“አሸባሪሪነት!” የነጻነት እዳችን፤ የገዢነት እዳቸው
በመጨረሻው መጨረሻ የነጻነት ፈላጊዎች ጥያቄ ግፍን በማብዛት፣ አዲስ ስም በመለጠፍ፣ በማሰር፣ በመግደል፣ በማሰደድ ተሸንፎ እንደማያውቅ የተረጋገጠ ነው። እነአቶ መለስ ዛሬ ለማስፈራሪያ ጥቂቶቻችንን መረጡ እንጂ የአሸባሪሪነት “ወንጀሉ” ኢትዮጵያ የነጻነት አገር ሆና ለማየት የሚመኙና ባመኑበት መንገድ የሚሠሩት ዜጎች ሁሉ ነው። በዚህ ቀልደኛ ክስ መካታት የነአቶ መለስን ትኩረት የመሳብ ማረጋገጫ ከመሆን አልፎ ተከሳሾቹ ከሌሎች የበለጠ ለኢትዮጵያ የሚያስቡ/የምናስብ ወይም የታገልን ተደርጎ የሚያስቆጥር አይደለም። ወይም እንደዚያ አይነት ስሜት አይሰማኝም። ብዙ ሠርተው በክሱ የተካተቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ምንም የሠራን (ያሸበርርን) ሳይመስለን የተካተተንም አለን። እርግጥ ማሸበርር መቻሌን ማወቄ አልከፋኝም። የእነአቶ መለስ ውቃቢ ተከሳሾቹን ከሌሎቹ “ወንጀለኞች” እንዴት አድርጎ እንደሚመርጥ ለማወቅ አልሞከርኩም፤ ትርጉም ስለሌለው። በክሱ ስማችን የተጠቀስነውም ሆንን ያልተጠቀሳችሁት ሚልዮኖች ነጻነትና ዴሞክራሲን በመጠየቁ “ወንጀል”ሁላችንም አንድ ነን፤ “እስክንድር ነጋ ነኝ! አንዱዓለም አራጌ ነኝ (I am Eskinder Nega, I am Andualem Arage. . .) እንደማለት! ለአቶ መለስ “ወንጀል” የሆነው የነጻነት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት ጥያቄ ቀዳሚ መተሳሰሪያችን ነው። በዚያው ምትሐታዊ ባለቅኔ ዮሐንስ ስንኝ ላሳርግ፤
ዘመን ቢያርቃችሁ፣
ስፍራ ቢለያችሁ፣
ዕንባ አጋጠማችሁ።
ሰው በሐሰት በአሸባሪነት፣ በአገር ክዳት እና በስለላ ሲከሰስ ምን ይሰማዋል? የክሱ የሚደርሰው እንደ ወንድሞቻችን እንደነ እስክንድር በአካል በፖሊስ ተይዞና ተንገላቶ፣ እንደነናትናኤል ተደብድቦ ሲሆን ምን እንደሚሰማ አላውቅም። የሰው ልጅ ሊያገኝ የቻለው (የሚገባው ወይም የሚችለው አላልኩም) የነጻነት ልክ እንደ ፀሐይ መውጣት “ተራ” የሕይወት አካል ተደርጎ ከሚቆጠርበት ካለሁበት አገር ሲሰማ ግን ስሜቱ ድብልቅልቅ ነው። መጀመሪያ በጣም ይገርማል፤ “አገሪቱ በምን አይነት ሰዎች ነው የምትመራው?” የሚል ሺህ ጊዜ ተጠይቆ ሺህ ጊዜ የተመለሰ የብሽቀት ግራሞት። ከዚያ ደግሞ ማመን ያቅታል፤ “እውነት ይህ ቴአትር የሚሠራው በእኔ አገር ነው?” የሚል እውነታን በምኞት ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራ አይነት። ከዚያ በኋላ “ምን ማለት ነው?” ብሎ መጠየቅ ይመጣል። ምንም።
በአሸባሪነት መከሰሴን በጠዋት ደውለው ያረዱኝ (በነገሩ ለመቀለድ ያበሰሩኝም ማለት ይቻላል) አሜሪካና ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ጓደኞቼ ናቸው። “ሐሎ አሸባሪው!” ምን አይነት ሰላምታ ነው? እንዲህ ተባብለን ስለማናውቅ አልገባኝም። “ምን አልክ?” ብዬ መልሼ ጠየኩ። እንዳልሰማሁ ገባው። የፈለገውን ያህል በክሱ አሳፋሪነት መሳለቅ ብንችል እንኳን፤ ነገሩ ማንንም የሚያስደስት አይደለም። ከዚያ ከአዲስ አበባም እንዲሁ መልእክቶች ደረሱኝ። የክሱን ይዘት ወይም የተጻፉትን ዘገባዎች ተሽቀዳድሞ ለማንበብ አንዳችም ጉጉት አልነበረኝም።
ይገርማል፣ መልሶ ደሞ አይገርም፤ አያስቅም፣ መልሶ ደሞ ያስቃል፤ አያስለቅስም። በመጨረሻ ነገሩን እንዲህ ብዬ ተቀበልኩት። ‘እነርሱም የገዢነት እዳቸውን እየኖሩ ነው፤ እኛም የነጻነት እዳችንን እየከፈልን ነው። ጥያቄው “ይህን እዳችንን በየፊናችን ከፍለን የምንጨርሰው መቼ ነው? ምን ያህልስ እዳ ይቀርብናል?” የሚል ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ ይህን እዳ የመክፈል ሩጫ ነው። የእዳችን ተፈጥሮ ግን ለየቅል ነው። እነርሱ በምርጫቸው (ታግለውም ጭምር?) በራሳቸው ላይ ያመጡት የገዢነት እዳ የእኛን ነጻነት በመንጠቅ ላይ የተመሠረተ ነው። የእኛ የነጻነት እዳ ግን በተቃራኒው ራሳችንን ከእነርሱ አገዛዝ ነጻ በማውጣት ላይ እንጂ የእነርሱን ነጻነት በመንጠቅ ላይ የሚቆም አይደለም። ስለዚህም የእኛ ነጻነት ለእነርሱም ጭምር የዘላለም እረፍት የሚሰጣቸው ነው፤ ከፍርሃትና ከጥላቻ ሰንሰለታቸው የሚፈታቸው።’
ከዚያ የክስ ቻርጁን ማንበብ ጀመርኩ። ንባቤ እንዳበቃ በክስ አቀራረቡ ጥልቀትና ምጥቀት በመመሰጤ ቀጣዩ ትምህርቴ ሕግ እንዲሆን አሰብኩ። ይህን ክስ ለማዘጋጀት ስንት ጥልቅ የሕግና የፍትሕ እውቀት ያላቸው ሰዎች እንደደከሙ ባሰብኩ ጊዜ ለሕግ አምላክ ሰገድኩ። ከዚያ ደግሞ አሸባሪነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ለአገራችን ያለውን አስፈላጊነት ስለተገነዘብኩ “በኢትዮጵያዊ አሸባሪነት”(ያው ከሌላው ዓለም የተለየ ትርጉም አለው) ዙሪያ ተጨማሪ ስልጠና ወይም ጥናት የማድረግ ፍላጎት አደረብኝ። ጥናቴን አጠናክሬ ለመቀጠል በአቶ መለስ ስም እምላለሁ። መለስ ይሙት! ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ በአንድ ወቅት ባቀረበው የመወያያ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንዲህ የሚል ግጥም ጠቅሶ አልነበረምን?
ሽንኩርት አንዱን በሉት፣ ደገሙትም ገማ
ነውር አይደለም ወይ፣ ታምቶ መቅረትማ።
የዘገየው መጣ!
የክሱ ይዘት እንኳን በፍርድ ቤት፣ ቡና እየጠጡም ቢሆን ለመነጋገርና ለመከራከር የሚበቃ አይደለም። ባይሆን ክሱ በተደረሰበት የጫት ምርቃና ውስጥ ሆኖ ሲነበብ የተለየ ትርጉም ይሰጥ እንደሆነ ደራሲዎቹ ቢነግሩን እመርጣለሁ። አቶ መለስ በቅርቡ እነ አልሻባብ ፕሮፌሽናል፣ የእኛዎቹ አሸባሪዎች (እኔም ተጨመርኩበት?) ደግሞ አማተር እንደሆኑ ነግረውን ነበር። ለአማተር አሸባሪዎች በፕሮፌሽናል ደራሲዎቻቸው ያዘጋጁት ክስ የወንጀል ልቦለድ እንዴት እንደማይጻፍ ለማስተማር ይረዳ ካልሆነ በቀር፣ በተለመደው አነጋገር፣ ተራ የባልቴት ወሬ ነው። እኔ እንደውም የክሱን ይዘት ትቼ በቋንቋውና በሰዋሰዉ ስገረም ነበር። በዚያ ሰሞን አንድ የቅርብ ወንድሜ የነገረኝን አንድ የኦሮሚኛ ተረት አስታወሰኝ፤ Attis Gaeee, Arekenkes Gaeee ይላል። በጨዋ ትርጉሙ “አንቺም አትረቢ፣ አረቄሽም አይረባ” እንደማለት ነው። እቅጩን ማወቅ የሚፈልግ ኦሮሞ ወዳጁን ይጥራ።
ይህን ክስ ከክስ ቆጥሬ ራሴን ለመከላከል ብቆም ለእነአቶ መለስ ቀልድ እውቅና እንደ መስጠት ይቆጠርብኛል። አገር ቤት በእስር ላይ የሚገኙት ወገኖቻችንም ቢሆኑ ራሳቸውን ለመከላከል ጠበቃ የሚያቆሙት ለወጉ ለደንቡ እንጂ መከላከል የሚያስፈልጋቸው እውነተኛ ተጠርጣሪዎች ሆነው ነው ብዬ አላምንም። ምናልባት በዘመነ መለስ መዘበቻ የሆነውን የፍርድ ቤት ነጻነት ጉዳይ ድጋሚ እንድንቆዝምበት እድል ይሰጠን ከሆነ ወደፊት እናየዋለን። መለስ የታሰሩት ሰዎች “አሸባሪዎች” ስለመሆናቸው ጥርጥር እንደሌላቸው በነገሩን በሳምንቱ አራቱ ተለቀዋል። “አቶ መለስ ያቅራሩበት ማስረጃ የት ገባ?” ብሎ መጠየቅ ጅልነት ነው፤ መጀመሪያም አልነበረም። ባይሆን አዲሱ ድራማ “እያሰሩ መልቀቅ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ የሚያጠነጥን እንዳይሆን መጠርጠር አይከፋም። (ለመሆኑ ታሳሪዎቹ እነጋሽ ደበበ ለምንና እንዴት ታሰሩ-ተፈቱ? ለደረሰባቸው እንግልት፣ በመልካም ስማቸው ላይ ለተፈጸመው ጥፋት፣ በቤተሰባቸው ላይ ለደረሰው ሰቀቀን የሚጠየቅ ሰው ይኖራል? በዚህ ጉዳይ ተበዳዮቹ አቃቤ ሕግን፣ ኢቲቪን እና አቶ መለስን መክሰስ ይችላሉ? ቀልዴን ነው! እንደውም ተፈቺዎቹ መሐሪና አስተማሪ መሪያችንን ማመስገን አለባችሁ።)
በግሌ ከክሱ ይዘት ይልቅ ዘግይቶ መምጣቱ የተለየ ትርጉም ሰጥቶኛል። የዛሬ ሁለት ዓመት እነአቶ መለስ የሸረቡልንን ተመሳሳይ የሽብርተኝነት ክስ ቀድመን ለማወቅ በመቻላችን ለስደት ስንዳረግ ለማመን የተቸገሩ ሰዎች ነበሩ። ገና የጸረ ሽብር ሕጉ ሲረቀቅ ሕጉ ጋዜጠኞችን ጭምር ለማፈን እንደሚውል የታወቀ ነው። ጥያቄው “የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው?” የሚል ብቻ ነበር። እንደዚህም ሆኖ ግን ሕይወታችንን፣ ኑሯችንን፣ ቤተሰባችንን እና ሠርቶ የመኖር፣ ለአገር ትንሽ ነገር የማበርከት ተስፋችንን ጥለን ከተሰደድነው ወጣት ዜጎች ይልቅ አቶ መለስና ጭፍሮቻቸው የሚዘላብዱትን ለማመን የመረጡ ነበሩ። ባልናገረውም በእነዚህ ሰዎች አዝኜባቸዋለሁ። ብዙዎቹ በየዋህነት ያደረጉት ይመስለኛል። ጥቂቶቹ በግል ምቾታቸው ውስጥ ሆነው ስለሚያስቡ፣ ምናልባት አሁንም አቶ መለስን አምነው ይህን ክስ እንደቁም ነገር ቆጥረውት ቢገኙ አልገረምም። ቀሪዎቹ ደግሞ ሐላፊነት የሚሰማው መንግሥት እንዳለቸው ለማመን ስለሚፈልጉ “እንዲህማ አይደረግም! አይከሷችሁም” በማለት የተሸወዱ ናቸው። “እንዲህማ ብለው አይከሱም፤ እንዲህማ አያደርጉም” እየተባለ ያላደረጉት ምን አለ? ሁልጊዜም “‘አያረጉትም’ እያሉ የሚመጣውን ሁሉ መቀበል የሚችሉ ብጹአን ናቸው!” የሚል ጥቅስ አንብቤያለሁ? አሁንም ሲደረግ አይተው ማመን ይችሉ ይሆን? ደግነቱ አምባገነን የጭካኔና የውሸት ውሉን አይስትም። ድንገት አዛኝና መሐሪ መስሎ ቢቀርብ፣ ለእውነት እንደቆመ ቢምል እንኳን ዞሮ ዞሮ ወደ ጭካኔው፣ ወደ ቂሙ፣ ወደ ውሸቱ መመለሱ አይቀርም። መጋለጡም የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው።
ዛሬ ድራማቸውን ያሳመሩ መስሏቸው በአዲስ ነገር ድረ ገጽ ላይ በጻፍነው ምክንያት የከሰሱን ለማስመሰል ቢሞክሩም ለመደበቅ የሚመች አልሆነላቸውም። በመሠረታዊ ይዘቱ በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ በጻፍናቸውና በድረ ገጹ ባተምናቸው መካከል ለአዲስ ክስ የሚያበቃ ልዩነት የለም። በግሌ በጭብጥ ደረጃ አገር ቤት በነጻነት ብኖር የማልጽፈውን ነገር አሁን በድረ ገጽ አልጻፍኩም። በአካል መራቃችን በሚሰጠን የነጻነት ስሜት የተነሣ የጽሑፎቻችን ድምጸት የተቀየረ ቢመስል፣ ወይም አገር ቤት ባለው አፈናና ራስን ሳንሱር የማድረግ ተዘዋዋሪ ሳንሱር የማናትማቸውን አሁን ብናስነብብ እንኳን በመሠረታዊ ይዘታቸው ከሰላማዊነት ወደ አሸባሪነት የሚያሸጋግሩ አይደሉም። ኢትዮጵያውያን አሸባሪ የማንሆነው የአቶ መለስን ክስ ስለምንፈራ አልነበረም፤ አይደለም። አሁን ማን ይሙት አገር ቤት እንዳይታይ የታገደው፣ ከስደት ጋራ እየታገልን የምንሰራው ድረ ገጽ ከጋዜጣችን በላይ ለአቶ መለስ “የሚያሳስብ” ሆኖ ነው የተከሰስነው? ድርጊቱ ወንጀል ነው የሚለውን የደንቆሮ ክርክር እንቀበለውና “ደገፋችኋቸው” ስለተባሉት ድርጅቶችስ በጋዜጣችን የጻፍነው አይበዛም? እዚህ ላይ የዛሬዎቹ ክሶች ቀድሞ ከተዘጋጀብን ክስ የሚለየው “ለጠላት አገር መሰለል” በሚለው 24ቱንም ተከሳሾች በሚመለከተው በአራተኛው ክስ በመካተታችን ብቻ ነው። እርሱም ቢሆን አዝነው ከተዉት ነው። ይህን ያልኩት ያለምክንያት አይደለም።
ከአገር ከመውጣታችን ከወራት ቀደም ብሎ ከአቶ በረከት ስምኦን ጋራ በአንድ የጋዜጠኞች ሽልማት ዝግጅት ላይ ተገናኝተን ነበር። ለውጭ አገር ሚዲያዎች የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ማኅበር ያዘጋጀው ውድድር የሽልማት ቀን ነበር። ቦታው አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስ። በዝግጅቱ በስተመጨረሻ ሁላችንም የወይን መለኪያችንን ይዘን በየአቅጣጫው ሞቅ ያለ ጨዋታ ጀመርን። ከቆይታ በኋላ ራሳችንን ከበረከት ጋራ አገኘነው። ሁልጊዜም በማይለው ደረቅ ፈግታ እና ቀላል አቀራረብ ተቀላቀለን። በረከት፣ታምራት ነገራ፣ ማስረሻ ማሞ፣ እኔ እና አንድ ሌላ ሰው በቆምንበት ወሬው ቀጠለ። በመካከል “አዲስ ነገሮች፤ አሁንማ ለይቶላችሁ ሻእቢያ የሚሠራውን ሁሉ ጀስቲፋይ ማድረግ ጀመራችሁ” አለን። በዚያ ሰሞን የአቶ መለስ እና የአቶ ኢሳይያስ ቡድኖች አንዱ ሌላውን ለመጣል አልፎም ለማስገደል ይፈልጋሉ እንደሚባል የሚጠቅስ ጽሑፍ አትመን ነበር። መነሻው ደግሞ ግንቦት 7 ሞከረ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት ነበር። ለበረከት ስምኦንና ለቡድኑ ግን ጽሑፉ የታየው በሌላ መንገድ ነበር። በተለይ ኢሳይያስን ለመገልበጥና ለማስገደል ፍላጎትና ሙከራ ነበር መባሉ መጠቀሱ ሳይከነክናቸው አልቀረም። በረከትም “ይህን ታሪክ ያነሳችሁት ሻእቢያም ተመሳሳይ ሙከራ ቢያደርግ ለማጽደቅ (ጀስቲፋይ ለማድረግ) ነው” በሚል ስሜት ተከራከረ። ከዚያ ትንሽ ልሞግተው ፈለኩ። “እንደ ጋዜጠኛ ‘ሻእቢያ እንደዚያ ማድረግ ይፈልጋል’ ስትሉን እንድናምናችሁ ከፈለጋችሁ፤ እነርሱም እናንተን ሲከሱ የማናምናቸው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቁት። ብዙም መነጋገር አልፈለገም። አክሎ ነገሩን ያነሳው እነግንቦት 7ን ከመደገፍ አልፈን ወደ ኤርትራ መዝለቃችንን ለማሳሰብ እንደሆነ ጭምር ጠቆም አደረገን። ማሳረጊያው ግን የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ ሆነ፤ “ለማንኛውም በስለት ላይ እየተራመዳችሁ እንደሆነ እወቁት (እርሱ በእንግሊዝኛ You are walking on the edge of a… ያለው መሰለኝ)፤ ተጠንቅቃችሁ ሒዱ ስለቱ ይቆርጣል” አለን። (በስለት ላይ ስለመራመድ ጥንቃቄ በእጁ ያሳየን ሁሉ ትዝ ይለኛል።) እኛን መታገስ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው ጭምር አከለበት። ይህን አቋሙን ሳስታውስ “ለካስ ገና ድሮ ሻእቢያን በመርዳት ለመከሰስ የሚያበቃ በቂ ወንጀል ፈጽመን ነበር” እንድል አድርጎኛል።
የቀረው ክስ ድሮም የነበረ ነው፤ ቦታና ስም እየቀያየሩ የሚጽፉት የእነበረከት/ሽመልስ ስውር ጸሐፊዎች “በአዲስ ዘመን ጋዜጣ” በሚያትሙት “የክስ ረቂቅ” (“አጀንዳ” የተባለው ዝነኛ አምድ) ተጽፎ ያለቀ ነው። እነዚህን “የአዲስ ዘመን” ክሶች “የክስ ረቂቅ” ያልኳቸው የሚጻፉት አስቂኞቹን የሽብርተኝነት ክሶች በሚያዘጋጁት ሰዎች ስለሆነ ጭምር ነው፤ እነዚህ ሲኒየር የክስ ደራሲዎች ሥራ ሲበዛባቸው ደግሞ ሐሳቡና የክርክር አካሔዱ እየተነገራቸው የሚጽፉ ቢሮ አልባ “አቃጥሮ አዳሪዎች” አሉ። ስም መጥራት ይቻላል። ሳይረሳ፤ የደኅንነቱም ባልደረቦች ይሳተፉበታል።
በአሁኑ ክስ ላይ የተደገሙት “የአዲስ ዘመን” ክሶች ናቸው። ልዩነት ክሶቹ መጀመሪያ በጋዜጣ ወጥተው ተሸጡ፣ አሁን ደግሞ ለፍርድ ቤት ቀረቡ። ግንቦት 7ንና ሐሳቦችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መደገፍ፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ማፍረስ/ማጥላላት…አገር ቤት ያሉትን ተቃዋሚዎች መደገፍ…። እነዚሁ ክሶች ዛሬም ድረስ አገር ቤት ባሉት የሞያ ባልደረቦቻችን በእነ ዳዊት ከበደ እና ተመስገን ደሳለኝ ላይ እየቀረቡ ነው። ክሶቹ በመሠረቱ አንድም ውሸት ናቸው አለዚያም ሕጋዊ መሠረት የላቸውም። ቁም ነገሩ ግን መንግሥታችን አንድን ዜጋ ለመክሰስ ወንጀሉ በተከሳሹ መታሰብ ወይም መፈጸም የማያስፈልገው መሆኑ ነው። መንግሥት ባልታሰበና ባልተፈጸመ ወንጀል ዜጎችን መከሰስ የሚችልባት ዴሞክርሲያዊ አገር ፈጥረናል። በዚህ መሰሉ ክስ ላይ ተመሥርቶ ራስን መከላከል፣ ስለ ፍትሕ ወይም ስለ ዳኝነት ነጻነት መነጋገር የሚገባ ሆኖ አላገኘሁትም።
የሚሸበር አያሳጣን!
በስም እና በተሰያሚ መካከል ባሕርያዊ ግንኙነት አለመኖሩ በሥነ ልሳን ተማራማሪዎች አዘውትሮ የሚነገር ነው። ጽጌረዳን ስሟን ብንቀይረው ሽታዋን/መልኳን አትቀይርም እንደሚባለው መሆኑ ነው። ነገሩ የእኛ ስምምነት ጉዳይ ብቻ ነው። አቶ መለስ እኛን “አሸባሪ” ስላሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያግባባው ትርጉሙ አሸባሪ አንሆንም። በምትኩ ግን ለቃሉ አዲስ ትርጉም ሰጥተን ተስማማምተን መቀጠል እንችላለን።
ከዚያ ይልቅ ከአቶ መለስ ጋራ ወደ ስምምነት ለመድረስ አጭሩ መንገድ የአሸባሪዎቹ ስም ይፋ እንደሆነ ሁሉ የተሸባሪዎቹም ስም በአደባባይ እንዲጠቀስ መጠየቅ ነው። እኔና መሰሎቼ “አሸባሪ” በመሆናችን እና በፈጸምነው “አሸባሪ” ድርጊት የተሸበራችሁት እነማን ናቸሁ? በሙሉ እርግጠኝነት የእኛ ተግባር ከአቶ መለስና በዙሪያቸው ከተሰበሰቡት ዞምቢዎች ሌላ የሚያሸብረው ቀርቶ የሚያሳስበውም ሰው የለም፤ ባይሆን የሚያስደስተው ይበዛል።
እነአቶ መለስ ይህንን የታጨቀ (loaded) ቃል (አሸባሪነት) መቀለጃ ማድረጋቸው አንድ ቀን እነርሱንም ሆነ አገሪቱን ሊጎዳ እንደሚችል ግን አያጡትም። በመንደሩ ነዋሪዎች ድንጋጤ መዝናናት የጀመረው እረኛ ታሪክ መደገሙ አይቀርም። የውሸታሙን እረኛ ታሪክ ብዙዎቹ አንባቢዎቼ የምታውቁት ይመስለኛል። እረኛው አንዳችም ነገር ሳይመጣበት “ቀበሮ በጎቼን በላ፣ ድረሱልኝ” ብሎ ተጣራ አሉ። መንደርተኛውም እውነት መስሎት ግልብጥ ብሎ ሊያድነው መጣ። ለካስ ውሸቱን ነው። እረኛው የመለስ ብጤ ፌዘኛ ኖሮ አሁንም ጨዋታውን ደገመው። መንደርተኛው አዘነ። በመጨረሻ የቀበሮና የጅብ መንጋ የእረኛውን ከብቶች ይመነትፋቸው ጀመር። እረኛው “ድረሱልኝ!” ብሎ ተጣራ፤ የሰማው አልነበረም።
“ሽብር/አሸባሪነት” የሚለውን አወዛጋቢ ፅንሰ ሐሳብ በዚህ መልኩ በአገር ደረጃ መቀለጃ ማድረግ በውስጥም በውጭም ኢትዮጵያን በጣም የሚጎዳ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል አያጠራጥርም። በዚህ አያያዝ ግን እውነተኛው አሸባሪ ቢመጣና መንግሥት “ድረሱልኝ” ቢል የሚሰማው አይኖርም። በዚህ ደግሞ ዜጎች ብሎም አገር መጎዳቷ አይቀርም። ነገሩን ለፈረንጅ ወዳጆቻችንን ለማስረዳት አቶ መለስ የፈጠሩትን አዲስ የፖለቲካ ባህል ማስታወስ ግድ ይላል እንጂ ኢትዮጵያውያን በአዲሱ “የአሸባሪነት” ትርጉም ሙሉ በሙሉ ተግባብተናል። “በአሸባሪነት ሳንከሰስ ለምን ቀረን?” እየተባለ በየሰፈሩ የሚነገረው ቀልድ በአዲሱ ትርጉም ለመግባባታችን ማረጋገጫ ነው። በአዲሱ የመለስ መዝገበ ቃላት ሽብርር እና አሸባሪሪን እንዲህ ይተረጉመዋል። (ማስታወሻ፦ አዲሱን የሽብር ትርጉም ከቀድሞው ለመለየት ይረዳ ዘንድ የአቶ መለስ ፈጠራ የሆነውን “ሽብርር” የመጨረሻ ፊደል እንደግመዋለን፤ ሽብርር፣ አሸባረረ፣ ተሸበረረ፣ አሸባሪሪ፣ ሽብርርተኝነት፣ ተሸባሪሪ፣ ሽብሬሬ …)
ሽብርር፦ የዜጎች ነጻነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፣ ስለእርሱ ማሰብና መመኘት፣ ለዚሁም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ መሥራት፤ ፍትሕ፤ እኩልነት፤ መተማመን
የሽብርር ተግባር፦ በንጉሠ ነገሥት መለስና በቤተሰባቸው፣ እንዲሁም በአጋፋሪዎቻቸው ላይ የሽብርር ስሜት እንዲፈጠር መመኘት፣ ማሰብ፣ ለተግባራዊነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሐሳብ፣ የጸሎት፣ የሞያ እና ሌላም ድጋፍ ማድረግ፤አምባገነናዊ የጥቂት ጥቅመኞች ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ የነጻነት ሥርአት እንዲተካ ማሰብ፣ መመኘት
አሸባሪሪ፦ ብጽዕ ወቅዱስ አምባገነን መለስ እና ሥርዓታቸው የሚፈጽሙትን ሕገ ወጥ ተግባር የጠላ፣ ያማ፣ ያጋለጠ፣ ቢለወጥ ብሎ የተመኘ፣ የለውጥ ሐሰቡን ለሌሎች ያካፈለ፤ በኢትዮጵያ ነጻነት እንዲሰፍን የጠራ፣ የጣረ፤ በግልጽም ይሁን በስውር በአቶ መለስ ላይ መጥፎ አመለካከት ካላቸው ጋራ የተባበረ፣ ሐሳባቸውን ለመደፍ ያሰበ፤ የአቶ መለስን ሥርአት በሰላማዊ ትግል ስለመለወጥ ያውጠነጠነ ወይም የተንቀሳቀሰ፣ ሥርአቱን በማንኛውም መንገድ ለመጣል የተነሳ እና ከዚህ ብጤዎቹ ሰዎች ጋራ የዝምድና፣ የጓደኝነት፣ የሰፈር ልጅነት ወይም ማናቸውም አይነት ተዛምዶ ያለው (የሐሳብ፣ የስልክና ኢንተርኔትን ጨምሮ)፣ …
ተሸባሪሪ፦ የተሸበረ፤ ከሥልጣኔ እወርዳለሁ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የማገኘው ጥቅም ይቀርብኛል፣ ለፍርድ እቀርባለሁ ብሎ የሚሰጋ፤ ስጋቱን ለማስቀረት አገር የሚያምስ፣ የሚያስር፣ የሚገድል፤ በረሐብ ለሚሰቃዩ “ሆዳችሁ ከሞላ ነጻነት ለምን ትጠይቃላችሁ?” ብሎ የሚሰብክ፤ እውነተኛ ዴሞክራሲን እና የዜጎችን ነጻነት የሚጸየፍ፤
በዚህ “የአቶ መለስን መዝገበ ቃላት” መሠረት ሁላችንም ያለንበትን በቀላሉ መለየት እንችላለን። ይህን ለማድረግ ክስ መመስረት፣ የዐቃቤ ሕግን እና የፍርድ ቤቶችን ጊዜ ማባከን አያስፈልግም። የአገራችንን መልካም ገጽታም በመጥፎ ስም ማንሳት አይገባም። በዚህ ትርጉም መሠረት መከላከልም ሳያስፈልገኝ አሸባሪነቴን አምናለሁ፤ ተገኝቶ ነው?! የሚሸበር አያሳጣን! “የኢትዮጵያ አሸባሪሪዎች ተባበሩ!” (ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለዐቃቤ ሕግ እልካለሁ፤ ለምሳሌ አቶ መለስ በፖለቲካና በጦርነት የለያዩን ኤርትራውያን ወንድሞቼ የሚወዷትን ከተማቸውን አሥመራን ለማየት እመኛለሁ። ከባርሴሎና ቀጥሎ አሥመራን የመጎብኘት እቅድ ስላለኝ በክስ ቻርጁ ውስጥ ይኸው ይካተት።)
በመጨረሻው መጨረሻ የነጻነት ፈላጊዎች ጥያቄ ግፍን በማብዛት፣ አዲስ ስም በመለጠፍ፣ በማሰር፣ በመግደል፣ በማሰደድ ተሸንፎ እንደማያውቅ የተረጋገጠ ነው። እነአቶ መለስ ዛሬ ለማስፈራሪያ ጥቂቶቻችንን መረጡ እንጂ የአሸባሪሪነት “ወንጀሉ” ኢትዮጵያ የነጻነት አገር ሆና ለማየት የሚመኙና ባመኑበት መንገድ የሚሠሩት ዜጎች ሁሉ ነው። በዚህ ቀልደኛ ክስ መካታት የነአቶ መለስን ትኩረት የመሳብ ማረጋገጫ ከመሆን አልፎ ተከሳሾቹ ከሌሎች የበለጠ ለኢትዮጵያ የሚያስቡ/የምናስብ ወይም የታገልን ተደርጎ የሚያስቆጥር አይደለም። ወይም እንደዚያ አይነት ስሜት አይሰማኝም። ብዙ ሠርተው በክሱ የተካተቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ምንም የሠራን (ያሸበርርን) ሳይመስለን የተካተተንም አለን። እርግጥ ማሸበርር መቻሌን ማወቄ አልከፋኝም። የእነአቶ መለስ ውቃቢ ተከሳሾቹን ከሌሎቹ “ወንጀለኞች” እንዴት አድርጎ እንደሚመርጥ ለማወቅ አልሞከርኩም፤ ትርጉም ስለሌለው። በክሱ ስማችን የተጠቀስነውም ሆንን ያልተጠቀሳችሁት ሚልዮኖች ነጻነትና ዴሞክራሲን በመጠየቁ “ወንጀል”ሁላችንም አንድ ነን፤ “እስክንድር ነጋ ነኝ! አንዱዓለም አራጌ ነኝ (I am Eskinder Nega, I am Andualem Arage. . .) እንደማለት! ለአቶ መለስ “ወንጀል” የሆነው የነጻነት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት ጥያቄ ቀዳሚ መተሳሰሪያችን ነው። በዚያው ምትሐታዊ ባለቅኔ ዮሐንስ ስንኝ ላሳርግ፤
ዘመን ቢያርቃችሁ፣
ስፍራ ቢለያችሁ፣
ዕንባ አጋጠማችሁ።
No comments yet... Be the first to leave a reply!