የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች እሰሩ!
የኦነግ እና የግንቦት 7፣ አልፎም የኦብነግ ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ድርጅቶቹን አሁን በተያዘው ፋሽን “ማዳከም ይቻላል” ተብሎ ታስቦ ይሆናል፤ ጥያቄዎቹን ማጥፋት ግን አይቻልም። የኢሕአዴግን ዘመቻ በተቃራኒው ካየነው ለእነዚህ ድርጅቶች የማያገኙት ድጋፍ እየሰጣቸው እንደሆነ መረዳት አይከብድም። በዚህም ልክ ኢሕአዴግ እንደደርግ በራሱ አንገት ላይ ገመድ እየጠመጠመ ይገኛል። የእነአቶ መለስ ትንቢትና ፍርሐት የሮበርት መርቶንን “ራሱን የሚፈጽም ትንቢት” (self-fulfilling prophesies) ያስታውሰኛል። መርተን እንደሚለው እነዚህ ትንቢቶች የሚደርሱት ዋናዎቹ ባለቤቶች “እውነት ናቸው፤ ይደርሳሉ” ብለው ስለሚያምኑ፤ በዚሁ እምነታቸው ላይ በመመሥረትም ተግባራዊ ምላሽ ስለሚሰጡ ነው። ለኢሕአዴግም በአጠቃላይ ተቃዋሚዎቹ በተለይ ደግሞ እነግንቦት 7 እና እነኦነግ በራሳቸው የሚፈጸሙ ትንቢቶች ሆነውበታል። ኢሕአዴግ እነዚህና ሌሎቹም ቡድኖች የሚያነሱትን የፖለቲካ ጥያቄ በፖለቲካዊ መንገድ ቢፈታ ቡድኖቹ/ጥያቄዎቹ እውነት ሆነው እንደሚያከስሩት፣ የጭቆና ስርአቱ ከስሩ እንደሚናድ ያውቃል። እነአቶ መለስ የዘነጉት ነገር እነዚህ ቡድኖች “በሕገ ወጥ” መንገድ ሊገለብጡዋቸው እንደሚችሉ መተንበይና ለትንቢቱም ምላሽ መስጠት በመጀመራቸው ከኪሳራው ሊያመልጡ የሚችሉበት እድል መዘጋቱን ነው። በሁለቱም በኩል ኢትዮጵያ አምባገነንነትን ከትከሻዋ አሽቀንጥራ ትጥላለች። ትንቢቱ ይደርሳል፤ ቀርቶም አያውቅም። እስከዚያው “የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች” አሸብሩ፣ ክበቡ፣ እሰሩ፣ ግደሉ።
የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች እሰሩ!
ከኦነግ እስከ ግንቦት 7፤ ከርዕዮት እስከ ደበበ
“ካዛብላንካ” የተባለውን ታዋቂ ፊልም አይታችሁት ይሆናል። በሞሮኮ የከተመው አሜሪካው ነጋዴ ሪክ (ዋናው ገጸ ባህርይ) ፊት ለፊት ባይገልጸውም ናዚዎችን ይጠላል፣ የጣልያኑን ፋሺስት ይጸየፋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መግቢያ (1941 እ.አ.አ) ላይ በፈረንሳዮች ስር የነበረችው ካዛብላንካ ወደጀርመኖቹ ልትተላለፍ በጭንቅ ተይዛለች። ከናዚ አምልጠው ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ስደተኞች ከተማዋን ሞልተዋታል። የጀርመኑ ናዚ ተወካይም ወደከተማዋ መጥቷል። በሙስና የተዘፈቀው ፈረንሳዊው የከተማዋ አስተዳዳሪ ሉዊስ ሬኖ ናዚዎችን ቢጠላም ሙስናውን ቀጥሏል። ሪክ የአንድ ወቅት ፍቅረኛውና ባሏ ከካዛብላንካ በአውሮፕላን እንዲወጡ ይረዳቸዋል። ሁለቱ የሚያመልጡት ሪክ ሉዊስን በመሣሪያ አስፈራርቶት የማምለጫ ጊዜ ስለሚያገኙ ነው። በዚህ መጨራሻ የጀርመኑ ተወካይ ወደ አውሮፕላን ጣቢያው ይደርሳል። ሪክ ጀርመናዊውን ይገለዋል። የሬኖ ወታደሮች ትእዛዙን ይጠብቃሉ። ለጥቅስነት የበቃ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል፤ ገዳይ እፊቱ እያለ “Round up the usual suspects”።
“የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች” በገፍና በግፍ ማሰር ግራ የገባቸው አምባገነኖች ሁሉ የጋራ ጠባይ ነውን? ዛሬ በአገራችን ሁሉም ሰው “የተለመደ ተጠርጣሪ” ሆኗል። አገሪቱ በሽብርተኞች የተሞላች እስክትመስል ድረስ የሚያዙ “ሽብርተኞች” ዜናና ጉዳይ መነጋገሪያ እየሆነ ነው። ለመሆኑ መንግሥት ይህን ያህል “ሽብርተኞችን” መያዝ ከቻለ፣ ያልተያዙት “ሽብርተኞች” ስንት ይሆኑ?
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ በድንገት “ሽብርተኛ” ሊባል የሚችልበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ተመቻችቷል። ይህን ለማስፈጸም የሚችል ሕግ ከነዳኞቹ፣ ሠራዊት ከነመሣሪያው ተዘጋጅቷል። የአቶ መለስ መንግሥት በብዙ መልኩ የመንግሥቱ ኀይለማርያምን ስትራቴጂ ቃል በቃል መድገም ጀምሯል። እርግጥ መንጌ ሕግን የመለስን ያህል መጠቀሚያ የማድረግ ብቃት አልነበራቸውም። አንዱ ማሳያ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን እስከመጨረሻው የመምታት፣ ከስራቸው ነቅሎና ገድሎ የመጨረስ ፖሊሲ ነው። በዚህ የደርግ ፖሊሲ ሕዝብና አገር ቢጎዳም ሕወሓት እና ሻእቢያ ግን ተጠቃሚዎች ነበሩ። ደርግ ተቃዋሚዎቹን ያጠፋልኛል ያለው ፖሊሲ “ከሕወሃትና ከሻእቢያ ጋራ በማንኛውም መንገድ ይገናኛሉ፣ የአማጽያኑን ሐሳብ የመደገፍ አዝማሚያ ሊኖራቸው ይችላል” ያለቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ማሰርና መግደል ነበር። በመጨረሻ ውጤቱ ይህ ፖሊሲ እነሕወሓትን የሚጠቅም፣ ደርግን ደግሞ ከሕዝብ ፈጽሞ የሚነጥል ነበር፤ በተለይም ከትግራይና ከኤርትራ ሕዝብ። አምባገነኖች ከታሪክ ለመማር ስለማይችሉ ታሪክን የደገሙ ሳይመስላቸው ታሪክን ይኖራሉ።
አሁን መለስ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥፋት “በሽብርተኝነት” ስም የጀመሩት ዘመቻ የደርግ ግልባጭ ነው፤ በአፈጻጸሙም በውጤቱም። ደርግ “ዓሳን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” ይል ነበር። መለስም ኦነግን እና ግንቦት 7ን ለማጥፋት “ባህራቸውን” ለማድረቅ ተነስተዋል። መለስ ባህሩን ለማድረቅ የተከተሉት መንገድ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን፣ ኦነግን እና ግንቦት 7ን በሐሳብም ይሁን በተግባር፣ በሕልምም ይሁን በቅዠት መደገፍ አደገኛ ወንጀል እንዲሆን ማድረግ ነው። ደርግም እንዲሁ ነበር ለማድረግ የሞከረው። ትግሬ (ትግራዋይ) መሆን በራሱ በሕወሓት/ሻእቢያ ደጋፊነት ለመጠርጠር የሚያበቃበት ጊዜና ሁኔታ ነበር። አሁንም ስትራቴጂው አልተቀየረም። ኦሮሞ መሆን በራሱ የኦነግ አባልና ደጋፊ ተደርጎ ለመጠርጠር የሚበቃ እየሆነ ነው። የኦነግ አባል የሆነ ዘመድ ያለው ሰው ዘመዱ ከአሜሪካ ደውሎለት ስለአካባቢው ሁኔታ ካወራ፣ ምሬቱን ከገለጸለት፣ ስለመለስ ካድሬዎች ድራማ ካወራለት አለቀለት። ለአሸባሪው ድርጅት መረጃ ሲያቀብል ተገኘ ማለት ነው። የስልክ ንግግሩ ቅጂ ይቀርባል፤ ማስረጃ አለን ይባላል። የግንቦት 7 አባል የሆነ፣ ባይሆንም የሚጠረጠር የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛ ካላችሁ እንዳይደውልላችሁ መጸለይ አለባችሁ። ራስህ ደውለህ “እንዳትደውልልኝ” እንዳትለው ይህን ማድረግ በራሱ የሚያስጠረጥር ነው፤ “የሚደብቁት ነገር ከሌለ ‘አትደውልልኝን’ ምን አመጣው?” ብለው የሚጠይቁ አዳማጮች አሉ። አገር ውስጥ የሚገኝ ተቃዋሚ አባል ብትሆንም እንዲሁ እንደእንቅስቃሴህ የዚሁ ወጥመድ ሰለባ ልትሆን ትችላለህ። ጋዜጠኛ መሆንም እንዲሁ ከመቅሰፍቱ ላይሰውርህ ይችላል። (ከመቅሰፍቱ የሚሰውረውን ታውቀዋለህ!) አንድ ቀን ከቢሮ ወይም ከቤት አጅበው ሊወስዱህ ይችላሉ። ክምር መረጃ አላቸው፤ ካስፈለገም ክምር መረጃ ይፈጥራሉ ወይም አንተ ራስህ በራስ ላይ ማስረጃ ትፈጥራለህ። ማእከላዊ በገባህ በአራተኛው ቀን “24” የተባለውን ፊልም የሚያስንቅ የሽብር ድራማ ደርሰህ፣ ዋናው ገጸ ባሕርይም አንተ ራስህ ሆነህ ትገኛለህ። ልክ እንደአገራችን ፊልመኞች ደራሲውም፣ ፕሮዲውሰሩም፣ ዋና ገፀ ባህርይውም አንተው ራስህ ሆነህ በቲቪ ትቀርባለህ። ፊልሙን የተሟላ ለማድረግ ደግሞ ሌሎች “የባለሞያ” እገዛ ያደርጉልሃል።
የማእከላዊ ምርመራ ምን ማለት እንደሆነ በቅርብ የተረዳሁት ለጥቂት ቀናት እዚያ ታስሬ በነበረበት ወቅት ነው። በታሰርኩበት ክፍል አጠገብ አንድ ቢበዛ 13 ዓመት የሚሆነው ልጅ አያለሁ። ከሌላው ታሳሪ በሙሉ ተለይቶ ይታያል፤ በጣም ልጅ በመሆኑ። በገባሁ ማግስት ስለልጁ ስጠይቅ ከልጁ በላይ የሚያሳዝን ታሪክ ሰማሁ። ነገሩ እንዲህ ነበር። አቃቂ/ቃሊቲ አካባቢ አንድ ሰው ተገድሎ፣ ሰውነቱ ተቆራርጦ በማዳበሪያ ተደርጎ ተጥሎ ይገኛል። ከዚያ በፊት የሟች ሚስት ባሏ እንደጠፋ፣ ከሦስት ጓደኞቹ ጋራ ተጣልቶ እንደነበር አመልካታ ነበር ይባላል። ነገሩ እንደተሰማም እነዚህ ሦስት ወጣቶች ይታሰራሉ፤ ማእከላዊ። ከዚያም የሠራችሁትን አውጡ ይባላሉ። “ከሟች ጋራ መጣላታችን እውነት ነው፤ ነገር ግን እንኳን ልንገድለው አልተደባደብንም” ይላሉ። እንደሚባለው በሟች ሚስት ገፋፊነትና እጅ መንሻ ጭምር የፈረደባቸው ወጣቶች ወደተለመደው የምርመራ ምእራፍ ይገባሉ። በመጨረሻ ድብደባው ሲበዛባቸው “አዎ፣ ጓደኛችንን ገድለነዋል” ብለው ይናዘዛሉ። ልብ በሉ፣ “ገድለነዋል” ብቻ አይደለም፤ “ገድለን፣ ቆራርጠን ጥለነዋል” ብለው ነው የሚናዘዙት። በስራው ጥራት ዘወትር የሚተማመነው ፖሊስም ምርመራውን ጨርሶ (ምርመራ ተጨረሰ የሚባለው እንዲህ ሲሆን ይሆን?) ለአቃቤ ሕግ ለመላክ ዝግጅት ይጀምራል።
ይህ ሁሉ ሲሆን በእውነተኛው ግድያ የተሳተፈ አንድ ሕሊና ሲረበሽ ይከርማል። ያ ሕሊና፣ የዚያ እስር ቤት ውስጥ ያየሁት ጨቅላ ልጅ ሕሊና ነበር። ልጁ የሟች ሚስት፣ የቀድሞዋ ከሳሽ እኅት ነው። ሟች የተገደለው በጓደኞቹ ሳይሆን በገዛ ሚስቱና በሁለት ወንድሞቿ ነበር። ይህ ትንሽ ልጅ ድርጊቱን ስላየ፣ በኋላ እንዳይናገር በማለት በግድ የክፋታቸው ተባባሪ አድርገውታል (የሰማሁትን ዝርዝር እዚህ መናገር አልፈለኩም)። ልጅ ነውና ከሕሊና የመደበቅን ክፋት በቅጡ አልተማረም፤ በመጨረሻ ነገሩን ለሌላ ሰው ተናግሮ ፖሊስ አዲስ ምርመራ ይጀምራል። ቤታቸውም ውስጥ የሟች ደም ፍንጣሪ ሁሉ ተገኝቷል አሉ። በአዲሱ ምርመራ (በቀድሞው መንገድ የተካሄደ ይሆን?) የሟች ሚስት፣ ትንሹን ልጅ ጨምሮ ከሁለት ወንድሞቿ ጋራ ታስረው አይቻቸዋለሁ።
ዛሬ “ሽብርተኛ” እየተባሉ የሚያዙት የብዙዎቹ ሰዎች ታሪክ ከዚህ የምርመራ ሂደት ድራማ የተለየ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም። ጋዜጠኛ ውብሸትን ጨምሮ “በሽብርተኝት” የተጠረጠሩ ሰዎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቶች ተናግረዋል። (የፍርድ ቤቶቹ ምላሽ አያስቃችሁም? “ከተፈጸመ እንዳይደገም”፣ ወይም ራሱ ደብዳቢው አካል ጉዳዩን እንዲያየው እግረ መንገድ ጠቅሶ ማለፍ።) ደርግ አገርን ከሚጎዳ፣ ሕዝብን ከሚያሰቃይ ይልቅ “ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ነበረበት” እየተባለ እንደቀለድ ይነገራል። ይህ ጥፋት የአገር ጥፋት፣ የትውልድ ጥፋት ነበር። ያቺው አገር፣ ያው ራሱ ትውልድ ግን ይህንኑ ጥፋት በባሰ መልኩ እየደገሙት ነው። ዛሬም መመሪያው “የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች ክበቡ” ነው። ድሮ ደርግ “የተለመዱ ተጠርጣሪዎች” ነበሩት። በአገሪቱ ለሚያጋጥሙ ማናቸውም ችግሮች ተጠርጣሪዎቹ እነዚሁ አካሎች ነበሩ። በሬዲዮ፣ በኢቲቪ፣ በአዲስ ዘመን፣ በፓርቲ ልሳን፣ በቀበሌ ስብሰባ፣ በሞያ ማኅበራት፣ በጾታ ማኅበር…አብዮት/መስቀል አደባብይ፣ ናዝሬት፣ ነቀምት፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ…ሁሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚወገዙት እነርሱው ነበሩ። ዛሬም የማውገዣ ቦታዎቹና ተቋማቱ እንኳን አልተቀየሩም። የውግዘቱ ይዘትና ቋንቋም እንዲሁ። የይዘት ሳይሆን የቃላት ለውጡን በምሳሌ እናስታውስ። ኢምፔሪያሊዝም ወደ ኒዎ ሌበራሊዝም፣ ሕወሃት/ሻእቢያ ወደ ኦነግ/አብነግ/ግንቦት 7፣ ተገንጣይ/አስገንጣይ ወደ ጠባብ/ትምክህተኛ፣ አልቱራቢ/በሽር ወደ ኢሳያስ..ተቀይረዋል።
የሚመራውን መንግሥት ከልቡ ያወጣ ሕዝብ ገበያ አይሄድም፣ ቢሮ አይገባም፣ በኢኮኖሚ አይሳተፍም፣ ለልማት ስራ አያዋጣም ማለት ቂልነት ነው። በመንግሥቱም ጊዜ እኮ “ለእናት አገር ጥሪ” (ስሙ እንዴት ደስ ይላል!) ሕዝብ አዋጥቱዋል፤ ለልማት ዘመቻ ዘምቷል፤ እረ ለጦርነትም ዘምቷል። እነዚህ ሁሉ ግን ሕዝቡ በሙሉ ልቡ እስከ መጨረሻው ከመንግሥቱ ጋር ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሊሆኑ አይችሉም። አሁንም ልክ እንደድሮው ሕዝቡ በውድም በግድም ለአባይ ግድብ ስላዋጣ ወይም ቦንድ ስለገዛ ለመለስ አገዛዝ የሕዝብ ፍቅር ማሳያ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። “ለእናት አገር ጥሪ” አለማዋጣት እና ለአባይ ግድብ አለማዋጣት በመሠረቱ ውጤታቸው ተመሳሳይ ነው። ደርግም ኢሕአዴግም የየራሳቸው መቅጫ አላቸው። ለጊዜው መዋጮው ከቅጣቱ የተሻለ እስከሆነ ድረስ ሕዝቡ የሚመርጠው መዋጮውን ነው። በተጨማሪ ደግሞ “የእናት አገር ጥሪውም” ይሁን “የአባይ ግድብ” በመሠረቱ ሊደገፉ የሚገባቸው ዓላማዎች ናቸው። አቶ መለስ እና ኮሎኔል መንግሥቱ ሕዝቡ ለአገሩ ወይም ለግል ጥቅሙ ብሎ የሚያደርገውን ሁሉ ለእነርሱ ፍቅር ሲል ያደረገ እየመሰላቸው ሳይሞኙ አልቀሩም።
ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ፣ ተቃዋሚዎችን ወይም የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሁሉ በጥርጣሬ የሚመለከት ፖለቲካ ፈጽሞ ሊረጋጋ አይችልም። የዴሞክራሲያዊ ስርአት መነሻ መሰረት መተማመን እና ይህንኑ ተቋማዊ የሚያደርግ አመራር ነው። አሁን የምንታዘበው ግን እርስ በርስ መጠራጠርን የፖለቲካ ሥርአቱ መለያ የሚያደርግ፣ መጠራጠርን ተቋማዊነት የሚያላብስ ፖለቲካ ነው።
የኦነግ እና የግንቦት 7፣ አልፎም የኦብነግ ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ድርጅቶቹን አሁን በተያዘው ፋሽን “ማዳከም ይቻላል” ተብሎ ታስቦ ይሆናል፤ ጥያቄዎቹን ማጥፋት ግን አይቻልም። የኢሕአዴግን ዘመቻ በተቃራኒው ካየነው ለእነዚህ ድርጅቶች የማያገኙት ድጋፍ እየሰጣቸው እንደሆነ መረዳት አይከብድም። በዚህም ልክ ኢሕአዴግ እንደደርግ በራሱ አንገት ላይ ገመድ እየጠመጠመ ይገኛል። የእነአቶ መለስ ትንቢትና ፍርሐት የሮበርት መርቶንን “ራሱን የሚፈጽም ትንቢት” (self-fulfilling prophesies) ያስታውሰኛል። መርተን እንደሚለው እነዚህ ትንቢቶች የሚደርሱት ዋናዎቹ ባለቤቶች “እውነት ናቸው፤ ይደርሳሉ” ብለው ስለሚያምኑ፤ በዚሁ እምነታቸው ላይ በመመሥረትም ተግባራዊ ምላሽ ስለሚሰጡ ነው። ለኢሕአዴግም በአጠቃላይ ተቃዋሚዎቹ በተለይ ደግሞ እነግንቦት 7 እና እነኦነግ በራሳቸው የሚፈጸሙ ትንቢቶች ሆነውበታል። ኢሕአዴግ እነዚህና ሌሎቹም ቡድኖች የሚያነሱትን የፖለቲካ ጥያቄ በፖለቲካዊ መንገድ ቢፈታ ቡድኖቹ/ጥያቄዎቹ እውነት ሆነው እንደሚያከስሩት፣ የጭቆና ስርአቱ ከስሩ እንደሚናድ ያውቃል። እነአቶ መለስ የዘነጉት ነገር እነዚህ ቡድኖች “በሕገ ወጥ” መንገድ ሊገለብጡዋቸው እንደሚችሉ መተንበይና ለትንቢቱም ምላሽ መስጠት በመጀመራቸው ከኪሳራው ሊያመልጡ የሚችሉበት እድል መዘጋቱን ነው። በሁለቱም በኩል ኢትዮጵያ አምባገነንነትን ከትከሻዋ አሽቀንጥራ ትጥላለች። ትንቢቱ ይደርሳል፤ ቀርቶም አያውቅም። እስከዚያው “የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች” አሸብሩ፣ ክበቡ፣ እሰሩ፣ ግደሉ።
በነገራችን ላይ!
ቢያንስ ለወጉ ያህል “እንኳን አደረሳችሁ” መባባል ነበረብን መሰለኝ። “ለምኑ?” ብሎ የሚጠይቅ ቢኖር መልሱ ብዙ ነው። የአዲስ ዓመት በዓል ከሕዝባዊና ባህላዊ በዓልነት ወደ መንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳ መድረክነት መለወጡን ለማየት እንኳን አደረሳችሁ! የአምናና የዘንድሮ የዘመን መለወጫ በዓላት ፍጹማዊ አምባገነን መንግሥታችን አንድም እርሱ የማይወደስበት የጋራ መድረክ እንዳይኖረን የሚያደርገው ወረራ አውራ ማሳያዎች ናቸው። ከብዙ ስሕተቱና መዘዙ ጋራ፣ ደርግ እንኳን ይህን ያህል ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትን የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ አልቻለም ነበር። ፕሮፓጋንዳው በጥቅስ እየታከከ፣ በካድሬ ሰባኪያን እየተዋበ በዐርብ ስግደት፣ በእሑድ ጸሎት እንኳን አልተው ብሎናል። አሁን ደግሞ ብሔራዊውን የአዲስ ዓመት በዓላችንን ከአዝማሪዎቹ ጋራ ተቆጣጥሮታል። በዚሁ ከቀጠልን ብዙም ሳንቆይ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓሎቻችን ሁሉ “ለሕዝብ ጥቅም” በቁጥጥር ስር መዋላቸው አይቀርም፤ ሙከራው ተጀምሯል። ምናልባትም እንቁጣጣሽ የሚለው “የትምክህተኞች” ስያሜ ሊቀየር ይችላል። እባካችሁ፣ በበዓል ቀን እንኳን እረፍት ስጡን። ገገሞች ስለሆናችሁ ልመና አይገባችሁ፣ የሰው ስሜትም አይገዳችሁ፤ ግን በናታችሁ አንዳንድ ጊዜ እንኳን ተዉን! የመተንፈሻ ጊዜ ስጡን!
Great piece Mesfin!!! The last two blogs were excellent.
It is true that the so called ‘anti-terrorist’ campaign by Zenawi’s regime is an improved version of Derg’s ‘red-terror’ campaign. The similarities between the two is uncanny. It indicates the fact that all dictators are born of the same mother. They have the same nature, live the same life, and die the same death.
We have recently witnessed also the fact that the Western backers of the regime know everything that takes place in the country. I am quite certain also that some of them have been providing the regime with their long experience of how to disarm and subjugate a society. All the political suppression taking place in Ethiopia is very much sophisticated and scientific. The people must be much smarter, courageous, and persistent in seeking its freedom.
I should end repeating your resentment. GEGEMOCH, ABO TEWUNA!!!!
መስፍኔ “ተቃዋሚዎችን ወይም የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሁሉ በጥርጣሬ የሚመለከት ፖለቲካ ፈጽሞ ሊረጋጋ አይችልም” ያልከው ሃሳብ ትክክልና ወያኔም የዚህ ተምሳሌት የሆነ ቡድን ሆኖል፡፡ በጣህረ ሞት ላይ ሆኖ የውር ድንብሩን በስጋትና በፍረሃት ህዝቡን እያሸበረ ይገኛል፡፡ ለነገሩ ህዝቡም ዝም አለ አልናገርም አለ ወያኔም ፈራ (የህዝቡን ዝምታ) ስለዚህ በግድ እንድንጮህና እንድናምፅ እየገፋፋን ነው፡፡ እስክናምፅና የወያኔም ግብዓተ መሬት እስኪፈፀም ድረስ ግን “የተለመዱትን ተጠርጣሪዎች ይሰሩ”
መስፍኔ መፃፍ አታቋርጥ!!
hi mesfine i always follow your articles and am always collecting them specially after that article of yours ” yihe ager yemanew?” and now am free at least to reply foe you and i like this article so much and i miss addiss neger realy i have almost all your paper at home who knows one day there will be a day which every body one who belongs to that county will be free to criticize what ever he feels is wrong..i like what you said …የግንቦት 7 አባል የሆነ፣ ባይሆንም የሚጠረጠር የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛ ካላችሁ እንዳይደውልላችሁ መጸለይ አለባችሁ።… really because i have an old friend who the think she is one of ginbot 7 or the others if she calls me am in danger i don’t know what to do… anyways miss you so much guys now am free to read your articles because am not in ethiopia…but i want to read you guys back at home