊት እኛ ተናግረን ነበር፡፡ ይሄን አካባቢ የሚያተራምሰው የዚህ ችግር ምንጭ ሻቢያ ነው፡፡ እስቲ ሻቢያን እንጨርሰውና አንድ ሃያ ዓመት እረፍት እናግኝ ብለን ነበር፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ይሄን አልተቀበለም፡፡ እንደገና ከ10 ዓመት በኋላ ሻእቢያ አሁን ከነካን የመጨረሻው ይሆናል የሚል ወሬ እየተደመጠ ነው፡፡ እየነካን እኮ ነው ግን ምን ተደረገ? ምንም፡፡ በየጊዜው ሰዎች እየታፈኑ ነው፣ ሰዎች እየተገደሉ ነው፤ ግን ምን ተደረገ? ስለዚህ ይሄ ለሕዝብ ግንኙነት ተብሎ የሚነገር ነው፡፡ መንግሥት ነው የሀገሩን ዜጎችና በሀገሩ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች ማስጠበቅ ያለበት፡፡ እንደውም በመንግሥት ስህተት ሰሞኑን የአፋር ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ውጣ ተብሎ መከራውን እያየ ነው፡፡ ይሄ ቅድም ዶ/ር ነጋሶ እንዳሉት መንግሥታዊ ተግባሩን አለመወጣት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የዜጎቻችንና የውጭ ዜጎች መሞት ያሳስበናል፤ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ያሳዝነናል፤ ሰው እንዲሞትና እንዲሰቃይ አንፈልግም ይሄ አቋማችን ነው” በማለት አቶ ገብሩ አስራት መልስ ሰጥተዋል፡፡
No comments yet... Be the first to leave a reply!