የአድዋ ልጆች፤ ምኒልክ፣ መለስ እና እኔ
የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አድዋ ምኒልክን ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስንም ወልዳለች። ልጅነታቸው ግን ለየቅል ነው። ምኒልክ ለአድዋ የመንፈስ ልጅ ናቸው፤ መለስ የደምና የአጥንት ልጅ ናቸው። የደምና የአጥንት ልጆች የመንፈስ ልጅነትንም ደርበው የማግኘት እድል አላቸው፤ ሁልጊዜም ግን ላይሳካ ይችላል። ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን አይቶ ድርብ ልጅነቱን ማድነቅ ነው፤ መለስን ተመልክቶ የደምና የአጥነት ሆኖ መቅረቱን መታዘብ ነው። መካ የተወልዶ ሁሉ በነብዩ መንፈስ እንደማይቃኝ፣ የቤተልሔሙ ልጅ ሁሉ በክርስቶስ መንገድ እንደማይሔድ መሆኑ ነው።
መጀመሪያ አድዋ ነበረች። ከአድዋም ጋራ የአድዋ የነጻነት መንፈስ ነበር። አድዋ ይሁን አለች። የአድዋ ድል ሆነም። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአድዋ የነጻነት መንፈስ በምድሩ ሁሉ ላይ ሆነ። መንፈሱ ጠፍቶም አያውቅም፤ አይጠፋምም።
ምኒልክ አድዋ ባይወለዱም የአድዋ ልጅ ናቸው። አድዋን ያህል የምኒልክን ፖለቲካም ሆነ በታሪክ ውስጥ ያላቸውን ሚና የወሰነ ቦታ የለም ማለት ከጥናት የቀደመ ድምዳሜ ሆኖ አይቀርም። እርሳቸውም በተራቸው በአድዋ የአገራቸውን እና የአፍሪካን ታሪክ ለውጠዋል፤ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነጻነት ተምሳሌት መሆኗን በድጋሚ አሳይተዋል። “የፖለቲካ መልክአ ምድር” (Political geography) ተመራማሪዎች የምኒልክን ፖለቲካ ከመልክአ ምድር አኳያ ስለማጥናቸው ወይም ይህንኑ ስለማሳተማቸው አልሰማሁም። ባይሆን በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ጂኦግራፊ መምህራችን ስለአዲስ አበባ የፖለቲካ መልክአ ምድር ሲነግሩን ከተማዋን በእንግዳ ዓይን ለማየት ካለማወቅ እንቅልፋችን አባንነውን ነበር። ለካስ በምኒልክ ቤተ መንግሥት ዙሪያ አዲስ አበባ ለየመኳንንቶቹ ስትመራ ቅርበቱና ርቀቱ ብቻ ሳይሆን የቦታው ከፍታነትና ረባዳነት ሳይቀር የቤተ መንግሥቱ ፖለቲካ ነጸብራው ኖሯል።
ጦር በአዝማቹ፣ አገር በመሪው ይጠራ ሆኖ እንጂ አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል መሆኑ ለጠላትም ለወዳጅም የተረዳ ነው። እምዬ ምኒልክም በዚህ አይወቀሱም፣ አድዋን “የእኔ ብቻ” ብለው አያውቁምና። ቀድሞውንስ የጦርነቱን አዋጅ ሲያውጁ መቼ ቋንቋ ለይተው፣ ዘር ቆጥረው ተጣሩና። የወቅቱ አቅማቸው ብቻ ሳይሆን የአድዋም መንፈስ ይህን አይፈቅድላቸውም። እንኳንም አልፈቀደላቸው።
ለአድዋ ዘመቻ ቤቱን ጥሎ ከየአገሩ ጥግ የተሰበሰበው የአገሬ ሰው ምንኛ ይደንቀው?! በጦርነቱ ብዙ የሚያስደንቅ ነገር ሆኗልና። ኀዘኑም ድሉም ያስደንቃል። የወራሪውን የግፍ ጥቃት በአካል የተቀበሉት የአድዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ምንኛ ጠንካሮች ናቸው! የእነርሱ የነጻነት መንፈስ ባይኖር የምኒልክ ጦር ጀግንነቱን የሚለኩስበት የተዳፈነ ረመጠ ባላገኘ ነበርና። ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አንሥቶ እስከ ስም አልባው የአድዋ አጥቢያ ጀግና፣ የድሉን ብርሃን ሳታዩ ላለፋችሁትም ሆነ በድሉ ደስታ ለተጠመቃችሁ፣ እኛን ልጆቻችሁን እና መላውን የሰው ልጅ በአድዋ የነጻነት መንፈስ አጥምቃችሁናልና ተመስገኑ፣ ክበሩልን። አራት ነጥብ። ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ አንድም የታሪክ ምርምር ጣጣ ነው፤ አለዚያም ታሪክን የጎሳ ፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረግ የአድዋን መንፈስ የካደ ትርኪሚርኪ ነው። (ትርኪሚርኪ የሚለው ቃል በስንት ጊዜ ትዝ አለኝ። የቃሉን ምንጭ ላውቀው አልቻልኩም። የጽሑፍ ቋንቋ ባይሆንም ምንጩን ለማፈላለግ አጋጣሚውን ተጠቀምኩበት። እንደ “ፍሬ ከርስኪ” ወይም “ስንክሳር” አላዋቂ በተሳሳተ ትርጉም የተከለው ቃል ይሆን?)
የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አድዋ ምኒልክን ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስንም ወልዳለች። ልጅነታቸው ግን ለየቅል ነው። ምኒልክ ለአድዋ የመንፈስ ልጅ ናቸው፤ መለስ የደምና የአጥንት ልጅ ናቸው። የደምና የአጥንት ልጆች የመንፈስ ልጅነትንም ደርበው የማግኘት እድል አላቸው፤ ሁልጊዜም ግን ላይሳካ ይችላል። ገብረ ሕይወት ባይከዳኝን አይቶ ድርብ ልጅነቱን ማድነቅ ነው፤ መለስን ተመልክቶ የደምና የአጥነት ሆኖ መቅረቱን መታዘብ ነው። መካ የተወልዶ ሁሉ በነብዩ መንፈስ እንደማይቃኝ፣ የቤተልሔሙ ልጅ ሁሉ በክርስቶስ መንገድ እንደማይሔድ መሆኑ ነው።
ምኒልክን በአቶ መለስ ዘመን መመዘኛ መገምገም እንደማይገባ ሁሉ መለስንም እንዲሁ በምኒልክ ዘመን መመዘን አይገባም። ጀግና እንደ አገሩ ብቻ ሳይሆን እንደ ዘመኑም ነውና። መለስ በአድዋ ጦርነት ዘመን መሪ ቢሆኑ ኖሮ ብሎ መወያየት ብዙ ፋይዳ የለውም፤ ባይሆን ጥሩ ልቦለድ ወይም ቴአትር ይወጣው ይሆናል። ምኒልክ ከደርግ ጋራ ተዋግተው በአቶ መለስ ቦታ ቢቀመጡ ኖሮ ማለትም እንደዚያው ነው። ማነጻጸር የሚቻለውና የሚገባው መሪዎቹ በየዘመናቸው ለአድዋ የአገራዊ ነጻነትና የልእልና መንፈስ ታማኝ ሆነው መገኘታቸውን ይመስለኛል።
አቶ መለስን በዚህ መንፈስ ስመዝናቸው መጻጉእ ሆነው ይታዩኛል፤ የጎበጡ፣ የታመሙ፣ የጫጩ። በምኒልክ መስፈርት መዝኑኝ ብለው በዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሱትን ጭቆና እንድናልፍላቸው ካለፈለጉ በቀር፣ አቶ መለስ ነጻነትን በጣም የሚፈሩና የሚሸሹ ሆነው ይታያሉ። በምኒልክ ዘመን ቀዳሚው ነጻነት የአገር ነጻነት ነበር። የምኒልክ የአድዋ መንፈስ ይህ አገራዊ ነጻነት ዳግም እንዳይደፈር አድርጎ አጽንቶልናል። የአቶ መለስ ዘመን የአድዋ የነጻነት መንፈስ በዋናነት ከውጭ ወራሪ መከላከልን ሳይሆን ከውስጥ ጨቋኝ ነጻ መሆንን የሚጠይቅ ነበር። ለዚህም ነበር እነአቶ መለስ ደርግን ጥለው ወደ ሥልጣን ሲመጡ እኔና መሰሎቼ በተስፋ የተቀበልናቸው። ተስፋው እኛ የፈጠርነው አዲስ ተስፋ አይደለም፤ የአድዋ የነጻነት መንፈስ ልጆች ሁሉ በዚህ ዘመን ሲጠብቁት የነበረ ተስፋ ነው። ዜጎች በፖለቲካ አቋማቸው፣ በብሔረሰባዊ ማንነታቸው፣ በሃይማኖታቸው ወዘተ. የማይዋርዱበት፤ ኢትዮጵያውያን የሰው ልጅ እድገት ያበራው መብት ሁሉ ባለቤቶች የሚሆኑበት….ከቀድሞው የቀጠለ አዲስ የዘመኑ አድዋ የነጻነት መንፈስ ነው። አቶ መለስና ጓዶቻቸው ግን ይህን የአድዋን የነጻነት መንፈስ ካዱት፤ በተግባር አዋረዱት።
ዛሬ ዛሬ መዝሙሩ “መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ” ማለት ሆኗል። የአድዋ የነጻነት መንፈስ ይህን ሲሰማ መሸማቀቁ አይቀርም። እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ምኒልክስ ጣልያንን አስገብተው መንገድና ፋብሪካ ማስገንባት ይችሉ አልነበረምን? ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው የምኒልክ ኢትዮጵያ ሀብታም አገር ሆና ነበርን? ከድህነት መላቀቅን የሚጠላም የሚቃወምም የለም። የአድዋ የነጻነት መንፈስም በድህነት መኖራችንን አይቀበልም። ነገር ግን ከቁሳዊ ሰቀቀን መላቀቅ የዘመናችን የአድዋ የነጻነት መንፈስ ብቸኛና በቂ ግብ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የዜጎች መብታና ነጻነት የሚታፈንበትን፣ መድሎዎና ጭቆና ተቋማዊና ሕጋዊ ቅርጹን ለውጦ የሚቀጥልበትን አገዛዝ የአድዋ የነጻነት መንፈስ አጥብቃ ትጸየፈዋለች።
መለስ የአድዋ የደምና የአጥንት ብቻ ሳይሆን የመንፈስም ልጅ መሆን ከፈለጉ ከመንፈሱ ጋራ መታረቅ ይኖርባቸዋል። የአድዋ የነጻነት መንፈስ ቸር ነው፣ ታጋሽ ነው፣ ሩህሩህ ነው፣ ታራቂ ነው። ታራቂዎቹን አያዋርድም፣ በታራቂዎቹ ላይ አያቅራራም። ክቡርነትዎ እና ወዳጆችዎ ሁሉ ወደ አድዋ እንዲመለሱ በዕለተ አድዋ ይጋበዛሉ። አድዋ እጇን ዘርግታ ትጠብቃችኋለች፤ የአድዋ ልጆች ወደ አድዋ ተመለሱ። የአድዋ የአጥንትና የስጋ ብቻ ሳይሆን የመንፈስም ልጆች ለሆናችሁት የአድዋ ልጆች፣ እኔም ወንድማችሁ ነኝ የአድዋ ልጅ። የአድዋ ልጆች ነን!
——–
ማስታወሻ፤ የሚቻል ሆኖ ሳለ ይህን ጽሑፍ የጂጂን “አድዋ” ሳይከፍቱ ማንበብ የተከለከለ ነው።
No comments yet... Be the first to leave a reply!