“ፈርጀ ብዙ ድህነት”-የ19 ዓመታት ፍሬ?
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት በሁለት ዲጂት ኢኮኖሚው እያደገ መኾኑን በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ይኹንና አሁንም የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና አስተዳደራዊ ድክመት ዋነኞቹ የአገሪቱ መለያ እንደኾኑ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 5.2 ሚልዮን ሕዝብ አስቸኳይ ርዳታ የሚሻ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ይፋ የኾነው የ“Investing Across Borders” ሪፖርት እንዳመለከተው አገሪቷ ከሰሃራ በታች ከሚገኙት አገራት ንጽጽር እንኳ ስትታይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ለውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት አበረታች ያልኾነች አገር ተብላም ተፈርጃለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አውታር ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ የኢኮኖሚ ባለሞያዎችን እና የኀልዮቶችን (Theories) ድጋፍ የሚሹበት ምክንያት ያላቸው አይመስሉም፡፡ ዘወትር እንደሚያደርጉት ኢኮኖሚውን “ያባብሉታል” ወይም ደግሞ በመሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔዎች ከለላ ባለጉዳዩን ሕዝብ ያዘናጉታል፡፡ አልፎ አልፎም ለተወሰነ ግብ ታልመው የጸደቁ ሕግጋትን በመጠቀም ኢኮኖሚውን እንዳሻቸው ይመሩታል፡፡ ሰሞኑንም ተመሳሳዩን ነገር ከመድገም አልቦዘኑም።
ከዐሥራ አምስት ቀናት በፊት ያልተሟላውን በጀት የመጨረሻው ተሰናባች ሸንጎ እንዲያጸድቅ ባደረጉበት ወቅት ተጨማሪ በጀት ለማስጸደቅ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡ የዕቅዱን ዓላማ በአንድ ነገር አስደግፈው ግልጽ አደረጉ። ለተከታታይ ዓመታት በኑሮ ውድነት ሲጎሳቆል የኖረውን ሠራተኛ መደጎም ነው አሉ፡፡ ይህ ቀላሉ የመፍትሄ አማራጭ/መንገድ ነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረድን አይጠይቃቸውም፡፡ ወደ ብሔራዊ ባንኩ ገዢ መደወል ብቻ ለቅለቱ በቂ ማስረጃ ይኾናል፡፡ እዚያ መፍትሄ አለ፡፡ በ2000 ዓ.ም ተሻሽሎ የጸደቀው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ” ገደብ ያልተበጀለት የመበደር አቅምን ለመንግሥት ሰጥቷል፡፡ አሁንም በድጋሚ የኾነው ይኼው ነው፡፡ በሳምንት ውስጥ 772 ሚሊዮን ብር ለሠራተኞች ደመወዝ በሚል መዝገብ ለ2003 ዓ.ም ሌላ በጀት ተዘጋጅቷል፡፡
ይህ ተጨማሪ በጀት በምን ያህል መጠን የሠራተኛውን ኑሮ እንደሚደጉም፣ የዋጋ ግሽበቱን እንዳያባብስ ስለሚወሰዱ ርምጃዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ዳሰሳ አልተደረገም፡፡ ብቻ ደመወዝ ይጨመራል፡፡ ይህ “ጊዜያዊ የማስታገሻ” ለ19 ዓመታት የተስተዋለ የመንግሥት ብቸኛ መፍትሄ ነው፡፡ እነዚህ የ“ሰነፍ እረኛ . . .” ዐይነት ተግባራት አጠቃላይ ድምር ላይ አዎንታዊ ለውጥ ሊያሰሙም ኾነ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ ኢኮኖሚው አሁንም የድኻውን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ የድኻውን ቁጥር በማብዛት ላይ ከመጠመድ አባዜው የሚያላቅቀው አልተገኘም።
ባለፈው ሳምንት የተሰማው አዲሱ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጥናት ውጤት ደግሞ አገሪቷን የዓለም ጭራ በማድረግ የአቶ መለስን የ19 ዓመት የኢኮኖሚ “ኀልዮት” አፈር ያለበሰዋል፤ አፈር ይለውሰዋል፡፡ ይፋ የኾነው አዲሱ የድህነት መሥፈርት መለኪያ ከኢትዮጰያ አጠቃላይ ሕዝብ 90 በመቶ ያህሉ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚዳክር እንደኾነ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ፈርጀ-ብዙ የድህነት መጠን አመልካች (Multidimensional Poverty Index-MPI) የሚል ሥያሜ የተሰጠው አዲስ የድህነት መሥፈርት በኦክስፎርድ የድህነት እና ልማት ኢኒሼቲቭ (Oxford Poverty and Human Development Initiative -OPHI) እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የጋራ ትብብር የተሠራ ሲኾን ከዚህ ቀደም ይሠራበት የነበረውን “በቀን አንድ ዶላር ” የድህነት መሥፈርት ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ይሠራበት የነበረው “በቀን አንድ ዶላር” መሥፈርት በግለሰቦች ገቢ ላይ ተመሥርቶ የሚሰላ ሲኾን 1.25 የአሜሪካ ዶላርን የድህነት ወለል መለኪያ የሚያደርግ ነው፡፡ ከ1990ዎቹ ጀምሮ እየተሰራበት ያለው ይሄው መስፈርት ቀደም ሲል “አንድ ዶላር” እንዲሁም ከግንቦት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ “በቀን 1.25 ዶላር”ን ለድኻ አገራት የኑሮ ደረጃ ማመላከቻ ያደርጋል፡፡ መሥፈርቱ ከገቢ ባሻገር ሌሎች ሰብአዊ የልማት ጉዳዮቹን የማያካትት መኾኑ በኢኮኖሚ ባለሞያዎች ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡
በመጪው ጥቅምት ወር በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የ2010 ሪፖርት ጋራ ተያይዞ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የድህነት መሥፈርት ግን ዋና የሰብአዊ አመልካች የሚባሉትን ትምህርት፣ ጤና እና የኑሮ ደረጃን በዐሥር ተዛማጅ ኢኮኖሚያዊ መመዘኛዎች በማስቀመጥ በቤተሰብ ደረጃ ሊኖር የሚችልን የድህነት መጠን ይለካል፡፡ የንጹህ ውኃ አቅርቦት፣ ንጽህና፣ የኀይል አቀርቦት እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች የአዲሱ መለኪያ ማሳያ በመኾን ያገለግላሉ፡፡ “ማን ነው ድኻ?” ከሚለው የተለመደ የኢኮኖሚ ጥያቄ ባሻገር “ለምን ድኻ ኾነ?” የሚለውንም መመለስ ግድ ይኾናል፡፡
ይኼው ጥናት እንደሚያሳየው፤ መረጃ በተሰበሰበባቸው 104 አገራት የድህነት መጠኑ እና ዐይነቱ የበዛ ሲኾን ከአንድ ዶላር በቀን መሥፈርት ጋራ ሲነጻጸር 1.3 ቢሊዮን ሕዝብ በተጨማሪ በፈርጀ ብዙ ድህነት መሥፈርት የዝቅተኛ ደረጃ መለኪያ ውስጥ ወድቋል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት አንዷ ስትኾን የፈርጀ ብዙ ድህነት አመለካቿ 0.58 ነው፡፡ ይህም በድኻዎች ቁጥር ብዛት እና ወደ ድህነት በሚወስዱ ምክንያቶች ብዛት የድኾች ሁሉ ድኻ እንድትኾን አድርጓታል፡፡ 70 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም ደግሞ ዘጠና በመቶ ሕዝብ በፈርጀ ብዙ ድህነት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ደረጃ ከጎረቤት ሶማልያ እጅግ ያነሰ ኾኖ ነው የሚገኘው፡፡ ከሶማልያ የፈርጀ ብዙ ድህነት አመለካቿ 0.51 ሲኾን ይህም ከኢትዮጵያ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ያመለክታል፡፡ ምጣኔው ከፍ እያለ ሲሄድ ውስብስብ ድህነትን ያመለክታል፡፡ ኬንያም የተሻለ ነጥብ አስመዝግባ ኢትዮጵያን በብዙ ርቀት እየመራቻት ነው፡፡
በድህነት የሚማቅቀው ማኅበረሰብ በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚያገኘው ድርሻም እንዲሁ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርት ከኾነ በተጠቀሱት መሥፈርቶች አመርቂ ውጤት አግኝቷል፡፡ አዲሱ ጥናት እንደሚገልጸው ግን በድህነት ስብስብ ውስጥ ከታቀፈው ማኅበረሰብ ከ20 በመቶ ያልበለጠው ብቻ የአምስተኛ ክፍል ደረጃን ያጠናቅቃል፡፡ በተመሳሳይ ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 8 ከኾናቸው ሕጻናት 84.9 በመቶ የሚኾኑት ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል የላቸውም፡፡
በማኅበራዊ አገለግሎት ዘርፎችም መልካም የሚባል ወጤት አልተገኘም፡፡ በድህነት ማዕቀፍ ውስጥ ከሚገኙት ዜጎች 85.7 በመቶ ያህሉ የመብራት ኀይል አገለግሎት የማያገኙ ሲኾኑ 89 በመቶ ያህሉ ደግሞ ኩበት እና ፍግ ለምግብ ማብሰያነት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ 88.7 በመቶ ያህሉ ደግሞ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ቴሌፎን እና የመሳሰሉት ንብረቶች የሏቸውም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት በሁለት ዲጂት ኢኮኖሚው እያደገ መኾኑን በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ ይኹንና አሁንም የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና አስተዳደራዊ ድክመት ዋነኞቹ የአገሪቱ መለያ እንደኾኑ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 5.2 ሚልዮን ሕዝብ አስቸኳይ ርዳታ የሚሻ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ይፋ የኾነው የ“Investing Across Borders” ሪፖርት እንዳመለከተው አገሪቷ ከሰሃራ በታች ከሚገኙት አገራት ንጽጽር እንኳ ስትታይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ለውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት አበረታች ያልኾነች አገር ተብላም ተፈርጃለች፡፡
በኑሮ ሪፖርትም ይኹን በአጠቃላይ አገራዊ ኹነት አገሪቷ ያላት ምስል እየደበዘዘ ይገኛል፡፡ ይህም ኾኖ ከዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ለአፍታም የማይጠፉት አቶ መለስ ዜናዊ ዛሬም የጥንድ ቁጥሮች የዕድገት ምጣኔን ዋነኛ መከራከሪያቸው ከማድረግ አልቦዘኑም፡፡ ነገም የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ነገ ቃላቸውን እንደሚጠብቁ ምንም መረጋገጫ የለም፡፡ ይህ ማለት ግን በመጪውም ጊዜ ለፓርላማ የሚቀርብ የ10 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የለም ማለት አይደለም፡፡ ዕድገት እና ድህነት እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚጓዙ ይመስል!?
gud saysema meskerem aytebam !
Good observation thank u z.