"; _gaq.push(['_trackPageview']);(function() { var ga = document.createElement('script'); ga.type = 'text/javascript'; ga.async = true; ga.src = ('https:' == document.location.protocol ? 'https://ssl' : 'http://www') + '.google-analytics.com/ga.js'; var s = document.getElementsByTagName('script')[0]; s.parentNode.insertBefore(ga, s); })();

አገቱኒ በመሥፍን መንፈሳዊ

ፕሮፌሰር ምን ማለታቸው እንደኾነ ባያብራሩትም የመጽሐፋቸው ርዕስ ያደረጉትን ቃል ከመዝሙረ ዳዊት የወሰዱት ይመስላል። “አገቱኒ” የሚለው የግእዝ ቃል “ከበቡኝ” የሚል ትርጉም ሲኖረው፤ በቤተክርስቲያን ሥርዓት የስቅለት ዕለት ከሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል አንዱ ነው። የመዝሙሩም አንዱ አርኬ “አገቱኒ ከለባት ብዙኃት” ይላል ትርጉሙም “ብዙ ውሾች ከበቡኝ” ተብሎ በ1953 ዓም የአማርኛ ትርጉም ላይ ተተርጉሟል። ይህም መዝሙር የኢየሱስ ክርስቶስን የሞት ጣዕር እንደሚገልጽ በጥንታዊው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይታመናል። ፕሮፌሰርን የከበቧቸው እነማን ናቸው? በርዕሱ ሊያስተላልፉት የፈለጉት መልእክት ምንድነው? የሚሉት አይቀሬ ጥያቄዎች በፕሮፌሰር አልተመለሱም።

“ለምን እንደኾነ እንጃ ‘ማፈር ደኅና ሰንብት’ የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ “  ይህች ዐረፍተ ነገር ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አንደበት የፈለቀችው በምርጫ 97 የምርጫ ክርክር ወቅት ነበር።  “ገዢው ፓርቲ የአፈጻጸም ብቻ ሳይኾን የአሰማም ችግርም አለበት”፣ “የአገዛዝ መሠረቱ ሕገ አራዊት ነው”።  የምርጫ 97 የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ሲነሳ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳይረሱ ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚሁ ንግግሮቻቸው እየተመነዘሩም ለውዝግብ ከዚያም አልፈው ለእስር ዳርገዋቸዋል። ዛሬም ፕሮፌሰሩ ምን ይናገሩ ይኾን ተብለው የሚጠበቁ ሰው ናቸው። “አገቱኒ ተምረን ወጣን” የተሰኘውም ሥራቸው በዚሁ ጉጉት የሚነበብ መጽሐፍ ነው።

ውስጥ 12 ምዕራፎችን ይዛለች። ሁለተኛውም የመጽሐፉ ክፍል ጸሐፊው በተለያዩ ጊዜያት በጋዜጦች እና በመጽሔቶች ያሳተሟቸው አምሥት ጽሑፎች ተካተውበታል። ከእነዚህም መካከል ፕሮፌሰር ራሳቸውን ከቅንጅት ምክር ቤት ሲያገሉ ለምክር ቤቱ የጻፉት ደብዳቤም በአባሪነት ይገኝበታል።

ፕሮፌሰር ምን ማለታቸው እንደኾነ ባያብራሩትም የመጽሐፋቸው ርዕስ ያደረጉትን ቃል ከመዝሙረ ዳዊት የወሰዱት ይመስላል። “አገቱኒ” የሚለው የግእዝ ቃል “ከበቡኝ” የሚል ትርጉም ሲኖረው፤ በቤተክርስቲያን ሥርዓት የስቅለት ዕለት ከሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል አንዱ ነው። የመዝሙሩም አንዱ አርኬ “አገቱኒ ከለባት ብዙኃት” ይላል ትርጉሙም “ብዙ ውሾች ከበቡኝ” ተብሎ በ1953 ዓም የአማርኛ ትርጉም ላይ ተተርጉሟል። ይህም መዝሙር የኢየሱስ ክርስቶስን የሞት ጣዕር እንደሚገልጽ በጥንታዊው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይታመናል። ፕሮፌሰርን የከበቧቸው እነማን ናቸው? በርዕሱ ሊያስተላልፉት የፈለጉት መልእክት ምንድነው? የሚሉት አይቀሬ ጥያቄዎች በፕሮፌሰር አልተመለሱም። አንባቢ የራሱን ግምት እንዲወስድ የተተወም ይመስላል።

የፕሮፌሰር መሥፍን “አገቱኒ” አብዛኛው ክፍል ያንጸባረቀው ደራሲው ስለሥልጣን ያላቸውን አመለካከት ነው። “እንደመቅድም፡ እኔ እና ሥልጣን” ከሚለው መግቢያቸው ጀምሮ ፕሮፌሰር ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከሥልጣን ጋር የነበራቸውን ተጋድሎ አሳይተዋል። በልጅነት የቄስ ትምህርት ቤትን ሥልጣን ሳይቀር ከሥልጣን ትዝታቸው አንዱ አድርገው ይጠቅሱታል።

“አስተማሪዬ (አለቃ ታምራት የሚባሉ ጎንደሬ ነበሩ) ከአለቆቹ አንዱ አደረጉኝ፤ በመጀመሪያ ስልጣን የቀመስኩት በዚህ ነው፤ ጣመኝ፤ አንድ ተማሪ ‘ጸ’ ስለው ‘ሰ’ ያለ እንደሆነ ጆሮው እስቲቀላ ማሸት አንዱ የሥልጣን መገለጫ ነበረ። በዚያ ላይ አለንጋ ወይም አርጩሜ አለ፤ የመጀመሪያ ደረጃ በሥልጣን የመባለግ ትምህርት ነበር!” ይላሉ ፕሮፌሰር።

በሥራ ዓለም በነበሩበት ሁሉ ያጋጠማቸውን ከሥልጣን ጋር መፋጠጥም ከአንድ አስፈሪ ጥፍራም ጭራቅ ጋር ግብ ግብ የመግጠም ያህል ይተርኩታል። “ወርቅነህ ገበየሁ ያመጣብኝ ጣጣ” ይሉታል ከካርታ ሥራ ድርጅት ወደ ጸጥታ መሥሪያ ቤት መዛወራቸውን ሲገልጹ:፡ ለቀረበላቸውም የሹመት ጥያቄም ምላሻቸው “የምትፈልገው ሬሳዬን ከሆነ አሁኑኑ አድርገው” ሲሉ ተቃውሟቸውን ያቀርባሉ። ሌላም የዚሁ አስፈሪ ሥልጣን ትዝታ አላቸው በዩነቨርሲቲ ኮሌጅ የክፍል ኃላፊ የኾኑት “በመከራ ሰው ጠፍቶ” እንደነበረ ያስታውሳሉ። ያንንም ቢኾን ግን ፕሮፌሰር “በዲሞክራሲያዊ መንገድ” “እንደተገላገሉት” ይገልጻሉ።

ራስ አንዳርጋቸው የአገር ግዛት ሚኒስቴር በነበሩ ጊዜ ረዳት ወይም ምክትል ሚኒስትራቸው እንዲኾኑ በጠየቋቸው ጊዜ የሰጧቸው ምላሽ እንደሚያሳፍራቸው ይገልጻሉ ፕሮፌሰር “የለም እንጣላለን” ለሥልጣኑ ያላቸውን ፍርሃት ገልጸዋል። ሳይፈልጉትም አንድ ወቅት በቅጣት መልክ “የጊሚራ አውራጃ ገዢ” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የጊምቢ አውራጃ አስተዳዳሪ” መባላቸውን ያስታውሳሉ። መጨረሻውንም ሲገልጹ “ከመጨረሻው ልጅ ካሣ ወልደማርያም መከተልኝ እና አዳነኝ በሁለተኛው እንደካሣ ወልደማርያም የሚመክትልኝ ሳይሆን አሳልፎ የሰጠኝ አክሊሉ ሀብቴ ነበር” ይላሉ።

በመርማሪ ኮሚሲዮን ውስጥ የነበሩበትንም ጊዜ ሲያስታውሱ “በሕይወቴ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች ቅርብ የሆንኩት የመርማሪ ኮሚሲዮን ሊቀመንበር በነበርኩበት አጭር ጊዜ ውስጥ ነው፤ ከማናቸውም ጊዜ ይልቅ ሥልጣን በጥፍሩ ይዞ ሊጎትተኝ የነበረበት ወቅት” እንደነበር ያስታውሳሉ። በማምለጣቸውም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። ከዚያም በኋላ የቀረቡላቸውን ሥልጣን ነክ ጥያቄዎች እንዴት እንደመለሱ በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር መሥፍን ከፍቅረ ሥልጣን በተጨማሪ ፍቅረ ነዋይንም እንዴት እንደሚጠየፉት ይናገራሉ። በአንድ ወቅት በልባቸው በድንገት ተጸንሶ የነበረውን መሬት የመግዛት እና ቤት የመሥራት ምኞት ከሥልጣን የማምለጥን ያህል እንዴት እንዳመለጡት ያስረዳሉ።

መጽሐፉ ጸሐፊው ስለራሳቸው የልጅነት እና የሥራ ሕይወት በመጠኑም ቢኾን የገለጹበት ከመኾኑ ባሻገር፤ በ1997 ዓም ምርጫ ላይም የበኩላቸው ያሉበትን ሰፊ ክፍልም አካቷል። ከምርጫ 97 በፊት በኢትዮጵያ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበሩበት ኹኔታ ምን ይመስል እንደነበረ፣ የቅንጅት መመስረት እና ባህርያቱ፣ የምርጫው ቅስቀሳ እና ምርጫው ከነውጤቱ የነበረበትን ኹኔታ ፕሮፌሰር ዳሰውታል። እርሳቸው እና ሌሎች የቅንጅት አመራር አባላት የታሰሩበትን ሁኔታ እና የፍርድ ሒደቱን አሳዛኝነት አሳይተውበታል። እስረኞቹን የቅንጅት አመራር አባላት እና መንግሥትን ለማስታረቅ ጥረት ያደርጉ የነበሩትን ሽማግሌዎች እንዲሁም የእርቁ ሒደት በይቅርታ መጠየቅ እና ምህረትን በማግኘት ስም የተጠናቀቀበትን ታሪክ በዝርዝር አሳይተዋል። ከመጽሐፉ ይዘቶችም ሁሉ የአንባብያንን ትኩረት ሊስብ የሚችለው ይኸው በፍርድ ቤቱ የነበረውን ኹኔታ እና ሽምግልናውን በጠያቂ (critical) አስተያየት ያዩበት ክፍል ነው።

ለቅንጅት መፍረስ ተጠያቂ የኾነው ማን እንደኾነም ለማሳየት ሞክረዋል። በፕሮፌሰር መሥፍን አስተያየት ለቅንጅት መፍረስ ተጠያቂ የኾኑት ሦስቱ አካላት “የቅንጅት አመራር፣ ሲ አይ ኤ እና ወያኔ/ ኢሕአዴግ” ናቸው። ፕሮፌሰር ለቅንጅት መፍረስ ኢሕአዴግን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ እንደማይቻል ረገጥ አድርገው አስረድተዋል። ገና ከቅንጅቱ መመስረት ጀምሮ በሁለቱ አባል ፓርቲዎች (በኢዴፓ እና መኢአድ) መካከል የነበረውን የቆየ ቁርሾ ለማስታረቅ ይደረግ የነበረውን ጥረት ዳስሰዋል። አባሪ አድርገው የመጽሐፉ አካል ባደረጉት የስንብት ደብዳቤያቸውም ውስጥ ከቅንጅት ምክር ቤት ራሳቸውን ያገለሉበት ምክንያት ይኸው የአቶ ልደቱ እና የኢንጂነር ኀይሉ ሻውል የማይፈታ ቅራኔ መኾኑን ገልጸዋል፤ ችግሩ ካልተፈታም ሊመጣ የሚችለውን ተንብየዋል።

እንደብዙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ትዝታውን እያደነቁ በሚያስታውሱት የሚያዝያ 30 ሰልፍም ላይ የነበረውን አንድ ትዕይንት ይጠቅሳሉ። መራጩ ሕዝብ ለሰላም እና ለለውጥ ያለውን ፍላጎት እያስታወሱ በማወደስ፤ በቅንጅት አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን እና ለመፍረሱም ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚቆጥሩትን “የሥልጣን ጥም” ለማስረዳት ይሞክራሉ። “ብርሃኑ ነጋ አስቀድሞ ወደደቡብ ሄዶ ስለነበረ የሚያዝያ 30ን ሙሉ ተዓምር አላየም፤ ልደቱ አያሌው ዘግይቶ በመምጣቱ እንደሰርገኛ በመኪና ላይ ኾኖ ገባ፤ በዚያ ቀን በመስቀል አደባባይ በመኪና የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ ከየት መነጨ?” ፕሮፌሰር በዚያ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የነበረውን ኹኔታ ከቅንጅት አመራሮች የዕለቱ ተግባር ጋር እያስተያዩ ይጠይቃሉ። በመጨረሻም ይኸው ትዕይንት ለቅንጅት እጣ ፈንታ የነበረውን ንግር ይተረጉማሉ። “የብርሃኑ አለመኖር፣ የልደቱ ለብቻው በመኪና ላይ ኾኖ እጆቹን ማውለብለብ፣ የሌሎቹ በሀይሉ ሻውል ዙሪያ መሰባሰብ የቅንጅትን የወደፊት አኪያሄድ አመላካች ነበሩ።” እነዚህም ሦስት ሰዎች በቅንጅት መፍረስ ውስጥ የነበራቸውንም ድርሻ ችግራቸው ነው ከሚሉት የሥልጣን ጥም ጋር ማስረጃ እየጠቀሱ አሳይተዋል። አቶ ልደቱ አያሌው የነበረባቸው ችግር ከሌሎቹ የተለየ እንዳልነበረም ተናግረዋል። የአቶ ልደቱን የተለየ የሚያደርገው ለቅንጅቱ መፍረስ የመጀመሪያ የኾኑ ርምጃዎችን መውሰዱ ላይ እንደነበረም አስረድተዋል። ከዚህም አልፎ አቶ ልደቱ ቅንጅትን “በምርጫ ቦርድ እና በወያኔ/ኢሕአዴግ ሊያስመቱ የሚችሉ ሐሳቦችን” ደጋግሞ መናገሩን ገልጸዋል።

“ሌላው በፕሮፌሰር መሥፍን መጽሐፍ ውስጥ የሚገለጠው ጠንካራ ተቺነታቸው ነው። ሐሳባቸውን ሲገልጹ እግረመንገዳቸውን የሚያገኙትን አግባብ ያልመሰላቸውን ነገር ሳይሸነቁጡት አያልፉም። ማኅበራዊ ኑሮውን፣የትምህርት ሥርዓቱን፣ ዩኒቨርስቲውን፣ ባለስልጣኖቹን፣ ሸምጋዮቹን፣ የፍርድቤቱን አኪያሄድ፣ መንግስትን ተቃዋሚዎችን… ትችቱም ከባድ ከመኾኑ የተነሳ ጸሐፊው ጠብ ያለሽ በዳቦ ባይ ያስመስላቸዋል። ነገር ግን የትችታቸውን ያህል በጎ ጎንን ለማድነቅ ወደኋላ አለማለታቸው ሲታይ ይህ ግምት ትክክል አለመኾኑ ግልጽ ይኾናል። ኋላ አለማለታቸው ሲታይ ይህ ግምት ትክክል አለመኾኑ ግልጽ ይኾናል። የገዢውንም ፓርቲ መልካም ነገሮች ቢኾን (ጥቂት ቢኾኑም) ያመሰግናሉ።በዚህም የመምህርነታቸው እውነተኝነት ይታይባቸዋል። ቀይ ብዕራቸው የተሳሳተውን ለመንቀፍ እና ያለማውን ለማመስገን ወደኋላ የማይል መስሎ ይታያል። ነቀፋቸውን ለመቀበል ሰሚ ጆሮ የሚያገኙ ባይመስልም። ያም ኾኖ “ይህ ስብእናቸው በሁለት ተቧድኖ ቡጢ በሚቃመሰው አንድነት ውስጥ ያለው ስፍራ ተገቢ ነወይ?” የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለብዙዎች የፕሮፌሰር መሥፍን እንኳን በአንድነት አንጃ ውስጥ ቀርቶ በቅንጅት ውስጥ መግባታቸው አይዋጥላቸውም። ሰውየው ከዚህ ይልቃሉ ብሎ የሚያስባቸው ብዙ ነው።

ፕሮፌሰር መሥፍን በመጽሐፋቸው ውስጥ ማንንም በቋሚ ጠላትነት እንዳልፈረጁ የሚጠቁሙ ፍንጮችን አሳይተዋል። በጠነከረ ትችት ድርጊታቸውን የሚያወግዟቸውን ሰዎች ጭምር ለበጎ ጎናቸው ያላቸውን አድናቆት ሳይገልጹ አያልፉም። በአሁኑ ወቅት ሆድ እና ጀርባ መኾናቸው ከሚታወቀው ኢንጅነር ግዛቸውን ጭምር ባልዋሉበት እንዳይወቅሷቸው ጥንቃቄ ሲያደርጉ ይታያል። ያደረጓቸውን በጎ ነገሮች ጭምር በማስታወስ አድናቆታቸውን ይገልፃሉ። በምርጫው ውስጥ ታይተው ለነበሩት አስገራሚ ውጤቶች የኔ የሚሉትን አስተዋጽዖ ሲናገሩ አይታይም። በተቃራኒው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በተጻራሪነት የሚታዩ ቢኾኑም በወቅቱ ትልቅ ድርሻ የነበራቸውን ሰዎች እያነሱ አድራጎታቸውን ማድነቃቸው አንባቢን ሊያስገርም ይችላል። “የሆነው ሆኖ ሀይሉ ሻውል፣ ብርሃኑ ነጋ እና ልደቱ አያሌው የ1997 የምርጫ ፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትጵዮያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስገርም የጋለ መንፈስ ትጋትና ቆራጥነት የመሩት እና ያንቀሳቀሱት ሰዎች መሆናቸው ጥርጥር የለውም፤ ስኬታማ ሥራቸውን ያገዘው ያደረባቸው የሥልጣን ጥም መሆኑን ስንገነዘብ የሥልጣን ጥምን በጎ ጎን እና አስፈላጊነት እንገነዘባለን።”

በፕሮፌሰር መሥፍን መጽሐፍ ውስጥ ጸሐፊው ስለራሳቸው የነገሩን እጅግ ጥቂት መኾኑ የሚያሳዝነን በነገሩን ጥቂት ነገር ውስጥ ያገኘነውን ብዙ ቁም ነገር መቁጠር ስንጀምር ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው የፕሮፌሰር መሥፍን ስብእና ወደ መንፈሳዊነቱ ያዘነበለ መኾኑ ያለ ብዙ ምርምር የሚገኝ ነገር ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበራቸውን መንታ ተጻራሪ ስብእና አሳይተው የማይፈለገውን “ጠበኝነትን” እንዴት መግራት እንደቻሉ ይገልጻሉ። ስለ ሥልጣንም ይኹን ስለ ፍቅረ ነዋይ ሽሽታቸው እና ለእውነት የመፋለም ጽናታቸው ሁሉ መንፈሳዊ ተጋድሎ እንጂ ሌላ ነገር አይመስልም።

በመጽሐፋቸው ምዕራፍ ሁለት ላይ ፕሮፌሰር “ክፉ ቀን ጥሩ ነው” በሚል ርዕስ የጻፉትን ተመስጧቸውን መጥቀስ እውነታውን ያጎላዋል። ከ97 ምርጫ ማግስት ጀምሮ በቅንጅት መሪዎች እና በሕዝቡ ላይ የነበረውን መከራ ሌላ ገጽታ ለማሳየት የጨለማውን ሌላ ገጽታ ይተነትናሉ። “ክፉ ቀን ጥሩ ነው ያስተዛዝናል፤ ክፉ ቀን ጥሩ ነው ደጋግ ሰዎችን ይቀሰቅስና የግፍን መራራነት እንዲቀንሱት አደርጋል።” ከዚህም ምዕራፍ ውጪ ያሉትን የመጽሐፉን ክፍሎች የጸሐፊውን መንፈሳዊ ስብእና ሳያስቡ ማንበብ አዳጋች ነው። ይህም ዝንባሌያቸው ከልጅነት ጀምሮ አብሯቸው የነበረ መኾኑን የሚያስገነዝበን ፍንጭ በልጅነት ታሪካቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።

አለቃ ታምራት ትምህርት ቤት እንዳለሁ አንድ እሙን የሚባል ጓደኛ ነበረኝ፤ እርሱ እና ሁለት ሌሎች ሆነን የዚህን ዓለም ከንቱነት ስናወራ ቆየን እና እንመንን ብለን ወዲያውኑ ወስነን ቀበናን ተሳግረን ራስ ካሣ ጫካ ገባን፤አውጡን፣ ቀጋውን፣ አጋሙን ስንበላ አመሸንና ጀምበር ቆልቆል ማለት ስትጀምር አንዱ ‘እናቴ ናፈቀችኝ!’ ሲል ወዲያው ሁላችንም ‘እኔም!’ ‘እኔም!’ እያልን ቁልቁለቱን ወርደን በየኔታችን ገባን፤ስለዚህ ለአንድ ቀን ያህል መንኛለሁ!” ፕሮፌሰር ከራስ ካሣ ጫካ በጊዜ ቢወጡም አሁንም ከመናኒነት ሕይወት የወጡ አይመስሉም።

2 Responses to “አገቱኒ በመሥፍን መንፈሳዊ”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

“በማይነጥፍ” ድጎማ የበጀት ጉድለት

በአማካይ በ10 ቢሊዮን ብር የሚጨምር ዓመታዊ በጀት፣ በ10 በመቶ ምጣኔ የሚሰላ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም በ10 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጀት ጉድለት። የ“መንታዊነት” ጠባይ ያላቸው ይመስል ምጣኔያቸው ልዩነት አስተናግዶ አያውቅም። እጅ ለእጅ ተያይዘው ይነጉዳሉ።

የኢኮኖሚ እድገት፤ የበጀት እድገት፤ የበጀት ጉድለት. . . የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተመለከተ የሰኔ ወር ሦስት ፍጹም የማይዘነጉ ጉዳዮችን ያሰማል። ጉዳዮቹ ሸንጎው በወጉ ተወያየባቸውም ወይም በጥድፈት ከክርክር ውጪ አደረጋቸው የኢትዮጵያ ፓርላማን ደጃፍ መርገጣቸው አይቀረም። በአማካይ በ10 ቢሊዮን ብር የሚጨምር ዓመታዊ በጀት፣ በ10 በመቶ ምጣኔ የሚሰላ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም በ10 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጀት ጉድለት። የ“መንታዊነት” ጠባይ ያላቸው ይመስል ምጣኔያቸው  ልዩነት አስተናግዶ አያውቅም። እጅ ለእጅ ተያይዘው ይነጉዳሉ።

በየዓመቱ መጨረሻ የበጀት እና ተያያዠ ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡት የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድም በመንግስት የወጪ ቁጥጥር እና ገቢ አሰባሰቡ ላይ አይዋጣላቸው እንጂ የሦስቱን ኢኮኖሚያዊ ተለዋዋጮች ምጣኔ አዛንፈው አያውቁም። ለአምስት አመታት በጉዳዩ ላይ ተዋጥቶላቸዋል። ባለፈው ሣምንትም የተደመጠው የ2003 ዓ.ም የበጀት ረቂቃቸው 77.2 ቢልዮን ብር ከመድረሱ በስተቀር ሦስቱን ጉዳዮች በተመለከተ አዲስ ተብሎ የሚጠቀስ ነገር አልታየበትም።

ቀጣዩ በጀት አሁን እየተገባደደ ካለው ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር በ19.7 በመቶ ብልጫ የታየበት ነው። በአማካይ ከዓመታዊው አጠቃላይ አገራዊ ምርት (Gross Domestic Product) ከዘጠኝ በመቶ በላይ የማይዘልቀው የካፒታል በጀት በ35.9 ቢልዮን ብር ድርሻ ከፍተኛ ሥፍራ አግኝቷል። ከዚሁ የካፒታል በጀት ውስጥ የመንገዶች ባለስልጣን የአንበሳውን ድርሻ አንስቷል-12 ቢሊዮን ብር።

እንደተለመደው በጀቱ ጉድለት አላጣውም። ከውጭም ከአገር ውስጥም ሊሰበስብ የታቀደው የገንዘብ መጠን ለወጪ ከታቀደው ጋር የተመጣጠነ አይደለም። ከ77.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ መንግስት ከተለያዩ ምንጮች አገኘዋለሁ ብሎ የገመተው 64.06 ቢሊዮን ብር ነው። ቀሪው ኢኮኖሚው የሚያስተናገደው የበጀት ጉድለት ይኾናል ማለት ነው። ጉድለቱ ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሚባል ነው፤ የአገሪቱን አማካይ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት 3.2 በመቶ ያህል ድርሻ ይይዛል። የበጀት ጉድለቱም ኾነ ይሟላል ተብሎ የታሰብው በጀት አሁንም ቢኾን በከፍተኛ ኹኔታ የውጭውን ዓለም ርዳታ እና የብድር ይኹኝታ የሚሻ ነው። ከ20 ቢሊዮን ብር ያለነሰ ከውጭ አበዳሪዎች እና ለጋሾች ይጠበቃል።

አቶ ሱፊያን ከአገር ውስጥ ምንጮች ከፍ ያለ ገንዘብ ይገኛል ብለው ቢያቅዱም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተስተዋሉት የግብር ሰብሳቢው ሪፖርቶች ግን ግምታቸውን ውድቅ የሚያደርጉ ናቸው። ከዚህ ይልቅ አገሪቱ ከውጭ በሚመጣ ርዳታ እና ብድር ላይ የበለጠ ጥገኛ መኾኗ ቀጥሏል። የበጀት ጉድለቱም መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ከዓመት ዓመት  እየጨመረ ለዋጋ ግሽበት እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ምክንያት ኾኗል። ከ1997 ዓ.ም እስከ 2001 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የተመዘገቡት የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከውጭ የተገኘው ብድር እና ርዳታ ሳይካተት 67 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የበጀት ጉድለት ታይቷል።

ይህም ኢኮኖሚው ምን ያህል በውጭ ድጋፍ ላይ እንደተንጠለጠለ የሚያሳይ መረጃ ነው። በኢኮኖሚ ሐልዮት ኾነ በተጨባጭ ተግባራት መመዘኛ ግን ይህን ያህል ተከታታይ የበጀት ጉድለት የሚያስተናገድ እና በውጭ ድጋፍ የቆመ ኢኮኖሚ እንደ ጤነኛ አይታይም። በፅንሰ ሃሳብም ኾነ በተግባር በተለይ የበጀት ጉድለት ለዋጋ ግሽበት  ምክንያት መኾኑ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት የሚጠይቀውን ጉልበት ያበዛዋል።

ገቢ እና ወጪ . . .

የበጀት ጉድለት የየትኛውም ኢኮኖሚ ጠባይ ነው። ባደጉትም ኾነ በአዳጊ አገራት የተለመደ እና የሚያጋጥም ክስተት ነው። በያዝነው ሳምንት ውስጥም አዲሱ የብሪታንያ ጥምር መንግስት ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የኾነው ይኼው ጉዳይ ነው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈ የመጣውን የበጀት ጉድለት እንዴት መቀነስ እንደሚቻል።

አልፎ እልፎም አንዳንድ አገራት ለሸቀጦች የሚኖርን ፍላጎት በከፍተኛ ኹኔታ በመጨመር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ሲሹ አዎንታዊ የኾነ የበጀት ጉድለት የሚያስተናግዱበት ጊዜ አለ። ይኹንና ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ያልተመጣጠነ እና በአገር ውስጥ ብድርም ኾነ በተለያዩ ገቢዎች የሚሸፈን ካልኾነ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ አውታሩ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ  ስለሚኾን አገራት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ አገራት የተመጣጠነ ወጪ እና ገቢ መፍጠር ከቻሉ ኢኮኖሚውን ከዋጋ ግሽበት፣ ከከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት እና ከቀውስ ሊታደጉት ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት የተመጣጠነ የበጀት ሚዛን መፍጠር አልቻለም። በየዓመቱ በአማካይ የመንግስት በጀት በ20 በመቶ ቢያድግም በከፍተኛ ኹኔታ የሚመነደገውን ወጪ የመሸፈን አቅም የለውም። በተከታታይ ዓመታት እንደተስተዋለው የመንግስት ወጪ ከአጠቃላዩ አገራዊ ምርት ጋር ያለው ምጣኔ 23 በመቶ የደረሰ ሲኾን በአንጻሩ የመንግስት ገቢ ከ13 በመቶ የዘለለ አይደለም።

ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነው የመንግስት ወጪ በቀጥታ ለካፒታል በጀት ድጎማ ከሚውለው የውጭ ድጋፍ እና ብድር በስተቀር ለመንግስት ሥራ ማስኬጃ የሚውል ነው። ከዓመት ዓመት እየጨመሩ ካሉ ወጪዎች አንዱ ለአገር መከላከያ እና ደህንነት የሚወጣው ነው። ከ1995 ዓ.ም ወዲህ በየዓመቱ በአማካይ ከ500 ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ድረስ ወጪው ጭማሬ ያሳያል። ከአምስት ዓመታት በፊት ሦስት ቢሊዮን የነበረው ወጪ በ2001 ዓ.ም 6.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ ከአንድ መቶ ፐርሰንት በላይ ተመንድጓል።

የትምህርት ዘርፉ ይበልጥ ግንባታዎች እና ማስፋፊያ ሥራዎች የተሠሩት ባለፉት አምስት ዓመታት ነበር። በየዓመቱ በአማካይ ለትምህርት የሚወጣው ገንዘብ በ14 በመቶ አድጓል። የአዳዲስ ትምህርት ቤቶችም ግንባታ እንዲሁ የ15 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። መምህራን ተቀጥረዋል። እንዲሁ በተመሳሳይ በየቀበሌው የጤና ኬላዎች ተከፈተዋል። የጤና ኤክስቴነሽን ባለሞያዎች ተቀጠረዋል። እነዚህ አዎንታዊ አንድምታ ያላቸው ለውጦች ወጪያቸው ጨምሯል። ይህም መንግሥት ያልተመጣጠነ ወጪ እንዲያወጣ አድርጎታል። እጅ ለእጅ ተያይዘውም የዋጋ ግሽበት እና በዓመት እስከ 60 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የንግድ ሚዛን ጉደለት ኢኮኖሚውን እየጎበኙት ነው።

ከመንግሥት ያልተሰላ ወጪ ባሻገር በዋነኝነት የመንግስት የግብር አሰባሰብ ደካማ መኾን በተከታታይ ለሚስተዋለው ጉድለት እንደ ምክንያት ይቀርባል። በግብር አሰባሰብ ረገድ ያለፉት ሁለት አመታት አንጻራዊ ለውጥ የተመዘገበባቸው ቢኾኑም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማግኘት አልተቻለም። በአመቱ መጨረሻ ውስን የኾነውን ግብር ከፋይ ከማጣደፍ በዘለለ የተሟላ የሚባል የግብር አሰባሰብ ሥርዓት አለተዘረጋም። አሁንም ቢኾን ከግብር የሚገኝ ገቢ ከአመታዊው አጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከ12 በመቶ ፈቀቅ ማለት አልቻለም። ታክስ ነክ ካልኾኑ የገቢ ምንጮች የሚገኘውም ገቢ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል በመኾኑ የመንግስትን የወጪ ፍላጎት የሚሞላ አይደለም። ይህም በመኾኑ የመንግስት የበጀት ጉድለት በከፍተኛ ኹኔታ በመባባስ ላይ ነው።

በ2003ቱም የበጀት አዋጅ ረቂቅ እንደተቀመጠው መንግስት ከግብር የሚገኛውን ገንዘብ ከፍ ለማድረግ ማቀዱን አስቀምጧል። እስከ 40 ቢሊዮን ብር የሚኾነው የበጀቱ ክፍል ከግብር ነክ ጉዳዮች ለመሰብሰብ ነው የታቀደው። የተጨማሪ እሴት ታክስ (Value Add Tax) ከ16 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ይጠበቅበታል። ይኹንና ባለፉት ዓመታት እንደታየው በአማካይ መንግሥት ካቀደው የግብር አሰባሰብ ሂደት ውስጥ እስከ 30 በመቶ ያህሉ ሳይሳካ የሚቀር ነው። ዘወትር ራስ ምታት ለኾነው የበጀት ጉድለት  መባባስም መፍትሄ ለመኾን አቅም ያንሰዋል።

የማይነጥፍ ድጎማ?

መንግስት ከውጭ የሚመጣን ድጋፍን በተመለከተ ተዋጥቶለታል ማለት ይቻላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በየዓመቱ ከውጭ ለጋሽና አበዳሪ ድርጅቶች እና አገሮች የሚገኘው ድጋፍ ባይኖር የመንግስት የበጀት ጉድለት ከዚህም በብዙ ደረጃ ይልቅ ነበር። ከ1995 ዓ.ም ወዲህ እንኳን ያሉት የቁጥር መረጃዎች በግልጽ እንደሚያስቀምጡት የውጭ መንግስታት ድጋፍ ያለ ርዳታ ሊከሰት ይችል የነበረውን የበጀት ጉድለት ከ40 በመቶ በላይ ቀንሶታል።

አገሪቷ በድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ምክንያትም ኾነ በአጋር አጋሮች ወዳጅነት ለመሰረታዊ ጉዳዮች ከሚውል ገንዘብ ጀምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማስኬጃን ለማንቀሳቀስ ደጋፍ የምትሻ ነች። በተለይ ለዘለቄታዊ ልማት መሠረታዊ የሚባለው የካፒታል በጀት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንድትኾን አድርጓታል። የጤና፣ የትምህርት እና ማህበራዊ ዋስትና ጉዳዮችም ከአገሪቷ አቅም በላይ እየኾኑ የመጡ ይመስላሉ። ለመጥቀስ ያህል እንኳን የ2003 የጤና በጀት 90 በመቶ ያህሉ በጀት የሚሸፈነው ከለጋሽ አገራት ይገኛል ተብሎ በታሰበ ደጋፍ ነው።

ይህ በድጎማና በብድር የተንጠለጠለ ኢኮኖሚ ወዴት እንደሚወስድ ለኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግልጽ ነው። ብዙዎች እንደሚያምኑት በድጋፍ ላይ ለዘላለም የሚቆም ኢኮኖሚ አይኖርም። ፈጥኖ ራስንም ወደ መቻል መንገድ ካለተገባ በስተቀር አፋፍ ላይ ያለውን ኢኮኖሚ በድጎማ ማስቀጠል አይቻልም። በዚህ ወቅት ለጋሽ አገራት  የድጋፍ እጃቸውን ለመዘርጋት የተስተካከለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ ይፈለጋሉ። አዳጊ አገራት ከመልማት አቅም ባሻገር ዴሞክራሲን ለማስፈን አለዚያም የለጋሾቻቸውን ልዩ ፍላጎቶች ለማሟላት ያላቸው ቁርጠኝነት የሚያገኙትን የድጋፍ መጠን የሚወስን ይኾናል።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

የያሬድ ሹመቴ የመጨረሻው ዙር የአጭር ፊልም አሸናፊ ኾኖ ተመረጠ

ያሬድ ሹመቴ በውድድሩ አሸናፊ የኾነው “ዲሞክራሲ ቪዲዮ ቻሌንጅ” በሚል ርእስ ከሦስት ደቂቃ ያልበለጠ ፊልም ከዓለም ዙሪያ በዩ ቲዩብ እንዲያስተላልፉ የስቴት ዲፓርትመንት ስያሜ ባወጣላቸው ስድስት የአህጉራት ክልሎች በሚካሄደው ውድድር ላይ ነው።

ሰኔ 14 ቀን 2002 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው የመጨረሻው የአጭር ፊልም ውድድር ስድስት አሸናፊዎች መካከል የፊልም ባለሞያው ያሬድ ሹመቴ አንዱ በመኾን አሸነፈ። ያሬድ ሹመቴ በውድድሩ አሸናፊ የኾነው “ዲሞክራሲ ቪዲዮ ቻሌንጅ” በሚል ርእስ ከሦስት ደቂቃ ያልበለጠ ፊልም ከዓለም ዙሪያ በዩ ቲዩብ እንዲያስተላልፉ የስቴት ዲፓርትመንት ስያሜ ባወጣላቸው ስድስት የአህጉራት ክልሎች በሚካሄደው ውድድር ላይ ነው። በስድስት የተከፈሉት ክልሎች የሰሜን፣ የደቡብ እና የመካከለኛው አሜሪካ፣ የአውሮፓ፤ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ፣ የሰብ ሰሃራ አፍሪካ፣ የደቡብ እና መካከለኛው እስያ እንዲኹም የምሥራቅ አፍሪካ እና ፓስፊክ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የፊልም ባለሞያዎች የመጀመርያ ዙር ውድድራቸውን ያጠናቀቁት እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2010 ላይ ነው። እያንዳንዱ ውድድር ከሚካሄድበት አገር ውስጥ ሦስት ተወዳዳሪዎች ማጣሪያውን በመጋቢት ወር አልፈዋል። በሁለተኛው ዙር ውድድር ከስድስቱ አገሮች ሦስት ሦስት ተወዳዳሪዎች ተመርጠው በድምሩ 21 ያህሉ ግንቦት 7 ቀን 2002 ዓ.ም አልፈዋል። ያሬድ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በመኾን ለመጨረሻው ውድድር ካለፈ በኋላ ከስድሰቱ የመጨረሻ አሸናፊዎች መካከል የመጀመርያውን ደረጃ በመያዝ አሸናፊ መኾኑን የሚያበስር የእንኳን ደስ ያለህ መልእክት ከአዘጋጆቹ በኢሜል እንደደረሰው ለአዲስ ነገር ገልጿል። “በፍጹም የመጀመርያው ተመራጭ እኾናለኹ ብዬ አላሰብኹም ነበር። ይህን ውድድር በማሸነፌ ግን እጅግ ደስ ብሎኛል” ብሏል። ያሬድ ያሸነፈበት ይህ አጭር ፊልም አንድ ደቂቃ ከአርባ ሁለት ሰከንድ የሚፈጅ ሲኾን ጭብጡ በኢትዮጵያውያን ልጆች ዘንድ የተለመደ ጨዋታን መሠረት ያደረገ ነው። ልጆች እርስ በርሳቸው እየተዛዘሉ ከፊት ለፊታቸው የሚወረውሩትን ድንጋይ በቻሉት መጠን አርቀው ከወረወሩ በኋላ ድንጋዩን በመምታት እየተፈራረቁ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው። አዛዩም ኾነ ታዛዩ ድንጋዩን መምታት ሲችል ብቻ ቀዳሚነትን የሚያገኝበት እና የሚታዘልበት ነው። ያሬድ ይህንኑ ፊልም “Democracy is fair play ” የሚል ስያሜ ሰጥቶታል። ሁለቱ ከአፍሪካ ያለፉት ተወዳዳሪዎች የብሩንዲ እና የደቡብ አፍሪካ ፊልም ሠሪዎች ናቸው። ግንቦት 9 ቀን 2002 ዓ.ም የያሬድ ሹመቴን አሸናፊነት አስመልክቶ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የእንኳን ደስ ያለህ ጥሪ እንዳደረገለት ይታወሳል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሰደር ዶናለድ ቡዝ ለያሬድ በተደረገው የግብዣ ሥነ ሥርዐት ላይ በመገኘት እንኳን ደስ ያለህ ካሉት በኋላ ለመጨረሻው ምዕራፍ እንዲደርሰም መልካም ምኞታቸውን ገልጸውለትም ነበር። ያሬድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቀረቡ ሠላሳ ያህል ፊልሞች መካከል ተወዳድሮ ነው ለዚህ የሁለተኛ ዙር ውድድር ያለፈው በመጋቢት ወር ነው። ይህ በዩ ቲዩብ አማካኝነት “የዲሞክራሲ ቪዲዮ ቻሌንጅ” በሚል የሚካሄደው የአጭር ፊልሞች ውድድር ስፖንሰር የተደረገው፤ በ“ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ኢንተርፕራይዝ”፣ በ “ኢንተርናሽናል ዩዝ ፌዴሬሽን”፣ በ“ኤን.ቢ.ሲ ዩኒቨርሳል”፣ በ“ናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲቱት”፣ በ“ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲቱት”፣ በ“ሞሽን ፒክቸር አሶሴሽን ኦፍ አሜሪካ”፣ በ“ቲስች(Tisch) ሰኩል ኦፍ አርትስ”፣ በ“ቴኪንግ አይቲ ግሎባል”፣ በ“ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝ ካሮላይና አነንበርግ ስኩል ኦፍ ኮሚዩኒኬሽን ኤንድ ጆርናሊዝም” እና በዩኤስ ስቴት ዲፓርትመንት ነው። የመጨረሻዎቹ ስድስቱ አሸናፊዎች ፊልሞች በዋሽንግተን ዲሲ፣ በኒው ዮርክ እና በሆሊውድ እንዲታዩ ይደረጋል። በተጨማሪም ውድድሩን ሲያካሂዱ በነበሩት www.videochallenge.America.gov እና www.youtube.com/democracychallenge. ላይ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባሉ። አሸናፊዎቹ ስፖንሰሮቹ ካዘጋጁላቸው ስጦታዎች መካከል የ10 ቀን የአሜሪካ ጉብኝት አንዱ ነው። በተጨማሪም ከመንግሥት ባለሥልጣነት፣ ከሚዲያ ሰዎች እና ከሲቪል ሶሳይቲ መሪዎች ጋራ እንዲገናኙ ይደረጋል። ከአሜሪካ የፊልም እና የቴሌቭዥን ኢንዱስትሪ ልምድ እንዲቀስሙ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። አሸናፊዎቹ የአሜሪካ ጉብኝታቸውን የሚያኪያሂዱት ግን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ነው።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

የትምህርት ነገር

በ2000 ዓ.ም. የመግቢያ ፈተናውን ያለፉት ተማሪዎች 22.2 በመቶ ቢሆኑም ዩኒቨርሲቲ የገቡት ግን 88.1 በመቶ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር 65.9 በመቶ የሚሆኑት ወዳቂ ተማሪዎች አለአግባብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደልድለዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ዓመት ከገቡት ተማሪዎች መካከል ሁለት ሶስተኛው ዩኒቨርሲቲ መግባት የማይገባቸው ነበሩ ማለት ነው፡፡ ከቀሪው አንድ ሦስትኛ መካከልም አብዛኛው ፈተናውን እንደነገሩ ያለፈ /ከ50 እስከ 60 በማግኘት/ ተማሪ ነው፡፡ በመግቢያ ፈተናው ከ60 በመቶ በላይ ያመጡት “እንቁ” ተማሪዎቻችን /ድንቄም እንቁ!/ 8.2 ከመቶ ብቻ ከሆኑ ተማሪ ቤቶቻችንን ለምን ወደ ሌላ ትርፋማ የስራ ዘርፍ አይዛወሩም?

www.helping-education-ethiopia.orgschools.html

በቅርቡ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ  “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተቋማት” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር፡፡ መጽሐፉ የትምህርት ጥራትን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን የያዘ ሲሆን፣ ቀልቤን የሳበው እና ያስደነገጠኝ የአዲስ ተማሪዎችን ብቃት በተመለከተ የተካተተው መረጃ ነው፡፡ ዝርዝር ትንተናውን ለኋላ አቆይቼ በሁለት ሰንጠረዦች ላይ ያየሁትን ብቻ ላካፍላችሁ፡፡ መረጃው የተገኘው ከአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት መሆኑን ጽሑፉ ያመለክታል፡፡

ሠንጠረዥ 2፣ የአጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት በጥሬ ማርክ/ከመቶ/

ዓመት ከ25 በታች ያገኙ ከ26-50ያገኙ ከ50 በላይ ያገኙ ከ75 በላይ ያገኙ
1999 44% 48.9% 7.6% 0.01%
2000 58% 36.6% 3% 0.07%

ይህን ቁጥር ስታዩ መቼም ራሳችሁን ሳትይዙ አትቀሩም፡፡ በ1999 ዓ.ም. ብሔራዊ ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 92.4 በመቶው ፈተናውን ወድቀዋል! በ2000 ደግሞ 97 በመቶው ፈተናውን አላለፉም፡፡ ይባስ ብሎም በ2000 ዓ.ም. ወደ 60 በመቶ የሚጠጉት ተማሪዎች 25 ከመቶ እንኳን ማግኘት አልቻሉም!! ይህን ውጤት ሳይ መጀመሪያ የመጣብኝ ስሜት፣  መንግሥት ለምን ትምህርት ቤቶቹን  ዘግቶ ችግሩን በጥልቀት አይመረምርም የሚል ነበር፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ጉዳዩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁሉ ሳያስፈልገው አይቀርም ነበር፡፡ ይህን አይነት ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች ይዞ የት መድረስ ይቻላል??

ነገር ግን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደለደሉትን ተማሪዎች ሁኔታ ስመለከት ደግሞ የመንግሥት ርምጃ ተቃራኒውን ሆኖ ነበር ያገኘሁት፡፡ የሚከተለውን ሰንጠረዥ ተመልከቱ

ሠንጠረዥ 3፣ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ትንተና /ከ500 ጥሬ ማርክ/

ዓመት ከ250 በታች ያገኙ ከ251-300ያገኙ ከ300 በላይያገኙ መግቢያ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ የተደለደሉ
1998 57.5% 32.5% 10% 97%
1999 46.3% 38.4% 15.3% 63.8%
2000 69.6% 22.2% 8.2% 88.1%

እግዜር ያሳያችሁ! በ2000 ዓ.ም. የመግቢያ ፈተናውን ያለፉት ተማሪዎች 22.2 በመቶ ቢሆኑም ዩኒቨርሲቲ የገቡት ግን 88.1 በመቶ ናቸው፡፡  በሌላ አነጋገር 65.9 በመቶ የሚሆኑት ወዳቂ ተማሪዎች አለአግባብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደልድለዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ዓመት ከገቡት ተማሪዎች መካከል ሁለት ሶስተኛው ዩኒቨርሲቲ መግባት የማይገባቸው ነበሩ ማለት ነው፡፡ ከቀሪው አንድ ሦስትኛ መካከልም አብዛኛው ፈተናውን እንደነገሩ ያለፈ /ከ50 እስከ 60 በማግኘት/ ተማሪ ነው፡፡ በመግቢያ ፈተናው ከ60 በመቶ በላይ ያመጡት “እንቁ” ተማሪዎቻችን /ድንቄም እንቁ!/  8.2 ከመቶ ብቻ ከሆኑ  ተማሪ ቤቶቻችንን ለምን ወደ ሌላ ትርፋማ የስራ ዘርፍ አይዛወሩም? /በሰማንያዎቹ አጋማሽ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ሰው የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት መምህራንን ሲያስፈራሩ፣ “እኛኮ ለናንተ ብለን ነው እንጂ ብንፈልግ ትምህርት ቤቱን ዘግተን ህንጻውን ማከራየት እንችላለን” ብለው እንደነበር የሰማሁትን አስታወሰኝ/፡፡

ብዙ መምህራን ጓደኞቼ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻቸውን የፈተና ወረቀት ሲያርሙ እዬዬያቸውን የሚያወርዱበት ምክንያት የገባኝ አሁን ነው፡፡ የመመረቂያ ወረቀት ስራ ቢዝነስም ለምን እንደተሰፋፋ የተገለጠልኝ አሁን ሳይሆን አይቀርም፡፡ መቼም ብዙዎቻችን የትምህርት ጥራት መውረዱን እንገነዘባለን፣ እናማርራለንም፡፡ ግን እንዲህ ራስ እስኪያዞር መውረዱን የምናውቅ አልመሰለኝም፡፡

መንግሥት ቀጣዩ የከፍተኛ ትምህርት የትኩረት አቅጣጫ 70 በመቶው በተፈጥሮ ሳይንስ እና ምህንድስና ዘርፍ፣ 30 በመቶው ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ተማሪዎቹስ ለእነዚህ ዘርፎች ብቁ ይሆኑ ይሆን? እስኪ የወደፊቱን ለመገመት ያህል ያለፈውን ውጤት እንይ፡፡

ሠንጠረዥ 2.2፣ የአጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች አማካይ ውጤት በትምህርት አይነት /በፐርሰንት/

ዓመት ቋንቋ ሒሳብ ሳይንስ ማኅበራዊ ሳይንስ አማካይ ውሁድ ውጤት
1999 33.6% 18.91% 26.97% 32.2% 29.3%
2000 29.4% 17.97% 22.7% 22.6% 24.95

ጉዳችንን እዩት እንግዲህ፡፡ ውጤቱ ከአመት አመት እያሽቆለቆለ ሄዶ፣ ኢንጅነሮቻችንና ዶክተሮቻችን እንዲሆኑ የምናሰለጥናቸው ተማሪዎች፣ በርካቶቹ በሂሳብ 19 ከመቶ ማግኘት ያቃታቸው፣ በሳይንስ 25 ከመቶ እንኩዋን የሌላቸው ናቸው፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎቻችን እንዲሆኑ የሚታሰቡትም እንዲሁ 25 ከመቶ ማግኘት ያቃታቸው ተማሪዎች ሆኑ፡፡ በዚህ አይነት ምን አይነት መሐንዲስ፣ ምን አይነት ዶክተር፣ ምን አይነት ኢኮኖሚስት ይኖረን ይሆን? ጉዳቱን የበለጠ የሚያደርገው ደግሞ የሚቀጥለውን ትውልድ የሚያንጹት እነዚሁ ልጆቻችን መሆናቸው ነው፡፡

የችግሩን መጠን ለማሳየት ቀንጨብ አድርጌ አቀረብኩት እንጂ ጽሑፉ ሌሎችንም ተመሳሳይ አስደንጋጭ አሀዞች ይዟል፡፡ ርዕሱን ሳስብ ትዝ ያለኝ የፕሮፌሰር መስፍን “የክህደት ቁልቁለት” የሚለው መጽሐፍ ነበር፡፡ ይህንንስ ምን እንበለው ይሆን? የትምህርት ቁልቁለት?

ለመሆኑ ችግሩ የት ነው? ስርዓተ ትምህርቱ ለተማሪዎች የማይመጥን ሆኖ ነው? ምናልባት ፈተናው አለቅጥ ከብዶ ይሆን? አስተማሪዎቻችን ብቃት ያልነካቸው ስለሆኑ ይሆን? የፕላዝማ ቲቪ ጦስ እንደሆነስ? የተማሪ እና መምህር ምጣኔ ችግርስ ሊሆን አይችልም? አሁንስ መንግስት ምን ርምጃዎች ወስዷል? ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ይህን ጉዳይ ያውቁታል? ሲያነሱትስ ተሰምተዋል? ዝርዝሩን እናንተና ባለሙያዎቹ ተመራመሩበት፡፡

እኔ ግን ራሴን አመመኝ፡፡

16 Responses to “የትምህርት ነገር”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 3

ሦስት ምርጫዎች ሕይወቴን ላይመለስ ቀየሩት። የመጀመሪያው ምርጫ በአገሬ ፖለቲካ ውስጥ ያለኝን ቦታ እና ሚና የምር ማሰብ እንድጀምር ጋበዘኝ። ሁለተኛው በተስፋ እና በቀቢጸ ተስፋ መካከል ተወኝ። ሦስተኛው በፍቅር የወደኩላትን ያቺኑ አገር ትቻት ለመሰደዴ ምክንያት ሆነኝ።….የዘንድሮውን ምርጫ በአካል ልመለከተውም ሆነ ልሳተፍበት አልቻልኩም፤ ምርጫ ባይሆንም ብኖር እወድ ነበር። ምርጫውን ከሩቅ ስመለከተው የአዲስ ነገርን ሕልሞች የበላ ጨካኝ ድራማ ሆኖ ይታየኛል። በ”አዲስ ነገር” ውስጥ ያየሁትን ሕልም ያፋፋሁ መስሎኝ በብዙ መልኩ ያስቀየምኳቸው፣ የበደልኳቸው ባለውለታዎቼ ያዝኑልኝ ይሆን ወይስ ያዝኑብኝ እያልኩ ማሰቤን አላቃምኩም። ሰዎቹን ብዙ ነገር ከልክያቸው ነበር፤ ጊዜ፣ አትኩሮት፣ እገዛ…። ይቅርታቸው ይገባኛል። ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚቀጩት ሕልሞች፤ የሚጠፉት ሕይወቶች፤ የሚበላሹት ኑሮዎች ስንት ይሆኑ ብዬ ስጠየቅ ከረምኩ። ለምን? ያልመለስኩት ጥያቄ ነው። ሦስተኛ ክፍል፤ ጉዞ ወደ ምርጫ 2002

ሌላ አምስት ዓመታት ከፊቴ ናቸው። ቀጣዮቹ ዓመታት በምርጫ 97 ጥላ ስር መውደቃቸው አልቀረም። ምርጫውን ተከትሎ የሆነው ነገር ሁሉ ለብዙዎቻችን ተስፋ አስቆራጭ እንቆቅልሽ ነበር። ለእኔ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የማሰላሰያ ነበሩ። ምን ሆነ? ለምን ሆነ? ጥያቄው ብዙ ነው። ከኢሕአዴግ አመራሮችና በኋላ ከተቀላቀሏቸው ጥሙቃን በቀር አብዛኛው ሕዝብ ቀጣዮቹን ዓመታት የሚገመግማቸው ከምርጫ 97 ዴሞክራሲያዊ ልምዱ በመነሣት ሆነ። ምናልባትም ለቀጣዮቹ 20 ዓመታትም ምርጫ 97ን አንደግመው ይሆናል፤ ማነጻጸራችን ግን አይቀርም። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ 97 (“ምርጫ 97” ስል እስከ ምርጫው ዕለት የነበረውን የዴሞክራሲ ፀሐይ ውጋገን በሩቅ የታየበትን ወቅት ማለቴ ነው) እንዲደገም ከሚገልጉት ዜጎች ይልቅ እንዳይደገም ለማደረግ ቆርጠው የተነሡትን መቁጠር ይቀላል፤ እጅግ ጥቂት ስለሆኑ።

እነዚህ አምስት ዓመታት የማሰላሰያ ቢሆኑልኝም ቀላል እና ተስፋ ሰጪ ግን አልነበሩም። የእውነተኛ ዴሞክራሲ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ሁሉ እየታደነ እንዲዳከም ወይም እንዲጠፋ አዋጅ የተነገረባቸው ዓመታት ነበሩ ቢባል ማጋነን አይመስለኝም። የተስፋ በሮች ይዘጉ፤ የዴሞክራሲ መንገዶች ይጥበቡ፤ ልዩ ድምጾች ይታፈኑ፤ ነጻ ኅሊናዎች ይገብሩ…የሚል በይፋ ያልተነገረ መፈክር ከጀርባ ይሰማ ነበር። አገሬ የጆርጅ ኦርዌልን “1984” በድጋሚ መተወን የጀመረች እስኪመስል ድረስ ከማሳዘን አልፈው የሚያስቁ “ዴሞክራሲያዊ” ድራማዎች በየዓይነቱ ፈሉ። የሕዝብን ፖለቲካዊ አስተያየት እና እውቀት የመቅረጽ ወይም የመመገብ እምቅ አቅም ያላቸው ነጻ ተቋማት ሁሉ ክተት ታወጀባቸው። ይህ ክተትም በተለይ በሚዲያው፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በገለልተኛ የሞያ እና የሠራተኛ ማኅበራት እንዲሁም ተሰሚነት አላቸው ወይም ሊያገኙ ይችላሉ በሚባሉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነበር።

በሌላ በኩል አንዳች የሃይማኖት ንቅናቄ እስኪመስል ድረስ (ልክ እንደ ደርግ ጊዜ) “ሁሉም” ሰው የፓርቲ አባል መሆን ጀመረ። ነጻነት ለፍርሃት ቦታው እንዲለቅ ሲደረግም ቀስ በቀስ ታዘብን። “አሁን ነጻነትና ዴሞክራሲ አስቸኳይ ጉዳያችን አይደለም፤ ቅድሚያ ለልማት” እየተባለ የዴሞክራሲ ጥያቄ ቅንጦት መሆኑ በተለያየ መንገድ መነገሩ ቀጠለ። “ጦርነት ሰላም ነው፤ ነጻነት ባርነት ነው፤ ድንቁርና ጥንካሬ ነው” የሚለው የኦርዌል ዓለም ራሱን እንደ አዲስ እየወለደ ይሆን? አንዳንዶች ጠየቁ።

በምርጫ 97 ማግስት ኢሕአዴግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከፍተኛ አደጋን ያዘሉ ናቸው። ከሃያ በላይ ጋዜጦችን በጅምላ ዘጋ፤ የተወሰኑት ደግሞ ከሰሰ። የቅንጅት አመራሮችን በጅምላ ማሰሩ ሳይበቃ “በዘር ማጥፋት” መክሰሱ ፖለቲካችንን እስከ ወዲያኛው ሊቀይረው እንደሚችል የሚያመዛዝን የሰከነ አመራር ሳይገኝ ቀረ። ክሱ “በእብድ” ሰዎች የተጠነሰሰ፤ “እብድ” ክስ ነበር። ውጤቱም ወደ ማኅበረሰባዊ እብደት ሊያመራ የሚችል አቅም ነበረው፤ እብደቱ እስከ አሁን ባይገለጽም ቂሙ በአጭር ጊዜ መጥፋቱን እጠራጠራለሁ። በተሳትፎ፣ በፍቅር፣ በመከባበር፣ በነጻነት እና ከሁሉም በላይ በተስፋ ተሞልቶ የነበረው ፖለቲካዊ ከባቢ ተረበሸ፤ ተቀየረ። የቅንጅት አመራሮች “በይቅርታ” መፈታት እንኳን ቀውሱን የሚያረግብ አቅም ማግኘት ተሳነው።

እነዚህ ዓመታት በሁለት ተቃራኒ ነገር ግን ተመጋጋቢ ሁኔታዎች መጨረሻቸው የተቆረጠላቸው ሆኑ። በአንድ በኩል ኢሕአዴግ “ሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ” እያለ በሚያቆላምጣቸው መሣሪዎች በመጠቀም የፖለቲካ ምኅዳሩን እስከ መጨረሻው ለማጥበብ በቁርጠኝነት ሠራ። የራሱ ጥላ የሚያስፈራው ድንጉጥ ተቆጣጣሪ ሆነ። በሌላ በኩል የተቃዋሚው ጎራ በዋናነት ራሱ በፈጠረው ውስጣዊ ቀውስ ተሽመደመደ። የእነዚህ ሁለት ሁኔታዎች ጥምረት የዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ተስፋ ከማጨለም የተለየ ውጤት ሊኖረው አይችልም ነበር። የሆነውም ይህ ነው።
አነሰም በዛም እነዚህ ሁኔታዎች በእኔ ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ ተጽእኖ ነበራቸው። መስከረም 1999 ላይ አንድ ወሬ ሰማን። ምርጫ 97ን ተከትሎ ተከልክሎ የነበረው የፕሬስ ሥራ ፈቃድ መስጠት ሊጀመር መሆኑን ሰማን፤ ከሚታመን ውስጥ አዋቂ። በዚያ ወቅት የአዲስ ነገር መሥራቾች የፕሬስ ሥራ ፈቃድ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ተስፋ በመቁረጥ አንድ ድረ ገጽ ለመክፈት በመጀምር ላይ ነበርን።

በታሪካዊ አጋጣሚ ከማስታወቂያ ሚንስቴር ፈቃድ ለመጠየቅ እኔ “ትክክለኛው” ሰው ሆንኩ። በማይጠበቅ ቅልጥፍና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎች በሁለት/ሦስት ሳምንት ውስጥ ፈቃዳችን ሰጡን። አዲስ ነገር እውን ሆነች። ከዚያ ሐሳባችን ሁሉ አዲስ ነገር ሆነ፤ “አዲስ ነገር” ሆነች። በየዕለቱ እየተገናኘን ጋዜጣዋ በምትመራባቸው መሠረታዊ መርሆች፣ አመለካከቶች እና አሠራሮች ላይ መወያየት ቀጠልን። እርግጥ እርስ በርስ በሚገባ እንተዋወቅ ስለነበር ሁሉም ነገር ከጥሬ የተጀመረ አልነበረም፤ እንዲያውም ሒደቱ የነበሩንን የጋራ አመለካከቶች ከጋዜጣ ሥራ አኳያ የማንጠር እና ሥራ የመከፋፈል ነበር።

አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት የአዲስ ነገር መሥራቾች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ርእዮተ አለማዊ አቋም የለንም። ፈጽሞ። ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እየተገባ ሲኬድ ደግሞ ልዩነታችን እየበዛ ነገር ግን የበለጠ እየተጋባባን የምንሔድባቸው አጋጣሚዎች ይበዙ ነበር። በሁለት ነገሮች ያለ ጥርጠር ሁላችንም አንድ አይነት እምነትና ተስፋ/ሕልም ነበረን። አቅማችን እና ፖለቲካዊ ከባቢው በፈቀደልን መጠን ለአገራችን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፤ እንችላለንም የሚለው ተስፋና እምነታችን የቡድኑ ምሰሶ ነበር ማለት እችላለሁ። ሁለተኛው መሠረታዊ መገናኛ መርሐችን ነጻነትና ገለልተኝነት (ኢንድፔንደንስ) ነው። በግልም ይሁን በቡድን ከምንደግፈውም ይሁን ከምንቃወመው ቡድን ወይም ግለሰብ ተጽእኖ ራሳችንን ነጻ ለማድረግ የማያወላውል አቋም መያዝ የነጻነታችን ዋና መሠረት መሆኑን ተስማምተን ነበር። በግለሰብ ደረጃ ነጻነታችንን ማስጠበቅ እንፈልግ የነበረው ከውጭ አካል ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከቡድናችንም ጭምር ነበር።

በኤዲቶሪያል ስብሰባዎች ላይ ትልቅ የአመለካከትና የአቋም ልዩነት ይንጸባረቅ የነበረው (አንዳንድ ጊዜ እስከ መጣላት የሚደረስም) በቀዳሚነት በመሥራቾቹ መካከል እንደነበረ የሚያውቅ ሰው የምለውን ነጻነት ይረዳው ይሆናል። በእኔ እምነት፣ የጻፍነው ነገር በአንባቢው ላይ የፈጠረው ግምት ምንም ይሁን (ልንቆጣጠረው ስለማንችል) እስከ መጨረሻው ግለሰባዊም ይሁን ተቋማዊ ነጻነታችንን ለድርድር አላቀረብንም።

ከሁሉም ቦታ ሊባል በሚችል መልኩ አብዛኛው አስተያየት “በዚህ ወቅት ጋዜጣ መጀመር አደጋ የለውም ወይ” የሚል ቃና ያልተለየው ነበር። እኛ ግን “የቻልነውን ያህል እንሞክረው” አልን። ሥራው በግለሰባዊም ሆነ በጋራ ሕይወታችን ላይ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል እናውቅ ነበር። በዚያ ወቅት አብረውን ጋዜጣ እንዲመሠርቱ የጠየቅናቸውና መዘዙን ፈርተው የራቁ ሰዎች በኋላ የጋዜጣዋን ስኬት ሲመለከቱ መጸጸታቸው አይቀር ይሆናል። አሁን መሥራቾቹ ሁሉ ለስደት መዳረጋችንን ሲመለከቱ ይጽናኑ ይሆን?

ለማንኛውም “አዲስ ነገር” ተጀመረች። ቀጠለች። ከሞላ ጎደል “አዲስ ነገር” በብዙ መልኩ የስኬት ታሪክ ነበረች፤ ከአንድ ጉዳይ በቀር። እርሱም ኢሕአዴግ ውስጥ መጀመሪያ ግድም “እነዚህ ሕጻናት ናቸው፤ ከሁለት ወር በኋላ የሚጽፉት ሲያልቅ ጸጥ ይላሉ፤ ስለዚህ አያሰጉም” ሲሉን በነበሩ ዘንድ ጭምር ሳናውቀው የስጋት ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለን መታሰቡን ማስቀረት ሳንችል ቀረን። ሰዎቹ ደግሞ ብቻቸውን አልነበሩም፤ ከተቃዋሚዎችም ወገን እኛን በተመለከተ የነበረው አስተያየት የተምታታ ነበር። የሁለቱም ችግር ነጻነታችንን እና “ገለልተኝነታችንን” እንዳለ መውሰድ አለመቻል ነው። የጋዜጣዋ አንደኛ ዓመት ከተከበረ በኋላም ከየአቅጣጫው የሚነሳው ጥርጣሬና ጥላቻ በግልጽ መነገር ሁሉ ጀመረ።

ወደ መጨረሻ ግድም እንዲያውም በሚኒስትር ማዕረግ ያሉ አንድ ሰው “አዲስ ነገር ከተጋበዘ በወርክሾፑ ዝግጅት ላይ አንሳተፍም” ብለው ለውጭ አገር ሰዎች እስከመናገር ደረሱ። አንድ ቁልፍ የፓርቲው ሰው ክራቫታቸውን እያስተካከሉ “ለአዲስ ነገር የአዲሱን ቢሮ ኪራይ የሚከፍልላቸው ሲአይኤ እንደሆነ ታውቃላችሁ” ብለው ሲናገሩ የሰሙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ነገሩ ግራ ቢገባቸው እኛኑ መጠየቅ ያዙ። እነዚህ ቁልፍ ሊባሉ የሚችሉ የኢሕአዴግ አባላት/አመራሮች የተፈጠረባቸውን ለቅዠት የቀረበ ስጋት ለማስወገድ ጥረት አደረግን።

እርግጥ ጥረቱ “በቂ አልነበረም” ብለው የሚወቀሱን ወዳጆች አላጣንም። “እንደምታስቡት ከጀርባችን ማንም የለም፤ እንደምትሰጉትም አሁን የተሰበሰብነው ጋዜጣ ለመሥራት እንጂ ፓርቲ ለማቋቋም ፍላጎት የለንም (መብታችን ቢሆንም)፤ ከሲአይኤም ሆነ ከ ‘አንድነት’ (በኋላ መድረክ ሆኗል) ጋራ የተለየ ግንኙነት የለንም፤ ብዙ ጊዜ ኢሕአዴግ ላይ የምናተኩረው ሁሉንም ነገር የያዛችሁት እናንተ ስለሆናችሁ ነው፤ ኢትዮጵያን በመሰሉ አገሮች መንግሥት በሁሉም ነገር ውስጥ ቁልፍ ሚና አለው ስለዚህ…” ብለን እውነተኛ ማንነታችንን እና ፍላጎታችንን በቅን መንፈስ ለማስረዳት ሞክረናል። ከዚህ በላይ ምን ማድረግ እንችል እንደነበር ዛሬም ድረስ አልተገለጠልኝም።
ለማንኛውም ብዙም ሳይቆይ “ተቃዋሚ ጋዜጦች” የሚባሉት በተለይም “አዲስ ነገር” ከምርጫው (ግንቦት 2002) በፊት መፍትሔ እንዲበጅላቸው መወሰኑን እንድንሰማው ሆነ፤ መቼም በየቦታው ሰው (አማርኛ ካፒታል “ሰ” የለውም እንጂ..) አይጠፋም አይደል? “መስከረምና ጥቅምት ላይ ዘመቻ ይከፈትባችኋል፤ ከዚያ ወደ መስመር ካልገባችሁ…” የምትል የውስጥ አዋቂ ማስታወሻም ወራት ቀደም ብላ ደረሰችን። ማሳታወሻዋ ትክክል ነበረች፤ እንደ ተባለውም…(ዝርዝሩ ለሌላ አጋጣሚ ይቆየን)።

ይህ በሚከናወንበት መካከል ጓደኛችን ብርቱካን ሚደቅሳ በድጋሚ ስትታሰር የቅርብ ተመልካች የመሆን ዕጣ ወደቀብኝ። አሳዛኝ ነበር። በወቅቱ እንደጻፍኩት የብርቱካን ወንጀል ፖለቲካን ያለሞራል መልሕቅ አልጫወተውም ማለቷ ነው። ፖለቲካችው ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባችንም አንዳችም የሞራል ልእልና (በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አጠራር ደግሞ “የመንፈስ ልእልና”) በሌላቸው ሰዎች እየተሞላ በመሆኑ እዚያ መካከል የልእልናው ባለቤት ለመሆን መሞከር እንደወንጀል ቢቆጠር ምን ይገርማል?

የብርቱካን መታሰር ከእርሷ በላይ ስለ መንግሥታችንና ውሳኔውን ስላስተላለፉት ባለሥልጣናት የበለጠ ይናገራል፤ ከዚያም አልፎ ማኅበረሰባችን ስለ ደረሰበት (ከይቅርታ ጋራ) የሞራል ቀውስ ይመሰክርብናል። ዛሬም ድረስ ይገርመኛል፤ ይህን ልብ የሚሰብር ፍርደ ገምድል ጭካኔ በአደባባይ ወጥቶ የሚገስጽ አንድ “ገለልተኛ” “ሽማግሌ” እንዴት ጠፋ? ለምን? ይህን የምፈልገው ብርቱካን እንድትፈታ ስለምፈልግ ብቻ አይደለም፤ አንድ የተስፋ ድምጽ ከሆነ ቦታ መስማት ስለምፈልግ ነው። “አይ የመንፈስ ልእልና ያላቸው ሰዎችማ አሉን፤ ለጊዜው ዝም ብለው ይሆናል እንጂ፤ ውስጥ ውስጡን እየደከሙ ይሆናል…” ብዬ መጽናናት አምሮኝ ነው። አንድ ሰው? አንዲት ትልቅ ሰው፤ አንድ ሼህ፤ አንድ ጳጳስ፤ አንድ የሆነ ሰው (ፖለቲከኞችን ሳይጨምር የማኅበረሰቡን ስሜት የሚናገር…) እንዴት ይጠፋል?…ለካስ አንድ ሰው ብዙ ነው?

ብርቱካን ከመታሰሯ በፊት መንግሥት ስለሰጣት ቀነ ገደብና ምን ማድረግ እንደሚሻል ካወራቻቸው ሰዎች አንዱ ነበርኩ። ለእኔ ከባድ ነበር። የእኔ አቋም ኢሕአዴግ የሚፈልገውን አድርጎ ለቀጣዩ ምእራፍ መዘጋጀት የሚል ነበር። “ጨዋታው” የተጀመረው ብርቱካን ባዘጋጀችው ፕላን ሳይሆን ኢሕአዴግ በቀረጸው ፕሮግራም በመሆኑ ለጊዜው ዋጋ ከፍሎ ይህን ለማስመለስ/ለማካካስ ሌላ ዝግጅት ማደረግ አይቻልም ወይ ባይ ነበርኩ። የእርሷ መታሰር በተቃዋሚው ጎራ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖም ለመገመት የሚከብድ አልነበረም። ብርቱካን ከመታሰሯ አንድ/ሁለት ቀን በፊት እንደነገረቺኝ ካማከረቻቸው ሰዎች ሁሉ እርሷ የወሰደችውን እርምጃ የደገፉላት ስዬ አብርሃ ብቻ ነበሩ። ጨዋታው እርሷን አስፈራርቶ ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ነበር፤ እንደውም ወደ ጨዋታው መካከል ገባችላቸው፤ ይለይላቸው ብላ መሰለኝ።

ብርቱካንም ሆነች እኔ ወዳላየነው ወደ 2002 ምርጫ የወሰደኝ ወቅት ከቀደሙት በተለየ አንድ ከበድ ያለ ጥያቄ አቅርቦልኛል። ብርቱካን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ እንድገባ ጋበዘችኝ፤ ሞገተቺኝ ማለት ሳይሻል ይቀራል? ወደ ፓርቲ ፖለቲካ የመግባትን አስፈልጊነት አምናለሁ፤ የተወሰኑ ሰዎችንስ ሳላበረታታ ቀረሁ ብላችሁ ነው? ጥያቄውን ሳልቀበለሁ ቀረሁ። ዛሬም ድረስ የማምንበት ምክንያት ነበረኝ። ፖለቲካ ማለት በመሠረታዊ ተፈጥሮውም ሆነ በሂደቱ በፓርቲ ፖለቲካ የታጠረ አይደለም፤ ምናልባትም የእኛ አገር ፖለቲካ አንዱ ችግር “ፖለቲካ” የፓርቲዎች እና የአባሎቻቸው ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታየቱ ነው ብዬ አምናለሁ። መንግሥታቱም የሚገፉን እንዲህ እንድናም ነው፤ እኛም ተመችተናቸዋል። በተጨማሪ፣ ቢያንስ ለጊዜው፣ አገሬን የተሻለ ላገለግላት የምችለው በጋዜጠኝነት/በመጻፍ ነው የሚል አመለካከት አለኝ። ብርቱካን ሳትረዳኝ የቀረች አይመስለኝም። እኔም በውሳኔዬ አልተጸጸትኩም።

ከ1998-2002 ባሉት ዓመታት ነጻነትን የሚያፍን ሕግ፣ አሠራር፣ ተቋም ወዘተ በየደረጃው ያልተዘጋጀበትን/ ያልተቋቋመበትን ወር ወይም ዓመት ማስታወስ ያስቸግራል፤ ስለሌለ። ዜጎች “ይሄ ምርጫ አልፎ በተገላገልን” እያሉ የሚመኙበት ሁኔታም የፖለቲካው መገለጫ ሆነ። ወቅቱ ለእኔም እጅግ አስቸጋሪ ነበር። የሚጽፉበት ጉዳይ ሳያጡ የሚጽፉበት ጉዳይ አለማግኘት ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ በመጨረሻዎቹ ወራት ነበር። ብዙ የሚጻፍበት ነገር አለ፤ ሊጻፍ የሚችለው ግን ጥቂቱ ብቻ ነው። እርሱም ቢሆን በጥንቃቄ መቀመጥ አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ማኪያቷቸውን ፉት እያሉ፣ ጋዜጣችንን እፊታቸው ዘርግተው “ምን ትፈራላችሁ? ምን ትሸፋፍናላችሁ?” እያሉ የሚቆጡ ሰዎች አሉ። ደግነቱ አብዛኞቹ አንባቢዎቻችን የምንለው የሚገባቸው ነበሩ፤ “በባዶ ቦታ” (ዳሽ) የሚሞላውን ከእኛ በላይ ያውቁት ነበር። እንደዚህም ሆኖ ግን በአንድ ጉዳይ ላይ እኛም ሌሎች ጋዜጦችም ዘግበን “አለቆቻችን” በእኛ መናደዳቸውን እንሰማ ነበር። የቸገረ ነገር ሆነ፤ መጻፍም አለመጻፍም የማይቻልበት ሁኔታ።

እንደ ብዙዎቹ የግል ጋዜጦች “ምርጫውን እንዴት እናልፈው ይሆን?” የሚል ጥያቄ ከሥራችን በላይ ያስጨንቀን ገባ። ወራቱ እንዴት ያልፉልን ይሆን? ምርጫው ምርጫ እንደማይሆን እናውቃለን፤ ታዲያ ምን ብለን ነው የምንዘግበው? የጋዜጣችንን አቀራረብ እንቀይርና ሌሎቹን ጋዜጦች እንምሰል? ግን ይህ ምን ማለት ነው? ለምሳሌ የፖለቲካ ጉዳይ መዘገብ ብናቆምስ ሰይፉ ወደ ሰገባው ይመለስልናል? ግን ደግሞ እኛ አንስተነው ፖለቲካ የማይሆን ምን ጉዳይ እናገኛለን? ለምን ጋዜጣውን አንዘጋውም? ዘግቶ መቀመጥ የባሰ ትርጉም አይኖረውም?

እነዚህን ጥያቄዎች ለመጨረሻ ጊዜ ለመመለስ በምንሞክርበት ወቅት ከጥቂት ሳምንታትና ወራት በፊት ያዘጋጀነው የአዲስ ነገር የሦስት ዓመት ተቋማዊ እቅድ ጠረጴዛችን ላይ ነበር። በሥራ ብቃታቸውና በነጻ አመለካከታቸው ብቁ ናቸው ያልናቸውን ሁለት ጋዜጠኞች የድርጅቱ ባለድርሻዎች ለማድግ የቀረበው ሐሳብ የመጨረሻ ውሳኔያችንን ይጠብቅ ነበር።

ተቋማዊ እቅዱ የመሥራቾቹን ግለሰባዊ እቅድም የሚመለከት በመሆኑም በየግላችን ሕይወታችንን ወደፊት እየተመለከትን ነው። የእኔ የግል እቅድ በሁለት ዓመታት ውስጥ (በ2003 መጨረሻ) አዲስ ነገርን ሙሉ በሙሉ ለመልቀቅ ነበር። አጠቃላይ ሕልማችን አዲስ ነገርን በሒደት ከመሥራቾቿ ጭምር ነጻ የሆነች ተቋም ማድረግ ነበር፤ መሥራቾቻቸው ሲታመው ታመው ሲሄዱ እንደሚሄዱት ጋዜጦች እንዳትሆን ለማድረግ። የጋዜጣችን አካል ሆኖ በየ15 ቀኑ የሚታተም “ልዩ ገጾች” (ሰፕልመንት) ለመጀመር ብዙ ጊዜ አልቀረነም ነበር። የኒውዮርኩን የጸሐፊዎች ፌሎውሺፕ ተወዳዳሪዎችን ማመልከቻም መቀበል ጀምረን ነበር። ምናልባት ከተሳካ በሚልም (ማምለጫ ከሆነን ለመሞከርም ጭምር) ነጻ የአዲስ ነገር የምርጫ ክርክር መድረክ ለማዘጋጀት ሐሳብ ነበረን። ነበረን።

በግሌ ከ1983 ጀምሮ ለኢሕአዴግ የመታመን ቅድሚያውን ባለመንፈግ እድል ለመስጠት ፈቃደኛ ያልነበርኩበትን ጊዜም ሆነ ጉዳይ አላስታውስም። ነገር ግን አንድም ጊዜ ኢሕአዴግ የምሰጠውን ዕድል የሚጠቀም፤ ሌሎችን ለማዳመጥ የሚፈቅድ፤ ልዩነቶችን ለማስተናገድ የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም። ብዙ የእኔ ብጤዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም እገምታለሁ። ቢሆንም ዕድል በመስጠቴ አልጸጸትም። የታሪኩ ምጸት ግን በመጨረሻ እኔው ራሴ የዚህ አመራርና የፖሊሲዎቹ ሰለባ መሆኔ ብቻ ነው። በስተመጨረሻም በኢሕአዴግ ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ማድረግ ቀርቶብኝ ለመኖር የምችል መሆኔን እንኳን እርግጠኛ ሳልሆን ቀረሁ። ይህ አገር የማነው? የቀረው ሁሉ ታሪክ ብቻ ነው።

የአገራችን ችግር ውስብስብ ከመሆኑ የተነሣ አንድ ፍቱን መድኀኒት አለው ብሎ መደምደም አይቻልም። ከ“የብቸኛ መፍትሔ አዙሪት” መውጣት ካልቻልንም አንዱን ችግር የፈታን መስሎን የባሰ አደጋ እየቀፈቀፍን መጓዛችን አያቆም ይሆናል። ዛሬ የመፍትሔ ዓለማችን የሚዞረው ፍጹም ተቃራኒ በሆኑ ሁለት ምህዋሮች ዙሪያ በሚሽከረከሩ “ብቸና መፍትሔዎች” ነው፤ “ኢሕአዴግ/መለስ ብቻ” ወይም “መለስ/ኢሕአዴግን ሳያጠፉ መፍትሔ የለም”። ቀድሞም እንዲሁ ነበር፤ “ደርግ ብቻ” ወይም “በመንግሥቱ መቃብር ላይ”።

የዘንድሮውን ምርጫ በአካል ልመለከተውም ሆነ ልሳተፍበት አልቻልኩም፤ ምርጫ ባይሆንም ብኖር እወድ ነበር። ምርጫውን ከሩቅ ስመለከተው የአዲስ ነገርን ሕልሞች የበላ ጨካኝ ድራማ ሆኖ ይታየኛል። በ”አዲስ ነገር” ውስጥ ያየሁትን ሕልም ያፋፋሁ መስሎኝ በብዙ መልኩ ያስቀየምኳቸው፣ የበደልኳቸው ባለውለታዎቼ ያዝኑልኝ ይሆን ወይስ ያዝኑብኝ እያልኩ ማሰቤን አላቃምኩም። ሰዎቹን ብዙ ነገር ከልክያቸው ነበር፤ ጊዜ፣ አትኩሮት፣ እገዛ…። ይቅርታቸው ይገባኛል። ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚቀጩት ሕልሞች፤ የሚጠፉት ሕይወቶች፤ የሚበላሹት ኑሮዎች ስንት ይሆኑ ብዬ ስጠየቅ ከረምኩ። ለምን? ያልመለስኩት ጥያቄ ነው።

ጽሑፌን በዚህ አሳዛኝ አንቀጽ ልዘጋው አልሻም። ያለፉት አምስት ዓመታት በጥቂት እውቀት፣ በጥቂት ሰው፣ በጥቂት ጥረት፣ በጥቂት ጊዜ ብዙ አዲስ ነገር መፍጠር እንደሚቻል አስተምሮኛል። ኢትዮጵያ እነዚህን ጥቂቶች ማድረግ የሚችሉ “ጥቂቶች” እንዳሏትም አምናለሁ። ቁም ነገሩ “ከእነዚያ “ጥቂቶች” አንዱ እኔ ነኝ፤ ስለዚህም የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ፤ ምንና እንዴት ላድርግ?” የሚለውን ለማሰብ ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው። ማሰብ ሕመምና ድካም አለው፤ እርሱንም ለመሸከም መፍቀድ ብቻ ነው። ባለቅኔው እንዳለው ብዙ ባልተሔደበት መንገድ ጫካውን ለማሰስ ማሰብ ነው።

“…Two roads diverged in a wood, and I–
I took the one less traveled by,
And that has made all the difference…”
[Robert Frost: The Road Not Taken (1915)]

መልካም ሐሰሳ እስከ ቀጣዩ ምርጫ፤ ባልተሔደበት መንገድ። ምርጫ ሦስት፤ አበቃ።

ማስታወሻ

ይህን ታሪክ በሦስት ክፍሎች ያቀረብኩት አንባብያን ከዚህ በመነሣት ያለፉት ምርጫዎች በግለሰቦች ሕይወት ውስጥ የነበራቸውን ፋይዳ እንዲያስታውሱ፣ ከተቻለም እንዲገመግሙ ለመጋበዝ ያህል ብቻ ነው። የእኔ ተሞክሮ የማይወክላቸው ብዙ ሕይወቶች እንዳሉም እረዳለሁ። ምርጫዎቹን ተስፋ ሰጪ የነጻነት ብስራቶች ሆነው ያገኙዋቸውም ይኖሩ ይሆናል። የሁላችሁንም ግለሰባዊ ልምድ ብንካፈል ፖለቲካችንን በተለየ መንገድ ለመረዳት እድል እናገኛለን። ስድብ ሳያስፈልገን፤ ስም መለጣጠፍ ሳያሻን ምርጫዎቹ በሕይወታችሁ ውስጥ የተዉትን አሻራ በፈለጋችሁት መንገድ እንድታካፍሉን ተጋብዛችኋል። ፕሮጀክቱን “ሕይወቴ በምርጫዎች መካከል” እንበለው? ሰላም ይሁን።

12 Responses to “ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 3”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

“ለዛሬ” ፊልም በስፔን የአጫጭር ፊልም ውድድር ላይ አሸነፈ

ንቦት 29 ቀን 2010 እ.ኤ.አ ታሪፋ በሚል በሚታወቀው በስፔን በተካሄደው የአጭር ፊልም ውድድር ላይ የዘላለም ወልደማርያም ፊልም ምርጥ የአጭር ፊልም አሸናፊ ኾነ። በ“Best Short Film Youth Jury Award” አሸናፊ የኾነው የዳይሬክተር እና ፕሮዲዩሰር ዘላለም ፊልም የሁለት ሺሕ ዩሮ ሽልማትም አግኝቷል። “ለዛሬ” ይህን አሸናፊነት የተቀዳጀው በታሪፋ ውስጥ ተመርጠው ከቀረቡ 15 ፊልሞች ጋራ ከፍተኛ የኾነ ፉክክር በማድረግ ነው።

ግንቦት 29 ቀን 2010 እ.ኤ.አ ታሪፋ በሚል በሚታወቀው በስፔን በተካሄደው የአጭር ፊልም ውድድር ላይ የዘላለም ወልደማርያም ፊልም ምርጥ የአጭር ፊልም አሸናፊ ኾነ። በ“Best Short Film Youth Jury Award” አሸናፊ የኾነው የዳይሬክተር እና ፕሮዲዩሰር ዘላለም ፊልም የሁለት ሺሕ ዩሮ ሽልማትም አግኝቷል። “ለዛሬ” ይህን አሸናፊነት የተቀዳጀው በታሪፋ ውስጥ ተመርጠው ከቀረቡ 15 ፊልሞች ጋራ ከፍተኛ የኾነ ፉክክር በማድረግ ነው። እነዚህ ዐሥራ አምስት ፊልሞች ከዐሥር የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ሲኾኑ ውድድሩ ከግንቦት 21 እስከ 29 ቀን 2010 እ.ኤ.አ ድረስ ሲካሄድ ቆይቷል።

በዚሁ ውድድር ላይ በምርጥ ሴት ተዋናይ የዳይሬክተር ካሮላይን ካማያ “ኢማኒ” የተባለው የኡጋንዳ ፊልም አሸናፊ ሲኾን፣ በኬንያዊው ዳይሬክተር ዋናሪ ካህዩ የተሠራው “ፍሮም ኤ ዊስፐር” የተባለው ፊልም ደግሞ በምርጥ ወንድ ተዋናይ አሸንፏል። በምርጥ ዳይሬክተር የኡጋንዳው ኢማኒ አሸናፊነቱን አረጋግጧል። በአጭር ፊልም ደግሞ ኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሞያ ዘላለም ወልደ ማርያም “ለዛሬ” በሚለው ፊልም በ”Young Jury Award”አሸናፊ ኾኗል። ቱኒዚያዊው ዳይሬክተር ዋሊድ ታያ ደግሞ “Le Icha” በሚለው ፊልሙ በምርጥ አጭር የ“RTVA” አሸናፊ ኾኖ ተመርጧል። በምርጥ ዶክመንታሪ ፊልም የሴኔጋሉ አልሳን ዲያጎ “Les Larmes De L’emigration” በሚል ፊልሙ ተሸላሚ ኾኗል። ከዚህ በተጨማሪ የታዳሚ ተሸላሚ ተመራጮች ከኢትዮጵያ “አትሌቱ” የሚለው የራሴላስ ላቀው- ደ. ፍራንክል ፊልም እና ከግብጽ በዮስሪ ናርስራላህ የተሠራው “ Ehki Shahrazade” የሚሉት ፊልሞች የተመረጡ ሲኾን በምርጥ ረዥም ፊልም የኀይሌ ገሪማ “ጤዛ” ተመራጭ ኾኗል።

በዚህ ውድድር ላይ በአጭር ፊልም ያሸነፈው “ለዛሬ” የተሰኘው ፊልም በደቡብ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ አንድ ቤት አልባ ልጅ የሚተርክ ፊልም ነው። ፊልም በጥሩ አቀራረጽ እና ውብ በኾነ መልእክቱ ስለ ዓለም አቀፉ የሙቀት መጠን መጨመር፣ አርቆ ስላለማስተዋል እና የወደፊቱን ትውልድ ባለማሰብ “በዛሬ” ላይ ብቻ መንጠልጠልን ያሳያል። ይህ ፊልም መልእክቱን ያስተላለፈው በ14 ደቂቃዎች ነው። የዚህን ፊልም ሙዚቃ የሠራው ዴቦ ባንድ እየተባለ የሚጠራው ሲኾን ተቀማጭነቱ በቦስተን ማሳቹሴትስ ነው። ሙዚቃው የኢትዮጵያውያንን የባህል ሙዚቃ እና በተለምዶ የሚታወቀውን የምዕራቡን ዓለም ኦርኬስትራ ያቀላቀለ ነው። “ለዛሬ” የሚለው ይኸው ፊልም በሚቀጥለው ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2002 ዓ.ም በ”ኢሜጅ ዛት ማተር” በኢትዮጵያ በሚካሄደው የአጫጭር ፊልሞች ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚኾንም ታውቋል።

3 Responses to ““ለዛሬ” ፊልም በስፔን የአጫጭር ፊልም ውድድር ላይ አሸነፈ”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው።

“ኢሜጅ ዛት ማተርስ” በሚል ርእስ የሚቀርብ የአጭጭር ፊልም ፌስቲቫል ከኢፌድሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ታዋቂ ከኾኑ የዓለም አቀፍ የፊልም ባለሞያዎች ጋራ በመተባበር ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2002 ዓም ድረስ በብሔራዊ ቴአትር ሊታይ ነው። የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኢሜጅ ዛት ማተር ሲኾን በዚህ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ከተለያዩ አገሮች የተሰባበሰቡ አጫጭር ፊልሞች ለዕይታ [...]

“ኢሜጅ ዛት ማተርስ” በሚል ርእስ የሚቀርብ የአጭጭር ፊልም ፌስቲቫል ከኢፌድሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ታዋቂ ከኾኑ የዓለም አቀፍ የፊልም ባለሞያዎች ጋራ በመተባበር ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2002 ዓም ድረስ በብሔራዊ ቴአትር ሊታይ ነው።

የፕሮግራሙ አዘጋጅ ኢሜጅ ዛት ማተር ሲኾን በዚህ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ከተለያዩ አገሮች የተሰባበሰቡ አጫጭር ፊልሞች ለዕይታ ይበቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ስፍራዎች የመጡ ታዋቂ የፊልም ባለሞያዎች ለምሥራቅ አፍሪካ የፊልም ባለሞያዎች ሥልጠና እንደሚሰጡ የኢሜጅ ዛት ማተር የሚዲያ ጉዳይ ሐላፊ አን ካሮላይን ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ “ዴዘርት ፍላወር” የተሰኘው እና በሕጻንነቷ የግርዛት ሰለባ የኾነችውን የሶማልያዊቷን ሱፐር ሞዴል ዋሪስ ዴሪን አስገራሚ የሕይወት ታሪክ የሚያስቃኘው ፊልም ለዕይታ ይበቃል። ዋሪስ ዴሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ዝነኛ እና ስኬታማ ከኾነች በኋላ የሴት ልጅ ግርዛትን በይፋ በማውገዝ እና ስለ በርካት ችግሮቹ በማስረዳት ትታወቃለች። በራሷ የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ አሳትማለች። ይህ መጽሐፍ በቅርቡ በሼሪ ሆርማን ዳይሬክተርነት  እና በኢትዮጵያዊቷ ሱፐር ሞዴል ሊያ ከበደ ተዋናይነት ወደ ፊልምነት ተቀይሯል።

የፌስቲቫሉ የሚዲያ ሐላፊ የኾኑት አን ካሮላይን “ይህ ፊልም ባለፈው ሚያዝያ ወር በጅቡቲ ለዕይታ በበቃበት ጊዜ በታዳሚዎች መካከል አስደሳች የኾነ የውይይት መንፈስ እንዲፈጠር ምክንያት በመኾን ስለ ሴት ልጅ ግርዛት ጤናማ ግንዛቤን ለመፍጠር አስችሏል” ብለዋል።

የፌስቲቫሉ የሚዲያ ተጠሪ እና አስተባባሪ የኾኑት የኬር አድቨርታይዚንግ እና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ካሳ “ጁን 15 ቀን 2010 ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ በብሔራዊ ቴአትር ፊልሙ ከታየ በኋላ የፓናል ውይይት ይካሄዳል። በዚህ ፊልም ላይ የታሪኩ ባለቤት የኾነችው ዋሪስ ዴሪ ከታዳሚዎች ለሚቀርብላት ጥያቄ መልስ ትሰጣለች ብለዋል”።

በዚህ የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል ላይ ላይ ከፍተኛ ሽልማት የሚያስገኝ የምሥራቅ አፍሪካ አጫጭር ፊልሞች ውድድር እንደሚካሄድም አዘጋጆቹ አስረድተዋል።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 2

ሦስት ምርጫዎች ሕይወቴን ላይመለስ ቀየሩት። የመጀመሪያው ምርጫ በአገሬ ፖለቲካ ውስጥ ያለኝን ቦታ እና ሚና የምር ማሰብ እንድጀምር ጋበዘኝ። ሁለተኛው በተስፋ እና በቀቢጸ ተስፋ መካከል ተወኝ። ሦስተኛው በፍቅር የወደኩላትን ያቺኑ አገር ትቻት ለመሰደዴ ምክንያት ሆነኝ።….ፖለቲካ ሕይወቴ ከኢሕአዴግና ከአዲሱ የአገራችን ፖለቲካ ጋራ እንዲህ ተጀመረ። ኢሕአዴግ በርእዮተ ዓለማዊ ምርጫው ለእኔ ማንነት እውቅና አይሰጥም፤ ይልቅም እኔን መሰል “አልቦ ብሔረሰብ” ወይም/እና “ድኅረ ብሔረሰብ” ሰዎች በ“እነርሱ” ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ሚና ልንጫወት እንደማንችል ያምናል፤ ስለዚህም ፖለቲካው ለእኛ ቦታ የለውም።
ክፍል አንድ ፤ ሁለት

[ማስታወሻ፡በዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ላይ አስተያየቶችችሁን ላካፈላችሁን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ። የእኔ ታሪክ ርእሰ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፤ ታሪኩ በሚያነሳቸው የተለያዩ ጭብጦች ላይ ያቀረባችኋቸው ምላሾች ግን የበለጠ ውይይት የሚገባቸው ናቸው። ይሁንና ከአስተያየቶቻችሁ በመነሣት “አልቦ ብሔር ወይም ድኅረ ብሔር” ያለኩትን ለጊዜው ስም ያልወጣለትን ማንነት “አዲስ አበባዊነት” ማለቴ ተገቢ አለመሆኑን አምኜበታለሁ። ስያሜው ማንነቱን ከአዲስ አበባ ጋራ ብቻ የሚያቆራኝና ዝግ የሚያስመስለው ነው። በዚህ ፍጥነት ሌላ ተተኪ ስያሜ ባላገኝለትም ስያሜውን ለጊዜው የምጠቀምበት የከተማ ማንነትን ወይም ድርብርብ/ብዙ ብሔረሰባዊ ማንነትን ወይም ከየትኛውም ያለመሆን ስሜትን በምርጫቸውም ይሁን በአስተዳደጋቸው ያዳበሩ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ማለቴ መሆኑን እንድታስታውሱልኝ ይሁን። በተጨማሪም “አልቦ ብሔረሰብ” እና “ድኅረ ብሐረሰብ” በማለት ልገልጸው የሞከርኩት ማንነት በመኖሩ ላይ ባልጠራጠርም አሁንም ስያሜው እያደር የሚጠራ መሆኑን ላስታውስ።]

***********************
አምስት ዓመታት አለፉ። ብዙ ተለወጥኩ። የፖለቲካው የሩቅ ታዛቢ አይደለሁም። የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ፤ ጋዜጠኛ እና በዚያውም በኩል አስተያየቴን በመሰንዘርና መረጃ በማቅረብ በአገሬ ፖለቲካ የምሳተፍ ንቁ ዜጋ ሆኛለሁ። 1997።

በግል የፖለቲካ አመለካከቴና አቋሜ ካለፈው እጅግ በበለጠ ግልጽ ሆኛለሁ፤ ወይም ወደዚያው እየተጓዝኩ ነው። በቀበሌ መታወቂያዬ ላይ ያለፈቃዴ የሚጻፈውን ብሔር ያለ ምንም ፍርሃት በላፒስ ሳጠፋ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማኝም። ክርክሬን ሊረዱ ከማይቸሉ የቀበሌ ካድሬዎች ጋራ መጨቃጨቁ ለውጥ ስለማያመጣ መታወቂያውን እንደተቀበልኩ አጠፋዋለሁ። ለካስ አንዳንዱ መፍትሔ በእጄ ኖሯል?!

ለታሪክ ጠባሳዎች እውቅና የማይሰጥና የተጎጂዎቹን ስሜት የመጋራት ትሕትና የሚጎደለውን “ኢትዮጵያዊነት” ፊት ለፊት እቃወማለሁ። በታሪክ በተለያየ መንገድ የተገፉት ወገኖቼ የሚሰማቸውን ሕመም ለመጋራት ስሞክር ጉዳዩን የራሴ ጭምር ለማድረግ በመፈለግ እንጂ እኔ ያልተነካሁ ሆኜ እያስተዛዘንኩ አለመሆኑን ማሰብ ጀምሬያለሁ። ታሪካቸው ታሪኬ ነዋ! የዚያኑ ያህልም በራሴ ማንነት (የትኛውም አካል የፈለገውን ስም ቢሰጠው) እንደምኮራ ከመናገር አላፍርም። አካባቢዬ ያወረሰኝና እኔም በፍላጎቴና በጥረቴ ያዳበርኩት ማንነቴ “አልቦ ብሔረሰብ” እና/ወይም “ድኅረ ብሔረሰብ” ስለመሆኑም እርግጠኛ ሆኛለሁ። ይህ ማንነቴ ደግሞ አሁንም በለውጥ ሒደት ውስጥ ያለ እንጂ እስከ ወዲያኛው ባለበት የሚቀጥል፣ እንዳይቀነስበት እንዳይጨመርበት ተብሎ በአደራ የተሰጠኝ አለመሆኑ የበለጠ ስሜት ይሰጠኝ ጀምሯል።

በዚያኛው ዓለም ግን ብዙ የተለወጡ ነገሮች የሉም። ፖለቲካውን የሚዘውረው ኢሕአዴግ ከ14 ዓመታት የሥልጣን ዘመን በኋላም የእኔንና የብጤዎቼን ድምጽ እውቅናና መደመጥ የሚገባው ሆኖ አላገኘውም። አሁንም ያሻውን ቅጽል እየደረተ በሚፈበርከው ስድብና አሽሙር ያራክሰን ይዟል። እኔ ብዙ ርቀት ሔጃለሁ። ዕድሜ ለራሱ ለኢሕአዴግ የአገራችንን የፖለቲካ ታሪክ በአዲስ ዐይን እንድመለከት ምክንያት ሆኖኛል። ለዚህም ማመስገን ይገባኛል። የብሔረሰብ ጥያቄን ለመረዳት ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎቹን የጥያቄውን አካሎች እስከ መቀበል ደርሻለሁ። ኢሕአዴግ እና ብጤዎቹ ግን አሁንም ከራሳቸው ድምጽ ጋራ ጥልቅ ፍቅር ውስጥ ናቸው። የሚደግፋቸው እንኳን ቢሆን ሌላ ድምጽ ለመስማት የሚችል ልብ አላገኙም።

“ለአዲስ አበቤዎች”ና የእነርሱን ሥነ ልቦናዊ ሞገድ ለሚጋሩ ዜጎች በህወሓትና በኦፌዴን፣ በኦሕዴድ እና ሶዴሕፓ፣ በኦነግ እና በብአዴን… መካከል ብዙ የይዘት/የጭብጥ ልዩነት የለም። ያለምንም ችግር አንዱ ሌላውን ሊተካው ወይም ሊያህለው ይችላል። በተቃራኒውም “ኢትዮጵያዊነት” ወይም “ኅብረ ብሔራዊ” በሚል የተሰባሰቡት ብድኖችም ከእነ ኢሕአዴግ በተሻለ ብዙ ማንነቶችንና ፍላጎቶችን የማስተናገድ ሐልዮታዊ ብቃት ቢኖራቸውም በተግባር ከዚያ እጅግ የራቁ እንደነበሩ ታዝበናል። ሁለቱም ትምህርት ያስፈልጋቸው ነበር፤ በቅጣትም በሽልማትም።

“አዲስ አበቤዎች” የአገራችንን ፖለቲካ ለእነዚህ ቡድኖች መተው እንደሌለብን ከገባን ሰንብቷል። በሁለቱም የፖለቲካ ጫፍ መሽገው የሚታኮሱት የፖለቲካ ልሒቃን ዘላቂ ፍላጎታችንን ለማስጠበቅ የሚታመኑ እንዳልሆኑ ደምድመናል። ሁለቱም ወደ መሃል እንዲመጡ ልናስተምራቸው እንደሚገባ ወስነናል። የምንጠብቀው ጊዜና አጋጣሚ ብቻ ነበር።

ከ1992 እስከ 1997 የነበሩት ዓመታት ብዙ የአገራችንን አካባቢዎች እንድጎበኝ፣ የመንግሥትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በንድፈ ሐሳብም ይሁን በተግባር እንድፈትሽ፣ በብዙ ቦታዎች የሚገኙ የመንግሥት ሐላፊዎችን እንዳገኝ፣ ተራ ከሚባሉት የከተማና የገጠር ወገኖቼ ጋራ በአካል እንድተዋወቅ የረዳኝ ነበር። በዚህ ሂደትም ከአክሱም እና ከባህርዳር እስከ ጅማ፤ ከድሬዳዋ እስከ ደምቢ ዶሎ፤ ከነቀምቴ እስከ ደሴ በተለያየ ጊዜና ምክንያት ተጉዣለሁ። በጋዜጠኝነት እና በመያድ ሠራተኝነት ያገኘኋቸው እነዚህ ዕድሎች በብዙ መልኩ ቀይረውኛል። ፖለቲካችን የቅንጦት ሳይሆን የተግባር መሆን እንዳለበትም አስረድተውኛል።

እነዚህ ዓመታት የፈጠሩት ማንነት በተለይም በ“መዝናኛ” ጋዜጣ ላይ አቀርባቸው በነበሩ “ለዘብተኛ” (እንደተመልካቹ መሆኑን ሳልረሳ) አቋሞቼ ሳይንጸባረቁ አልቀሩም። ከብዙ ልዩነቶቼ ጋራ (የምጋራቸውን አመለካከቶችም ሳላስቀር) ኢሕአዴግ ለፈጸማቸው በጎና የተሻሉ ነገሮች እውቅና መስጠት በማብዛቴ “ወያኔ ነው” የሚሉኝ አንባቢዎች እንደነበሩ አስታወሳለሁ። ብዙም ቅር አይለኝም ነበር፤ ምክንያቱም የዴሞክራሲ ሽግግር ትግልና ልምምድ ኅብረተሰባዊ መሆኑን መረዳት ችዬ ነበርና ነው።

እንዲህ እንዲህ እያልን ወደ ምርጫው ደረስን። እነሆ ምርጫ 97 መጣልን። እርሱንም ተከትሎ ቅንጅት መጣ። ጓደኛዬ ብርቱካን ሚደቅሳ በትክክል እንዳለችው ቅንጅት መንፈስ ነበር። “አዲስ አበባውያን” ለቅንጅት ድምጻችንን መስጠታችን ፈጽሞ የማንጸጸትበት እርምጃ ነው። ለምን? ይህ ምርጫ “አዲስ አበባውያን”ን በተገቢው መጠን ያሳተፈ የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ነበር። ከዚያም ባልተናነሰ ለሁለቱም የፖለቲካ ጎራዎች መልእክታችንን በማያሻማ ብቻ ሳይሆን በማያዳግም መልኩ ያደረስንበት ምርጫም ነበር።

1997 በተለይም እስከ ምርጫው የነበረው ፖለቲካዊ ድባብ በተስፋ የተሞላ ነበር። ሁለት ተዋናዮች በተለይ መስጠውኛል። አንደኛው ጋዜጦች ናቸው፤ ሁለተኞቹ ወጣት ፖለቲከኞች ናቸው። የዚያ ዓመት ጋዜጦች የተለዩ ነበሩ፤ በጥሩም በመጥፎም። በኋላ ኢሕአዴግ መንግሥታዊ እብደት ይዞት ጅምሩን ሁሉ ባይነደው ኖሮ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትና የሚዲያ ተቋማት ትልቅ ልምድ ይቀስሙበት ነበር። ይህን ስል ከጋዜጦቹ አስደንጋጭም አሳፋሪም ስህተት ይሠሩ የነበሩ መኖራቸውን በመካድ አይደለም። አንዳንዶቹ ስሕተቶችም መታረም የሚገባቸው በመሆናቸው ላይ እስማማለሁ።

ነገር ግን ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን በመለማመድ ላይ የምንገኝ እንደመሆናችን እርማቱ የመማማር ሂደት እንጂ ጦርነት የማወጅ መሆን ባልተገባው ነበር። ኢሕአዴግ ግን ከጦርነት ባልተናነሰ እልህ በጋዜጦች ላይ ዘመተ። ራሱን ለዴሞክራሲ ፈተና ያዘጋጀ ባለመሆኑም ነገሩን በትእግስትና በማስተማር መፍታት ተስኖት በጋዜጦቹ ላይ የፈሪ በትሩን አሳረፈባቸው። ዛሬም ድረስ ጋዜጦች በኢሕአዴግ አመለካከት “የጸረ…” ተቀጥላዎች ናቸው። በዚህ ጉዳይ ድርጅቱ እጅግ ቀደም ብሎ ያወጣቸው ውስጣዊ ሰነዶች የማይናወጽ የጠላትነት ፍረጃውን በግልጽ ያሳይሉ። አገሪቱ ከዚህ ስብራት ዛሬም አላገገመችም።

ሌላው አስደናቂ ነገር የወጣቶች ወደ ፖለቲካ መሳብ ነበር። እኔ እንኳን የማውቃቸው ስንት ወጣቶች ነበሩ! በወቅቱ በእውንም ይሁን በምኞታችን ተፈጥሮ የነበረው ወይም የተፈጠረ የመሰለን የነጻነት ከባቢ፣ ይህንንም ከባቢ ተጠቅሞ ለአገር አስተዋጽኦ የማድረግ ቁርጥ ፍላጎት አስገራሚ ነበር። ወጣቶች ወደ ፖለቲካ ተመለሱ ተባለ። እውነትም መመለስ ጀምረው ነበር።

በዚያ ላይ ብርሃኑ ነጋ የሚባል አንድ ሰው መጣ። ተማሪዎቹን ምሳና ቢራ በመጋበዝ ነጻነቱ የሚታወቅ፣ በአስገምጋሚ ድምጹ ኢኮኖሚክስን እና ፖለቲካል-ኢኮኖሚን ለተራው ሰው ስሜት በሚሰጥ መንገድ መተንተን የሚችል አንድ ሰው ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ አለ። ሰውየው ከየት እንደመጣና ወዴት መሄድ እንደሚፈልግ ሲናገር ሰዎች ራሳቸውን እርሱ ውስጥ ማግኘት ጀመሩ። ደነገጡም። በቃ የምርጫ 97 ፊሽካ በይፋ ተነፋ። (መቼም ይህን ስል ሌሎቹ ፖለቲከኞች ቁልፍ ሚና አልነበራቸውም ማለቴ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሌላው ቢቀር ልደቱን እና ኢንጂነር ኀይሉን መጥቀስ ይቻላል። የአዲሱ ፖለቲካ የፖስተር ሰው ግን “ብሬ” ነበር።)

ሌላው ቢቀር ለእኔ ትውልድ ሰዎች የብርሃኑ ዓይነት የፖለቲካ ሰው አይተን አናውቅም። ድንቅ የመናገር ተሰጥኦ እና ችሎታ ስላለው ብቻ ግን አይደለም። ብርሃኑ የዘመኑን መንፈስ የሚወክሉ ንግግሮችንም ማቅረብ ይችል ነበር። ሲናገር ተዘጋጅቶ አስቦበት እንደሚመጣ ያስታውቃል። አድማጮቹን እንደሚያከብር ይታያል። ልዩነቶችን ለማቻቻል ደፋር ይመስላል። ብርሃኑ ለወጣትም ለሽማግሌም ጆሮ የሚሆን የቋንቋ አጠቃቀም አለው። ከልቡ የሚናገር ይመስላል። ተስፋ አለው፤ ተስፋውን ማከፈል ይፈልጋል። ፍቅርና በጋራ መኖር የንግግሮቹ ጉዳዮች ናቸው። ጥይት ስለማይተኮስበት የነጻት ትግል ሲያወራ አድማጮቹን በተስፋ ሞላቸው። ሰውየው በእውነት እነዚህን ሁሉ ይሁን አይሁን ለውጥ አየመጣም። ከሆነ እሰየው ነው፤ ካልሆነም ይህን “ምትሃት” መፍጠር ችሏል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ብርሃኑን ሊቀናቀን የሚችል አጠቃላይ ፖለቲካዊ ተክለ ስብእና ያለው ተፎካካሪ አልነበረውም። ተምሯል፤ ያስተምራል፤ በኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ማኅበር ባሳየው ብቃት ምሁራዊ ተአማኒነትን ማግኘት ጀምሯል፣ በሰብአዊ አቀራረቡ ቀላል የሚባል ሰው ነው። ውጤታማ ከሚባል ቤተሰብ የመጣ ነው። ብርሃኑ ጉራጌ መሆኑ ከብሔረሰብ ፖለቲካ “ነጻ” ተደርጎ እንዲታይ ተጨማሪ ዕድል ሰጥቶታል። ሌላ ማን አለ?

መለስ ዜናዊ። እርሳቸው ለአደባባይ የምርጫ ፖለቲካ ፈጽሞ የሚሆኑ ሰው አይደሉም፤ ፈርዶባቸው እንጂ። ቃላት አስተካክለው ይደረድራሉ እንጂ የሚደመጥ አቀራረብ የላቸውም (እርግጥ “የቅንድባቸው ውበት” ትዝ ብሎን አያውቅም ነበር)። ንግግራቸው በተለይ ደጋግመው ሲያዳምጡት ሩቅ፣ ደረቅና መንቻካ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እጅግ ሲበዛ ጨዋነት ይጎድለዋል፣ የሚያስደነግጥ አነጋገርም አይታጣበትም። አንድ ወዳጄ በአቶ መለስን ንግግሮች ለመመሰጥ ሁለት ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው በተረብ መልክ ይናገር ነበር። ለፖለቲካ ወይም ለአቶ መለስ ለራሳቸው እንግዳ መሆን (አለማወቅ) እና/ወይም የእርሳቸውን ንግግር ማድነቅና መረዳት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የህልውናህ መሠረት መሆን ናቸው።

ያንጊዜም ሆነ ዛሬ ፍቅርና ተስፋ የሚባሉትን ቃላትም ሆነ ሐሳቦች (ኮንሰፕትስ) በመለስ ንግግሮች ውስጥ ፈልጌ አገኘሁ የሚል ሰው ተገኝቶ አያውቅም። ለተፎካካሪዎቻቸው ቦታ መስጠትና መታገስ የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደማያውቁ የንግግራቸው ድምጸትና ቃና ያሳብቅባቸዋል። ለብዙ ዓመት ስለተናገሩ ይሁን ወይም ስሜታቸውን መግለጽ ስለማይችሉ መለስ እውነት የሚናገሩ አይመስሉም። እውነት መለስ “ግማሽ መንገድ ላይ እንገናኝ” እያሉ ዘንባባ ሲያነጥፉ ማን አምኗቸው ያውቃል? ግን እኮ የምራቸውን ሊሆን ይችላል። በዚህ በኩል የምሬን ያሳዝኑኛል። ሥራ ሆኖባቸው የሚናገሩ እንጂ ከጉዳዩ ጋራ አንዳች ሰብአዊ ግንኙነት ያላቸው አይመስሉም። በአጭሩ አቶ መለስ ሲናገሩ ሰው ሰው አይሉም። መለስም በእውነት እነዚህን ሁሉ ይሁኑ አይሁኑ ለውጥ አያመጣም። ከሆነ ያሳዝናል፤ ካልሆነም ይህን በምርጫ ወቅት አስፈላጊ የሆነ የፖለቲካ “ምትሃት” መፍጠር አልቻሉም። አቶ መለስ የፈጠሩት የፖለቲካ ምትሃት ተቃራኒውን ነው። ሌላው የኢሕአዴግ የምርጫ ፊታውራሪ አቶ በረከት ነበሩ። ብዙ ማለት የሚያስፈልግ አልመሰለኝም።

ልደቱ አያሌው። ልደቱ በብርሃኑ ጥላ ተሸፍኖ የቀረ ወጣት ፖለቲከኛ ነው፤ ትልቋ ኮከብ ትንሿን እንደምትሸፍናት። ምናልባት እርሱ ከቅንጅት በመነጠሉ ከጥላው ያመለጠ ይመስለው ይሆናል፤ አልመሰለኝም። ክፉ አጋጣሚ ሆነና የብርሃኑ ኮከብ በደመቀችበት ወቅት እርሱም መድረኩ ላይ አብሮት ቆመ። በዚያ ላይ ዝና ለብርሃኑ በነበረችበት ጊዜ ተጣሉ። ከዚያ በተቀረ ልደቱ ግማሽ መለስ ግማሽ ብርሃኑ ይመስለኛል። ይሄ ጥሩ ይሁን መጥፎ እስከ አሁን አልገባኝም። አቶ ኀይሉ ሻውልም ይሁኑ ሌሎቹ የቅንጅት የምርጫ ምልክት የሆኑት እጅግ በኋላ ነው። ስለዚህ ውድድሩም ውስጥ አልነበሩበት። እነ ፕ/ር በየነ እና ዶ/ር መረራ ራሳቸውም ቢሆኑ ወደዚህ ፉክክር እንግባ ብለው አያውቁም

የብርሃኑ አይነት በመግነጢሳዊ ንግግር ሐሳብን የማጋራትና የመማረክ ችሎታ ያላቸው ፖለቲከኞች በየስንት ዓመቱ እንደሚገኙ አላውቅም። የዛሬው ብርሃኑ ከዚያን ጊዜው ብርሃኑ ጋራ ያለውን ዝምድና መፈለግ የተመልካች ፋንታ ነው። የብርሃኑ እና የልደቱ ሚና ብዙ ወጣቶችን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ መማረኩ ግን ከምርጫው ትዝታዎቼ አንዱ ነው።

ለብዙዎቻችን የምርጫ 97 መንፈስ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የነጻነት እና በአጠቃላይም የአዲስ ተስፋ ጅማሬ ነበር። በታሪክ አጋጣሚ ሊባል በሚችል ሁኔታ የዚህ አዲስ ተስፋ ተምሳሌት ቅንጅት ሆነ።
ለማንኛውም ምርጫው ተካሄደ። መቼም የሌላውን መናገር ባልችል የሰፈሬ ምርጫ የፍቅር ነበር። ሰው ለምን እንዲህ ጨዋ ይሆናል? ለምን በጣም ሥነ ስርዓት ማክበርና ማስከበር ያበዛል? ይሄ የጤና ነው? ዛሬም ሆነ ያን ጊዜ ምርጫ 97ን እውን ላደረጉት ሁሉ ክብርና ምስጋናዬ አይለያቸውም፤ ኢሕአዴግንም ጨምሮ። እነሆ የምርጫው ቀን መሸ፤ እንደመሸም ቀረ። እስከ አሁንም አልነጋም።

ለእኔ የምርጫ 97 እውነተኛ ተምሳሌት ሚያዝያ 30 ነው። ሰልፉ ለቅንጅት ስለነበረ ግን አይደለም። ሙሉ ነጻነት የሚነበብባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ደስተኛ ፊቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ያን ዕለት ስለነበር ነው። ብዙ ነጻነት የሚሰማቸውን ሰዎች አንድ ቦታ ማየት እንዴት ደስ ይላል? በነጻነት ተስፋ የተሞሉ ወጣቶችን መመልከት እንዴት ድንቅ ነው? ይህን እውን ያደረጉ የፖለቲካ መሪዎች (ከኢሕአዴግም ከተቃዋሚዎችም) መኖራቸው እንዴት መታደል ነው?

የሆነው ሁሉ በብዙ ያማሩ ቃላት መግለጽ ይቻላል። እጅግ ድንቁ አገላለጽ ግን ዕንባ ነው። ዕንባ ያረገዙ ብዙ ውብ ዐይኖችን ማየት፤ ዕንባቸውን መቋጠር ያቃታቸውን የጎልማሶችና የአዛውንቶችን ዐይኖች መመልከት፤ በጥላቻና በጥርጣሬ ሳይሆን በክብርና በመንከባከብ ዓይን የሚመለከቱ የፖሊስ ዐይኖችን በአገሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ…።

ይህ ዕንባ ግን ብዙ አልቆየም። በሳምንት ዕድሜ ተባብረን ቀጨነው። ጨቃኞች ነን፤ ተስፋን መግደል እንችልበታለን። ክፉዎች ነን የገነባነውን ማፈርስ እንወዳለን። ንፉጎች ነን፤ ከእኛ ሳይቀነስ ሌሎች በማግኘታቸው እንደንግጣለን። እናም በኢሕአዴግ ቆራጥ አመራር የምርጫ 97ን ተስፋ ሰቀለነው። ንጹሐን ተገደሉ፤ መገደላቸው ትክክል እንደነበረ በአደባባይ ተነገረ። ሕይውት ራሷ ፍርሃት ሆነች። ሁላችንም ፈራን፤ ሁላችንም። ገዳይም ተገዳይም እኩል ፈሩ። ኢሕአዴግ ኪሳራችን ያነሰን ይመስል የቅንጅትን መሪዎችና ጋዜጠኞችን በጅምላ አሰረ። ከማሰሩ ደሞ የክሱ ዓይነት ባሰ። የኢሕአዴግ ታማኝ አገልጋይ ያልሆነ ወይም ፓርቲውን በምንም መልኩ ሊጎዱ እንደማይችሉ ከታመነላቸው ጥቂት ምርጦች በቀር ሁሉም ሰው በመሠረቱ “ተጠርጣሪ ወንጀለኛ” ሆነ ወይም እንደዚያ እንዲያስብ ተደረገ። ሰብአዊ መብት፣ ነጻነት…የሚባለው ፉከራ በሂደት ድምጹ ጠፋ።

ጨዋታ ፈረሰ፤ ዳቦው ተቆረሰ…አልን። የሆነውንና የተደረገውን በብዙ የኀዘን ቃላት መሳል ይቻላል። እጅግ ድንቁ ስዕል ግን ዕንባ ነው። በፍርሃትና በዕንባ የተሞሉ የወጣቶች ዐይኖች፤ በዕንባ የራሱ የሚንቀጠቀጡ የእናቶችና የእኅቶች ከንፈሮች፤ በተስፋ መቁረጥ የደረቁ የአባቶች ዐይኖች…ለማየት የሚያስፈሩ “የአግአዚና የፌዴራል” ዐይኖች። ሁለቱንም ዕንባዎች አውቃቸዋለሁ። የወጣትነት ዕንባዎች ስለሆኑም ትዝታቸው ቅርብ ነው። ከባለቤቴ ተደብቄ ወይም የተደበቅሁ መስሎኝ ያነባኋቸው ስለሆኑ አልረሳቸውም፤ እርሷ አታለቅስ ይመስል።

ምርጫ 97 ጥልቅ እንቆቅልሽ ሆነብኝ። የገባኝ በመሰለኝ መጠን የማልመልሰው ጥያቄ ይመጣል። ምንድን ነው የሆነው? አንድ አብሮ የመኖር የመንግሥትነት ረጅም ታሪክ ያለው ማኅበረሰብ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዴት ከአንድ የስኬት ጫፍ ወደ ሌላ የውድቀት አዘቅት ራሱን ሊወረወር ይችላል? ይህ የግለሰቦች ብቻ ችግር ነውን? ስኬቱን እውን ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደምን በራሳቸው ስኬት ደንግጠው የገነቡትን ለማፍረስ ተፋጠኑ? ስኬቱን አይፈልጉትም ነበር ማለት ነው? እውነት ይህ ማኅበረሰብ ጤናማ ነው? ዴሞክራሲ እና ነጻነትንስ የምር ይፈልገዋል? ታዲያ ለምን ስኬቱን ሳያፈርስ ልዩነቶቹን የሚፈታበት መንገድ ሳያገኝ ቀረ? ለመሆኑ በዚህ ያተረፈው ማነው? የከሰረውስ? ጥፋቱንስ በአንድ ወገን ላይ ደፍድፎ መቀመጥ ይገባል? በአገር ደረጃ የምርጫው መነቃቃት የፈጠረውን ተስፋ ተከትለን ስንተም ሳናስበው የረሳናቸው፣ የገፋናቸው፣ ስጋት የሆንባቸው ወገኖቻችን ይኖሩ ይሆን? ጥያቄው ብዙ ነው። የዚህ ጤናው የተጓደለ፣ ሕልሙ ያልሰመረለት ማኅበረሰብ አባል መሆኔ እውነት ነው። አንዳች ትርጉም ያለው ነገር ማድረግ እችል ይሆን? የፖለቲካ ሕይወት በተስፋና በቀቢጸ ተስፋ መካከል ዥዋዥዌ መጫወት ሆነ ማለት ነው? ምርጫ 97 እዚህ የጥያቄ ገበታ ላይ ትቶኝ/ን ሔደ።
ምርጫ ሁለት፤ አበቃ።

(ምርጫ 3 ይቀጥላል።)

22 Responses to “ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 2”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 1

ሦስት ምርጫዎች ሕይወቴን ላይመለስ ቀየሩት። የመጀመሪያው ምርጫ በአገሬ ፖለቲካ ውስጥ ያለኝን ቦታ እና ሚና የምር ማሰብ እንድጀምር ጋበዘኝ። ሁለተኛው በተስፋ እና በቀቢጸ ተስፋ መካከል ተወኝ። ሦስተኛው በፍቅር የወደኩላትን ያቺኑ አገር ትቻት ለመሰደዴ ምክንያት ሆነኝ።….ፖለቲካ ሕይወቴ ከኢሕአዴግና ከአዲሱ የአገራችን ፖለቲካ ጋራ እንዲህ ተጀመረ። ኢሕአዴግ በርእዮተ ዓለማዊ ምርጫው ለእኔ ማንነት እውቅና አይሰጥም፤ ይልቅም እኔን መሰል “አልቦ ብሔረሰብ” ወይም/እና “ድኅረ ብሔረሰብ” ሰዎች በ“እነርሱ” ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ሚና ልንጫወት እንደማንችል ያምናል፤ ስለዚህም ፖለቲካው ለእኛ ቦታ የለውም።

ሦስት ምርጫዎች ሕይወቴን ላይመለስ ቀየሩት። የመጀመሪያው ምርጫ በአገሬ ፖለቲካ ውስጥ ያለኝን ቦታ እና ሚና የምር ማሰብ እንድጀምር ጋበዘኝ። ሁለተኛው በተስፋ እና በቀቢጸ ተስፋ መካከል ተወኝ። ሦስተኛው በፍቅር የወደኩላትን ያቺኑ አገር ትቻት ለመሰደዴ ምክንያት ሆነኝ።

ኢሕአዴግ በ1983 ሥልጣን ሲይዝ እኔና ጓደኞቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነን። የመንግሥት ለውጡን ተከትሎ ረጅም መንገድ በእግራችን እየተጓዝን፣ አለዚያም ኳስ ተጫውተን ደክሞን ስንመለስ፣ አለዚያም በአንደኛችን ቤት ተሰብስበን ስናወካ ፖለቲካ ቀልባችንን መሳብ ጀምሮ ነበር። ምን የማናወራው ነገር ነበር? ፌዴራሊዝም፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ፣ ሃይማኖት፣ መለስ ዜናዊ እና መንግሥቱ ኀይል ማርያም፣ ቡትሮስ ጋሊ እና ኢሳይያስ አፈወርቂ…። የመንግሥቱ ኀይለማርያምን መሄድ የሰማነው ስታዲየም ኳስ ልንመለከት ሄደን ነው። ብዙም ቅር አላለንም፤ እንዲያውም በግድ ታፍሶ የመዝመት አደጋ እንደተወገደልን ስናስብ የበለጠ ነጻነት ተሰምቶናል። እርግጥ አዲሶቹን መሪዎችም አናውቃቸውም፤ ስለእነርሱ የማይወራም አልነበረም። ቢሆንም ግን ዕድል ሊሰጣቸው እነደሚገባ አምነናል። ያ ልጅነት!…አለ ሙሉቀን መለሰ።

ጊዜውም ሄደ…ነጎደ። ብዙ ነገር ሆነ። የሽግግር ትውልድ የሆነው የእኔ ዘመን ወጣት ግራ መጋባቱ አልቀረለትም- በሁሉም ነገር። ተስፋና እንጉርጉሮ የየዕለት እጣችን ሆነ። ሁለቱም በቅርብ ያሉ ጉዳዮች ናቸው…በቀላሉ የሚገኙ። ሕገ መንግሥት ሊጸድቅ ነው ተብሎ ብዙ ሽር ጉድ ተባለ፤ ዝርዝሩ ባይገባንም በመንግሥቱም ጊዜ ተመሳሳይ ሽር ጉድ ነበር። የሁለቱ ሕግጋተ መንግሥት ልዩነት ብዙ ባይገደንም የታሪኩ ተመልካቾች ሆንን።

ምርጫም ሆነ…ምርጫውን የምር የወሰደ አንድም የሰፈራችን ሰው ትዝ አይለኝም። ከዚያ ይልቅ ሕገ መንግሥቱ በጸደቀ ዕለት በጉባኤው ፊት የዘለሉት ሰው የበለጠ ትዝ ይሉናል። ብቻ “አዲሶቹን ሰዎች ገና አላወቅናቸውምና የሚሉትን እናድርግ” በሚል ፍርሃት ሰዎች ሳይመርጡ አልቀሩም።
ቀስ በቀስም የሰፈራችን አልፎም የከተማችን አዋቂዎች ሕይወት የብሔረሰብ ውጥረት በስስ ክንዱ ሲነካው ይታወቀን ጀመር…ለወጣቶቹ። አፍ አውጥተን ባናወራም “እኔ ምንድነኝ?” ብሎ መጠየቅ ተጀመረ። ይህ ትዝ ያላለው ደግሞ በአዲሱ ትምህርት የተነኩ ጓደኞቹ ያስታውሱታል። ደግነቱ በዚያም ይቀለዳል… “አንተ ምንድነህ?”… “እንጃ”… “አንተ ማን ነገረህ?” ሕይወት እና ማንነት አዲስ ቀለም አገኙ…ተሰጣቸው…ለእኛ!

ሌላ ምርጫ መጣ። 1992። የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ቀበሌ ሄድኩ። ከቀበሌያችን በረንዳ ላይ የማይነቃነቁትን ዝነኛ የቀበሌ ሰው አገኘኋቸው። ይዘውኝ ገቡ። ስም፣ የቤት ቁጥር…ግድግዳውን ተደግፈው ማርጀት የጀመሩ ፋይሎችን እያየሁ እመልሳለሁ፤ እርሳቸውም ልክ እንደማያውቁኝ ሆነው ይጠይቃሉ፤ ይጽፋሉ። ነገሩ ገብቶኛል፤ አጠገባቸው ያለችውን አዲስ የቀበሌ ሹመኛ ፈርተው ነው እንጂ እርሳቸውስ እንዲህ አልነበሩም። ሴትየዋ ብዙም የማናስታውሳት የቤት እመቤት ነበረች፤ ድንገት ፖለቲከኛ ብቻ ሳትሆን የቀበሌው አዛዥ ናዛዥ የሆነችበትን ምክንያት ሲታማ ሰምተናል። ለእኔ ብዙ ግድ የሚሰጠኝ ግን አልነበረም።

ሰውየው ጥያቄያቸውን ቀጥለዋል፤ “ብሔረሰብህ ምንድን ነው?” ደነገጥኩ። “ሰው ስምና የቤት ቁጥር ጠይቆ ሲያበቃ ዘሎ እንዲህ ያለ መልስ የሌለው ጥያቄ ያቀርባል?” አልኩ በልቤ። ጥያቄው ከዚህ በፊትም ቀርቦልኝ ያውቃል። የዚያን ቀኑን ያህል ግን ስሜቴን ነክቶት አያውቅም። “የምን ብሔረሰብ? እኔ ብሔረሰብ የለኝም፤ ከፈለጉ ትልልቆቹን ጠይቁ” አልኩ የምነተፍረቴን። “መስፍኔ” አሉኝ ሰውየው በምናውቀው ቅላጼያቸው። “ሳላውቅህ ቀርቼ አይደለም ይህን ሁሉ የምጠይቅህ፤ ጊዜው ተቀይሯል…አሁን ብሔረሰብህን ካልሞላሁት ካርዱን ልሰጥህ አልችልም። ፎርሙ ሁሉ ተቀይሯል እኮ…አታየውም…” ምክርም ልመናም ይመስላል። የድንጋጤም ቢሆን ትንሽ መከራከር አለብኝ።

“ብሔረሰብ መምረጥ እችላለሁ?”
“አትችልም። ብሔረሰብማ አይመረጥም።” (እንደእውነቱ ግን መምረጥ ቢቻል እንኳ የምመርጠው አልነበረኝም። የምፈልገው ቢኖርማ ኖሮ ዝም ብሎ እገሌ ነኝ ማለት ነው፤ ሌላ የምርመራ ውጤት አቅርብ አልባል?)
“ኢትዮጵያዊ ወይም አዲስ አበባ የሚባል ብሔረሰብ የለም?”
ጎልማሳው ሰው እና ሴትየዋ ሳቃቸውን መቆጣጠር የቻሉ አልመሰለኝም። ምስኪን እኔ!

ስለብሔረሰብ ማንነት ቀድም ብሎም ብናወራም ጥያቄው በዚህ መልኩ መምጣቱ በጣም ቆጨኝ፤ ረበሸኝ። ሰውየው የሚያውቁት እናቴን ብቻ ስለነበር የእርሷን ብሔር ለእኔም ሰጡኝ። ልኬ ይሁን አይሁን ለእርሳቸው ጉዳያቸው አይደለም። ዋናው ነገር የዚያ ብሔር “ደም” እኔም ውስጥ እንዳለ በተሰጣቸው መመሪያ መደንገጉ ነው። እርሳቸው የተባሉትን ፈጸሙ እንጂ ምን አደረጉ? አባቴን ቢያውቁት ኖሮ ደግሞ ዛሬ በመንግሥት መዝገብ ውስጥ ያለው “ማንነቴ” ሌላ ይሆን ነበር። ይህን የደረሰብኝን “እንግልት” በቁጭት ከነገርኳቸው ጓደኞቼ አንዱ ይህንኑ ሽሽት ሳይመዘገብ ቀረ። ዋ ልጅነት…አለ…

ብሔረሰባዊ ማንነት ለእኔ ትርጉም አልነበረውም። ስሙ ምንም ይሁን የነበርኩትና ያለሁት ሰው ማንነት ተስማምቶኝ ነበር። ሌሎች ስለሚመርጡት ማንነትም እንደማያገባኝ አውቅ ነበር። ላለው ማንነቴ (ስም ከሌለው) አዲስ ስም መስጠት ይሻላል ወይስ የማይገባኝን ማንነት እኔ ላይ መጫን? ትርጉሙ ባይገባኝም ብሔረሰብ ኖረኝ። እርግጥ ሁላችንም እንደዚህ አልነበርንም። ጥቂቶቹ የሰፈራችን ልጆች ስለብሔረሰብ ማንነትና ጥያቄ ከእኛ የተለየ መረዳት እያዳበሩ ነበር። ብሔረሰባዊ ማንነታቸውን ያለፍርሃትና ያለሃፍረት በነጻነት ሲናገሩ ቅሬታ አይሰማኝም ነበር። ኦሮሞ ነኝ፤ አማራ ነኝ፤ ጉራጌ ነኝ፤ ትግሬ ነኝ…ሲሉ ቅሬታ ተሰምቶኝ አያውቅም። ደስታቸው ደስታዬ ነው። ኩራታቸው ኩራቴ ነው። ነገር ግን እኔ አንድ ብሔረሰብ የለኝም፤ ወይም በአንድ ጊዜ የብዙ ብሔረሰብ አባል እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሁሉንም እንደሆንኩ ወይም አንዳቸውንም እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። ይህ የማን ጥፋት ነው?

ይህ ጥያቄ ፖለቲካን በንቃት እንድንከታተለው ገፋፋን፤ ከኳስ ጨዋታ ግን አልተለየንም። በሒደት የመለስን የንግግር ችሎታ ማድነቅ ጀምረን የነበርን ወጣቶች ሰውየው በእኛ ማንነት ላይ ባለው (መቼም ያን ጊዜ አንቱ እያልን አናወራም) አቋም የተነሣ ክፉኛ ጥርጣሬ ይገባን ጀመር።

በተደጋጋሚ በሚያደርገው ቃለ ምልልስ በብሔረሰቦች መብት ላይ የሚያንጸባርቀው ሐተታ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስገኝለት አካባቢ ነበር። እኛን ግን እስከወዲያኛው እያጣን ነበር። ገባውም አልገባውም በየቃለ ምልልሱ በማናውቀውና በአብዛኛውም በማያገባን ጉዳይ የማያወርድብን ስድብና ዘለፋ አልነበረም። “ለእርሱ ሁል ጊዜም ከፊቱ የሚታየው መንግሥቱ ኀይለማርያም ወይም የሆነ ባላባት ብቻ ነው” እያልንም እንተቸው ገባን፤ እኛን የሚሰማበት መንገድም ፍላጎትም ያለው ባይመስለንም ።
እኛ ለአቶ መለስና ለተከታዮቹ ዕድል ልንሰጣቸው፤ ስጋታቸውን በቅንነት ልንካፈላቸው ዝግጁ ነበርን። ነገር ግን እነርሱ በሚገነቧት “አዲስ” ኢትዮጵያ ቦታ እንደሌለን በተለያየ መንገድ እንደተነገረን ተሰማን። የመገለል ስሜትም ይጎበኘን ጀመር። ደግነቱ የኳስ ፍቅራችን ሁሉንም ነገር ለብዙ ሰዓታትና ቀናት ያስረሳናል። ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሕመምን በኳስ ማስታገስ/መርሳት የጀመርነው ያን ጊዜ ይሆን እንዴ?

ሁሉም ነገር “ብሔረሰብ ላላቸው” ብቻ የተፈቀደ መሰለ። የአንዱ ብሔረሰብ አባልነት የማይሰማን ወይም የሁሉም የሆንን የሚመስለን “አልቦ ብሔረሰብ” ሰዎች ያለ ጥፋታችን ማፈርና መሸማቀቅ ጀመርን። ሕይወትም የብሔረሰብ ማንነት ፖለቲካ ትኩሳትን ተከትላ መልኳን በመጠኑ መቀየር ጀመረች። በክፋት፣ በንቀት ወይም በፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ሳይሆን በቅን ኅሊናችን ብሔረሰባዊ ስሜት ማስተጋባት ያልቻልን/ያልመረጥን ሰዎች የቀበሌ ካድሬዎች ቀንደኛ ጠላት ተደረግን። መታወቂያችን ላይ የብሔር ስም በመጻፉ ጥያቄ በማንሳታችን “ነፍጠኛ”፣ “አማራ” (እርሱም ስድብ ሆኖ ነበር ለካ!) እና “ደርግ” ተባልን። እንዲህ እንዲሰማኝ የሚያደርግ ስሕተት የሰራሁት መቼ ነው? ስሕተቱስ ምንድን ነው? በተለየ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሔር አባልነት ባይሰማኝ የእኔ ጥፋት ነው? ሲጀመርስ ጥፋት ነው?

ይህን ተከትሎ የመጣው ምርጫ ለእኔና ለጓደኞቼ የመጀመሪያችን ነበር፤ 1992። የምርጫ ቅስቀሳው ብዙም ስሜት የሰጠን አልነበረም። ይልቅ አዋቂዎቹ የሰፈራችን ሰዎች ቀስ በቀስ ከየብሔር አቻዎቻቸው ጋራ ለየብቻ መሰብሰብ መጀመራቸውን በግልጽ ማየት ጀምረናል። ይህን የሚያደርጉት ጊዜውን መስሎ ለማሳለፍ ይሁን ከልብ አምነውበት ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። በተቃራኒውም በብሔረሰብ መደራጀትን በመቃወም “ኢትዮጵያዊነት” በሚል መሰባሰብ የጀመሩም ነበሩ። ግራ ተጋብቶ ግራ በሚያጋባው በዚህ የፖለቲካ ሽግሽግና ለውጥ ውስጥ እኛ ለእጣችን ተትተናል፤ ያስታወሰንም ያለ አይመስልም።

እኛ የወደፊቱ ያሳስበናል፤ ፖለቲካው በትናንት ጉዳይ እየቀለጠ ነው። ከዚያ ይልቅ ፖለቲካዊ አለዚያም ኢኮኖሚያው ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ብሔረሰባቸውን በየሳምንቱ በሚቀያይሩ ሰዎች መቀለድ አዲሱ ፖለቲካ በቀልድ መልክ እንዲገባን የሚያግዘን ነበር። በመጨረሻ ግድግዳው ላይ የተጻፈልን መልእክት ግን አጭርና ግልጽ ነው፤ “ፖለቲካው ‘ለአልቦ-ብሔረሰቦች’ ቦታ የለውም!”

የፖለቲካ ሕይወቴ ከኢሕአዴግና ከአዲሱ የአገራችን ፖለቲካ ጋራ እንዲህ ተጀመረ። ኢሕአዴግ በርእዮተ ዓለማዊ ምርጫው ለእኔ ማንነት እውቅና አይሰጥም፤ ይልቅም እኔን መሰል “አልቦ ብሔረሰብ” ወይም/እና “ድኅረ ብሔረሰብ” ሰዎች በ“እነርሱ” ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ሚና ልንጫወት እንደማንችል ያምናል፤ ስለዚህም ፖለቲካው ለእኛ ቦታ የለውም። ቢቻል ማንነታችንን እያጥላሉ ወደ አንዱ ጫፍ ሊገፉን ይፈልጉ ይሆናል፤ ካልተቻለም እንደሌለን ቆጥረው ፖለቲካቸውን ይቀምራሉ። አስቂኙ ነገር እኔን መሰል (በታሪክ አጋጣሚም ይሁን በምርጫቸው) “አልቦ ብሔረሰብ” የሆኑት ዜጎች ብዛት የፓርላማ መቀመጫ ከተሰጣቸው አንዳንድ ብሔር/ብሔረሰቦች በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ደግነቱ ለካስ መቆጠርም አንችልም፤ መቁጠሪያው አያውቀንማ!

የነበረን አማራጭ ብዙ አይደለም። ለእኛ የተሻለ ቦታ ያላቸው የሚመስሉት “ኅብረ ብሔራዊ” በመባል የሚጠሩት ወይም ራሳቸውን የሚጠሩት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው። እነርሱም ቢሆኑ ስለ እኔ ብጤው “አገር አልባ” ትውልድ ስለማሰባቸው እርግጠኞች አልነበርንም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ግን እኛን ሊያስገባ የሚችል ቦታ አላቸው፤ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ። ምርጫው ሲቃረብ የአሁኑ ኢዴፓ መኖሩን ሰማን።

ካልተሳሳትኩ በሰፈራችን ስለ ፓርቲው ሲናገር የሰማነው አብዱራህማን አህመዲንን ነበር፤ አብዱራህማን 22 ማዞሪያ በጎረቤት ቀበሌ ነዋሪ ነበር። እንኳን ስለ ርእዮተ ዓለማቸው እና ሰለ ፖሊሲዎቻቸው ዝርዝር ቀርቶ ስላቀረቡት እጩ እንኳን ግድ አልነበረንም። እውነትም እጩዋቸው ማን እንደሆነ ማስታወስ አልቻልኩም። እኔና ጓደኞቼ ለኢዴፓ ድምፅ ሰጠን። ያው እንደምንጊዜውም ኢሕአዴግ አሸነፈ ተባልን። አልተናደድንም። ኢዴፓ ተሸነፈ ተባልን። አልገረመንም። እኛም ተሸነፍን ማለት ነው?

ይህ ወቅት የማንነት ሐሳሰዬ ጅማሬ ሆነ። መጻሕፍት አነበብኩ፤ የውይይት “ክበቦች”ን ጎበኘሁ፤ ሳናውቃቸው በሚመሠረቱ ቡድኖች ክርክር ተሳተፍኩ፤ ምስጢሩ ሃይማኖት ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ብዬም ሞከርኩት። ታሪክን፣ ፖለቲካን፣ ብሔረተኝነትን…ለመረዳት የተደረገ አካባቢው ለራሱ እጣ የተተው የአንድ ወጣት ረጅም ጉዞ። ከሁሉም በላይ ደግሞ “እኔ የት ነኝ?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኝት በተደረገ ሐሰሳ ውስጥ አለፍኩ። ምስጋና ለዚያ ጥያቄ ይሁንና ዛሬ እኔ እኔን ሆኛለሁ። በነበረውና አሁን ባለው (አልቦ ብሔረሰብ ወይም/እና ድኅረ ብሔረሰብ) ማንነቴ አልጠራጠርም፤ በዚህ ማንነቴ በአገሬ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ መብቴን ከማንም በደጅ ጥናት የማላገኘው መሆኑን ከነክብሩና ከነሐላፊነቱ እረዳለሁ።

በዚህ ማንነቴ በብሔረሰብ ማንነታቸው በሚኮሩ ወንድሞቼና እኅቶቼ ላይ ቅንጣት ታህል ጥላቻ ወይም ክፉ ስሜት የለኝም። ከእነርሱ ጋራ የታሪካችንን ጠባሳዎች በቁጭትና በፍቅር አስታውሳለሁ። ታሪክን ወደ ኋላ መልሶ ማስተካከል ባይቻልም ጠባሳው እንዲሽር አብሬያቸው እቆማለሁ፤ ያለ አንዳች የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት። እነዚህን ወንድሞቼን ልቤን ከፍቼ፣ ኅሊናዬን አንጽቼ በቅንነት ልረዳቸው እንደሞከርኩትና እንደ ተቀበልኳቸው ሁሉ እነርሱም በፈንታቸው ለእኔና ለብጤዎቼ ይህንኑ እንዲያደርጉ ብጠይቃቸው ምን ነውር አለበት?

ጥያቄዬ ብዙም ከባድም አይደለም። በጠባቡ የተተረጎመ ብሔረሰባዊ ማንነት እንደሌለው አንድ ሰው ተቀበሉኝ/ን። ይህንንም የእናንተን ብሔረሰባዊ ማንነት ወይም ለእርሱ ያላችሁን ልባዊ ክብር በመቃወም ወይም በማቃለል የተፈጠረ ተፎካካሪ ማንነት አድርጋችሁ አትመልከቱት። በእኔና በብጤዎቼ ማንነት ላይ የራሳችሁን ትርጉም አትጫኑበት። የሚሰማችሁን ስትነግሩን እንዳመንናችሁ፤ ስለማንነታችን የሚሰማንን ስንነግራችሁ እመኑን እንጂ አትጠራጠሩን። የእናንተ ክቡር ብሔረሰባዊ ማንነት ከእኛ ማንነት ውጭ ይኖራል፤ የእኛም ማንነት እንዲሁ ለብቻው ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሁለቱ ማንነቶች አንዱ በሌላው ውስጥ ዘሩን እንደሚያገኝ ይሰማኛል።

ይህ የእኔ/ኛ ማንነት ምንድን ነው? ምን ስም ይሰጠው? ካሻችሁ አዲስ አበባዊነት በሉት፤ ፊንፊኔያዊነት ብትሉትም ብዙ ለውጥ የለውም።(አዲስ አበባዊነትን በተመለከተ ሐሳቤን በሌላ ጽሑፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ።) ቁም ነገሩ አንድ ስም ያልወጣለት ማንነት ያለን ዘመዶቻችሁ ተፈጥረናል- በታሪክና በአካባቢ ሁኔታ ወይም በምርጫችን። ምርጫ አንድ፤ አበቃ።
(ምርጫ 2 ነገ ይቀጥላል።)

29 Responses to “ሕይወቴን የቀየሩ ሦስት “ምርጫዎች”- ምርጫ 1”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

በአሶሳ 23 እጣን ለቃሚዎች ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ

ግንቦት 13 ቀን 2002 ዓ.ም በእጣን ለቀማ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወደ 23 የሚጠጉ ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን የአካባቢው እማኞች ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡

ከወደ አሶሳ የሚሰማው ዜና መልካም አይደለም። ከአዲስ አበባ 660 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው አሶሳ ከተማ በምትገኘው ‹‹ክሙሩክ›› በተባለች ወረዳ ግንቦት 13 ቀን 2002 ዓ.ም በእጣን ለቀማ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ወደ 23 የሚጠጉ ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው ማለፉን የአካባቢው እማኞች ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡
ምንጮች እንደሚሉት በዕለቱ እጣን ለቀማ ላይ የነበሩ ሰዎች የማያውቋቸው ነገር ግን የቤንሻጉል ጉምዝ ክልል ተወላጆች ናቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች መሣሪያ ታጥቀው ሲያልፉ ተመልክተዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ይህንን ለማንም እንዳይነግሩ ቢያስጠነቅቋቸውም ስጋት የገባቸው እጣን ለቃሚዎቹም ነገሩን ለወረዳው አስተዳደርና ፖሊስ ያሳውቃሉ። ብዙም ሳይቆይ ታጣቂዎቹ ተመልሰው መጥተው ‹‹አትናገሩ ብለናችሁ አልነበረም ወይ?›› በማለት የተኩስ ሩምታ መክፈታቸውን በሕይወት ከተረፉት ምስክርነት ተሰምቷል። ምንጮቻችን እንደሚሉት ታጣቂዎች በዚያ አልተመለሱም፤ የአካባቢውን የጸጥታ ክፍል ኃላፊ እና አንድ ሌላ የመንግሥት ሰው ገድለዋል ተብሏል፡፡
ስለሁኔታው እስከ አሁን ከመንግሥት ወገን በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በወረዳዎቹ በቻይና ኮንትራክተር አማካይነት ይሰራ ነበረውን መንገድ ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ሥራዎች፣ ትምህርት እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ለጊዜው ቆመዋል። 23ቱን ሰዎች ገደሉ የተባሉት ታጣቂዎች እስከ አሁን አልታወቁም፤ አልተያዙምም ተብሏል።

One Response to “በአሶሳ 23 እጣን ለቃሚዎች ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ከኢቲቪ የምርጫ ወጎች

ከጥቂት ደቂቃዎች ክርክር እና ውይይት በኋላ ጋዜጠኛው ጎመን በጤና ያለ ይመስላል፡፡ ማይኩን ይዞ እንደገና ለቀረጻ ተዘጋጀ። “ከየአቅጣጫው ወደ መቀሌ ስታዲየም ለሰልፍ የመጣው ሕዝብ ቁጥር ወደ መቶ ሺህ ይጠጋል…” ሲል አነበበ። “አስር ሺህ” ባለበት የቴሌቪዥን መስኮት “መቶ ሺህ” ሲል አነበበ፡፡ ስንት የኢቲቪ ተመልካቾች በደቂቃዎች ውስጥ የተላፈውን ይህን የአስር ሺህ እና የመቶ ሺህ ሕዝብ ቁጥር ልዩነት ልብ እንዳሉት ባይታወቅም በዕለቱ ግን እንዲህ ያለው አሳፋሪ ዘገባ በጣቢያው ተላፏል፡፡…ታማኙ ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛን (የኢቲቪ ሰዎች ሲቀልዱ “ኀይለ ራጉኤል ሁለተኛ” ወይም “ዳግማዊ ኀይሌ” ይሉታል) በአውሮፕላን መቀሌ መድረሱ ሲረጋጥ ዕድለ ቢሱ ጋዜጠኛ የ“ሰላም ባስ” ትኬት ቆርጦ ባስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ታዘዘ፡፡ ምን አማራጭ አለው? በኢቲቪ መኪና ቅብርር ብሎ፣ አቀባበል ተደርጎለት መቀሌ የገባው ጋዜጠኛ ኩስስ ብሎ በ“ሰላም ባስ” የሁለት ቀን ጉዞ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ የምርጫ መልስ ግምገማ ወዴት እንደሚያሳፍረውስ ማን ያውቃል?

(ወረቱ ተስፋዬ – ከኢቲቪ)

(የአዘጋጁ ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ በትክክል የተፈጸመና ጉዳዩን ከሚያውቁ የኢቲቪ ሠራተኞች የደረሰን ነው።)

ምርጫው ሊደረግ ስድስት ቀናት ቀርተውታል፡፡ መቀሌ ሽር ጉድ በዝቶባታል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ምርጫውን በሚገባ እንዲያሸንፍ ተጨማሪ ቅስቀሳ አስፈልጎታል፡፡ ለዚህም እንዲረዳው የከተማውን ሰው ሰልፍ ጠርቷል፡፡አንድም ሥራ የፈታ መኪና በአካባቢው አይታም፡፡ አውቶብሱ፣ የጭነት መኪናው፣ ታክሲው፣ የፓርቲው፣ የመንግሥት መኪና ሁሉም ከየአቅጣጫው ያገኘውን ሰው እየጫነ በመቀሌ ስታዲየም ያራግፋል፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ የሚወጣው ሰውም ወደ አንድ አቅጣጫ ይጓዛል፡፡ አራት በር ያለው የመቀሌ ስታዲየም ግን ያስገባውን ሰው አየሁ አይልም፡፡ በአንዱ በር የሚገባ በሌላው ይወጣል፡፡

በስታዲየሙ ተንቀሳቃሽ የስርጭት ጣቢያውን የተከለው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሰልፉን ዘገባ ለማስተላለፍ ጓጉቶ ይጠባበቃል፡፡ የካሜራ እና የጊዜያዊ ስቱዲዮ ባለሙያዎቹ ከወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፡፡ ይሞክራሉ፡፡ ጋዜጠኛው ዘገባውን ለማቅረብ ይጣደፋል፡፡ የምሥራቹን ዜና እንዲያበስር የተመደበው ጋዜጠኛ ይጽፋል፤ ያነባል፡፡ ዞር ዞር እያለ የስርጭቱን መተላፍ ይጠባበቃል፡፡

በአንድ እጁ ማይኩን ይዞ ተስተካክሎ ቆመ፡፡ የቀትታ ስርጭቱ ተጀመረ፡፡ ያዘጋጀውን ዜናም አነበበ “……ከተለያየ አቅጣጫ ለድጋፍ ሰልፉ ስታዲየም የተገኘው ሕዝብ አስር ሺህ ይኾናል…….።” አጭሩን ዜና አስተላልፎ እንደጨረሰ በልቡ “እፎይ!” አለ። የጣቢያው ስርጭት ወደ ሌላኛው የሰልፉ ክፍል ተዛወረ፡፡

ጋዜጠኛው ግን “እፎይ!” ለማለት ቸኩሎ ነበር። ዞር ሲል በቁጣ የተሞሉ ሰዎች ይፈልጉታል። የህወሓት ሰዎች እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው ጠበቁት። ምክንያት? “እንዴት የሰልፈኛውን ቁጥር አስር ሺህ ትላለህ?” ቁጣው ቀጠለ። “ይህ ሁሉ ሰው አስር ሺህ ብቻ ነው? ወይስ ከጸረ ሰላም ኀይሎች ጋር ግንኙነት አለህ?”

ትንሽ እንደ መደንገጥ ብሎ የነበረው ጋዜጠኛ ትንፋሹን አሰባስቦ የዘገባውን ተገቢነት ለማስረዳት ትግል ጀመረ። አልተበገረም፤ ያልተለመደ ጥንካሬ አሳየ። እንዲህም አለ “ስቴዲየሙ ውስጥ ያለው ሰው አምስት ሺህ አይሞላም፤ እኔ እንዲያውም እየገባ የሚወጣውን ሰው ሁሉ ገምቼ ነው አስር ሺህ ያደረኩት።” የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም። ግምገማው እንደሆነ አይቀርለትም። አንድ ተጨማሪ መከራከሪያ ጣል አደረገ፤ “አስር ሺህ እኮ ብዙ ቁጥር ነው!”
“ዛሬ በዚህ ስታዲየም የተገኘው ሕዝብ ከመቶ ሺህ ይበልጣል፡፡ አንተ ግን ቀንሰህ አስር ሺህ ማለትህ ከባድ ስህተት ስለሆነ ገብተህ እንደገና የማታስተካክል ከኾነ ትልቅ ችግር ይፈጠራል” አሉ የህወሓት ሰዎች። ማስፈራሪያው ቀጠለ፡፡

ይህን ከፕሮግራም ውጭ ድንገት የተጀመረ ድራማ ከበው በጉጉት የሚከታተሉት ሰዎች በታሪኩ ተመስጠው የራሳቸውን ስሌት ማውጣት ማውረድ ጀመሩ። የአገሪቱ ትልቁ ስታዲየም የአዲስ አበባው ነው፤ ቢበዛ የሚይዘው 35000 ሰው ነው። በቅርቡ የዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ትልቁ የደቡብ አፍሪካ ስታዲየም እንኳ ይይዛል የተባለው 95000 ተመልካች ነው። ታዲያ ሚጢጢየዋ የመቀሌ ስታዲየም መቶ ሺህ ሰው የምትይዘው በምን ስሌት ነው? ጋዜጠኛው እንዲህ ብሎ አልተከራከረም፡፡ እንዲህ እያሰበ እንደነበረ ግን በድንጋጤ የተከፈተ አፉን ሳይዘጋ ሰዎቹን ያይበት የነበረው አስተያየት ያሳብቅበታ፡፡

ከጥቂት ደቂቃዎች ክርክር እና ውይይት በኋላ ጋዜጠኛው ጎመን በጤና ያለ ይመስላል፡፡ ማይኩን ይዞ እንደገና ለቀረጻ ተዘጋጀ። “ከየአቅጣጫው ወደ መቀሌ ስታዲየም ለሰልፍ የመጣው ሕዝብ ቁጥር ወደ መቶ ሺህ ይጠጋል…” ሲል አነበበ። “አስር ሺህ” ባለበት የቴሌቪዥን መስኮት “መቶ ሺህ” ሲል አነበበ፡፡ ስንት የኢቲቪ ተመልካቾች በደቂቃዎች ውስጥ የተላፈውን ይህን የአስር ሺህ እና የመቶ ሺህ ሕዝብ ቁጥር ልዩነት ልብ እንዳሉት ባይታወቅም በዕለቱ ግን እንዲህ ያለው አሳፋሪ ዘገባ በጣቢያው ተላፏል፡፡

ጋዜጠኛው ተገዶ የራሱን ዘገባ ቢያስተባብልም ይቅርታ አልተደረገለትም፡፡ “ስህተቱ” ኾን ተብሎ ላለመሠራቱ የህወሓት ሰዎች ማረጋገጫ አላገኙም። ስለዚህ ምርጫውን በሚፈለገው መንገድ የሚዘግብ ጋዜጠኛ እንዲቀየርላቸው ለጣቢያው ኃላፊ ለአቶ ዘራአይ አመለከቱ፡፡ ምንጠፍቶ! ደሞ ለልማታዊ ጋዜጠኛ! አንድ ሌላ ታማኝ ጋዜጠኛ በበራሪ አውሮፕላን ተላከ፡፡ ለነገሩ ይህ “የተሳሳተው” ጋዜጠኛም ቢሆን በታማኝነቱ ዝናው እየተሰማለት የነበር ነው። ምን ነክቶት እምቱን እንዳጎደለ አይታወቅም እንጂ በጣቢያው የተደረጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ክርክሮች እና ሌሎች ከምርጫው ጋር የተያያዙ ውይይቶችን እንዲመራ የተመረጠ ጋዜጠኛ ነበር፡፡ በመቀሌው ሰልፍ ላይ ግን እምነት አጎደለ፡፡ እነዚህ ገንዘብ የተረፋቸው ተቃዋሚዎች በተለይም የዐረና ሰዎች ጉቦ ሰጥተውት ይሆን? ወይስ ሥልጣን ከያዝን እንሾምሃለን ብለውት ይሆን?

ታማኙ ጋዜጠኛ ታደሰ ሚዛን (የኢቲቪ ሰዎች ሲቀልዱ “ኀይለ ራጉኤል ሁለተኛ” ወይም “ዳግማዊ ኀይሌ” ይሉታል) በአውሮፕላን መቀሌ መድረሱ ሲረጋጥ ዕድለ ቢሱ ጋዜጠኛ የ“ሰላም ባስ” ትኬት ቆርጦ ባስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ታዘዘ፡፡ ምን አማራጭ አለው? በኢቲቪ መኪና ቅብርር ብሎ፣ አቀባበል ተደርጎለት መቀሌ የገባው ጋዜጠኛ ኩስስ ብሎ በ“ሰላም ባስ” የሁለት ቀን ጉዞ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ የምርጫ መልስ ግምገማ ወዴት እንደሚያሳፍረውስ ማን ያውቃል? አይ ኢቲቪ!

14 Responses to “ከኢቲቪ የምርጫ ወጎች”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

አዲሱ የፕሮፓጋንዳ ሰው፤ ሬድዋን ሑሴን

መልካም ቆይታ። ሰውየው ንግግራቸውን ሊጀምሩ ነው። ቃላት ከአንደበታቸው ይፈሳሉ። ዐረፍተ ነገሮች ይመሠርታሉ። ያለማቋረጥ። የመናገር ተሠጥዖ እንዳላቸው፤ የፓርቲ ፖለቲካን በጊዜ እንደጠጧት መገመት ይቻላል። ነገር ግን የሚሉትን በጥንቃቄ እንደማይመትሩ የአጠቃላይ ንግግራቸው ጭብጥ ያሳብቃል። መተንተን ይጀምራሉ፣ በመካከል ያስጠነቅቃሉ፤ በመፈረጅ እና በመኮነን ያጅቧቸዋል። ገፋ ሲልም በመፈረጅ ይቋጩታል።ለእርሳቸው ይህ ቀላል ነው። የንግግር ተሰጥዖ የመታደላቸውን ያህል የንግግራቸው ይዘት ብዙ እንደሚያውቁ አያመላክትም፤ ቢያንስ የፓርቲያቸውን ያልተጻፈ ትምህርት፡፡ ሬድዋን ለአቶ መለስ ሥልጣን የሚያሰጋ የድጋፍ መሠረት የላቸውም። የኢሕአዴግ ምንጮች እንደሚሉት ይህን ቦታ እንዳይዙ የሚያደርጋቸው ተግዳሮት የሚመነጨው ከ1992 በፊት ለኢሕአዴግ የነበራቸው አመለካከት ብቻ ነው።

አዲሱ የፕሮፓጋንዳ ሰው፤ ሬድዋን ሑሴን

መልካም ቆይታ።  ሰውየው ንግግራቸውን ሊጀምሩ ነው። ቃላት ከአንደበታቸው ይፈሳሉ። ዐረፍተ ነገሮች  ይመሠርታሉ። ያለማቋረጥ። የመናገር ተሠጥዖ እንዳላቸው፤ የፓርቲ ፖለቲካን በጊዜ እንደጠጧት መገመት ይቻላል። ነገር ግን የሚሉትን በጥንቃቄ እንደማይመትሩ የአጠቃላይ ንግግራቸው ጭብጥ ያሳብቃል። መተንተን ይጀምራሉ፣ በመካከል ያስጠነቅቃሉ፤ በመፈረጅ እና በመኮነን ያጅቧቸዋል። ገፋ ሲልም በመፈረጅ ይቋጩታል።ለእርሳቸው ይህ ቀላል ነው። የንግግር ተሰጥዖ የመታደላቸውን ያህል የንግግራቸው ይዘት ብዙ እንደሚያውቁ  አያመላክትም፤ ቢያንስ የፓርቲያቸውን ያልተጻፈ ትምህርት፡፡

ይላሉ ሰውየው። ይህ አባባል በኢህአዴግ ሰዎች ዘንድ የሚወደድ አይደለም።  ይገርማቸዋል፤  ”….ምኒልክ ከ120 ዓመት በፊት ማሰብ የቻሉትን የዛሬ ተቃዋሚዎች ማሰብ አለመቻላችሁ ነው።” ይላሉ የአንደበታቸውን ሰይፍ ከሰገባው ሲመዙ።  ገባችሁ!?

ሬድዋን ሲናገሩ ለነገዬ አይሉም። ስለ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እስር ሲናገሩ “…ወንጀል የሚሠራ፤ ሕግ

የሚተላለፍ  ሰው አይነካ ትላላችሁ፤ ስትመረጡ ምን ልትሠሩ ነው?. . ለዚህ ነው ተቃዋሚዎች

ሐላፊነት አይሰማችሁም የምንለው” ይላሉ ።”…ተሳስተሽ ከኾነ አርሚ፤ መንግሥትም ለምኗል፤ በሽማግሌ አስለምኗል፤ ይህን ካላረምሽ ችግር ነው የሚከተለው፤  ሕጉ መተግበር ስላለበት አላርምም ስላለች ነው የገባቸው።”ሲሉ ተከራክረዋል።

አዲስ አባባ መስተዳድር ከባለ አደራ አስተዳደር ወጥታ በ2000 ዓ.ም  የአቶ ኩማ ደመቅሳ  አስተዳደር ከተማዋን ሲረከብ የአዲስ አበባ ነዋሪ እና በውስጡ የሚኖሩትን ”የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች”  በ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወንጌል”  አሳምኖ የሚያጠምቅ ሰው ከወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ዋና ከተማዋ ገባ። በሁለት ዓመታት ውስጥ ወጣቶችን፣  ሴቶችን፣  የመንግሥት የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን፣ መምህራንን ፣ የአነስተኛ እና ጥቃቅን ማኅበራትን እና ለቁጥር የሚያታክቱ ማኅበራት አባላትን በአዲስ አበባ፣ በፍቼ እና በአላጌ በሚገኙ ማሠልጠኛዎች እየተወሰዱ አምነው፤ ተጠመቁ።  ዋናው አጥማቂ ደግሞ ሬድዋን ሁሴን ናቸው። ከአዲስ አበባ 135 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ፍቼ  እና አዲስ አበባ የሚቀመጡ ከኾነ ከማይጠፉበት “አምስት ኪሎ”  አካባቢ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተገድበው የነበሩት አቶ ሬድዋን የ2002 ዓ.ም የምርጫ ክርክር ወደ አደባባይ አምጥቶአቸዋል።

አቶ ሬድዋን የኢሕአዴግ አዲስ “ኮከብ”  ኾነው በወጡበት የዘንድሮው የምርጫ ክርክር ተቃዋሚዎችን “መለወጥ ያቃታቸው እና ራሳቸውን ለማየት ድፍረት የሌላቸው” ሲሉ ሲወርፏቸው ነበር።  “በ18 ዓመት እኛ ስንለወጥ እናንተ ባላችኹበት የምትረግጡት ምን ጉድለት አለብን ብላችሁ ስለማትንቀሳቀሱ ነው” ሲሉ ተችተዋል። የሚናገሩት ስለ ተቃዋሚዎች ብቻ አይመስልም። የኢሕአዴግ የቅርብ ምንጮች የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር የኾኑትን የአቶ በረከት ስምዖንን ቦታ እንደሚረከቡ በድፍረት የሚናገሩላቸው አቶ ሬድዋን “ስለ ተቃዋሚዎች መለወጥ አለመቻል“ የተናገሯት ቃል ስለራሳቸውም የተናገሩት አስመስሎባቸዋል። አዲሱ የፕሮፓጋንዳ ሰው አቶ ሬድዋን ከዐሥር ዓመት በፊት የኢሕአዴግ  ተቺ ብሎም ተቃዋሚ ነበሩ። “በ18 ዓመት እኛ ስንለወጥ”… ያሉት ።

በምርጫ 97 ድንጋጤ ማግስት

በ97 በነበረው ምርጫ ኢሕአዴግ ሽንፈቱን ያመነው በከተሞች ብቻ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ። ሽንፈቱን የተረዳውም “ተቃዋሚዎች ከእኔ የተሻለ ፖሊሲ እና አማራጭ ስላላቸው ሳይኾን ኅብረተሰቡ የእኔን ፖሊሲ እና ዓላማ አልተረዳም” በሚል ነበር። በአንዳንድ የደቡብ ኢትዮጵያ ዞኖች በተለይም የጉራጌ ዞንን በመሳሰሉ አካባቢዎች የደረሰበት ሽንፈትንም እንዲሁ በጤና አልወሰደውም። አቶ መለስ “ስህተት መሥራት፤ ግን ስህተትን አለመድገም” በሚሉት መርህአቸው እየተመሩ በአዲስ አባበ እና በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ እና የሕዝብ አደረጃጀት ሥራ እንዲሠራ ወሰኑ። “የ97 ስህተት የማይደገመው የላቀ የሕዘብ አደረጃጀት ሲኖረን ነው።”  የሚለው በሁሉም የድርጅቱ የበላይ አመራሮች እና ካድሬዎች የታመነበት ነበር።

“በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባን እና መላውን የኢትዮጵያ ከተሞች በአምስት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እጃችን ማስገባት አለብን የሚል ስምምነት ነበር።” ይላሉ ሐሳባቸውን ለአዲስ ነገር ያካፈሉ የኢሕአዴግ ምንጭ። ለዚህም ከፍተኛ የሕዝብ አደረጃጀት ሥራ በአዲስ አበባ ለመሥራት “የኢሕአዴግ የአዲስ አባባ ኮሚቴ” ተዋቀረ። በሕዝበ አደረጃጀት ከፍተኛ ልምድ አላቸው የሚባሉ አመራሮች መጡ። የፓርቲ ሥራ ከመንግሥት ሥራ ጋራ እንዲቆራኝ መሥረት ተጣለ።

ስምንት አባላት ያሉት ይህ ኮሚቴ በቀድሞው የኢህአፓ ታጋይ፤ የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዝን ድርጅት የቴሌቪዥን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር እና የአባይ ባንክ መሥራች በኾኑት  አቶ ሕላዌ ዮሴፍ የሚመራ ነው።።  ይህ ኮሚቴ በአዲስ መልክ ሁለት ክፍለ ከተሞችን በአንድ ዞን እያስገባ ከፍተኛ የፓርቲ ሥራ አጧጧፈ። በአዲስ አበባ በሚያዝያ ወር የ“ባለ አደራ አስተዳደሩን “ ለመተካት የተደረገው የ 2000 ዓ.ም የክልል እና ተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። “ከመቼውም ጊዜ በላቀ የተሻለ የፓርቲ ሥራ ተሠራ፤ በውጤቱ ቢያንስ አነስተኛ መራጭ እንዳይወጣ ማድረግ  ተቀዳሚ ግብ ነበር፤  እርሱም ከሞላ ጎደል ተሳክቶ ነበር” ይላሉ እኝህ ውስጥ አዋቂ።

እነ አቶ ሕላዌ መሠረቱን የጣሉለትን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚወስድ ግንባር ቀደም ካድሬ ይፈለግ ነበር። ኢሕአዴግ ዐይኑን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ጣለ።  ደቡብ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት “የተካኑ” የሚባሉ ሰዎችን ማፍራት ይዟል። አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ካሊድ አሕመድ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ መኩሪያ ኀይሌ ከሌሎቹ አጋር የኢሕአዴግ ፓርቲዎች በላቀ ጎላ ብለው መታየት ጀምረዋል።

በወቅቱ የደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ሐላፊ፣ የደኢሕዴን ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ ሬድዋን ሑሴን ደግሞ በተናጋሪነታቸው ይታወቃሉ። በዚያ ላይ የሕዝብ አደረጃጀት ልምድ አላቸው። የሁሉም ዐይን ሰውየው ላይ አረፈ። ሬድዋንም ወደ አዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሐላፊነት ተመደቡ፡፡

ሥራው ቀላል እና ግልጽ ነው። “ፓርቲውን በሕዝብ ውስጥ ማሥረጽ።” “ከፍተኛ ቁጥር ያለው አባል መመልመል፤ የተመለመሉትንም ከእምነታቸው እንዳይናወጹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ማስረጽ - ሁለተኛ ተፈጥሯቸው እስኪመስል። ” በከተማው አስተዳደር ውስጥ የፓርቲ ሥራ ከመንግሥት ሥራ ጋራ የጨው እና የውኃ ያህል እስኪወሃዱ ድረስ ሬድዋን እረፍት የላቸውም። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የፓርቲውን ጥቅም በዘላቂነት እንዲያስከብሩ ይታትራሉ። ሬድዋን በሚመሩት የአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ አራት ወሳኝ የመመልመያ እና መከታተያ መዋቅሮችን  ይመራሉ። የአባላት ሥልጠና፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን እና ትምህርት፣ ግብር መልስ እና ሱፐርቪዥን እና የሕዝብ አደረጃጀት ናቸው።

እነዚህ መዋቅሮች በየክፍለ ከተማው ተመሳሳይ መዋቅር አላቸው። እስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የእዝ መዋቅር። “ሬድዋን በክፍለ ከተማ የሚገኙ ሐላፊዎችን ይገመግማል፣ አቅጣጫ ይሰጣል። ይህ መዋቅር እስከ ቀበሌ የሚደርሱትን መዋቅሮች በዋናነት የሚቆጣጠር ነው።”

ከወራቤ እስከ አዲስ

የሬድዋን አለቃ የኦሕዴዱ ሙክታር ሰይድ ናቸው፤ እርሳቸው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሐላፊ እና ሥራ አስፈጻሚ አባል  ናቸው። ውስጥ አዋቂዎቹ እንደሚሉት ግን የአቶ ሬድዋን እውነተኛ አለቃ አቶ በረከት ስምኦን ናቸው። “መመሪያ እና አቅጣጫ የሚቀበሉት ከአቶ በረከት ነው፤ አንዳንድ ጊዜ አቶ መለስ በቀጥታ ለአቶ ሬድዋን መመሪያ ያስተላልፋሉ።” ይላሉ ውስጥ አዋቂው። አቶ ሙክታር ለደንቡ  ነው አለቃነታቸው።

ከ2000ዓ.ም በኋላ በኢህአዴግ “የአባላት ማጥለቅለቅ” ሥራ በዋናነት ሲሠሩ የከረሙት አቶ ሬድዋን  በኢሕአዴግ የውስጣዊ መዋቅር በፍጥነት ወደ ላይኛው የሥልጣን እርከን መምዘገዘጋቸው አቶ መለስንም ኾነ ሌሎቹን የፓርቲውን “ቁማርተኞች” የሚያሰጋ አይደለም። ለአዲስ ነገር ሐሳባቸውን ያካፍሉ አስተያየት ሰጭ ”ህወሓት በትጥቅ ትግል በነበረበት ወቅት ይህ ሥራ ይሠራ የነበረው እነ ተወልደ ወልደማርያምን እና አለምሰገድ ገብረ አምላክን በመሳሰሉ ታጋዮች ነበር። እነዚህ ሰዎች የነበራቸው የፖለቲካ ተሰሚነት የጎላ ነበር” ይላሉ። አቶ መለስ ይህን ቦታ ለአቶ ሬድዋን ሲሰጡ ጥልቅ ምክንያት አላቸው። “አቶ ሬድዋን ልካቸውን ያውቃሉ። ባይኾን ለሌላ ሽልማት እንዲታጩ ይተጋሉ እንጂ፤ ልባቸው ወደ አቶ ወንበር መቼም ዐያይም” ሲሉ ይናገራሉ። በዚህ ፍጥነት የኢሕአዴግ “ግንባር ቀደም” ካድሬ ወደ መኾን መምጣታቸው ራሱ ራሳቸውን አቶ ሬድዋንን ሳይገርማቸው አይቀርም።

አቶ ሬድዋን የ1987 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባዮሎጂ ምሩቅ ናቸው። ከምረቃ በኋላ ለማስተማር ጂንካ የተወሰነ ጊዜ አሳልፈዋል። ደቡብ ኢትዮጵያ ብዙም አልቆዩም። አዲስ አባባ መጥተው አወሊያ ትምህርት ቤት መምህር ኾኑ። የአወሊያ ትምህርት ቤት ቆይታቸው አስደሳች የኾነም፤ ያልኾነም ነበር። ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋራ በተደጋጋሚ ይጋጩ እንደነበር ይነገራል። በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የስልጤን የማንንት ጥያቄ በዋናነት በማቀንቀን ይታወቃሉ። “ስልጤ በደቡብ ክልል ውስጥ ውክልና  ይገባዋል

ከሚለው አልፎ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር ተሟግተዋል።” በወቅቱ በርካታ የስልጤ ተወላጆችን በቅርብ ማግኘት በመቻላቸው በጉዳዩ እንዲገፉበት ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዚያውም የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ስሕዴፓ)ሲያቋቁም  ከመሪ ተዋንያኑ አንዱ ሆነው ብቅ አሉ፡፡

ኢሕአዴግም እንደለመደው በአሁኑ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የቀድሞ የአለማያ ዩኒቨርስቲ የደን ልማት(ፎረስትሪ) ጥናት ተማሪ በነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራውን “የስልጤ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” (ስሕዴድ) አቋቋመ። ሁለቱ የስልጤ ሕዝብ ድርጅቶች እርስ በርስ ይፎካከሩ ሲልም በግልጽ ይተቻቹ ነበር። ፀባቸው ሌላ አይደለም። እውነተኛ የስልጤ ሕዝብ ተወካይ ማን ነው?የሚለው ነው።  ሬድዋን የእነ አቶ ሲራጅን  ስሕዴድ፣ “አሻንጉሊት” እና  “የኢሕአዴግ ተላላኪ” በማለት እስከ እስከ መወጀል ይደርሱ እንደነበር ይነገራል።

በ1992 ዓ.ም “የስልጤ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና ከጉራጌ ሕዝብ የተለየ ማንነት ያለው መኾኑ በሕዝብ ውሳኔ ሲረጋገጥ የአቶ ሬድዋንም ሚና እና የፖለቲካ አቅጣጫ ተቀየረ።” ይላሉ ለአዲስ ነገር ሐሳባቸውን ያካፈሉት ውስጥ አዋቂ። በ1992 በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የሬድዋን ፓርቲ ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ተወዳድሮ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገቡ። ሬድዋን በፓርላማ በቆዩባት አጭር ወቅት በኢሕአዴግ ምን ያህል እንደ ተዋጡ ተገነዘቡ። ለፖለቲካ ግባቸው ስሕዴፓ ሳያንስባቸው አልቀረም።

ፓርላማ ከገቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሬድዋን እና ጓዶቻቸው ስሕዴፓን አፍርሰው ድሮ ሲተቹት የነበረውን የአቶ ሲራጅን ስሕዴድ ተቀላቀሉ። የፓርላማ ውክልናቸውን ጥለው “የስልጤ ዞን የሕዝብ ጉዳዮች አደረጃጀት” ሐላፊ በመኾን እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ቆዩ። በ1997 ዓ.ም ከስልጤ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በመወዳደር የደቡብ ክልል ምክር ቤትን ተቀላቀሉ። ከዚያ በኋዋላ ነው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የትምህርት ቢሮ ሐላፊ ብሎም የደኢሕዴን የሥራ አስፈጻሚነትን የተቀላቀሉት።

የስልጤ ዞን በምርጫ 97 ልክ እንደ ደሴት ነበረች። በዙሪያው የነበሩት አጎራባች ክልሎች በአብዛኛው የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች የመረጡ ሲኾን ስልጤ ግን ስህዴድን/ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን መርጣለች። በ97 ዓ.ም የነበረው የተቃዋሚዎች ማዕበል ጉዟቸውን አፋጥኖላቸዋል። በአምስት ዓመት ውስጥ ከወራቤ ከተማ ተነስተው የኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ “ወንጌል” ዋና አጥማቂ ኾነው ወጡ፤ በምድረ በዳ የሚጮሁ።

አዲስ በረከት”?

የኢሕአዴግ ዋና  የፕሮፓጋንዳ ሰው አቶ በረከት ስምዖን ቀስ በቀስ ከፓርቲው የአደባባይ ሥራዎች ለመውጣት በሩ ጋራ ይገኛሉ።  ኢሕአዴግ “ዱላ መቀባበል” በሚለው ጨዋታ “የፊት መሥመር ተሰላፊ የነበሩት ወደ ኋላ ኾነው፣ የድርጅት ሥራ የሚሠሩት ወደ ፊት የሚመጡበት ነው” በሚለው መሠረት “ትጉህ ባርያ” የነበሩት አቶ ሬድዋን የአቶ በረከት ስምዖንን ቦታ ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሬድዋንም የተስፋ ምድር ይህች ናት። የአቶ በረከትን ቦታ ማግኘት።

አቶ ሬድዋንን ኢሕአዴግ ግንባር ቀደም የምርጫ ተከራካሪ አድርጎ ለማምጣት በፓርቲው ውስጥ በዚሁ ታሪካቸው የተነሳ የሐሳብ ልዩነት እንደነበር ይነገራል። “ድሮ ይቃወመን በነበረ ሰው መወከል!” በሚል። ዋናው ነገር ሬድዋን ሥራቸውን አይዘነጉም። “የተለያዩ ማኅበራትን ታደራጃለህ”፤ “ከጀርባ ትቆጣጠራለህ”፤ የሚለው የፖለቲካ ቅኝት እየተሰጣቸው ለሚፈልገው ዓላማ ይሰናዳሉ። አቶ ሬድዋንም ይህችን አሠራር ከአዲስ አባባ የክፍለ ከተማ ስበሰባዎች፣ በፍቼ እና በአላጌ ተግብረዋታል። የአዲሱ በረከት ጠንካራ ጎኑም ይህ ነው።

7 Responses to “አዲሱ የፕሮፓጋንዳ ሰው፤ ሬድዋን ሑሴን”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

አኬዥያ ኦፕን ኤይር የተሰኘ የጃዝ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

ወሎ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ትሮፒካል ጋርደን ውስጥ ከ12 ባንዶችን ያሰባሰበ የኦፕን ኤይር ጃዝ ፌስቲቫል እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለአዲስ ነገር አስታወቁ። ከአዘጋጆቹ መካከል አንዱ የኾነው ታዋቂው የቤዝ ጊታር ተጫዋች ሔኖክ ተመስገን እንደገለጸው ይህ ዝግጅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታዩትን በመሣርያ የተቀነባበሩ የጃዝ የሙዚቃ ዝግጅቶች በቤተሰብ ደረጃ በትንሽ ቦታ ላይ ከማሳየት ባለፈ ለጃዝ አፍቃርያኑ መልካም የኾነ አጋጣሚን መፍጠር ነው።

ሰኔ ስድስት እና ሰባት ቀን 2002 ዓ.ም አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ትሮፒካል ጋርደን ውስጥ ከ12 ባንዶችን ያሰባሰበ የኦፕን ኤይር ጃዝ ፌስቲቫል እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለአዲስ ነገር አስታወቁ።

ከአዘጋጆቹ መካከል አንዱ የኾነው ታዋቂው የቤዝ ጊታር ተጫዋች ሔኖክ ተመስገን እንደገለጸው ይህ ዝግጅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታዩትን በመሣርያ የተቀነባበሩ የጃዝ የሙዚቃ ዝግጅቶች በቤተሰብ ደረጃ በትንሽ ቦታ ላይ ከማሳየት ባለፈ ለጃዝ አፍቃርያኑ መልካም የኾነ አጋጣሚን መፍጠር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ዐይነት የሙዚቃ ፌስቲቫሎች እየተካሄዱ የጃዝ ፌስቲቫል አለመኖሩ የሐሳቡ መነሻ እንደኾነ ሔኖክ ለአዲስ ነገር ገልጿል። “አሁን በዚህ መንገድ የምንጀምረውን የጃዝ ፌስቲቫል ቀስ በቀስ ወደ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል እንዲያድግ ማድረግ ትልቁ ግባችን ነው” ብሏል።  የዝግጅቱ መግቢያ 100፡00 ብር ሲኾን፣ ለቪ.አይ.ፒ. በተዘጋጀው ቦታ ላይ መግባት ለሚፈልጉ 200፡00 ብር ያስከፍላል። አዘጋጆቹ ከዐሥር ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት ምንም ዐይነት ክፍያ ሳይጠይቁ እንደሚያስተናግዱም አስታውቀዋል።

የዚህ ፌስቲቫል አዘጋጆች ሔኖክ ተመስገን(ቤዝ ተጨዋች)፣ ግሩም መዝሙር (ጊታር)፣ አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺዎታ(አቀናባሪ እና ፒያኖ ተጨዋች)፣ ናትናኤል ተሰማ (ድራመር) እና በጋራ አሰተባባሪ ኾኖ የሚሠራው ቢንያም ዘውዴ ናቸው። ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ይኸው ፌስቲቫል ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ድረስ የሚቆይ ሲኾን ሙዚቃ የሚጀምረው ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ እንደኾነ ታውቋል።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

“እፍታ” ቅጽ ስድስት በቅርቡ ለኅትመት ሊበቃ ነው

ከአንድ መቶ በላይ የሚኾኑ ትረካዎችንም ይዟል።

ማኅሌት አሳታሚ “እፍታ” ቁጥር ስድስትን በመጭው ወር ለገበያ እንደሚያቀርብ የማኅሌት አሳታሚ አርታኢ የኾነው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዓለም አየሁ ገላጋይ ለአዲስ ነገር ገልጸ።  “በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከስድሳ በላይ የሚኾኑ የደራስያን፣ የገጣምያን እና የጋዜጠኞች ሥራዎች ተካተዋል። ከአንድ መቶ በላይ የሚኾኑ ትረካዎችንም ይዟል።” ብሏል ዓለም አየሁ ገላጋይ።  የአንጋፋ እና የወጣት ጸሐፍትን ሥራዎችንም ማካተቱን ጨምሮ ለአዲስ ነገር አስረድቷል። በሚቀጥለው ወር ለገበያ የሚቀርበው “እፍታ ቁጥር ስድስት” ለኅትምት ከመብቃቱ በፊት ጋዜጠኛ እና ደራሲ ተስፋዬ ገብረ አብ የተለያዩ ደራስያንን፣ ገጣምያንን እና ጋዜጠኞችን ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ( የራሱን ጨምሮ) በማሰባሰብ እና የአርትኦት ሥራውን በመሥራት ጭምር በፋና ዲሞክራሲ አሳታሚ ሥር አምስት ተከታታይ መጻሕፍትን “እፍታ” በሚል ስያሜ ለአንባብያን አቅርቦ ነበር። ይኹን እንጂ ተስፋዬ ከአገር ከወጣበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ “እፍታ ቁጥር ስድስት” ለረዥም ዓመታት ሳይታተም ቆይቷል።

ተስፋዬ አምስተኛውን ኅትመት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባስመረቀበት ወቅት ቀጣዩን የ”እፍታ” ቅጽ የማሳተም ሐላፊነት በዋነኛነት የሰጠው ለኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር እና የሥነ ጥበብ ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦች እና አሳታሚዎች ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ ሥራዎቻቸው ከተካተቱት መሀል ስብኀት ገብረ እግዚአብሔር፣ ሣኅለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም፣ አስፋው ዳምጤ፣ ነብይ መኮንን፣ መኩርያ መካሻ፣ እንዳለ ጌታ ከበደ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ ዳዊት ጸጋዬ፣ ጽጌሬዳ ኀይሉ እና ሌሎችም በርካታ ስመጥር ጸሐፍት ይገኙበታል።

ማኅሌት አሳታሚ ከዚህ ቀደም የስብኀትን “ሌቱም አይነጋልኝ”፣ “ትኩሳት” እና “ሰባተኛው መልዐክ” የተሰኙ መጻሕፍቶቹን እንደወረዱ ለኅትመት ያበቃ ሲኾን የአዳም ረታን “አለንጋ እና ምስር”፣ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” እና በቅርቡ በገበያ ላይ የዋለውን “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” የሚሉ ሥራዎቹን አሳትሟል። ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ዐየሁ ገላጋይን “ቅበላ” እና የሌሊሳ ግርማን “የንፋስ ሕልም እና ሌሎች ምናባዊ ታሪኮች” ለኅትመት ማብቃቱ ይታወሳል።

ለዚህ ጽሑፍ አስተያየት በመስጠት የመጀመሪያ ይሁኑ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

ኢትዮጵያ “ከኋላ ቀር የግብርና ኢኮኖሚ ወደ ሞደርን ኢኮኖሚ” ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች?!

ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ “ከኋላ ቀር የግብርና ኢኮኖሚ ወደ ሞደርን ኢኮኖሚ” ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች የሚለውን ዜና ሰምተዋል? የእንደራሴዎቿ የምርጫ እንቅስቃሴ እና ውጤት ትንፋሽ ያሳጣት አገር ከምርጫ ወሬ ባሻገር የሚነገር ነገር የሌላት አይደለችም። በምርጫው ዜናዎች ሽፋን በቅርቡ የተሰማው ኢኮኖሚያዊ “ወግ” ሌላ ቀልብ የሚስብ ጉዳይ ነው። አገሪቷም ገና ብዙ እንዲወራላት የሚያደርግ አስገራሚ መረጃዎች እንዳሏት አልሸሸገችም። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የነበረው የፈጣንና ዘላቂ ልማት የአምስት ዓመት ዕቅድ (Plan for Accelerated and Sustained Development to End Poverty-PASDEP) ውጤት ይፋ ኾኗል። እቅዱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች(MDGs) ለማሳካት ይረዳ ዘንድ በመንግስት ከተወጠኑ ጥቅል ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት እቅዶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ነው። የልማት እቅዱን ውጤቶች ይፋ ያደረገው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከተለመዱት “ድንቅ” ኢኮኖሚያዊ ምጣኔዎች ወግ ባሻገር አዲስ የሚባል ጉዳይ ወደ መድረኩ አምጥቷል። እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኾነ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ አገሪቷ “ከኋላ ቀር የግብርና ኢኮኖሚ ወደ ሞደርን ኢኮኖሚ” ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች። ለ“ዘመናዊ ኢኮኖሚው” ሽግግር ምክንያት የኾኑ ለውጦች በዝርዝር ተጠቅሰዋል።

የእንደራሴዎቿ የምርጫ እንቅስቃሴ እና ውጤት ትንፋሽ ያሳጣት አገር ከምርጫ ወሬ ባሻገር የሚነገር ነገር የሌላት አይደለችም። በምርጫው ጣጣዎች ሽፋን በቅርቡ የተሰማው ኢኮኖሚያዊ “ወግ” ሌላ ቀልብ የሚስብ ጉዳይ ነው። አገሪቷም ገና ብዙ እንዲወራላት የሚያደርግ አስገራሚ መረጃዎች እንዳሏት አልሸሸገችም።

ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የነበረው የፈጣንና ዘላቂ ልማት የአምስት ዓመት ዕቅድ (Plan for Accelerated and Sustained Development to End Poverty-PASDEP) ውጤት ይፋ ኾኗል። እቅዱ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች(MDGs) ለማሳካት ይረዳ ዘንድ በመንግስት ከተወጠኑ ጥቅል ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት እቅዶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ነው። የልማት እቅዱን ውጤቶች ይፋ ያደረገው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከተለመዱት “ድንቅ” ኢኮኖሚያዊ ምጣኔዎች ወግ ባሻገር አዲስ የሚባል ጉዳይ ወደ መድረኩ አምጥቷል። እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኾነ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ አገሪቷ “ከኋላ ቀር የግብርና ኢኮኖሚ ወደ ሞደርን ኢኮኖሚ” ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ለ“ዘመናዊ ኢኮኖሚው” ሽግግር ምክንያት የኾኑ ለውጦች በዝርዝር ተጠቅሰዋል። በተከታታይ ዓመታት የተመዘገበ አማካይ የ11.8 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት፣ ከፍተኛ የማኅበራዊ ፕሮግራሞች ሽፋን እና የመሰረታዊ ልማት ዝርጋታ ዋነኞቹ የለውጡ ግብዓቶች ተደርገዋል። መንግሥት ባለፉት ዓመታት “ስኬቶቼ ናቸው” ያላቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ ተጠቅሰዋል። ለቀጣዩም አምስት ዓመታት የተዘገጀውን እቅድ ለመተግበር ዝግጁ መኾኑን ከወዲሁ አሳውቋል። በቀጣዩ ፕሮግራም የሚኾነውም “ሽግግሩን ማስቀጠል” ነው ተብሏል።

ነገር ግን አዲሱ የመንግሥት የ“ዘመናዊ ኢኮኖሚ” ሽግግር እውን የመኾን ወግ ከዚህ ቀደም እንደተነገሩት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለምሁራዊ ክርክር የሚበቃ አይመስልም። ባለፉት አራት ዓመታት የተመዘገቡት ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር አልታየባቸውም። ከዚህ ይልቅ ስማዊ የኾነ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ጎልቶ መታየቱ “የዘመናዊ ኢኮኖሚ” ሽግግር ጅማሬን የመንግሥት ፉከራ ብቻ እንዲኾን አድርጎታል።
በኢኮኖሚያዊ ኃልዮቶች መሰረት ከአንድ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ወደ ሌላኛው ሽግግር ለማድረግ ወሳኝ የሚባሉት ኢኮኖሚያዊ ተለዋዋጮች የተሻለ የሚባል ለውጥ ማሳየታቸው የግድ ነው ። የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እየቀነሰ በአንጻሩ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻ እያደገ መምጣት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማት መበራከት እና መስፋፋት እንዲሁም ተጨባጭ የማኅበራዊ ጉዳዮች መሻሻል ወሳኝ የሚባሉ የለውጥ ምልክቶች ናቸው። ወደ ቀጣዩ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የመሸጋገርንም የምስራች ይነግራሉ። ለእዚህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ ሽግግር ተጠቃሽ የምትኾነው አፍሪካዊቷ ቦትስዋና ነች። ቦትስዋና ዛሬ በምሳሌነት ወደሚጠቀስላት የተሳካ የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ከመድረሷ በፊት የዴሞክራሲያዊ ሽግግሯ ቀዳሚ ነበር። ከእንግሊዝ ግዛትነት ነጻ ከወጣች በኋላ ከመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓቷ ጎን ለጎን ነጻ የገበያ እንቅስቃሴን፣የተሳካ የግል ንብረት ባለቤት መብትን፣ የተረጋጋ የዋጋ ሥርዓትን እና አጠቃላይ ማህበራዊ ለውጥን በማምጣት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት መካከል ለመቀላቀል ችላለች። ከቢሮክራሲ የፀዳውም የኢንቨስትመንት ፖሊሲዋ በ2009 ዓ.ም ምርጥ የኢንቨስትመንት ሥፍራዎች ተብለው በአለም ባንክ የደረጃ ሠንጠረዠ ከተመዘገቡ አገራት ተርታ እንድትመደብ አስችሏታል።

ከዚህ አንጻር ያለፉት የኢትዮጰያ አራት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሲመዘኑ የዘመናዊውን ኢኮኖሚ ጅማሮ ለማብሰር አቅም ያንሳቸዋል። እንደ መረጃዎች ከኾነ ኢኮኖሚው ከተነገሩለት በርካታ ተዓምራት ይልቅ የታዩበት በርካታ ሳንካዎች የጎሉ ኾነዋል። መንግስት ዘወትር በሚናገርለት አመታዊ አማካይ የኢኮኖሚ እድገት ምጣኔ እንኳን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሠፊ ልዩነት ይታያል። ለዚህም የአይኤምኤፍን እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን ሪፖርቶች መመልከቱ በቂ ነው። በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚ ባለሞያዎችም ኾኑ ሌሎች ታዛቢዎች ሂደቶችን መለስ ብለው እንዲገመግሙ እና ያለፉትን አራት ዓመታት “ግስጋሴዎች” በጥንቃቄ እንዲያጤኑ የሚያነቃቃ ደወል ኾኗል።
የአርሶ አደሮች “ዘመናዊ ኢኮኖሚ”

ከእጅ ወደ አፍ ከኾነው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የዘመናዊ ኢኮኖሚ መገለጫ ወደ ኾኑት የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎች የሚኖር የምጣኔ ለውጥ ለመሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ዋነኛ ጉዳይ ነው። በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኝ ትርፍ የሰው ኃይል (Surplus labour) ወደ ኢንዱስትሪው እና አገልግሎት ክፍለ ኢኮኖሚዎች ሽግግር እንዲያደርግ ይጠበቃል። የግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ የሚገኘው ትርፍ ምርት ከከተሜው ቀለብ ተርፎ ለሚነቃቁት ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት መዋል አለበት።

ከዚህም ባሻገር ግብርናው ከዓመታዊው አጠቃላይ አገራዊ ምርት (Gross Domestic Product) ይዞት የቆየውን ከፍተኛ ድርሻ ለሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች መልቀቅ ይኖርበታል። በዚህ የሽግግር ወቅት ከገጠር ወደ ከተማ የሚኖር ፍልሰት፣ አነስተኛ ነገር ግን ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ተመጣጣኝ እድገት ያለው የአገልግሎት ዘርፍ መኖር የኢኮኖሚው ጠባይ ይኾናል።
ይሁንና ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ እነዚህን የዘመናዊ ኢኮኖሚ የሽግግር መለያዎችን ለማየት አልታደለም። እንደ አለፉት ዘመናት ሁሉ አሁንም 80 በመቶ ያህሉ የሰው ኃይል ተከማችቶ የሚገኘው በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ነው (Inflation Dynamics and Food Prices in an Agricultural Economy: The Case of Ethiopia)። 95 በመቶ የሚኾነውም የሰብል ምርት የሚገኘው ከአንድ ሄክታር ባነሰ መሬት ላይ ከሚያርሱ አደሮች ከመኾኑም ከአርሶ አደሮች ተርፎ ለገበያ የሚቀርብ ምርት እጅግ አነስተኛ ነው። ከዚህ ይልቅ ለራሱም መትረፍ ተስኖት በየዓመቱ ለእርዳታ እጁን የሚዘረጋው አርሶ አደር ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀብ ላይ ይገኛል::

በተጨማሪም በመንግስት ስሌት ኢኮኖሚው ባለፉት አራት አመታት በአመካይ በአመት 11 በመቶ ቢያድግም ሽግግር በተባለው ወቅት ማደግ ከሚጠበቅበት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ይልቅ በከፍተኛ ምጣኔ በመገስገስ ላይ የሚገኘው የአገልግሎት ዘርፉ ኾኗል። ለመጥቀስ ያህል ባለፈው ዓመት የአገልግሎት ዘርፉ ከአጠቃላዩ ዓመታዊ አገራዊ ምርት የነበረው ድርሻ 44 በመቶ የደረሰ ሲኾን የኢንዱስትሪው ግን 13 በመቶ ብቻ ኾኖ ይገኛል። ግብርናው ቀሪውን 43 በመቶ ድርሻ በመያዝ አሁንም የኢኮኖሚው ዋልታ ነው።

የአገልግሎት ዘርፈም መስፋፋት በውስን ከተሞች ላይ ያተኮረ ነው። ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርም ለማድረግ ያለው አቅም የተወሰነ ነው። ከግብርና ወደ አገልግሎት ዘርፍ ከሚደረግ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጥ ይልቅ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖር ሽግግር ዘለቄታዊ ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንደሚያመጣ የልማት ኢኮኖሚ ኃልዮቶች ይተነትናሉ። ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ የኾነውም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የ2010 የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሪፖርት እንደሚያሳየው የአገልግሎት ዘርፉ እድገት ከሌሎቹ ልቆ መገኘቱ ቀጣይ የአህጉሪቷ ልማት ላይ ተፅዕኖ ሊያስከትል ይችላል ሲለ ስጋቱን ያስቀምጣል።
እድገት እና ጥሪት ጅምር ላይ ያለን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በተሻለ ኹኔታ ለማፋጠን አገራዊ ቁጠባ ወሰኙ መሳሪያ ነው። እያደገ የሚሄድ የቁጠባ ባህል ጅምር ባለበት ኢኮኖሚ ሥራ ፈጣሪዎች ስለሚበረታቱ የስራ መስኮች በበቂ ኹኔታ ይስፋፋሉ፤ ኢንዱስትሪም በሁለት እግሩ ለመቆም ብርታት ያገኛል። ማህበረሰቡ የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብርም የተረጋጋ የዋጋ ሥርዓት እና የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።
ያለፉት አራት ዓመታት ለሽግግሩ ጅማሮ ምክንያት ኾነዋል ያለው መንግስት ምርታማነትን በማሳደግ የማኅበረሰቡን የቁጠባ ባህልም ኾነ የተረጋጋ የዋጋ ሥርዓትን ለመፍጠር አልቻለም። ከዚህ ይልቅ ከባለፉት ዓመታት በባሰ ሁኔታ የማኅበረሰቡ አነስተኛ የቁጠባ ባህል በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ኾኗል። የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ባለፉት አርባ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ኹኔታ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገበባቸው አመታት ቢኖሩ ያለፉት አራት አመታት ኾነዋል፤ እስከ 90 በመቶ የሚደርስ የምግብ ዋጋ ግሽበት ተከስቷል ። ይሁንና የማህበረሰቡ ንጥር ወርሃዊ ግቢ መሻሻልን ባለማሳየቱ ምክንያት የሸመታ ፍላጎታቸውን ባለበት ለማስቀጠልም ኾነ ዝቅተኛ የሚባለውን የሸመታ መጠን ለመጠበቅ ስለሚቸገሩ ቁጠባን እርም ይላሉ። ችግሩ ድግሞ በከተሞች ተባብሶ የታየ ነው።

ባለፈው መጋቢት 2002 ዓ.ም ዮናስ ዓለሙ የተባሉ የኢኮኖሚ ተመራማሪ “Household-Level Consumption in Urban Ethiopia: Inflation and Idiosyncratic Shocks” በሚል በሠሩት ጥናት የዋጋ ግሸበቱ በከተሜው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመለካት ሞክረዋል። እንደ ጥናት ውጤቱ ከኾነ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ የዜጎችን የሸመታ ጠባይ ከመቀየሩ ባሻገር ጥሪት እንዳይቋጥሩ ምክንያት ኾኗል። ጥናቱ ለናሙና ከወሰዳቸው ሸማቾች 38 በመቶ ያህሉ ቀድሞ ይሸምቱት ከነበረው መጠን ያነሰ እንዲሸምቱ ሲገደዱ፤ 21 በመቶ ያህሉ ደግሞ መሠረታዊ የሚባለውን የሸመታ መጠን ለመከወን የወዳጅ ዘመድ ድጋፍ እንዲሹ አስገድዷቸዋል።

የዋጋ ግሽበቱ በከተሞች መባባሱ መንግሥት ስለ 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እያወራም ቢኾን የድህነት ቁጥሩ ሊቀንስ አልቻለም። ከዚህ ይልቅ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በሚል በብዛት ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ አቅርቦት የዋጋ ግሽበቱ ነዳጅ በመኾን ችግሩን የማባባስ ሚና ተጫውቷል። በኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ለዓመታት በተሰበሰቡ የገንዘብ አቅርቦት እና የዋጋ ግሽበት ዝምድናን በሚያሳዩ የቁጥር መረጃዎች ላይ የተሰሩ ዳይናሚክ የኢኮኖሚክስ ጥናት ሞዴሎች እንደሚያሳዩት የአንድ በመቶ የገንዘብ አቅርቦት (Broad Money Supply) የዋጋ ግሽበትን 1.49 በመቶ የማባባስ ሚና ይኖረዋል።

ከላይ የተጠቀሱትን ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ጨምሮ ሌሎች ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት እንደሚለው ወደ “ዘመናዊው” ኢኮኖሚ መግባት አልጋ በአልጋ እንዳለኾነ መመልከት ይቻላል። መንገዱ ግን ሙሉ ለሙሉ የተዘጋ አይደለም። የነጻ የገበያ ሥርዓትን መዘርጋት፣ የግል ንብረት ባለቤትነትን ዋስትና ማስጠበቅ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚጋብዙ ፖሊሲዎችን መንደፍ፣ ምኀበራዊ ዋስትናዎችን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ እና ማኀበራዊ ተቋማትን ማስፋፋት እና የመሳሰሉት የመንግስት እርምጃዎች ወደታቀደው ግብ እንደሚወስዱ የእነ ቦትስዋና ልምድ ዋቢ ማድረግ ይቻላል።

11 Responses to “ኢትዮጵያ “ከኋላ ቀር የግብርና ኢኮኖሚ ወደ ሞደርን ኢኮኖሚ” ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች?!”

  1. ጥሩ ግምገማ ነዉ።

  2. ግርማ ሞገስ 1 July 2010 at 12:20 am

    ጥሩ አጻጻፍ ነው። ከበድ ያለ ጉዳይ ለአንባቢ በአጭሩ ሊጨበጥ እንዲችል ተደርጎ ቀለል ባለ መንገድ ቀርቧል። ድንቅ ችሎታ!

Leave a Reply

You must be to post a comment.

Bad Behavior has blocked 1033 access attempts in the last 7 days.