የሽብርተኝነት ፖለቲካ እና የአቶ መለስ ቁማር
(ይህ ጽሑፍ አገር ቤት ለሚታተመው “ፍትሕ” ጋዜጣ የተጻፈና የወጣ ነው። የጋዜጣው አዘጋጆችካደረጓቸው አነስተኛ ማስተካከያዎች በቀር በጋዜጣው የወጣው ጽሑፍ ይኼው ነው። ጽሑፉን ለጋዜጣው ከላኩ በኋላ ያገኘኋቸውን መረጃዎችና ማስተካከያዎች እዚህ ተካተዋል።)
ከአንድ የሴናተሮች ቡድን ጋር የተገናኙ አንድ ምንጭ እንደሚሉት አሜሪካ የሁለቱን ጋዜጠኞችም ሆነ የሌሎቹን ኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸውን መፈታት የምትፈልገው በኢትዮጵያ ያለው ሥርአት ዴሞክራሲያዊ ይሆናል በሚል እምነት አይደለም። የራሳቸውን ቃል ለመጠቀም “ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ የምንፈልገው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ውስጥ እንዳትገባ ለመከላከል ነው።” አራት ነጥብ። መለስ ከዚህ በተቃራኒው የዓለም አቀፉን ትኩረት በጨቋኝ ገጽታቸው መሳብ ይፈልጉ ይሆን? ካልፈለጉ ከነአሜሪካ ጋራ ይስማማሉ። ቀሪው የተለመደውን የማርያም መንገድ ፈልጎ ስዊድናውያኑን መፍታት ይሆናል። ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬስ? ጥያቄ ነው።
በኦብነግ በኩል ግን ዜናው “በረከተ መርገም” ነው። እዚህ ያነጋገርኳቸው የኦብነግ አባላት ፊት ለፊት ባይናገሩትም በጋዜጠኞቹ መያዝ ድርጅታቸው እንዳልከሰረ ይምናሉ። “በሁሉቱም መንገድ ማትረፋችን አይቀርም ነበር” ነው ሒሳቡ። ጋዜጠኞቹ ተሳክቶላቸው ዘገባቸውን ይዘው ቢወጡ በሆነ መንገድ መለስን የሚያጋልጥ እንደሚሆን ጥርጥር እንዳልነበረው አንድ የኦብነግ የወጣቶች ማኅበር መሪ አጫውቶኛል። ብዙ ተመልካቾች ኦብነግ ጋዜጠኞችን ለመርዳት የሚያነሳሳ ጠንካራና ምክንያታዊ (ሌጂቲሜት) ፍላጎት እንዳለው ይምናሉ። አሁን ጋዜጠኞቹ መያዛቸውም ቢሆን በተዘዋዋሪ የሚናገረው ኦጋዴን ውስጥ “ዓለም ሊሰማው የማይገባ” ነገር መኖሩን ይመስላል።
(ይህ ጽሑፍ አገር ቤት ለሚታተመው “ፍትሕ” ጋዜጣ የተጻፈና የወጣ ነው። የጋዜጣው አዘጋጆችካደረጓቸው አነስተኛ ማስተካከያዎች በቀር በጋዜጣው የወጣው ጽሑፍ ይኼው ነው። ጽሑፉን ለጋዜጣው ከላኩ በኋላ ያገኘኋቸውን መረጃዎችና ማስተካከያዎች እዚህ ተካተዋል።)
“ሙሽራዬ ቀረ”
ለአውሮፓውያን በቀናት ልዩነት የሚመጡትን ገናን እና የዘመን መለወጫ በዓላትን ያለ “በረዶ” መቀበል የተለመደ አይደለም። አምና በኦክቶበር መጨረሻ “በበረዶ ዝናብ” (ስኖውፍሌክስ የሚሉት) መታጠን ጀምራ የነበረቸው የሰሜን አውሮፓዋ ከተማ ስቶክሆልም ዘንድሮ በጥጥ መሳዩ የበረዶ ዝናብ ለመጎብኘት የዲሴምበርን መጨረሻ መጠበቅ ነበረባት። ከገና (ዲሴምበር 25) ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ መጣል የጀመረው ስኖውፍሌክስ ግን ስቶክልማውያንን እንዷጓጓቸው ቀርቷል። በዚህ ወቅት ነጠላ አጣፍተው የሚያስደቀድሱ ሴቶች መስለው ይታዩ የነበሩት ዛፎች ዘንድሮ ያለልብሳቸው ገናን አክብረዋል። ከቀኑ 10.00 ሰዓት ገደማ ጀምሮ የሚያረበውን ጨለማ ፈካ የሚያደርገው መሬቱን ሁሉ የሚያለብሰው በረዶም እስካሁን የለም። ስቶኮልማውያን (የተለመደ የከተማው ነዋሪዎች ራሳቸውን የሚጠሩበት ስም ነው) ለገና አሁን ደግሞ ለአዲሱም ዓመት በረዶውን እየጠበቁት ነበር። አልመጣም።
የቀረባቸው ግን “በረዶ” ብቻ አይደለም። “ገናን አብረውን ይውላሉ” ያሏቸው በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙት ሁለቱ ጋዜጠኞቻቸው ማርቲን ሽብዬ እና ጆዋን ፐሹንም ጭምር ናቸው። ሁለቱ “ሙሽሮች” በነጩ በረዶ ተከበው፣ ነጩ ስኖውፍሌክስ ተነስንሶባቸው ቤተሰብ በዓመት አንድ ጊዜ በሚሰባሰብበት የገና በዓል እንደሚመጡ የገመቱ ጥቂቶች አልነበሩም። አንድ ጋዜጠኛ “ለገና አይፈቱም?” ብሎ ጠየቀኝ። “ለየትኛው ገና?” አልኩት ፍርድ ከመሰጠቱ ሁለት ወር ቀድሞ። ዐይኑን አፍጥጦ በድንጋጤ ጠየቀኝ፤ “እውነትህን ነው? ምንም ማስረጃ ሊቀርብባቸው አይችልም እኮ?” ቢገረሙ ግን አይፈረድባቸውም፤ ኢትዮጵያን እኛ በምናውቃት መልኩ አያውቋትም፤ ለምንስ ያውቋታል?
ማርቲን እና ጆዋን በኢትዮጵያ መያዛቸው እንደተሰማ ነገሩ አስደንጋጭ ዜና ብቻ ነበር። ወሬው ጆሮ ጭው የሚያደረግ የሆነው ጋዜጠኞቹ በሽብርተኝነት እንደሚከሰሱ የተሰማ እለት ነው። ከስዊድናውያን ጋዜጠኞች እና ወዳጆቼ ብዙ ስልክ ያስተናገድኩበት አንዱ ቀን እርሱ ነበር። ሌላው ቀርቶ ራሱ “ሽብርተኝነት” የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ሰምተውት የማያውቁት ያህል ሆኖ ሳይሰማቸው አልቀረም። “እናንተ አገር የተለየ የሽብርተኝነት ስታንዳርድ አለ እንዴ?” ብሎ አንዱ ጋዜጠኛ ጠይቆኝ ነበር፤ መልሱን በሒደት አግኝቶታል። እነጆዋን መጠነኛ እውቅና ያላቸው ወጣት ጋዜጠኞች ናቸው። ላለፉት አምስት ወራት ያነጋገርኳቸው ብዙዎቹ ስዊድናውያን እንደሚያምኑት እነማርቲን “ሽብርተኝነት” የሚለው ቅጽል እንዳይጨመርላቸው ለመሟገት ጋዜጠኞች መሆናቸው ብቻ ይበቃቸዋል።
ጋዜጠኞቹ ወደ ኦጋዴን መሔዳቸው፣ ለመግባት የመረጡበት መንገድ እና ለመጋፈጥ የወሰኑት አደጋ መነጋገሪያ ከመሆን አላመለጠም። ሆኖም ከጥቂቶች በቀር እነማርቲንን የሚከስ የለም። በግጭት አካባቢዎች ሰርጎ በመግባት የሚዘጋጁ ዘገባዎችን ማንበብ ለስዊድናውያን ያልተለመደ ነገር አይደለም። እንኳን የጋዜጣ/የመጽሔት ጽሑፍ ቀርቶ ፊልምም በዚሁ መንገድ ይሠራሉ። መዘዘኛው የስዊድን የነጋጅ ኩባንያ ሉንዲን፣ በሱዳን ነዳጅ አውጥቶ ለመሸጥ ከመንግሥት ጋራ በገባው ውል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያደረሰው መፈናቀል፣ የነዳጅ ቁፋሮና ምርቱን ደኅንንት ለመጠበቅ የተሰማሩት የመንግሥት ወታደሮች በአካባቢው ላይ ያደረሱትን ግፍ የሚዘግበው ፊልም ከእነዚሁ የሚደመር ነው። እነማርቲን አዲስ አበባ ላይ የሚሰማቸው አላገኙም እንጂ፣ ወደ ኦጋዴን የተጓዙበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ሉንዲን ከሌሎች አጋር ኩባንያዎቹ ጋራ በኦጋዴን አድርሶታል ወይም ምክንያት ሆኗል የሚባለውን ቀውስ ለመመርመር ጭምር ነበር። ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በኦጋዴን የተሰማሩት ወይም ተሰማሩ የሚባሉት ኩባንያዎች ምንና እንዴት እንደሚሰሩ ጠይቀን አናውቅም። ከፊርማ ስነ ስርዓቱ ጀርባ ምን እንደሚከተል ማን ያውቃል? በኦጋዴን በቀጠለው ቀውስ እነዚህ ኩባንያዎች የጨመሩት ነገር ይኖር ይሆን?
ለብዙዎቹ ተመልካቾች የጋዜጠኞቹ “በሽብርተኝነት” እና “ሽብርተኝነትን በማገዝ” መከሰስ ስለጋዜጠኞቹ ከሚናገረው በላይ ስለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሊደብቀው ስለሚፈልገው ነገር ይናገራል። በዚህ የመደበቅ ዘመቻ የሚከሰሱት ግን የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርል ቢልድት ጭምር ናቸው። እነማርቲን የመያዛቸው ዜና እንደተሰማ ቢልድት የሰጡት መልስ እጅግ አጠያያቂ ሆኗል። “(ሰዎች) ወደዚህ አካባቢ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ ስንሰጥ ነበር፤ ምክንያቱም አካባቢው አደገኛ ስለሆነ ነው።” በሌላ አነጋገር “ማን ሒዱ አላቸው፤ ይበላቸው” አይነት ነው። ይቺ የቢልድት ንግግር የጫረቻት እሳት ዛሬ የበለጠ ጎልታ እየታየች ነው፤ እሳቷ ሰውየውን መልሳ እንዳትበላቸውም ያሰጋል። ያለምክንያት አይደለም። በአንድ በኩል ቢልድት “ሉንዲን ግሩፕ” ከተባለው የነዳጅ ድርጅት ጋራ የጥቅምና የታሪክ ግንኙነት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ስዊድን ነው፤ ጋዜጠኞች ያጋለጡት ባለሥልጣን ተዋርዶ ሥልጣን የሚለቅበት አገር ነው፤ በሙስና ከወሰዱት ግማሹን ለፓርቲ እየሰጡ፣ ወይም ኢንዶውመንት በሚባል ጫካ እየተደበቁ የሚኖሩበት አገር አይደለም። አገሩ የመላእክት ነው ማለቴ ግን አይደለም። (ማረፊያ ታሪክ፤ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ፣ ቀጣዩዋ መሪ እንደሚሆኑም በስፋት ይነገርላቸው የነበሩ አንድ ፖለቲከኛ መንግሥት በሚሰጣቸው ክሬዲት ካርድ ነዳጅ ለመሙላት አንድ ማደያ ላይ ይቆማሉ። ነዳጁ ተሞላ። ወዲያው እዚያው የሚሸጥ ቸኮሌት ያዩና ውል ይላቸዋል፤ ሲፈርድባቸው። 50 ብር የማይሞላውን (17 ክሮነር ግድም) የቸኮሌቱን ሒሳብ ከግላቸው ሳይሆን ከዚያው የመንግሥት ክሬዲት ካርድ ይከፍላሉ። ይቺ ነገር አንዱ ጋዜጠኛ እጅ ትገባለች። እዚህ ሁሉም ነገር እንደመንግስተ ሰማያት በግልጽ መዝገብ ይመዘገባል፤ የተመዘገበውን ጋዜጠኛ ሲጠይቅ መደበቅ ደግሞ የለም። ሴትየዋ “ቸኩዬ ነው፤ ይቅርታ” ቢሉ ማን ሊሰማቸው። “በትንሽ ካልታመንሽ…” ተብለው ከሥልጣን ለቀቁ።)
የቢልድት ንግግር አጣጥሎ የጻፈው “የዳገንስ ኒሔተር” እለታዊ ጋዜጣ ኤዲተር ቦርን ዊማን በሚኒስትሩ ላይ ተሳልቆባቸዋል።
“ይህ ‘አካባቢው አደገኛ ስለሆነ እንዳትሔዱ አስተንቅቀናችሁ ነበር’ የሚለው አስተያየት የጋዜጠኝነትን ተልእኮ ያለመረዳት ችግር ነው። ‘ሊጋለጥ የሚችል ነገር ወዳለበት ቦታ አትሒዱ! ሔዳችሁ ችግር ከገጠማችሁም ራሳችሁን ውቀሱ!’ እንደማለት ነው። ይህ ከጋዜጠኝነት ተልእኮ ተቃራኒ ነው፤ ጋዜጠኝነት ሐይለኞች ገበናቸውን ወደሚደብቁባቸው አካባቢዎች ሔደን እንድንመረምር ይጠይቀናል። ይህን የሚፈጽሙ ጋዜጠኞች ክብር ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ይህን የሚያደርጉት የኅብረተሰባቸውን (መረጃ የማግኘት) ፍላጎት ለማሟላት ስለሆነ ነው” ብሏል። ጸሐፊው አክሎም ኦጋዴን ለገለልተኛ ታዛቢዎች ዝግ ቀጣና መሆኑን ያወሳና “ታዲያ በዚህ አካባቢ ያለውን እውነት የሚያወጣው ማን ነው? የነዳጅ ኩባንያዎቹን ጥቅም ለማስጠበቅ በተሰማሩት ወታደሮች የሚፈጸመውን እስራት፣ ስቃይ፣ ግርፋት፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር የሚያጋልጠው ማነው?” ሲል ይጠይቃል።
የእነማርቲንን የኦጋዴን ዘመቻ በካርል ቢልድት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት አይታወቅም። እርግጥ ማርቲንን “ሶሻሊስት ነው” በማለት ለማጥላላት የሚተቹ ጥቂት የኢንተርኔት አስተያዮች ይሰማሉ። ነገሩ “ማርቲን አሁን ስልጣን በለቀቁት ሶሻል ዴሞክራቶች የተላከ ነው፤ ፖለቲካዊ አላማ አለው” የማለት ቃና ቢኖረውም ክርክሩ በጋዜጠኞች ዘንድ የሚረባና የሚወሳ አልሆነም። ውጭ ጉዳይ ቢልድትንም ከወቀሳ አልታደጋቸውም።
ካርል ቢልድት እና ሉንዲን ግሩፕ
ቢልድት ከዚህ ቀደም (እ.አ.አ ከ1991-94) የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ፣ በኋላም የአውሮፓ ኅብረት የባልካን ልዩ ልኡክ በመሆን ያገለገሉ ባለጸጋ ፖለቲከኛ ናቸው። ከስዊድን ጥቂት ሀብታም ፖለቲከኞችም አንዱ ናቸው ይባልላቸዋል። ከ2000 እ.አ.አ ጀምሮ የአዲሱ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እስከተሾሙበት እስከ 2006 ድረስ የሉንዲን ግሩፕ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ነበሩ። ብዙውን ሀብታቸውን ያፈሩትም በዚህ ወቅት ነው እየተባለ ይነገራል።
ሉንዲን በደቡብ ሱዳን በወሰደውና ከ1997-2003 (እ.አ.አ) በቆየ አንድ የነዳጅ ቁፋሮ ፕሮጀክት ከፍተኛ ወቀሳ ደርሶበታል። የአውሮፓውያን ድርጅቶች ስብስብ የሆነው “ኢኮስ” (European Coalition on Oil in Sudan-ECOS) በ2010 ባቀረበው ሪፖርት የስዊድኑ ሉንዲን ከማሌዢያው ፔትሮናስ እና ኦኤምቪ ጋራ በመቀናጀት በደቡብ ሱዳን በሰራበት ወቅት ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ጠቁሞ ነበር። ሦስቱ አገሮች ማለትም ስዊድን፣ ኦስትሪያ እና ማሌዢያም የሉንዲንን የሱዳን ቆይታ እንዲመረምሩ ሪፖርቱ ጠይቆ ነበር።
ሉንዲን በሱዳን በነበረበት ጊዜ የኩባንያውን የጸጥታ ችግር ለማስወገድ የተሰማሩለት የመንግሥት ወታደሮች እንዲሁም በየሰፈሩ የነበሩት ከሉንዲን ጋራ የጥቅም ትስስር ነበራቸው የሚባሉ የታጠቁ ሚሊሻዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት ግፍ ረዘም ያለ ጥናታዊ ፊልም ወጥቶታል። “ይህን ፊልም የተመለከተ ሰው የነዳጅ ኩባንያዎች አንዳችም የስነ ምግባር መርህ የሌለው አሠራር ሊከተሉ እንደሚችሉ በቀላሉ ይረዳል” ብላኛላች ፊልሙ መስከረም ውስጥ እዚህ ስቶክሆልም ሲቀርብ ከነበሩት አስተባባሪዎች አንዷ።
ሪፖርት እንደዋዛ በማይታይበት በዚህኛው የዓለማችን ክፍል ያለው የስዊድን ዓለም አቀፍ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ( International Prosecution Chamber) “ኢኮስ” (ECOS) “ያልተከፈለ እዳ” ( “Unpaid Debt”) በሚል ርእስ ያቀረበውን ሪፖርት እንደዋዛ አላለፈውም። ጉዳዩን በከፍተኛ ደረጃ ይዞ ምርመራውን ቀጥሏል። በቅርቡም 40 የሉንዲን ኦይል/ፔትሮሊየም ሐላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ስለጉዳዩ ሊያውቁ ይችላሉ የተባሉ ሰዎች ለጥያቄ ተጠርተዋል። ከእነዚህ የመጀመሪያ ዙር ተጠያቂዎች ዝርዝር ውስጥ የካልድ ቢልድት ስም አልተካተተም፤ ይህ ለራሳቸውም ለሌሎችም ሳያስገርም አይቀርም። ሆኖም ምርመራው ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም።
ማርቲን እና ጆዋን እንዳሰቡት ወደ ኦጋዴን ገብተው ቢሆን ኖሮ ሉንዲንና የእርሱ አጋር የነበሩት የማሌዢያ ኩባንያዎች አድርገውታል የሚባለውን ነገር ለመመርመር እድል ያገኙ ነበር። ገና ከመሔዳቸው በፊት ይህን ሪፖርት ለማተም ያቆበቆቡ ሚዲያዎች አንዱና ዋናው ፍላጎት ጉዳዩ ከካርል ቢልድት ጋራ የሚያያዝ በመሆኑም ጭምር ነበር።
ካርል ቢልድት በሁለቱ ጋዜጠኞች ክስ ላይ የወሰዱት አቋም “የቆሸሹ እጆች” እንዳሏቸው የሚያሳይ ነው ሲሉ የሚተቿቸው አሉ። ቢልድት ስለጋዜጠኞቹ ብዙ ከመናገር ተቆጥበው ከርመዋል። በተናገሩባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ጠንከር ያለ ቃል ከመሰንዘር ሲቆጠቡ ነበር። እርሳቸውና ደጋፊዎቻቸው ይህን የሚያደርጉት ጉዳዩን በጸጥታ ዲፕሎማሲ ለመያዝ በወሰዱት አቋም ነበር።
የትብብር ዲፕሎማሲ-የጸጥታ ዲፕሎማሲ-የሽንፈት ዲፕሎማሲ
ጋዜጠኞቹ እንደተያዙና ክስ እንደተመሰረተባቸው ሰሞን የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አጣብቂኝ ውስጥ ነበር። “ጥቂቶቹ ሐላፊዎች በኢትዮጵያ ነጻ ፍርድ ቤት እንዳለ የማሰብ ቅዠት ውስጥ ነበሩ” ይላል ጉዳዩን በትጋት የሚከታተለው የዳገንስ ኒሔተር ጋዜጠኛ። ሌሎቹ ደግሞ በቀጥታ አደባባይ ወጥቶ ማውገዙ መለስ ዜናዊን ሊያስቆጣና ያልተፈለገ ውጤት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ነበራቸው። መለስ በቅርብ በወጡ የዊኪሊክስ ኬብሎች የተሳሉበት ቁጡነትና “አትድርሱብኝ” ባይነት፣ ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋራ ያላት ግንኙነት መቀዛቀዝና ይህም የሚያስከትለው የተጽእኖ መዳከም፣ በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ እጅ የወደቀውና ይሙት ይኑር የማይታወቀው የስዊድን ዜግነት ያለው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅ እጣ ፈንታ፣ እንዲሁም የነማርቲን ክስ ለማስፈራራት የተደረገ ስለሆነ መከሰሱ ራሱ በቂ ስለሆነ ይለቀቃሉ የሚሉት ግንዛቤዎች የመንግሥቱን “የጸጥታ ዲፕሎማሲ” ፖሊሲ ሳይቀርጹት አልቀሩም።
ስዊድን ከኢትዮጵያ ጋራ የነበራት የረጅም ዘመን ግንኙነት በዲፕሎማሲ እና በትብብር ላይ የተመሰረተ ነበር። አማርኛ እና ኦሮሚኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ ከ1950 ጀምሮ የነበሩ ታሪኮችን በቅርበት ለመመስከር የሚችሉ ስዊድናውያን ቁጥር ጥቂት አይደልም። አንዳንዶቹም ከኢትዮጵያ ጋራ በፍቅር የወደቁ ናቸው፤ ከኢትዮጵያውያን ጋራ የተጋቡትን የተዋለዱትን ሳልቆጥር። የስዊድን አለም አቀፍ ልማት ተቋም (ሲዳ) በታሪኩ ስኬታማ የልማት ሥራዎችን ካከናወነባቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ይህ እርዳታቸው ደግሞ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ሳያበቃ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጊዜም ቀጥሎ ነበር። እርዳታው ከትምህርት ቤት ግንባታ እስከ እውቀት/ትምህርት እድል፣ ከወታደራዊ ስልጠና እስከ የናቹራል ሒስትሪ ሙዚየም (አአዩ)፣ ከደርግ ትልልቅ የግብርና ሙከራ ፕሮጀክቶች (በተለምዶ ካዱ እና ዋዱ የሚባሉት) እስከ የመሬት ፖሊሲ ጥናት እገዛ የዘለቀ ነበር።
በዘመነ መለስ ዜናዊም የመጀመሪያ ዓመታት ትብብሩ እንደቀጠለ ነበር። ስዊድን እና መንትያ ጎረቤታቸው ኖርዌ፣ እነ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “ጫካ” በነበሩበት ዘመን የሞራል እና የዲፕሎማሲ እርዳታ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መልክ የሚሰጡት እርዳታም በአንድ ወቅት ለእነህወሓት እጅግ አስፈላጊ ነበር። ይህ መንፈስ ግን ብዙ አልተጓዘም። አቶ መለስ እና አቶ ኢሳይያስ ሥልጣን እንደያዙ በቅድሚያ ከተናጀሱዋቸው አገሮች አንዷ ስዊድን ሆነች። ዛሬ ስዊድን ከሁለቱም አገሮች ጋራ ያላት ግንኙነት በታሪካቸው ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ እውነታ ስዊድን በሁለቱም አገሮች ላይ ያላትን ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶታል። ስዊድን አሁን ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የእርዳታ መጠን እንደ ድሮው ከቀዳሚዎቹ አምስት አገሮች ዝርዝር ውስጥ አትገኝም። ይህም በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነው የአቶ መለስ መንግሥት ጭምር የምር የማይወስዳት አገር አስመሰሏታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከስዊድን ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ለማቀዝቀዝ የወሰኑት ከአራት ዓመታት በፊት ነበር። መለስ በአደባባይ የሰጡት ማብራሪያ “ከአገሪቱ ጋራ ይህ ነው የሚባል የኢኮኖሚም ሆነ ሌላ ትብብር የለንም” የሚል ቃና ያለው ቢሆንም እውነታው ሌላ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ስዊድን ባለፈው አስርት አመት አጋማሽ ጀምሮ ዲሞክራሲን እና ሰብአዊ መብትን በመላው ዓለም የማስፋፋትና የመደገፍ ሐላፊነት አለብን የሚል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መነሻ ነድፋለች። ይህም በእነአቶ መለስ ቦታ ሆኖ ለሚያየው ሰው “የጦርነት አዋጅ” ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። ስዊድን በ1997 የኢትዮጵያ ምርጫ ቀውስ ወቅት የአውሮፓ ኅብረት ለያዘው ጠንካራ አቋም አንዷ ቀስቀሽ እንደነበረች በስዊድን የዲፕሎማቲክ ኮሪደሮች ተደጋግሞ ይነሳል። ይህን ተከትሎ ነው “አርቆ አሳቢው” ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የስቶክሆልም ኤምባሲያቸውን ደረጃ ከአምባሳደር ወደ ጉዳይ ፈጻሚ ዝቅ እንዲል ያደረጉት። በስዊድን የመጨረሻው አምባሳደር የነበሩት አሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የተደረጉት ዲና ሙፍቲ ናቸው። ስቶክሖልም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአካባቢው ላሉት ለዴንማርክ፣ ለኖርዌ፣ ለፊንላንድ እና ለአይስላንድም ጭምር የሚሰራ ነው። ለአምስት አገሮች የሚሰራውን ኤምባሲ ደረጃ ዝቅ ማድረግ መልእክቱ ፖለቲካዊ ከመሆን ውጭ ሌላ ትርጉም እንዳይኖረው የሚያግድ ነው።
ስዊድኖች ግን በዲፕሎማሲ ባህል እንደተለመደው አጸፋውን አልመለሱም፤ የአዲስ አበባው ኤምባሲያቸው አሁንም በአምባሳደር ደረጃ የሚመራ ነው። ምናልባት ይህን ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ስለሆነ ሊሆን ይችላል የሚሉ ግምቶች አሉ። ሙሉው መልስ ግን ይህ ብቻ ላይሆን ይችላል።
ፊት ለፊት ባይነገረም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አማጽያን የለየላቸው ቀዳሚዎቹን የሚያስነቁ አምባገነኖች መሆናቸው በስዊድናውያን ልብ የመካድ ስሜት ሳይፈጥር እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። ከነአሜሪካ በተለየ መልኩ ሌላ የበለጠ ዋጋ የሚሰጡት ከኢትዮጵያ ጋራ የተያያዘ ፍላጎት ስለሌላቸውም፣ ይህ የመካድ መንፈስ ሲያሳድዳቸው ቢገኝ አይገርምም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክርሲያዊ ስርአት እንደሌለ የማይስማማ ፖለቲከኛ አልገጠመኝም። እንደ አሜሪካኖቹና እንደ እንግሊዞች እንኳን ለመዋሸትና ለማድበስበስ አይሞክሩም።
አገሪቱን ለአስርት ዓመታት የመራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በተለይ ለብርቱካን ሚደቅሳ ያሳየው ድጋፍም አቶ መለስ የጠረጠሩትን የሚያረጋግጥ ነበር። ብርቱካንን ለሻካሮቭ ሽልማት በማጨት መሪነቱን የወሰዱት የስዊድን የአውሮፓ ኅብረት ሚኒስትር ነበሩ።
የአገሪቱ የዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሐና ኤልኩዊስት ኦክቶበር ውስጥ ለተካሔደ አንድ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ሲናገሩ መንግሥታቸው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት በማይከበርባቸው አገሮች ለሚገኙ የነጻነት ናፋቂዎች እገዛ የመስጠት የሞራል እና የታሪክ ግዴታ እንዳለበት እንደሚያምን ገልጸው ነበር። በየአገሩ የታሰሩና የተሰቃዩ የዴሞክራሲ ምልክት የሆኑ ሰዎችን በምስል እያስደገፉ፣ ታሪካቸውን እየቀነጨቡ ሙግታቸውን ሲያቀርቡ ካነሷቸው ሰዎች አንዷ ብርቱካን ሚደቅሳ ነበረች። እኚህ ሚኒስትር አሁን ስልጣን የያዘው “የቀኝ” ፓርቲ (ሞደሬት ይሉታል በአገሩ አሰያየም) አባል ናቸው። ሐና “ሰዎች ነጻነትን ይፈልጋሉ፤ ነጻነትም ሰዎችን ይፈልጋል። ይህንን የማገዝ የሞራል ሐላፊነት እንዳለብን እረዳለሁ። ብዙዎቹ ለጋሽ አገሮች በግብዝነት አምባገነኖችን ስንረዳ ቆይተናል። ይህ ስሕተት እና የማያዛልቅ እንደሆነ ተረድተናል።” ሲሉ ተናግረዋል። መልእክቱ ግልጽ ነው፤ በተለይ አዲስ አበባን በመሳሰሉ አምባገነኖች በነገሡባቸው ከተሞች ሆነው ሲሰሙት።
በዚህ ድባብ ውስጥ እነማርቲንን ለማስፈታት የተሻለ የሚሆነው መንገድ “የጸጥታ ዲፕሎማሲ” ነው ብሎ የወሰነው የስዊድን መንግሥት ሙከራው ያመጣው ውጤት አልታየለትም። በክስ ሒደቱ አጋማሽ ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያውን “የሽብርተኛ ድርጅት አባል የመሆን” ክስ ውድቅ ሲያደርግ አንዳንዶች ይህን “የጸጥታ ዲፕሎማሲው” ውጤት አድረገው ለማየት ከጅሏቸው ነበር። በቀጣዩ ክርክር ሁለተኛው ማለትም ከአሸባሪ ድርጅት ጋራ የመተባባር ክስ ውድቅ ተደርጎ፣ ጋዜጠኞቹ በሕገ ወጥ መንገድ በመግባት ብቻ ይቀጣሉ የሚለው ተስፋ የታያቸው ነበሩ። በመጨረሻ የተሰማው ብይን እና የቅጣት ውሳኔው “የጸጥታ ዲፕሎማሲ” የሽንፈት አዋጅ ተደርጎ ተቆጥሯል።
በዚህ የሽብርተኝነት ክስ ድራማ አሜሪካ የሚኖራትን ሚና ስዊድናውያን በንቃት ይከታተሉታል። የአውሮፓ ኅብረትንም እንዲሁ። እስከ አሁን እንደታየው ሁለቱም ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት የመክሰሱ ነገር እንዳሳሰባቸው፣ የአሁኑንም ነገር እንደሚከታተሉት ከመግለጽ ያለፈ ቃል መናገርን አልመረጡም። የሶማልያ ቀውስና ውጊያ እንደገና ማገርሸት አቶ መለስን ለመውቀስና ለመክሰስ የማያመች አድርጎባቸዋል። የሶማልያ ቀውስ እስካልተፈታ አሜሪካንም ትሁን የአውሮፓ ኅብረት አቶ መለስን እስከመጨረሻ የመግፋት አማራጭ እንደሌላቸው በሁሉም ዘንድ የጋራ ግንዛቤ የተፈጠረ ይመስላሉ።
ከአንድ የሴናተሮች ቡድን ጋር የተገናኙ አንድ ምንጭ እንደሚሉት አሜሪካ የሁለቱን ጋዜጠኞችም ሆነ የሌሎቹን ኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸውን መፈታት የምትፈልገው በኢትዮጵያ ያለው ሥርአት ዴሞክራሲያዊ ይሆናል በሚል እምነት አይደለም። የራሳቸውን ቃል ለመጠቀም “ጋዜጠኞቹ እንዲፈቱ የምንፈልገው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ውስጥ እንዳትገባ ለመከላከል ነው።” አራት ነጥብ። መለስ ከዚህ በተቃራኒው የዓለም አቀፉን ትኩረት በጨቋኝ ገጽታቸው መሳብ ይፈልጉ ይሆን? ካልፈለጉ ከነአሜሪካ ጋራ ይስማማሉ። ቀሪው የተለመደውን የማርያም መንገድ ፈልጎ ስዊድናውያኑን መፍታት ይሆናል። ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬስ? ጥያቄ ነው።
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ፣ የስዊድን መንግሥት የፍርድ ቤቱን ሒደት በትግስት፣ ሳይናገር መከታተሉን አመስግነዋል። ይህ የጸጥታ ዲፕሎማሲ ጋዜጠኞቹን በይቅርታ ያስፈታቸው እንደሆነ ግን “መገመት አልችልም፤ ነገር ግን ሊሆን ይችላል” ሲሉ ለሲዊድን ሬዲዮ በስልክ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የተሰማ ባልመሰለኝ አንድ ሌላ ኢንተርቪው ፕሬዚደንት ግርማ የይቅርታው ጉዳይ “እንዳቀራረቡ ነው” ብለዋል። ስዊድኖች ዜጎቻቸውን ለማስፈታት ማወቅ ያለባቸውም ይህንኑ ነው፤ “አቀራረቡን።”
ከዳዊት ይስሐቅ እስከ ማርቲን ወጆዋን
የስዊድን ዜግነት ያለው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅ አስመራ ውስጥ ከተሰወረ አስር ዓመት አልፎታል። እ.አ.አ በ2011 “ሰቲት” የተባለችውን ጋዜጣ ማዘጋጀት እንደጀመረ ከሌሎች ሰዎች ጋራ ከታፈነ ወዲህ የት እንዳለ፣ ይሙት ይኑር እንኳን አይታወቅም። ስዊድን ይህን ዜጋዋን ለማስፈታት ያልሞከረችው ነገር አልነበረም። ውጤቱ ግን ዳዊትን ከእስር የሚያስፈታ አልሆነም። በተቃራኒው ዜናው እንኳን ከአስመራ ጎዳናዎች ጠፍቷል። ስውዲን ውስጥ ግን ስለ ዳዊት ያልሰማ ስዊድናዊ ማግኘት ያስቸግራል።
ዳዊትን (እነርሱ ይስሐቅ እያሉ ነው የሚጠሩት) ለማስፈታት ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ስዊድናያን የሞያ አጋሮቹ እና ፖለቲከኞቹ ብዙ ሞክረዋል። ኢሳይያስ በመጨረሻ የሰጡት መልስ “ምን አገባችሁ ወይም አላየነውም” የሚል አይነት አናድጅ መልስ ሆናባቸዋል። በምትኩ ዓመታት በተቆጠሩ መጠን ኢሳይያስ ጫናውን ወደ ስዊድናውያኑ ለማዞር ሁሉ ሞክረዋል። በቅርቡ የዳዊት ባለቤት እና የቅርብ ቤተሰቦቹ የስዊድን ሚዲና እና መንግሥት ቢቻል ስለ ዳዊት ምንም እንዳይል ይህም ካልሆነ የቤተሰቡን ስም እንዳያነሱ ጠይቀዋል። የዚህ መነሻ የኢሳይያስ መንግሥት በዳዊት ቤተሰቦች ላይ የፈጠሩት ጫና ውጤት ተደርጎ ታይቷል።
ይህ ተሞክሮ በታሪክ፣ በባህልና በአመራር ከኢሳይያስ ጋራ የሚመሳሰሉት የኢትዮጵያው መሪ በቀላሉ እልህ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል የስጋት ስሜት የፈጠረባቸው ሰዎች ገጥመውኛል። “የጸጥታ ዲፕሎማሲው” አንዱ መነሻም ይህ ሊሆን ይችላል። አቶ መለስ እነማርቲንን ለሌሎች ጋዜጠኞች መቀጣጫ ብቻ ሳይሆን ለውጭ መንግሥታትም የጭካኔያቸውን ልክ ማሳያ አድርገው እንዳይጠቀሙባቸው ያለው ስጋት ተጨባጭ ነው። ስለነማርቲን ፍርድ ባነሱ ቁጥር ቀድሞ የሚመጣው የዳዊት ጥላ ነው።
ጭው የሚያደርግ ዜና
የነማርቲን በሽብር ወንጀል መከሰስ የፈጠረው ድንጋጤ ከስድስት ወር በኋላ ወደ መጨረሻ ጡዘቱ የደረሰው ተከሳሾቹ “ጥፋተኛ” በተባሉበት ቀን ነው(ዲሴምበር 21, 2011)።
ይህ ውሳኔ በተከሳሾቹ አገር በስዊድን ሲሰማ ከጠዋጡ 3፡00 ገደማ ነበር። ጋዜጠኞቹ ከተያዙ ጀምሮ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርባቸው የቆዩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬድሪክ ሬንፌልድት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ላለፉት ወራት እንዳደረጉት በዚህ ቀን በዝምታ ማለፍ አልቻሉም። ቀድመው ድምጻቸውን ያሰሙትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። በአጭር መግለጫቸውም ፍርዱ በጣም አስደንጋጭ መሆኑን እና በከፍተኛ ደረጃ እንደሚከታተሉት፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎችም ጋራ እንደሚነጋገሩበት፤ መንግሥታቸው ተከሳሾቹ በጋዜጠኝነት ተልእኮ ላይ እንደነበሩ ብቻ እንደሚያምን፤ በቶሎ መፈታት እንደሚገባቸው አስታውቀዋል። ይህም እስከዚያን እለት ከተናገሩት ሁሉ ጠንካራው ተብሎ ተመዝግቦላቸዋል። ለአቶ መለስ ስልክ ሳይደውሉ እንዳልቀረም አንደኛው ጋዜጣ ጽፏል፤ የአዲስ አበባ ኔትወርክ ጥሪ ከተቀበለ።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካርል ቢልድት የትችት ናዳ ሲያውርዱባቸው በሰነበቱት ጋዜጠኞች ፊት ለመቅረብ ረዘም ያለ ሰዓት ዝግጅት አስፈልጓቸዋል። ከሰዐት በኋላ ድንገት የጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ የብዙዎቹን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መቋረጥ ያስከተለ ነበር፤ ግን አጭር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ያሉትን በላሌ ቋንቋ ከመድገም አላለፉም፤ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ያሉት ሲጨመቅ “ነገሩን በከፍተኛ ደረጃ እንከታተለዋለን፤ ሁሉንም ሙከራዎች እናደርጋልን።” ነው።
በዕለቱ አመሻሽ ላይ እና በማግሱት የወጡት ሁሉም ጋዜጦች ስለዚሁ ፍርድ ጽፈዋል። የቴሌቪዢን እና የሬዲዮ ጣቢያዎቹም ዋና ርእሰ ጉዳያቸው ይኸው ብይን ነበር። ከረር ያላ አቋም ካንጸባረቁት ታዋቂዎቹ ጋዜጦች አንዱ የአገሪቱ ጥልቁ ዕለታዊ ጋዜጣ “አፍቶንብሎዴት” ነው። ጋዜጣው በማግስቱ ባወጣው እትሙ “የኢትዮጵያውን አምባገነን በግልጽ ቋንቋ አናግሩት” (Tala klarspråk med diktaturens Etiopien) ሲል ጽፏል። ጋዜጣው አክሎም “በኢትዮጵያ የፍርድ ቤት ነጻነት የለም፤ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ የሕግ አይደለም። አገዛዙ የራሱን እና የነዳጁ ኩባንያዎቹን ጥቅም ለማስጠበቅ ሌሎች ጋዜጠኞች ስለአካባቢው እንዳይዘግቡ ያስፈራራቸዋል። ወንጀሉ በኦጋዴን ምን እንደሚካሔድ ለዓለም ለማሳወቅ መፈለጋቸው ነው።” ሲል ነገሩን ከፍርድ ቤት አውጥቶ ወደ ፖለቲካ አደባባይ ከቶታል። “ኤክስፕረሰን” በበኩሉ አንድ የጋዜጠኞቹን ጠበቃ በመጥቀስ “እጅግ አስገራሚ/አስደንጋጭ ውሳኔ” በሚል ርእስ ዘገባውን አስነብቧል። በሌሎች ጋዜጦችም የስዊድን መንግሥት ጉዳዩን “በጸጥታ ዲፕሎማሲ” ለመያዝ የመረጠው መንገድ ለውጥ አለማምጣቱን በማስታወስ ካርል ስልጣን እንዲለቁ ጥያቄ ያቀረቡ ጽሑፎች ተነበዋል።
እነአቶ መለስ በትግል ሜዳ በነበሩበት ዘመን ወደሚቆጣጠሩት አካባቢ አስርገው ያስገቡት ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ቤንግት ኒልሶን መለሰን “የማኪያቬሊ ልዑል” ብሏቸዋል። “ኢትዮጵያ በአንድ ፓርቲ የምትገዛ አገር ነች፤ ፓርቲው ደግሞ በመለስ ዜናዊ ቁጥጥር ስር ነው። እርሱ ፖለቲካውን የሚመራው በደንበኛ የማኪያቬሊ ስልት ነው። ውረር – ከፋፍል፣ ሸልም- ቅጣ በሚል መርህ። እርሱ እንደ (ማኪያቬሊ) ልዑል ነው። ሁሉም እንዲንበረከኩለት ይፈልጋል። ጋዜጠኞቹም በፊቱ ይቅርታን ከጠየቁት በይቅርታ የእስር ዘመናቸውን ሊያሳጥርላቸው ይችላል።”
የጋዜጠኞች ማኅበራትም በየአቅጣጫው ድምጻቸውን ማሰማት ከጀመሩ ሰንብተዋል። እነማርቲን ከታሰሩ ጀምሮ ሰልፍ በማድረግ፣ የውይይት እና የፊልም ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ በየሚዲያው በመጻፍ ወዘተ ጉዳዩን ሲከታተሉ ቆይተዋል። ይህ ጋዜጠኞች ሲሳደዱና ሲታሰሩ ተቃውሞን መግለጽ የማይቻልበት አገር አይደለም፤ እዚያ ስለነእስክንድር ሰልፍ መውጣት ቢከለከልም እዚህ እንኳን ስለነማርቲን ስለርእዮትና ስለነውብሸትም ጭምር ሐሳብን በሰልፍ መግለጽ ይቻላል። እዚህ ይህ መብት ሊከለከል እንደሚቻል ሁሉ ሳይረሱት አይቀሩም። በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እነእስክንድር በታሰሩ ሰሞን ጋዜጠኞችና ሌሎች አንዷለምን የመሳሰሉ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ ተሰልፈዋል። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እና ዓርብ ዕለት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በነማርቲን ላይ የተወሰነውን ቅጣት ተቃውመው ድምጻቸውን አሰምተዋል።
አወዛጋቢው ካርል ቢልድት በበኩላቸው ጋዜጠኞቹ የ11 ዓመት እስራት በተፈረደባቸው ቀን ከቤተሰባቸው ጋራ “ወደ ዓመታዊ እረፍታቸው” ሔደዋል። “ካሰብኩትና ከተዘጋጀሁበት እጅግ ስለቆየሁ ልቀር አልችልም። ሁሉንም ነገር ግን አስተካክያለሁ” ብለዋል በግል ብሎጋቸው ላይ። በዚሁ ቀን ምክትላቸው ለነቢቢሲ መግለጫ ሲሰጡ የሰማችሁትም ለዚህ ነው። እሳቸው ወደ እረፍት፣ እነማርቲን ወደ ቃሊት ወርደዋል። ሁለቱም መመለሳቸው አይቀርም።
የተጣለው ጆከር
በጨዋ አነጋገር መለስ በሽብርተኝነት ጉዳይ የፖለቲካ ቁማር እየተጫወቱ ነው። ቁማሩ አገር ውስጥ ካሉት የፖለቲካ ኀይሎች ጋራ ብቻ አይደለም፤ በኢትዮጵያን ፖለቲካ በማንኛውም መንገድ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል ከሚባሉ የውጭ ኀይሎች ጋራም ጭምር ሆኗል። ብዙዎች ግን አሁንም መለስ ከዚህ ቁማር ምን እና እንዴት እንደሚያተርፉ እየጠየቁ ነው።
የሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች የሽብርተኝነት ክስ ኦጋዴንን እና ኦብነግን በብዙ ጋዜጠኞች የማስታወሻ ደብተር የተጻፈ ስም አድርጎታል።፡ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው። ድሮም “ለነጻነት” ለሚታገሉ አናሳ ቡድኖች ስስ ልብ ያላቸው የስካንዴኒቪያን የፖለቲካ ተቋማት ከቀዛቃዛው ጦርነት ማክተም ጋራ አቋማቸው ቢለሳለስም ጥላው ግን ፈጽሞ አለቀቃቸውም። ይህ ለኦብነግ እና ለሌሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ይቀሰቅሳቸው ይሆን? ባለፈው የረዱዋቸው “የነጻነት ታጋዮች” “ጨቋኝ አምባገነን” ሆነው መውጣታቸው ምን ትምህርት ሰጥቷቸው ይሆን? እነዚህን ጥያቄዎች ለማሰብና ለማብራራት ስዊድናውያን ጥቂት ጊዜ ይፈልጋሉ።
በኦብነግ በኩል ግን ዜናው “በረከተ መርገም” ነው። እዚህ ያነጋገርኳቸው የኦብነግ አባላት ፊት ለፊት ባይናገሩትም በጋዜጠኞቹ መያዝ ድርጅታቸው እንዳልከሰረ ይምናሉ። “በሁሉቱም መንገድ ማትረፋችን አይቀርም ነበር” ነው ሒሳቡ። ጋዜጠኞቹ ተሳክቶላቸው ዘገባቸውን ይዘው ቢወጡ በሆነ መንገድ መለስን የሚያጋልጥ እንደሚሆን ጥርጥር እንዳልነበረው አንድ የኦብነግ የወጣቶች ማኅበር መሪ አጫውቶኛል። ብዙ ተመልካቾች ኦብነግ ጋዜጠኞችን ለመርዳት የሚያነሳሳ ጠንካራና ምክንያታዊ (ሌጂቲሜት) ፍላጎት እንዳለው ይምናሉ። አሁን ጋዜጠኞቹ መያዛቸውም ቢሆን በተዘዋዋሪ የሚናገረው ኦጋዴን ውስጥ “ዓለም ሊሰማው የማይገባ” ነገር መኖሩን ይመስላል። እዚህ የሚገኙ የኦብነግ አባላትና ደጋፊዎች ከስዊድናውያን ጋዜጠኞች ጋራ በተያያዙ መድረኮች ሁሉ ይገናሉ፤ ኢትዮጵያውያን በሚያደርጓቸው ሰልፎች ላይ ጭምር ተገኝተው አጋርነታቸውን አሰምተዋል። ስለኦብነግ ከዚህ በላይ ወደ ዝርዝር መግባት የፍትሕን አዘጋጆ “በሽብርተኝነት” ሊያስከስስ በሚችልባት ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እንዲከበር ድምጻቸውን ሲያሰሙ ተመልክቻለሁ።
የስዊድናውያኑ ፍርድ የአቶ መለስ መንግሥት የሚያደርሰውን የፖለቲካ ጭቆና በተለይም ደግሞ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማፈን የሚሔደውን ርቀት ለማስተባበል በማይመች መንገድ ለዓለም ያሳወቀ ሆኗል። ምናልባትም ከዚህ በኋላ ምእራባውያን መለስን ለማነጋገር የሲፒጄን ሪፖርት መጥቀስ አያስፈልጋቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ስሱ የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን አፈና ዓለም የዚህን ያህል ተረድቶት አያውቅም ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ መልኩ “የጸረ ሽብር” ሕጉ ኢላማ የሆኑት “ግንቦት 7” እና “ኦነግ” የትኩረቱ ተጠቃሚዎች ናቸው፤ ከተጠቀሙበት።
መለስ ይህን ቁማር ሲጫወቱ ያላቸው ማስያዣ ብዙ አይደለም፤ ግን ቢያንስ ለጊዜው አስተማማኝ ይመስላል። ለአገር ውስጡ ቁማር መተማመኛቸው እንደፈለጉ የሚያሾሩት የጦር ሠራዊት ነው። አብዛኛው ተቃዋሚ “ፍርድ ቤት” እና “ፖሊስ” በሚባሉት ማሽኖች በቁጥጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ ናቸው፤ ወይም ከዚህ እንዲያልፉ ጊዜ አይሰጣቸውም። ከዚህ ካለፈም የቁርጥ ቀን መጥቶ ታማኝነቱ ያልተረጋገጠው የጦር ሠራዊት ብቸኛ ማስያዣቸው ነው። ቢያንስ በስጋ ጭምር የሚዛመዷቸው ብዙዎቹ የጦሩ መሪዎች እስከመጨረሻው ከመለስ ጋር ይዘልቃሉ?
ለውጪው ቁማር ብቸኛዋና መተኪያ የሌላት መከላከያቸው ሶማልያ ናት። ሶማልያ እስካልተረጋጋች ድረስ መለስ ዋናው የአሜሪካ አጋር ሆነው የመቆየት እድል አላቸው። ስለዚህ ሶማልያ እንዳትረጋጋ “እየጸለዩና” እየሠሩ መቆየት ይበቃቸው ይሆናል። የአገር ውስጥ ፖለቲካው ገንፍሎ እስካልወጣ ድረስ ዋነኛ ሸሪኮቻቸው አሜሪካና እንግሊዝ ትተዋቸው እንደማይሔዱ ይገምታሉ። የቀረው ጸሎት “እውር ቻይናን እዚህ ያደረሰ፣ እኛንም አይተወንም” የሚል ነው። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደነገሩን ከሆነ መለስ በልጅነታቸውም ቢሆን የካርታ ጨዋታው የሚያሸንፉበት እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆኑ ጨዋታውን አይቀጥሉም። በዚህኛው የፖለቲካ ቁማር እርግጠኛ ናቸው ወይስ የደነገጠ ቁማርተኛ ናቸው? ጆከር ጥለው ሊያሸንፉ? የተጣለው ጆከር ማነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ።
Mesfin,
It is an eye opening analyses you made in this article. I think it would have been and still can be translated in to English so as to address the global audience so that our depressing cry would be heard!
Thanks for your great contribution and keep enlighetening us with your analyses as usual.
God bless you!!
In our today society terrorism is something very delicate, I won’t take at face value what all you have said about terrorism in Ethiopia.
Of course the overly broad provision of the current anti terrorism proclamation in Ethiopia takes the tendency of criminalizing the exercise of freedom expression and these waves of arrest and prosecution constitutes an assault to all freedom loving citizens of Ethiopia.
But the bottom line is Ethiopia surrounded with clouds of Terrorism danger, every citizen has an obligation to play a part in prevention of it, of course we need really carefully crafted proclamation of anti terrorism law.